በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የብሪታንያው “የተረሳው እጅግ አዋቂ ሰው”

የብሪታንያው “የተረሳው እጅግ አዋቂ ሰው”

የብሪታንያው “የተረሳው እጅግ አዋቂ ሰው”

ብሪታንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ሮበርት ሁክ በዘመኑ የነበሩት ባልደረቦቹ “በምድር ላይ ከኖሩ ሰዎች በሙሉ ተወዳዳሪ የሌለው የፈጠራ ሰው” በማለት ይጠሩት የነበረ ሲሆን ባሁኑ ጊዜ ደግሞ የእንግሊዙ ሊዮናርዶ ዳ ቪንቺ ተብሎ ለመጠራት በቅቷል። * በ1635 የተወለደው ሁክ በ1662 የለንደን ሮያል ሶሳይቲ የሙከራዎች ውጤት ኃላፊ ሆኖ የተሾመ ሲሆን በ1677 ደግሞ የዚሁ ማኅበር ጸሐፊ ሆኗል። በመጨረሻም በ1703 አረፈ። ይሁን እንጂ በሳይንሱ መስክ በጣም የታወቀ ሰው ቢሆንም አስከሬኑ በሰሜን ለንደን አካባቢ በውል በማይታወቅ መቃብር ውስጥ ይገኛል።

በግለሰቡ የሕይወት ታሪክ ዙሪያ ጽሑፍ ያዘጋጁት ስቲቨን ኢንዉድ “የተረሳው እጅግ አዋቂ ሰው” ብለው የሚጠሩትን የሁክን የተረሳ ዝና ወደ ቦታው ለመመለስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሳይንስና የታሪክ ሊቃውንት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ከዋክብትን በመከታተል ጥናት የሚያካሂደው የለንደኑ ሮያል ኦብዘርቫተሪ ግሪንዊች፣ በ2003 ሁክ የሞተበትን 300ኛ ዓመት ባከበረበት ወቅት አንዳንድ ታላላቅ የፈጠራ ሥራዎቹና ግኝቶቹ ለሕዝብ እንዲታዩ አድርጎ ነበር። ለመሆኑ ሮበርት ሁክ ማን ነበር? ይህን ለሚያክል ዘመን ተረስቶ የቆየውስ ለምንድን ነው?

ሁክ ትቶት ያለፈው ቅርስ

ሁክ በጣም የተማረና ከፍተኛ ችሎታ ያለው የፈጠራ ሰው ነበር። ከበርካታ የፈጠራ ሥራዎቹ መካከል ዘመናዊ መኪናዎች የሚጠቀሙባቸው ኮሮቼራ ወይም ዩኒቨርሳል ጆይንት፣ ወደ ካሜራ የሚገባውን የብርሃን መጠን ለማስተካከል የሚያስችለው አይሪስ ዳያፍራምና የሰዓቶችን አሠራር የሚቆጣጠረው የሰዓት እሽክርክሪት ማስተካከያ ይገኙበታል። እስከዛሬ ድረስ የሞላዎችን የመለጠጥ አቅም ለማስላት የሚያገለግለውንና የሁክ ሕግ የተባለውን ቀመር ያገኘው እርሱ ነው። ሮበርት ቦይል የተባለው እውቅ ብሪታንያዊ የፊዚክስና የኬሚስትሪ ሊቅ የተጠቀመበትን የነፋስ ፖምፓ የሠራው ሁክ ነው።

ይሁን እንጂ በጣም ልቀው ከሚታዩት የሁክ የፈጠራ ሥራዎች አንዱ፣ በለንደን ዝነኛ የመሣሪያዎች ሠሪ የነበረው ክሪስቶፈር ኮክ ቆየት ብሎ አሻሽሎ የሠራው ጥምር አጉሊ መነጽር ወይም ኮምፓውንድ ማይክሮስኮፕ ነው። ሁክ በዚህ መሣሪያው አማካኝነት የቡሽን አሠራር ሲመረምር የተመለከተውን የንብ እንጀራ የመሰለ ቅርጽ ለመግለጽ “ሴል” የሚለውን ቃል ፈጠረ። ቆየት ብሎም ይህ ቃል ሕያዋን ፍጥረታት የተሠሩበትን መሠረታዊ ሕዋስ ለመግለጽ ውሏል።

ለሁክ ከፍተኛ ዝና ያስገኘለት በ1665 የታተመው ማይክሮግራፊያ (ትናንሽ ሥዕሎች) የተባለው መጽሐፍ ነበር። ይህ መጽሐፍ ሁክ በትክክልና በጥሩ ሁኔታ የሣላቸውን በራሱ አጉሊ መነጽር የተመለከታቸውን የጥቃቅን ነፍሳት ሥዕል ይዟል። ከእነዚህም መካከል ከፍተኛ ዝና ያተረፈለት የአንዲት ቁንጫ ሥዕል ነበር። ይህ ሥዕል 30 በ45 ሴንቲ ሜትር መጠን ያለው ሲሆን የቁንጫን ጥፍሮች፣ መንደፊያዎችና የውጭ ሽፋን ያሳያል። እነዚህ ነፍሳት በአብዛኛው የሚኖሩት የሰውን ደም እየመጠጡ መሆኑ በተለይ የዘመኑን ባለጠጎች እጅግ አስደንግጧል። ወይዛዝርቱ ይህን ሥዕል ሲመለከቱ ራሳቸውን እንደሳቱ ይነገራል!

ሁክ በአጉሊ መነጽሩ የታየውን በሰው እጅ የተሠራውን የመርፌ ጫፍ ከተፈጥሯዊ ነገሮች ጋር ካወዳደረ በኋላ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አጉሊ መነጽር [ከመርፌ የበለጠ] ብዙ ሺህ ጊዜ እጥፍ ሹል የሆኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ነገሮችን የማየት አጋጣሚ ይሰጠናል።” ለዚህም የጥቃቅን ነፍሳትን ፀጉር፣ ጥፍርና ሻካራ ሽፋን እንዲሁም ቅጠሎች ላይ ያሉ ፀጉሮችን እንደ ማስረጃ ጠቅሷል። እነዚህ “የፍጥረት ሥራዎች” የፈጣሪያቸውን ሁሉን ቻይነት እንደሚያውጁ ተሰምቶታል። ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ፣ አጉሊ መነጽር “ለመጀመሪያ ጊዜ የሕያዋን ፍጥረታት አስገራሚ ውስብስብነት ግልጽ ሆኖ ሊታይ የቻለበት አዲስ ዓለም” አስገኝቶልናል ብሏል።

ሁክ ቅሪት አካሎችን በአጉሊ መነጽር መርምሮ፣ ከሞቱ ረዥም ዘመን የሆናቸው ሕያዋን ፍጥረታት ቅሪት መሆናቸውን የተገነዘበ የመጀመሪያው ሰው ነበር። ማይክሮግራፊያ ሌሎች በርካታ አስደናቂ ሳይንሳዊ ማብራሪያዎችም ይዟል። እንዲያውም በሁክ ዘመን የኖረው እውቅ ጸሐፊ ሳሙኤል ፔፒስ ማይክሮግራፊያን “ካነበብኳቸው መጻሕፍት ሁሉ ተወዳዳሪ ያላገኘሁለት የጥበብ መጽሐፍ” ሲል ጠርቶታል። በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ታሪክ ምሁር የሆኑት አለን ቻፕማን “በዘመናዊው ዓለም ላይ ዘላቂ አሻራ ከተዉት መጻሕፍት አንዱ ነው” ብለውታል።

ለንደንን መልሶ መገንባት

በ1666 በለንደን ተከስቶ ከነበረው ታላቅ ቃጠሎ በኋላ ሁክ በቀያሽነት እንዲሠራ ተሾመ። ጓደኛውና በሳይንስ መስክ ባልደረባው ከነበረው ከንጉሡ ቀያሽ ከክሪስቶፈር ሬን ጋር ሆኖ የለንደንን ከተማ መልሶ በመገንባት ሥራ ተካፍሏል። በሁክ ንድፍ ከተሠሩት ሕንጻዎች መካከል ለቃጠሎው መታሰቢያ እንዲሆን የተሠራው 62 ሜትር ቁመት ያለው የለንደን ሐውልት ይገኝበታል። ሁክ ይህን ያለ ድጋፍ የቆመና በቁመቱ ከዓለም አንደኛ የሆነ ሐውልት ሲሠራ የራሱን የስበት ንድፈ ሐሳብ ሊሞክርበት አስቦ ነበር።

ሮያል ኦብዘርቫተሪ ግሪንዊችን የሠራው ሬን እንደሆነ ቢነገርም በንድፍ አወጣጡ ላይ ከፍተኛ ድርሻ የነበረው ሁክ ነው። የመጀመሪያው የብሪቲሽ ሙዚየም ሕንጻ የነበረው ሞንታግዩ ሃውስ ከሁክ በርካታ የሥራ ውጤቶች መካከል ሌላው ነው።

ሁክ በሥነ ፈለክ መስክም ከፍተኛ እውቅና ያገኘ ሲሆን ባለመስተዋት ቴሌስኮፕ ለመሥራት የመጀመሪያው ሰው ነበር። ይህን ቴሌስኮፕ በስኮትላንዳዊው የሂሣብና የሥነ ፈለክ ሊቅ በጄምስ ግሪጎሪ ስም ሰይሞታል። ሁክ ጁፒተር የተባለችው ፕላኔት በራሷ ዛቢያ ላይ እንደምትዞር የገለጸ ሲሆን ማርስን የሚያሳየው ንድፉ ደግሞ ከሁለት መቶ ዓመታት በኋላ የማርስን የእሽክርክሪት ፍጥነት ለማስላት አገልግሏል።

ታዲያ ለምን ተረሳ?

አይዛክ ኒውተን በ1687 ማቲማቲካል ፕሪንሲፕልስ ኦቭ ናቹራል ፊሎዞፊ የተባለ መጽሐፉን አሳተመ። የሁክ ማይክሮግራፊያ ከወጣ ከ22 ዓመት በኋላ የወጣው ይህ የኒውተን መጽሐፍ የስበትን ሕግ ጨምሮ የእንቅስቃሴ ሕጎችን ያብራራ ነበር። ይሁን እንጂ አለን ቻፕማን እንደገለጹት ሁክ “ከኒውተን በፊት ብዙዎቹን የስበት ንድፈ ሐሳብ ክፍሎች አብራርቶ ነበር።” በተጨማሪም ኒውተን በብርሃን ባሕርይ ላይ የተለያዩ ሙከራዎች ለማድረግ የተነሳሳው በሁክ ሥራ ላይ ተመስርቶ ነበር።

የሚያሳዝነው ግን ብርሃንንና ስበትን በተመለከተ በሁለቱ ሰዎች መካከል የተነሳው ጭቅጭቅ እርስ በርሳቸው እንዲቃቃሩ ምክንያት ሆነ። እንዲያውም ኒውተን ማቲማቲካል ፕሪንሲፕልስ ከተባለው መጽሐፉ የሁክን ስም ፈጽሞ እስከማውጣት ደረሰ። በተጨማሪም አንድ ምንጭ እንደሚለው ኒውተን፣ ሁክ ለሳይንስ ያበረከተውን አስተዋጽኦ ከማንኛቸውም መዛግብት ለማጥፋት ሞክሯል። ከዚህም በላይ፣ ኒውተን የሮያል ሶሳይቲ ፕሬዚዳንት ከሆነ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የሁክ መሣሪያዎች (አብዛኞቹ በእጅ የተሠሩ ናቸው)፣ በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎቹና ትክክለኛ ምስሉን የያዘው ብቸኛ ሥዕል ደብዛቸው ጠፋ። በእነዚህ የታሪክ ክስተቶች ምክንያት የሁክ ዝና ለሁለት ምዕተ ዓመታት ያህል ተረስቶ ቆየ።

ኒውተን “ከሌሎች ይበልጥ አርቄ ማየት የቻልኩት በታላላቅ ሰዎች ትከሻ ላይ ቆሜ ነው” የሚሉትን ዝነኛ ቃላት የጻፈው የካቲት 5, 1675 ለሁክ በጻፈው ደብዳቤ ላይ መሆኑ የሚገርም ጉዳይ ነው። በእርግጥም የሥነ ሕንጻ፣ የሥነ ፈለክና የሳይንሳዊ ሙከራ ሊቅ እንዲሁም የፈጠራ ሰውና ቀያሽ የነበረው ሮበርት ሁክ የዘመኑ ታላቅ ሰው ነበር።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 ከ15ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ እስከ 16ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ የኖረው ዳ ቪንቺ ጣሊያናዊ ሲሆን ሠዓሊ፣ ቅርጻ ቅርጽ ሠሪ፣ መሐንዲስና የፈጠራ ሰው ነበር።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የሁክ የበረዶ ቅንጣቶችና የአመዳይ ቅርጽ ሥዕል

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሁክ የአጉሊ መነጽር ንድፍ

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቡሽ ውስጥ የሚታየውን የንብ እንጀራ የመሰለ ክፍት ቀዳዳ ለመግለጽ “ሴል” የሚለውን ቃል የፈጠረው ሁክ ነበር

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ማይክሮግራፊያ” የተባለው የሁክ መጽሐፍ በአጉሊ መነጽር የተመለከታቸውን ነገሮች ሥዕል ያካተተ ነበር

[በገጽ 27 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የቁንጫ መጠን

ወይዛዝርት የሁክን የቁንጫ ሥዕል ሲመለከቱ ራሳቸውን ስተዋል ተብሎ ይነገራል

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሞንታግዩ ሃውስ ከሁክ በርካታ የሕንጻ ንድፎች መካከል አንዱ ነበር

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመለጠጥን ሕግ የሚያሳይ የሁክ ሥዕል

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዓለም በቁመቱ አንደኛ የሆነውና ያለ ድጋፍ የቆመው ሐውልት የለንደን የመታሰቢያ ሐውልት ነው

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሮያል ኦብዘርቫተሪ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ሞላ፣ አጉሊ መነጽርና የበረዶ ቅንጣቶች:- Images courtesy of the Posner Memorial Collection, Carnegie Mellon University Libraries

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Images courtesy of the Posner Memorial Collection, Carnegie Mellon University Libraries

[በገጽ 28 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]

የሞላ ሥዕል:- Image courtesy of the Posner Memorial Collection, Carnegie Mellon University Libraries; የለንደን የመታሰቢያ ሐውልት:- Matt Bridger/DHD Multimedia Gallery; ሮያል ኦብዘርቫተሪ:- © National Maritime Museum, London