በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጋብቻ ማዕበሉን መቋቋም ይችል ይሆን?

ጋብቻ ማዕበሉን መቋቋም ይችል ይሆን?

ጋብቻ ማዕበሉን መቋቋም ይችል ይሆን?

“እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው።”—ማቴዎስ 19:6

ንካራ መስለው ይታዩ የነበሩ ቤቶች በጎርፍ ተጠራርገው ተወስደዋል፤ መዋቅሮቻቸውም ተፍረክርከዋል። በቅርቡ የተከሰተ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ በምድር ዙሪያ በርካታ አካባቢዎችን በመታበት ወቅት የብዙ ሕንጻዎች ጥራትና ጥንካሬ ከባድ ፈተና ላይ ወድቋል።

አንድ ለየት ያለ ማዕበል ደግሞ ዘመናት ባስቆጠረው የጋብቻ ተቋም ላይ ጉዳት እያደረሰ ሲሆን መሠረቶቹንና ጠቅላላ መዋቅሩንም እያናጋው ነው። ከቤተሰብ ጋር በተያያዘ ታሪክ ጸሐፊ የሆኑት ስቴፋኔ ኩንትዝ የተባሉ ሴት “መጨረሻው ምን እንደሚሆን ባይታወቅም፣ ጋብቻ በግልና በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ከነበረው ቁልፍ ቦታ ተፈናቅሏል” በማለት ተናግረዋል።

እንዲህ ያለው አዝማሚያ የሚያስከትለው መዘዝ ይታይሃል? ጋብቻ በማኅበረሰቡ ውስጥ የነበረውን የተከበረ ቦታ እያጣ መሆኑ ይሰማሃል? መልስህ አዎን ከሆነ፣ ለዚህ ዓይነቱ አካሄድ መንስኤው ምንድን ነው? ደግሞስ አንድ ሰው ደስተኛ ትዳር እንደሚኖረው ተስፋ ለማድረግ የሚያበቃ ምን ምክንያት አለ? ለመሆኑ ጋብቻን አደጋ ላይ የጣለው ምንድን ነው?

ጋብቻ ጥቃት እየተሰነዘረበት ነው

በጋብቻ ላይ የሚሰነዘሩት ጥቃቶች አዲስ አይደሉም፤ እንዲያውም የሰው ልጅ ታሪክ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የነበሩ ናቸው። የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ወላጆቻችን ያዳበሯቸው ባሕርያትና ዝንባሌዎች በዛሬው ጊዜ በጋብቻ ውስጥ ለሚፈጠረው ቀውስ ምክንያት ሆነዋል። አዳምና ሔዋን ለራስ ወዳድነት ምኞታቸው በመሸነፍ ኃጢአት በመፈጸማቸው ‘ኀጢአት ወደ ዓለም ገባ።’ (ሮሜ 5:12) ብዙም ሳይቆይ ሰው “የልቡም ሐሳብ ዘወትር ወደ ክፋት ብቻ ያዘነበለ” እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘው የታሪክ መዝገብ ይናገራል።—ዘፍጥረት 6:5

በሰው ልጅ ባሕርይ ረገድ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ምንም ያህል ለውጥ አልታየም። ትዳርን ለችግር ከሚዳርጉት አጥፊ ዝንባሌዎች መካከል በራስ ወዳድነት የግል ደስታን ማሳደድ ይገኝበታል። አዲስ ሥነ ምግባራዊ አቋም እየተከተለ ባለው ዘመናዊ ዓለም ውስጥ ጋብቻ ራሱም ቢሆን ሊሠራ የማይችልና ጊዜ ያለፈበት ተቋም መስሎ ሊታይ ይችላል። ጋብቻን ከማፍረስ ጋር የተያያዙት ሕጎች መላላትም ቀደም ሲል መፋታት ያስከትል የነበረውን መጥፎ ስምና የሃፍረት ስሜት አስወግዶታል።

የአንድን ነገር ውጤት በቶሎ ለማየትና ወዲያውኑ እርካታ ለማግኘት የሚፈልጉ ትዕግሥት የሌላቸው ግለሰቦች፣ መፋታት የሚያስከትለው መዘዝ እምብዛም አያሳስባቸውም። እንደዚህ ያሉ ግለሰቦች ነፃነትና በራስ ፈቃድ መመራት የሚባለው ማባበያ ስለሚማርካቸው መፋታት ደስታ ያስገኛል ብለው ያምናሉ።

ሌሎች ደግሞ በትዳራቸው ውስጥ እንደ እሾህ ያሉ አስጨናቂ ችግሮች ሲደርሱባቸው፣ ልዩ ሕክምና ይሰጣሉ ወደሚባሉ ሰዎችና የጋብቻ አማካሪዎች ዘንድ በመሄድ ወይም እነዚህ ሰዎች ያዘጋጁዋቸውን መጻሕፍት በማንበብ ምክር ለማግኘት ይጥራሉ። የሚያሳዝነው ግን አንዳንዶቹ ዘመናዊ የጋብቻ ጠበብት ተብዬዎች በአብዛኛው የሚቀናቸው ለጋብቻ ጥብቅና መቆም ሳይሆን ፍቺን ማበረታታት ነው። ዘ ኬዝ ፎር ሜሬጅ የተሰኘው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ሰዎች ሊያገኙት የሚመኙት ነገር የነበረው ትዳር፣ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ምናልባትም ለመጀመሪያ ጊዜ የማያቋርጥና በሚያስገርም ሁኔታ ስኬታማ የሆነ ጥቃት እየደረሰበት ነው። አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ያለው ጥቃት ቀጥተኛና በአንድ የተወሰነ ጽንሰ ሐሳብ ላይ የተመሠረተ ሲሆን ጥቃቱን የሚሰነዝሩትም ለትዳር ጓደኛ ታማኝ ሆኖ ለመኖር የዕድሜ ልክ ቃል ኪዳን መግባት የማይሆን ነገር ወይም ጭቆና እንደሆነ የሚያምኑ ጠበብት ተብዬዎች ናቸው።”

ስለ ጋብቻ የነበረው ግንዛቤ ተቀይሯል

ሰዎች ስለ ጋብቻ ባሕርይና ዓላማ የነበራቸው ግንዛቤም ተቀይሯል። ለትዳር ጓደኛ ታማኝና ደጋፊ መሆን ጉልህ ሥፍራ የሚሰጠው ነገር መሆኑ ቀርቶ በምትኩ በትዳር ጓደኛ ላይ ተረማምዶ የራስን እርካታ ብቻ መፈለግ እየተዘወተረ መምጣቱን ሳትታዘብ አልቀረህም። ይህ ዓይነቱ ጋብቻን ከግል ጥቅም አንጻር ብቻ የመመልከት አዝማሚያ “በ1960ዎቹ ጀምሮ በ1970ዎቹ ተባብሶ እንደቀጠለ” ሜሬጅ ኤንድ ፋሚሊ የተሰኘው መጽሔት ይናገራል። ድሮ ድሮ ለማግባት ምክንያት የሚሆነው ሰዎች፣ እንደ ፍቅርና ታማኝነት እንዲሁም የቅርብ ወዳጅነት የመሳሰሉትን ነገሮች ለማግኘት እንዲሁም ልጅ ለመውለድና የጋራ ግቦችን ለማሳካት የነበራቸው ፍላጎት ሲሆን በዛሬው ጊዜ ግን እነዚህ ግፊቶች ኃይላቸው ተዳክሟል።

በቅርብ ጊዜያት የታዩ አያሌ ክስተቶችም በብዙ አገሮች በጋብቻ ላይ የደረሰውን ከፍተኛ ለውጥ አፋጥነውታል። አንደኛ፣ በብዙ አገሮች ወንዱ አባወራ፣ ሴቷ ደግሞ የቤት እመቤት በመሆን የነበራቸው ባሕላዊ የሥራ ድርሻ ተለውጧል። ሴቶች ከቤት ውጪ ተቀጥረው መሥራታቸው ባልና ሚስት ሠራተኛ የሆኑባቸው ቤተሰቦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አድርጓል። ሁለተኛ፣ ከጋብቻ ውጪ ልጆችን መውለድ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱ በአንድ ወላጅ ብቻ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች እንዲበራከቱ ምክንያት ሆኗል። ሦስተኛ፣ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ሳይጋቡ አብሮ መኖርን የጋብቻ ምትክ አድርጎ የመመልከት አዝማሚያ እየተስፋፋ መጥቷል። (“የጋብቻን ያህል አስተማማኝ አይደለም” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) አራተኛ፣ ተመሳሳይ ጾታ ያላቸው ሰዎች መጋባትና እንዲህ ያለውን ጋብቻ ሕጋዊ ለማድረግ የሚደረገው እንቅስቃሴ ሰፊ ተቀባይነት እያገኘ ነው። እነዚህ ዘመናዊ አዝማሚያዎች ለጋብቻ ባለህ አመለካከት ላይ ተጽዕኖ አድርገውብሃል?

የፍቺ ቁጥር መጨመር

መፋታት ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱ ጋብቻን ይበልጥ የሸረሸረው እንዴት እንደሆነ ለመረዳት በብዙ አገሮች ያለውን የፍቺ ሁኔታ እንመልከት። በቅርቡ የወጣ ሪፖርት እንዳመለከተው በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ “የተፋቱ ሰዎች ቁጥር በ1970ና በ1996 መካከል ባለው ጊዜ በአራት እጥፍ ጨምሯል።” በግምት ከአምስት ሰዎች ውስጥ የአንዱ ትዳር በፍቺ ፈርሷል። ለትዳር መፍረስ ይበልጥ የሚጋለጡት እነማን ናቸው? በፍቺ ካከተሙት ጋብቻዎች ውስጥ 60 በመቶ የሚሆኑት የፈረሱት በመጀመሪያዎቹ አሥር ዓመታት ውስጥ እንደሆነ አኃዛዊ መረጃዎቹ ያሳያሉ።

በሌሎች አገሮችም የፍቺ ቁጥር አሻቅቧል። በ2004 በእንግሊዝና በዌልስ የተፈጸመው ፍቺ ጠቅላላ ቁጥር 153,490 ደርሶ ነበር። በአውስትራሊያም ከሚፈጸመው ጋብቻ ውስጥ 40 በመቶ የሚሆነው በፍቺ እንደሚደመደም ይገመታል። በኮሪያ ሪፑብሊክ በ2003 167,100 ባለትዳሮች የተፋቱ ሲሆን ይህም በ2002 ከተፋቱት ሰዎች በ21,800 ይበልጣል። ከአራት ትዳሮች ውስጥ አንዱ በሚፈርስባት በጃፓን አሁን ያለው የፍቺ ቁጥር ከአውሮፓ ጋር እኩል ሊሆን ነው። “ቀደም ባሉት ዘመናት ጋብቻ በፍቺ የሚደመደመው ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ካጋጠመ ብቻ ነበር” በማለት በጃፓን ቀይ መስቀል ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ስለ ቤተሰብ የሚያጠኑ ባለሞያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። “አሁን ግን ፍቺ ግለሰቡ በሚመርጠው አኗኗር ላይ የተመካ ቀላል ውሳኔ ሆኗል።”

በብዙ አገሮች ዘመናት ያስቆጠሩ ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ወጎች ለጋብቻ ጥንካሬ ጠቃሚ ድርሻ አበርክተው ነበር። አሁን ግን በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ የመጣውን የፍቺ ማዕበል ሊገቱት አልቻሉም። ለምሳሌ ያህል፣ ጋብቻን እንደ ቅዱስ የምትቆጥረውን የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ተመልከት። በ1983 ቤተ ክርስቲያኗ የጋብቻ ጥምረትን በተመለከተ የነበራትን ሕግ ማላላቷ ካቶሊኮች በቀላሉ እንዲፋቱ በር ከፍቷል። በመሆኑም ከዚያ ጊዜ ወዲህ የጋብቻ ውልን ማፍረስ እየጨመረ መጥቷል።

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የጋብቻን ጥምረት የሚያቆራኙት ገመዶች እየተፈቱ ነው። ይሁን እንጂ ለትዳር መፍረስ መንስኤ የሆኑት ሁሉም ችግሮች በግልጽ የሚታዩ አይደሉም። እንደ እውነቱ ከሆነ በኅብረተሰቡ ዘንድ ተንሰራፍቶ ከሚታየው አጠቃላይ የሆነ የመዋቅር መፈራረስ ሌላ ዋናው የትዳር መፍረስ መንስኤ ከአብዛኛው የሰው ልጅ እይታ የተሰወረ ነው።

የማዕበሉ ስውር መንስኤ

የራስ ወዳድነት ተምሳሌት የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ በዚህ ዓለም ላይ ስውር የሆነና እየጨመረ የሚሄድ ጎጂ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ይህን የሚያደርገው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ከሰማይ ወደ ምድር አካባቢ ስለተጣለና በጣም ስለተቆጣ ነው። በእርግጥም ሰይጣን የቻለውን ያህል ብዙ ‘ወዮታ’ ወይም መከራ ለማምጣት ቆርጦ የተነሳ ሲሆን መለኮታዊ ምንጭ ያለው የጋብቻ ተቋም ደግሞ የቁጣው ዒላማዎች ከሆኑት ነገሮች አንዱ ነው።—ራእይ 12:9, 12

ኢየሱስ፣ ሰይጣን ከሰማይ የሚባረርበትን ጊዜ አስመልክቶ ሲናገር “ክፋት ስለሚገን የብዙ ሰዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል” ብሏል። (ማቴዎስ 24:12) በተመሳሳይም ሐዋርያው ጳውሎስ “ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉ፤ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክሕተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ለዕርቅ የማይሸነፉ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በከንቱ በትዕቢት የተወጠሩ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ” በማለት ጽፏል። (2 ጢሞቴዎስ 3:2-4) እነዚህ አስከፊ ባሕርያት በተወሰነም ደረጃ ቢሆን ባለፉት ዘመናት ሁሉ ነበሩ፤ ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እነዚህ ባሕርያት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ጎልተው እንደሚታዩ ብዙ ሰዎች ይስማማሉ።

የጋብቻን ተቋም እያዋከቡት ካሉት ማዕበሎች አንጻር ራሳችንን ከአደጋ ለመጠበቅ እንዲሁም እውነተኛ ደስታ የሰፈነበትና ዘላቂ ትዳር እንዲኖረን ምን ልናደርግ እንችላለን? የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ይህን ጥያቄ ይመረምራል።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ማንኛውንም የማይፈለግ ነገር መጣል በለመደ ኅብረተሰብ ውስጥ፣ ሰዎች ከሌሎች ጋር ባላቸው ግንኙነትም ተመሳሳይ አመለካከት ሊያዳብሩ ይችላሉ።”—ሳንድራ ዴቪስ፣ የቤተሰብ ሕግ ባለሞያ

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

“የጋብቻን ያህል አስተማማኝ አይደለም”

ተቃራኒ ጾታ ያላቸው ብዙ ሰዎች የጋብቻ ውል ሳይኖራቸው አብረው ይኖራሉ። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ጥምረት “የጋብቻን ያህል አስተማማኝ አይደለም” በማለት የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታዎች ቁጥጥርና መከላከያ ማዕከል ያቀረበው ዘገባ ይገልጻል። ከእነዚህ ወንዶችና ሴቶች መካከል አንዳንዶቹ ከጋብቻ በፊት አብረው የሚኖሩት በትዳር ውስጥ የሚጣጣሙ መሆናቸውን ለመገምገም ነው። ሳይጋቡ አብሮ መኖር የማይጣጣሙ ሰዎች ትዳር እንዳይመሠርቱ በመርዳት ከዚያ በኋላ የሚፈጸመውን ጋብቻ ለማሻሻል ይረዳል? ሜሬጅ ኤንድ ፋሚሊ የተሰኘው መጽሔት እንደሚገልጸው ከሆነ ማስረጃው የሚያሳየው ከዚህ በተቃራኒ ነው። “አብረው ሲኖሩ ከቆዩ በኋላ ጋብቻ የፈጸሙ ሰዎች በትዳራቸው ብዙም እንደማይረኩ . . .፣ ችግሮች እንዳሏቸው እንዲሁም . . . ትዳራቸው የመፍረሱ አጋጣሚ ከፍ ያለ እንደሆነ ሪፖርት ተደርጓል” በማለት መጽሔቱ ይናገራል።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የዕድሜ መርዘም በትዳር ላይ ተጽዕኖ የሚያደርገው እንዴት ነው?

ከቀድሞው ዘመን ጋር ሲነጻጸር በአሁኑ ጊዜ ሰዎች ረዥም ዕድሜ ይኖራሉ። አስደሳች ሊሆን የሚገባው ይህ ሁኔታም እንኳን በጋብቻ ላይ ውጥረት ጨምሯል። ቀደም ባሉት ዘመናት ቢሆን ኖሮ በሞት ምክንያት የሚያከትሙ ትዳሮች በዛሬው ጊዜ ግን በፍቺ እየፈረሱ ነው። ለአብነት ያህል፣ በጃፓን ለረዥም ጊዜ በትዳር የኖሩ ሴቶች የተጠናወታቸውን እንግዳ በሽታ ተመልከት። ዘ ዋሽንግተን ፖስት እንደገለጸው በሙያው የተሠማሩ ሰዎች ይህን እንግዳ በሽታ “ሪታየርድ ሃዝባንድ ሲንድረም” (ጡረታ የወጡ ባሎችን የመጥላት አባዜ) ብለው ሰይመውታል። ለ40 ዓመታት በትዳር የኖረች አንዲት ሚስት ባሏ ጡረታ የወጣበትን ጊዜ በማስታወስ በወቅቱ የተሰማትን ስትገልጽ እንዲህ ብላለች:- “ከእንግዲህ እፈታዋለሁ። ሥራ ይውል በነበረበት ጊዜ እንኳ ወደ ቤት ሲመለስ እሱን ማገልገል መርሮኝ ነበር። አሁን ጭራሽ ቀኑን ሙሉ ከእርሱ ጋር ቤት መዋል ልታገሠው ከምችለው በላይ ነው።”