በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለሕመምተኞች ደም በመስጠት የሚደረግ ሕክምና ወደፊት ይቀጥል ይሆን?

ለሕመምተኞች ደም በመስጠት የሚደረግ ሕክምና ወደፊት ይቀጥል ይሆን?

ለሕመምተኞች ደም በመስጠት የሚደረግ ሕክምና ወደፊት ይቀጥል ይሆን?

ለሕመምተኞች ደም በመስጠት የሚደረግ ሕክምና፣ በሐሩር ክልል በሚገኝ ጥቅጥቅ ያለ ጫካ ውስጥ ከመጓዝ ጋር በተወሰነ መጠን እንደተመሳሰለ ይኖራል፤ በጫካዎቹ ውስጥ ያሉት የታወቁ መንገዶች በግልጽ የሚታዩ ቢሆኑም በጥንቃቄ መጓዝ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ያልተጠነቀቁ ሰዎችን ሊጎዱ የሚችሉ አዳዲስና ስውር አደጋዎች ሊኖሩ ይችላሉ።”—ኢየን ፍራንክሊን፣ ለሕመምተኞች ደም በመስጠት የሚደረግ ሕክምና ፕሮፌሰር

ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው የኤድስ ወረርሽኝ በ1980ዎቹ ዓመታት የዓለም ሕዝብ ለደም ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጥ ካደረገ ወዲህ በደም ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉትን “ስውር አደጋዎች” ለማስወገድ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሯል። እንዲህም ሆኖ ታላላቅ እንቅፋቶች እንደተጋረጡ ናቸው። ሰኔ 2005 ላይ የዓለም ጤና ድርጅት “ምንም ችግር የማያስከትል ደም የመውሰዱ አጋጣሚ ከአገር አገር በእጅጉ ይለያያል” በማለት ገልጿል። ድርጅቱ እንዲህ በማለት የገለጸው ለምንድን ነው?

ብዙ አገሮች ደምን ከለጋሾች ለመቅዳት፣ ለመመርመር እንዲሁም ራሱን ደምንና የደም ውጤቶችን ለማጓጓዝ የሚያስችል አስተማማኝ የሆነ የተቀናጀ ፕሮግራም የላቸውም። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ደምና የደም ውጤቶች፣ በደንብ ባልተያዙ የቤት ውስጥ ማቀዝቀዣዎችና ለመዝናናት ወጣ ሲባል ምግብ ለመያዝ በሚያገለግሉ ማቀዝቀዣዎች ውስጥ ለአደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ ይቀመጣሉ! አስተማማኝ የደኅንነት መስፈርቶች ካልወጡ በስተቀር ሕመምተኞች ከሚኖሩበት ቦታ በመቶዎች ወይም በሺዎች በሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቆ ከሚገኝ ሰው በተወሰደው ደም ምክንያት ክፉኛ ሊጎዱ ይችላሉ።

ከበሽታ ነፃ የሆነ ደም—ሊደረስበት የማይችል ግብ

አንዳንድ አገሮች የደም አቅርቦታቸው ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አስተማማኝ እንደሆነ ይናገራሉ። እንዲህም ቢሆን ጥንቃቄ የሚጠይቁ ጉዳዮች አሉ። በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ የደም ጉዳይ የሚመለከታቸው ሦስት ድርጅቶች በሕብረት ያሰራጩት መረጃ በመጀመሪያው ገጹ ላይ እንዲህ ይላል:- “ማስጠንቀቂያ:- ሙሉ ደምና የደም ክፍሎች የተገኙት ከሰው ደም በመሆኑ እንደ ቫይረስ ያሉ በሽታ አስተላላፊ ሕዋሳትን ሊይዙ ይችላሉ። . . . ደም ለጋሾችን በጥንቃቄ መምረጥም ሆነ የላብራቶሪ ምርመራዎች ማድረግ አደጋውን አያስወግዱትም።”

የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማኅበራት ፌዴሬሽን ከፍተኛ ባለ ሥልጣን የሆኑት ፒተር ካረለን “ስለ ደም አቅርቦት አስተማማኝነት በእርግጠኝነት ዋስትና መስጠት ፈጽሞ አይቻልም” የሚል ሐሳብ የሰነዘሩበት በቂ ምክንያት አላቸው። አክለውም “ሁልጊዜ አዲስ በሽታ መከሰቱ የማይቀር ሲሆን እንዲህ በሚሆንበት ወቅት ደግሞ በሽታው መኖሩን ለማወቅ የሚያስችል ምርመራ አይኖርም” ብለዋል።

እንደ ኤድስ ያለ፣ መኖሩ ሳይታወቅ በቫይረሱ ተሸካሚ ግለሰብ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የሚቆይና በደም አማካኝነት በቀላሉ ሊተላለፍ የሚችል አዲስ በሽታ ቢከሰትስ? የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የጤና ተቋማት ውስጥ የሚሠሩት ዶክተር ሃርቪ ክሌይን ሚያዝያ 2005 በፕራግ፣ ቼክ ሪፑብሊክ በተደረገ አንድ የሕክምና ስብሰባ ላይ ንግግር ሲያቀርቡ ወደፊት ሊከሰት የሚችለውን ይህን ሁኔታ አሳሳቢ ብለውታል። አክለውም “የደም ክፍሎችን ከለጋሾች የሚሰበስቡት ሰዎች፣ ደም በመውሰድ ምክንያት የሚከሰቱ ወረርሽኞችን ለመከላከል ያላቸው ብቃት ኤድስ ብቅ ባለበት ዘመን ከነበረው የተሻለ አይደለም” ብለዋል።

ስህተቶችና የደም ከሰውነት ጋር አለመስማማት

በበለጸጉ አገሮች የሚገኙ ሕመምተኞች ደም ከመውሰድ ጋር በተያያዘ ያሉባቸው ከባድ ስጋቶች ምንድን ናቸው? በደም አያያዝ ረገድ የሚሠሩት ስህተቶችና የተወሰደው ደም ከሰውነት በሽታ መከላከያ ጋር ሊጋጭ መቻሉ ናቸው። ግሎብ ኤንድ ሜይል የተባለ ጋዜጣ በካናዳ በ2001 የተደረገን አንድ ጥናት በማስመልከት እንደዘገበው ለሕመምተኞች ደም ከመስጠት ጋር በተያያዘ “በስህተት ከሌላ በሽተኛ የደም ናሙና በመወሰዱ፣ ናሙናዎች ላይ የተሳሳተ ምልክት በመለጠፉና ሕመምተኛው ሳያስፈልገው ደም እንዲወስድ በመታዘዙ” ሞት ሊያስከትሉ ይችሉ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ስህተቶች ተከስተዋል። እንዲህ ባሉት ስህተቶች ምክንያት በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከ1995 እስከ 2001 ባሉት ጊዜያት ቢያንስ ቢያንስ የ441 ሰዎች ሕይወት ተቀጥፏል።

የሌላን ሰው ደም የሚወስዱ ሰዎች፣ የሌላ ሰው አካል የተተካላቸው ግለሰቦች ለሚያጋጥማቸው ዓይነት አደጋ የተጋለጡ ናቸው። የሰውየው በሽታን የመቋቋም ተፈጥሯዊ ኃይል ባዕዱን አካል ላይቀበል ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ደም መውሰድ በሽታ የመቋቋም ተፈጥሯዊ አቅምን ሊያሳጣ ይችላል። ይህ ሁኔታ ሕመምተኛው ከቀዶ ሕክምና በኋላ ለበሽታ እንዲዳረግና ቀደም ሲል በሰውነቱ ውስጥ ቢኖሩም ጉዳት የማያስከትሉበት በነበሩ ቫይረሶች እንዲጠቃ ምክንያት ሊሆን ይችላል። በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሱት ፕሮፌሰር ኢየን ፍራንክሊን ሐኪሞች “ለታካሚዎች ደም ከመስጠታቸው በፊት አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሁለት ሦስቴ ማሰብ” እንደሚገባቸው ማበረታታታቸው ምንም አይገርምም።

ባለሙያዎች አመለካከታቸውን በግልጽ እየተናገሩ ነው

ቁጥራቸው እያደገ የመጣው እንዲህ ያለ እውቀት ያላቸው የጤና አጠባበቅ ሠራተኞች፣ ለሕመምተኞች ደም በመስጠት የሚደረግ ሕክምናን በተመለከተ ከፍተኛ ጥንቃቄና ማስተዋል የተሞላበት ግምገማ እያደረጉ ነው። ዴይሊይስ ኖትስ ኦን ብለድ የተባለ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ሲል ዘግቧል:- “አንዳንድ ሐኪሞች፣ የሌላ ሰው ደም አደገኛ መድኃኒት እንደሆነና ለሌሎች መድኃኒቶች በወጣው መስፈርት ቢመዘን ጥቅም ላይ እንዳይውል ይታገድ እንደነበር ይናገራሉ።”

ብሩስ ስፒስ የተባሉ ፕሮፌሰር፣ የልብ ቀዶ ሕክምና ለሚደረግላቸው ሕመምተኞች ዋና ዋና የደም ክፍሎችን ስለመስጠት በ2004 መገባደጃ ላይ እንዲህ ብለዋል:- “ደም በመስጠት የሚደረግ ሕክምና ለሕመምተኛው የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኝ በእርግጠኝነት የሚገልጹ [የሕክምና] ጽሑፎች አሉ ቢባል እንኳን በጣም ጥቂት ናቸው።” እኚሁ ሰው እንደጻፉት እንዲያውም “ከባድ የመቁሰል አደጋ ሲያጋጥም ካልሆነ በስተቀር” ለሕመምተኞች ደም መስጠት “በኒሞኒያ፣ በኢንፌክሽን፣ በልብ ድካምና በአንጎል ውስጥ ደም መፍሰስ የመጠቃትን አጋጣሚ” ስለሚጨምር “ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል።”

ብዙ ሰዎች ደም መስጠትን በተመለከተ የወጡት መመሪያዎች የሚጠበቀውን ያህል ወጥ አለመሆናቸውን ሲያውቁ ይገረማሉ። ጌብሪየል ፔድራሳ የተባሉ ዶክተር በቅርቡ በቺሊ ለሚገኙ የሥራ ባልደረቦቻቸው “ለሕመምተኞች ደም መስጠት ግልጽ መመሪያ የሌለው ሕክምና ነው” ብለዋቸዋል። ይህ ሁኔታ “በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸውን መመሪያዎች . . . ተግባራዊ ማድረጉን አስቸጋሪ ያደርገዋል” ሲሉ አክለው ገልጸዋል። የኤድንበርግና የስኮትላንድ የደም አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ብራየን መክላለንድ “ደም መስጠት የአንድን ሰው አካል ለሌላው መተካት በመሆኑ ቀላል ጉዳይ እንዳልሆነ” እንዲያስታውሱ ለሐኪሞች መናገራቸው ምንም አያስገርምም። ዶክተሮች “ሕመምተኛው እኔ ወይም ልጄ ብንሆን ኖሮ ደም እንድንወስድ እስማማለሁ?” የሚል ጥያቄ እንዲያነሱ ሐሳብ አቅርበዋል።

እንደ እውነቱ ከሆነ፣ በርካታ የጤና አጠባበቅ ሠራተኞች ለንቁ! መጽሔት አዘጋጆች የሚከተለውን ሐሳብ ከሰጡት ስለ ደም የሚያጠኑ ባለሙያ (hematologist) ጋር ተመሳሳይ አመለካከት አላቸው፤ እኚህ ሰው እንዲህ ብለዋል:- “ለሕመምተኞች ደም መስጠትን በሚጠይቅ ሕክምና ላይ የምንሠራ ዶክተሮች፣ ደም መውሰድም ሆነ ለሕመምተኞቻችን መስጠት አንፈልግም።” በሕክምናው ዓለም በሚገባ የሠለጠኑ አንዳንድ ባለሙያዎች ያላቸው ስሜት ይህ ከሆነ ታካሚዎችስ ምን ሊሰማቸው ይገባል?

ሕክምናው ይቀየር ይሆን?

‘ለሕመምተኞች ደም በመስጠት የሚከናወን ሕክምና በርካታ አደጋዎች ቢኖሩትም፣ በተለይ ደግሞ ሌሎች አማራጮች እያሉ አሁንም በስፋት ጥቅም ላይ የሚውለው ለምንድን ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ይህ የሆነበት አንዱ ምክንያት በርካታ ሐኪሞች የሕክምና ዘዴዎችን ለመለወጥ ፈቃደኞች ባለመሆናቸው ወይም ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ያለ ደም የሚደረጉ አማራጭ ሕክምናዎች መኖራቸውን ባለማወቃቸው ነው። ትራንስፊውዥን በሚባል መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ እንደዘገበው “ሐኪሞች ደም ለመስጠት የሚወስኑት ቀደም ሲል ባገኙት ትምህርት፣ ከሌሎች ሐኪሞች በወረሱት እውቀትና ‘በምርመራ ውጤት’ ላይ ተመሥርተው ነው።”

በተጨማሪም የቀዶ ሕክምና ዶክተሩ ችሎታ በሕክምናው ወቅት በሚፈሰው የደም መጠን ላይ የሚያመጣው ለውጥ አለ። በለንደን፣ እንግሊዝ የሚገኙ ቤቨርሊ ሃንት የሚባሉ ዶክተር እንደሚከተለው ብለዋል:- “በሕክምና ወቅት የሚፈሰው ደም ቀዶ ሕክምናውን እንደሚያከናውነው ባለሙያ በእጅጉ ይለያያል፤ በመሆኑም በቀዶ ሕክምና ወቅት የደም መፍሰስን ማስቆም የሚቻልባቸውን ዘዴዎች በተመለከተ ለቀዶ ሐኪሞች በቂ ማሠልጠኛ የመስጠቱ አስፈላጊነት እየጨመረ ሄዷል።” ሌሎች ደግሞ ደም ከመውሰድ ውጪ ያሉት አማራጭ ዘዴዎች ዋጋቸው በጣም ከፍተኛ እንደሆነ ይናገራሉ፤ ሆኖም ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ሁኔታው ከዚህ ተቃራኒ ነው። የሆነ ሆኖ በርካታ ሐኪሞች ዶክተር ማይክል ሮዝ የተባሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ከተናገሩት ከሚከተለው አባባል ጋር ይስማማሉ:- “እንደ እውነቱ ከሆነ ደም ሳይወስድ የታከመ ማንኛውም ሕመምተኛ፣ አለ የሚባለው ከፍተኛ ጥራት ያለው ሕክምና ተደርጎለታል።” *

አንተስ የምትፈልገው ከፍተኛ ጥራት ያለው ሕክምና አይደለም? ከሆነ ይህንን መጽሔት ከሰጡህ ሰዎች ጋር የምትመሳሰልበት መንገድ አለ። ደም መውሰድን በተመለከተ ስላላቸው ለየት ያለ አቋም ለማወቅ እባክህ የሚቀጥለውን ርዕስ አንብብ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.19 በገጽ 8 ላይ የሚገኘውን “ደም መውሰድን የሚተኩ አማራጭ ሕክምናዎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

‘ሐኪሞች ለታካሚዎች ደም ከመስጠታቸው በፊት አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሁለት ሦስቴ ማሰብ ይኖርባቸዋል።’ፕሮፌሰር ኢየን ፍራንክሊን

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ሕመምተኛው እኔ ወይም ልጄ ብንሆን ኖሮ ደም እንድንወስድ እስማማለሁ?”ብራየን መክላለንድ

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ደም መውሰድ በሚያስከትለው ከፍተኛ የሳምባ ጉዳት ሳቢያ መሞት

ደም መውሰድ የሚያስከትለው ከፍተኛ የሳምባ ጉዳት (Transfussion-related acute lung injury) የታወቀው በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነበር፤ ይህ ለሕይወት አስጊ የሆነ ችግር የሚከሰተው ሰውነት የተወሰደውን ደም ሳይቀበለው ሲቀር ነው። በዚህ ችግር ሳቢያ በየዓመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሚሞቱ በአሁኑ ጊዜ ታውቋል። ነገር ግን በርካታ የጤና ሠራተኞች ምልክቶቹን ስለማያውቋቸው የሟቾቹ ቁጥር ከዚህ በእጅጉ እንደሚበልጥ ባለሙያዎች ይገምታሉ። እንዲህ ዓይነቱ የሳምባ ጉዳት የሚፈጠረው ለምን እንደሆነ ባይታወቅም ኒው ሳይንቲስት መጽሔት እንደዘገበው፣ ይህ እንዲከሰት የሚያደርገው ደም “በዋነኝነት የሚገኘው . . . በተደጋጋሚ ደም እንደ መውሰድ ባሉ ምክንያቶች የተነሳ ቀደም ሲል ለተለያዩ የደም ዓይነቶች ተጋልጠው ከነበሩ ሰዎች” ነው። አንድ ዘገባ እንደሚያሳየው ደም በመውሰድ ምክንያት የሚከሰት ከፍተኛ የሳምባ መጎዳት፣ በዩናይትድ ስቴትስና በብሪታንያ ደም ከመውሰድ ጋር በተያያዘ ለሚከሰተው ሞት ዋነኛ ምክንያት ከሆኑት ነገሮች አንዱ ሲሆን ይህም “ለደም ባንኮች እንደ ኤች አይ ቪ ካሉት በሰፊው ከሚታወቁት በሽታዎች የባሰ ችግር” ሆኖባቸዋል።

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕላዊ መግለጫ]

ደምን ያስገኙት ንጥረ ነገሮች

በጠቅላላው ሲታይ ደም ለጋሾች የሚሰጡት ሙሉውን ደም ነው። ብዙውን ጊዜ ግን ፕላዝማ ብቻ ይለግሳሉ። በአንዳንድ አገሮች ሙሉው ደም ለታካሚዎች ቢሰጥም ደሙ ከመመርመሩና ለሕመምተኞች ደም በመስጠት ለሚከናወን ሕክምና ከመዋሉ በፊት በዋና ዋና ክፍሎቹ መከፋፈልም በጣም የተለመደ ነው። አራቱን ዋና ዋና የደም ክፍሎች፣ ተግባራቸውንና እያንዳንዱ ዋና ክፍል ከጠቅላላው ደም ምን ያህል እንደሚሆን ልብ በል።

ፕላዝማ ከጠቅላላው ደም ውስጥ ከ52 እስከ 62 በመቶ የሚሆነው ፕላዝማ ነው። ፕላዝማ የደም ሕዋሳትን፣ ፕሮቲኖችንና ሌሎች ንጥረ ነገሮችን በመያዝ የሚያጓጉዝ ፈዛዛ ቢጫ ቀለም ያለው ፈሳሽ ነው።

ከፕላዝማ ውስጥ 91.5 በመቶ የሚሆነው ውኃ ነው። ሰባት በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የተለያዩ ፕሮቲኖች ሲሆኑ የፕላዝማ ክፍልፋዮች የሚገኙት ከእነዚህ ነው። (ፕሮቲኖቹ 4 በመቶ አልቡሚን፣ 3 በመቶ ገደማ ግሎቡሊንና ከአንድ በመቶ ያነሰ መጠን ያለው ፋይብሪነጅን ናቸው።) ቀሪው 1.5 በመቶ የሚሆነው የፕላዝማ ክፍል የተሠራው እንደ አልሚ ምግቦች፣ ሆርሞኖች፣ የምንተነፍሳቸው ጋዞች፣ ኤሌክትሮላይቶች፣ ቫይታሚኖችና ናይትሮጅን ነክ ቆሻሻዎች ካሉ ሌሎች ንጥረ ነገሮች ነው።

ነጭ የደም ሕዋሳት ነጭ የደም ሕዋሳት ከሙሉው ደም ውስጥ ከአንድ በመቶ ያነሱ ናቸው። እነዚህ ሕዋሳት ወደ ሰውነት ውስጥ የገቡ ሊጎዱ የሚችሉ አካላትን በማጥቃት ያጠፋሉ።

ፕሌትሌቶች ፕሌትሌቶች ከሙሉው ደም ውስጥ ከአንድ በመቶ ያነሱ ናቸው። ፕሌትሌቶች በቆሰለ ሰውነት በኩል ደም እንዳይፈስ ለማገድ ደምን ያረጋሉ።

ቀይ የደም ሕዋሳት ከሙሉው ደም ውስጥ ከ38 እስከ 48 በመቶ የሚሆኑት ቀይ የደም ሕዋሳት ናቸው። እነዚህ ሕዋሳት፣ ሕብረ ሕዋስ ውስጥ ኦክስጅንን ያስገባሉ፤ ካርቦን ዳይኦክሳይድን ደግሞ ያስወጣሉ። በዚህ መንገድ ሕብረ ሕዋሱ በሕይወት እንዲቀጥል ያደርጋሉ።

ፕላዝማ የተለያዩ ንጥረ ነገሮችን ሊያስገኝ እንደሚችል ሁሉ ከሌሎቹ ዋና ዋና የደም ክፍሎችም ጥቃቅን ክፍልፋዮችን ማዘጋጀት ይቻላል። ለምሳሌ ያህል፣ ሄሞግሎቢን ከቀይ የደም ሕዋስ የሚገኝ ክፋይ ነው።

[ሥዕላዊ መግለጫ]

ፕላዝማ

ውኃ 91.5%

ፕሮቲኖች 7%

አልቡሚን

ግሎቡሊን

ፋይብሪነጅን

ሌሎች ንጥረ ነገሮች 1.5%

አልሚ ምግቦች

ሆርሞኖች

የምንተነፍሳቸው ጋዞች

ኤሌክትሮላይቶች

ቫይታሚኖች

ናይትሮጅን ነክ ቆሻሻዎች

[ምንጭ]

ገጽ 9:- በክብ ቅርጾች ውስጥ ያሉት ደምን ያስገኙ ንጥረ ነገሮች:- This project has been funded in whole or in part with federal funds from the National Cancer Institute, National Institutes of Health, under contract N01-CO-12400. The content of this publication does not necessarily reflect the views or policies of the Department of Health and Human Services, nor does mention of trade names, commercial products, or organizations imply endorsement by the U.S. Government

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ደም መውሰድን የሚተኩ አማራጭ ሕክምናዎች

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ፣ የይሖዋ ምሥክሮች የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች ላለፉት ከስድስት የሚበልጡ ዓመታት ትራንስፊውዥን ኦልተርኔቲቭ ስትራቴጂስ—ሲምፕል፣ ሴፍ፣ ኢፌክቲቭ (በደም ምትክ የሚሠራባቸው የሕክምና ዘዴዎችቀላል፣ አስተማማኝና ውጤታማ) የሚለውን የቪዲዮ ፊልም በአሥር ሺዎች የሚቆጠር ቅጂ በሕክምና መስክ ለተሠማሩ ሰዎች ያሰራጩ ሲሆን ፊልሙ ወደ 25 ገደማ በሚሆኑ ቋንቋዎች ይገኛል። * ፊልሙ፣ በአሁኑ ጊዜ እየተሠራባቸው ያሉ ያለ ደም የሚደረጉ ውጤታማ የሕክምና ዘዴዎችን በተመለከተ በዓለም ታዋቂ ከሆኑ ሐኪሞች ጋር ውይይት ሲደረግ ያሳያል። ሰዎች በቪዲዮ ፊልሙ ላይ ለተገለጸው መልእክት ትኩረት እየሰጡ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘው ብሔራዊ የደም አገልግሎት በ2001 መጨረሻ ላይ ፊልሙን ካየ በኋላ የዚህን ፊልም ቅጂ ከደብዳቤ ጋር አያይዞ በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ለሚገኙ የደም ባንክ ሥራ አስኪያጆችና አማካሪ ሂማቶሎጂስቶች (ስለ ደም የሚያጠኑ ባለሙያዎች) በሙሉ ልኳል። “የጥሩ ሕክምና አንዱ ዓላማ በተቻለ መጠን ለሕመምተኞች ደም አለመስጠት መሆኑ ይበልጥ እውቅና እየተሰጠው” ስለመጣ ባለሙያዎቹ ፊልሙን እንዲመለከቱ ተበረታተዋል። “[የፊልሙ] አጠቃላይ መልእክት ምስጋና ሊቸረው የሚገባና ብሔራዊ የደም አገልግሎት አጥብቆ የሚደግፈው ነው” በማለት ደብዳቤው ይገልጻል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.57 ትራንስፊውዥን ኦልተርኔቲቭስ—ዶክዩመንትሪ ሲሪስ (በደም ምትክ የሚሰጡ ሕክምናዎች—ተከታታይ ጥናታዊ ፊልሞች) የሚል ርዕስ ያለውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ ዲቪዲ መመልከት ከፈለጉ የይሖዋ ምሥክሮችን መጠየቅ ይችላሉ። በዚህ ዲቪዲ ውስጥ ከላይ የተጠቀሰው ፊልምም ይገኛል።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ደምን መከፋፈል ጥቃቅን የደም ንጥረ ነገሮችን ለሕክምና መጠቀም

ሳይንስና ቴክኖሎጂ ፍራክሽኔሽን በሚባለው ዘዴ አማካኝነት የደም ክፍልፋዮችን ለማወቅና ለመለያየት አስችሏል። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ ከባሕር ውኃ ውስጥ 96.5 በመቶውን የሚሸፍነው ንጹሕ ውኃ ሲሆን ፍራክሽኔሽን በሚባለው ዘዴ በመጠቀም እንደ ማግኒዚየም፣ ብሮሚንና ጨው ያሉትን ሌሎች ንጥረ ነገሮች ለይቶ ማውጣት ይቻላል። በተመሳሳይም ከሙሉው ደም ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ፕላዝማ ነው፤ ከፕላዝማ ውስጥ ደግሞ ከ90 በመቶ የሚበልጠው ውኃ ሲሆን የቀሩትን እንደ አልቡሚን፣ ፋይብሪነጅንና የተለያዩ ዓይነት ግሎቡሊኖች ያሉ ፕሮቲኖችን ጨምሮ ሌሎች ንጥረ ነገሮችን ለይቶ ማውጣት ይቻላል።

አንድ ዶክተር ሕክምና ሲያደርግ አንዱን የፕላዝማ ክፋይ በብዛት መውሰድ እንደሚያስፈልግ ሐሳብ ሊያቀርብ ይችላል። ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን ፕላዝማን በረዶ በማድረግና ከዚያም በማቅለጥ የሚገኘው በፕሮቲን የበለጸገው ክራዮፕሪሲፒቴት ነው። ይህ የማይቀልጥ የፕላዝማ ክፍል አርጊ የሆኑ ነገሮች በብዛት የሚገኙበት ሲሆን በአብዛኛው የሚሰጠው ሕመምተኞች ያጋጠማቸውን የደም መፍሰስ ለማስቆም ነው። እንዲሁም በዋነኝነት ከደም ክፍልፋዮች የተቀመሙ ወይም እነዚህ ክፍልፋዮች በትንሹ የተጨመሩባቸው መድኃኒቶችን በመስጠት ጭምር የሚደረጉ ሕክምናዎችም አሉ። * አንዳንድ የፕላዝማ ፕሮቲኖች ደግሞ ለበሽታ ለሚዳርጉ ተሕዋስያን ተጋልጠው የነበሩ ሰዎችን በሽታ የመከላከል አቅም ለማሳደግ ሲባል በመርፌ በተደጋጋሚ ይሰጣሉ። ለሕክምና የሚያገለግሉ ሁሉም የደም ክፍልፋዮች ለማለት ይቻላል በደም ፕላዝማ ውስጥ የሚገኙ ፕሮቲኖችን ይይዛሉ።

ሳይንስ ኒውስ እንደዘገበው ከሆነ “በአብዛኛው በደም ውስጥ አሉ ተብለው ከሚገመቱት በሺዎች ከሚቆጠሩ ፕሮቲኖች ውስጥ ሳይንቲስቶች ለይተው ያወቁት በመቶዎች የሚቆጠሩትን ብቻ ነው።” ወደፊት ደምን በተመለከተ ያለው ግንዛቤ ባደገ መጠን ከእነዚህ ፕሮቲኖች የተሠሩ በርካታ አዳዲስ መድኃኒቶች ብቅ ይሉ ይሆናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.63 የእንስሳት ደም ክፍልፋዮችም በአንዳንድ መድኃኒቶች ውስጥ ይጨመራሉ።

[በገጽ 6, 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አብዛኞቹ የሕክምና ባለሙያዎች ደም እንዳይነካቸው በጣም ይጠነቀቃሉ