በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ሲሞቱ መላእክት ይሆናሉ ብሎ ያስተምራል?

መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ሲሞቱ መላእክት ይሆናሉ ብሎ ያስተምራል?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ሲሞቱ መላእክት ይሆናሉ ብሎ ያስተምራል?

ንሿ አርዪሮ ገና የሰባት ዓመት ልጅ እያለች በሞት አንቀላፋች። በሐዘን የተደቆሱት ወላጆቿ ነጭ ልብስ ለብሶ በሬሳ ሣጥን ውስጥ የተቀመጠውን አስከሬኗን ትኩር ብለው ይመለከታሉ። እነርሱን ለማጽናናት በማሰብ የቤተ ክርስቲያኑ አገልጋይ “አምላክ ሌላ መልአክ ስላስፈለገው ትንሿ አርዪሮ ከእርሱ ጋር እንድትሆን ወስዷታል። አሁን ነፍሷ ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ዙፋን ዙሪያ እየበረረች ነው” አላቸው።

መላእክት የሞቱ ሰዎች ነፍስ እንደሆኑ የሚያስተምሩት ሃይማኖቶች ጥቂት ቢሆኑም በዚህ ትምህርት አጥብቀው የሚያምኑ ብዙ ሰዎች አሉ። የመዝናኛው ዓለምም ለሕያዋን እርዳታና ጥበቃ በማድረጋቸው ‘መላእክት ስለሆኑ’ የሞቱ ሰዎች የሚገልጹ ፊልሞችንና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን በማቅረብ ይህ አመለካከት ሰፊ ተቀባይነት እንዲያገኝ አድርጓል።

የምትወዳቸው ሰዎች ሲሞቱ መላእክት ይሆናሉ ብለህ በእርግጠኝነት ትጠብቃለህ? መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ ምን ያስተምራል? እስቲ መልሱን ለማግኘት በመጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መላእክት እንዲሁም ሙታን ስለሚገኙበት ትክክለኛ ሁኔታ ምን እንደሚል እንመርምር።

መላእክት—ልዩ የሆኑ ፍጥረታት

መላእክት የማይታዩና በመንፈሳዊው ዓለም የሚኖሩ ኃያላን የአምላክ አገልጋዮች ናቸው። ሕልውናቸው የተመካውም በሰዎች ላይ አይደለም። መላእክት በአምላክ የተፈጠሩ ሲሆኑ መንፈሳዊ አካል አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መላእክት ሲናገር “እርሱ ስላዘዘ ተፈጥረዋልና፣ የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑት” ይላል።—መዝሙር 148:2, 5

መጽሐፍ ቅዱስ ሱራፌልንና ኪሩቤልን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ታማኝ መላእክት በየደረጃቸው የተሰጣቸውን ኃላፊነት በታዛዥነት እንደሚወጡ ይናገራል። (መዝሙር 103:20, 21፤ ኢሳይያስ 6:1-7፤ ዳንኤል 7:9, 10) አምላክ እነዚህን ሁሉ መላእክት ወደ ሕልውና ለማምጣት ሲል ሰዎች እንዲሞቱ አድርጓል ማለት ነው? እርግጥ ነው፣ ይህ ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ነገር ነው። ለምን?

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው መላእክት የተፈጠሩት ሰዎች ወደ ሕልውና ከመምጣታቸው ከረጅም ጊዜ በፊት ነው። ይሖዋ ከጊዜ በኋላ የሰው ልጆች መኖሪያ የምትሆነውን ምድርን ሲፈጥር፣ በንጋት ከዋክብት የተመሰሉት መላእክት ‘ዘምረዋል እንዲሁም እልል ብለዋል።’ (ኢዮብ 38:4-7) ስለዚህ መላእክት የሰው ልጅ ምድር ላይ ከመፈጠሩ በፊት ሕልቆ መሳፍርት ለሌላቸው ዘመናት ኖረዋል።

ከዚህም በላይ መላእክትና ሰዎች በአፈጣጠራቸው በጣም የሚለያዩ ሲሆኑ በይሖዋ ዓላማ ውስጥ ያላቸው ቦታም የተለያየ ነው። * አምላክ ሰውን የፈጠረው ‘ከመላእክት ጥቂት አሳንሶ’ በመሆኑ እነዚህ መንፈሳዊ ፍጡራን ከሰዎች የበለጠ የአእምሮ ችሎታና ኃይል አላቸው። (ዕብራውያን 2:7) መላእክት ትክክለኛ “መኖሪያቸው” ሰማይ ነው። (ይሁዳ 6) ሰዎችን በተመለከተ ግን የአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ በምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ ነበር። (ዘፍጥረት 1:28፤ 2:17፤ መዝሙር 37:29) የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ለአምላክ ቢታዘዙ ኖሮ በፍጹም አይሞቱም ነበር። ከዚህ ማየት እንደሚቻለው፣ ከመጀመሪያው ጀምሮ መላእክትና ሰዎች በአምላክ ዓላማ ውስጥ የተለያየ ቦታ ነበራቸው።

ሰዎች ሲሞቱ ምን ይሆናሉ?

ልንመረምራቸው የሚገቡን ሌሎች ጠቃሚ ጥያቄዎች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው:- ሰዎች ሲሞቱ ምን ይሆናሉ? ሌላ አካል ኖሯቸው በሕይወት ይቀጥላሉ? ምናልባትም በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ መላእክት ሆነው ይኖሩ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ “ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን ምንም አያውቁም” በማለት ቀላልና ግልጽ የሆነ መልስ ይሰጣል። (መክብብ 9:5) ስለዚህ ሰው ሲሞት ከሕልውና ውጪ ይሆናል። ይህም ሙታን ምንም የሚያውቁትና የሚሰማቸው ነገር የለም ማለት ነው።

ታዲያ ሙታን ተስፋ አላቸው? አዎን! መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያሳየው በሞት ያንቀላፉ ብዙ ሰዎች የትንሣኤ ተስፋ አላቸው። አብዛኞቹ ሙታን ሰብዓዊ ሕይወት አግኝተው በምድር ላይ በገነት ለዘላለም ለመኖር ይነሳሉ።—ሉቃስ 23:43፤ ዮሐንስ 5:28

ጥቂቶቹ ደግሞ ለሰማያዊ ሕይወት ይነሳሉ። ቁጥራቸውም አነስተኛ ሲሆን በአጠቃላይ 144,000 ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ 144,000ዎች መላእክት እያልን ከምንጠራቸው መንፈሳዊ ፍጡሮች የተለዩ ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ እነዚህ 144,000 ሰዎች የማይጠፋ ሕይወት ተሰጥቷቸው ከክርስቶስ ጋር ነገሥታትና ካህናት ይሆናሉ። ፈራጅ የመሆንም መብት አላቸው። (1 ቆሮንቶስ 6:3፤ ራእይ 20:6) ታዲያ እነዚህ የሞቱ ሕፃናት ናቸው? በፍጹም። እስከ መጨረሻው የተፈተኑ የክርስቶስ ተከታዮች ናቸው!—ሉቃስ 22:28, 29

እስቲ የሞቱ ሰዎችንና ሕያዋን መላእክትን እያነጻጸርን እንመልከት። የሞቱ ሰዎች “ምንም አያውቁም”፤ ከዚህ በተቃራኒው ግን መላእክት ራሳቸውን ያውቃሉ፣ ስሜት አላቸው እንዲሁም የፈለጉትን ማድረግ ይችላሉ። የራሳቸውን ምርጫ ማድረግ የሚችሉ ፍጥረታት ናቸው። (ዘፍጥረት 6:2, 4፤ መዝሙር 146:4፤ 2 ጴጥሮስ 2:4) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሙታን ‘እንደጠፉ’ ወይም ምንም ማድረግ እንደማይችሉ የተገለጸ ሲሆን መላእክት ግን “ኀያላን” እንደሆኑ ተደርገው ተገልጸዋል። (ኢሳይያስ 26:14 የ1954 ትርጉም፤ መዝሙር 103:20) ከዚህም በተጨማሪ የአዳም ዝርያ የሆኑት ሰዎች በኃጢአትና በአለፍጽምና ምክንያት የሚሞቱ ሲሆን አምላክን የሚፈሩ መላእክት ግን ፍጹም ከመሆናቸውም በላይ በይሖዋ ፊት የመቆም መብት አላቸው።—ማቴዎስ 18:10

መላእክት የሞቱ ሰዎች ነፍሳት ናቸው የሚለው አመለካከት በቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ወይም በፊልሞች ውስጥ ቢሠራበትም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አይደለም። ከዚህ በላይ በዝርዝር የቀረበው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የምንወዳቸው ሰዎች ሲሞቱ ምን እንደሚሆኑ የሚነገሩትን የተሳሳቱ አመለካከቶች እንድናስወግድ ይረዳናል። ከሰው በተለየ መልኩ የተፈጠሩትና ኃያል የአምላክ አገልጋዮች የሆኑት ታማኝ መላእክት ከሰው የሚበልጥ ኃይል እንዳላቸውና የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም ሁሌም ዝግጁ እንደሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጥልናል። ይሖዋ እርሱን ከልባቸው ለሚያከብሩትና ሊያገለግሉት ለሚፈልጉ ሰዎች፣ መላእክት ጥበቃና እርዳታ እንዲያደርጉላቸው ፈቃዱ መሆኑ ያስደስታል።—መዝሙር 34:7

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.10 “መልአክ” የሚለው ቃል “መልእክተኛ” የሚል ትርጉም አለው፤ ይህ ቃል አንዳንድ ጊዜ ሰፋ ያለ ትርጉም ስለሚሰጠው የአምላክ አገልጋይ የሆኑ መንፈሳዊ ፍጥረታትንና ሰዎችንም ጭምር ለማመልከት ተሠርቶበታል። በዚህ ርዕስ ውስጥ የምንጠቀምበት ግን መጽሐፍ ቅዱስ መላእክት ብሎ የሚጠራቸውን መንፈሳዊ ፍጡራንን ለማመልከት ነው።

ይህን አስተውለኸዋል?

▪ በሞት የተለዩህ የምትወዳቸው ሰዎች አሁን መላእክት ሆነው በሰማይ አምላክን እያገለገሉ ናቸው?—መክብብ 9:5,10

▪ ልጆች የሚሞቱት አምላክ እርሱን የሚያገለግሉትን መላእክት ቁጥር ለመጨመር ብሎ ስለሚወስዳቸው ነው?—ኢዮብ 34:10

▪ ሙታን ሕያዋንን መርዳት ይችላሉ?—ኢሳይያስ 26:14

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“[መላእክት] እርሱ ስላዘዘ ተፈጥረዋልና፣ የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑት።”—መዝሙር 148:2, 5