‘እንደ ሚዳቋ የምዘልበት’ ጊዜ ይመጣል
‘እንደ ሚዳቋ የምዘልበት’ ጊዜ ይመጣል
ፍራንቼስኮ አባቴማርኮ እንደተናገረው
“አምላክ እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ እንዲደርስ ለምን ፈቀደ? ለምን በእኔ ላይ?” እነዚህን ጥያቄዎች ለበርካታ ጊዜያት ጠይቄአለሁ! እጅና እግሬ ሽባ ሆኖ የሕይወት ዘመኔን ሁሉ በተሽከርካሪ ወንበር ላይ የማሳለፉ ነገር ፈጽሞ ሊዋጥልኝ አልቻለም።
የተወለድኩት በ1962 ጣሊያን ውስጥ ባሲሊካታ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በምትገኝ አንዲት አነስተኛ ከተማ ውስጥ ሲሆን በተወለድኩበት ዕለት ሕይወቴ አክትሞ ነበር ለማለት ይቻላል። እናቴ በምጥ ጊዜ ችግር ሲያጋጥማት ዶክተሩ አንዳንድ መድኃኒቶች ወጋት። መድኃኒቶቹ ከባድ የጎንዮሽ ጉዳት ስለነበራቸው ከሦስት ቀናት በኋላ ሰውነቴ ይንዘፈዘፍ ጀመር። እጅና እግሬ ሽባ ከመሆኑም በላይ ድምፅ የሚፈጥረው የጉሮሮዬ ክፍል ጉዳት ደረሰበት።
ዕድሜዬ እየጨመረ ሲመጣ አካላዊ ሁኔታዬ በጣም ያስጨንቀኝ ጀመር። ብስጩ እየሆንኩ የመጣሁ ሲሆን አጠገቤ ባገኘሁት ሰው ሁሉ ላይ በቁጣ እደነፋ ነበር። ከመላው ዓለም እንደተገለልኩ ስለተሰማኝ ሕይወቴ ትርጉም የለሽ ሆነብኝ። በ25 ዓመቴ ከባድ የስሜት ቀውስ ውስጥ ገባሁ። አምላክ ብዙ ሥቃይ እንዲደርስብኝ የፈቀደበት ምክንያት ስላልገባኝ ‘አምላክ የለም’ ወደሚል ትክክል ወደሚመስል መደምደሚያ ደረስኩ።
አመለካከቴ ተለወጠ
በ1987 መገባደጃ ላይ አንድ ቀን ጠዋት ደጃፍ ላይ ቁጭ ብዬ ሳለሁ ጥሩ አለባበስ ያላቸው ሁለት ወጣት ወንዶች ወደ እኔ መጡ። ወንድሜን ለማነጋገር እንደፈለጉ ስለተሰማኝ እንደምንም ተጣጥሬ እቤት እንደሌለ ነገርኳቸው። “እኛ ግን ማነጋገር የፈለግነው አንተን ነው” የሚል ምላሽ ሰጡኝ። እምብዛም እኔን ማነጋገር የሚፈልግ ሰው ስላልነበረ መልሳቸው በጣም አስደነቀኝ።
“በአምላክ ታምናለህ?” ሲሉ ጠየቁኝ። “እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ሆኜ እንዴት ላምን እችላለሁ?” ብዬ በቁጣ መለስኩላቸው። ውይይት ከጀመርን በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን ተረዳሁ። ከዚያም ክሪኤሽን (ሕይወት—እንዴት ተገኘ? በዝግመተ ለውጥ ወይስ በፍጥረት?) * የተባለውን መጽሐፍ ሲሰጡኝ እያቅማማሁ ተቀበልኳቸው። ተመልሰው እንደሚመጡ ነገሩኝ። እኔ ግን ባይመጡ እመርጥ ነበር።
ሁለቱ የይሖዋ ምሥክሮች ቃላቸውን ጠብቀው ስለመጡ ውይይታችንን ቀጠልን። ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ “በዚያን ጊዜም የዕውር ዐይኖች ይገለጣሉ፤ የደንቈሮም ጆሮዎች ይከፈታሉ። አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘላል፤ የድዳውም አንደበት በደስታ ይዘምራል” የሚለውን ኢሳይያስ 35:5, 6ን እንዳነበቡልኝ ትዝ ይለኛል። እነዚህ ቃላት አስደሳች ቢሆኑም አሁን ካለሁበት ሁኔታ ጋር ምንም ግንኙነት ያላቸው አልመሰለኝም። እንደ ሚዳቋ ልዘል ይቅርና ራሴን ችዬ መቆም እንኳ አልችልም። ያም ሆነ ይህ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያስጠኑኝ ተስማማሁ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በጊዜው የነበሩብኝን ችግሮች ይፈታልኛል የሚል እምነት አልነበረኝም። ወደፊት ሙሉ ጤንነት ታገኛለህ የሚለው ተስፋም ቢሆን ፈጽሞ የማይመስል ነገር ሆነብኝ።
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮቹ አካባቢያቸው በሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ እሁድ ቀን በሚደረገው ስብሰባ ላይ እንድገኝ ጋበዙኝ። የተሰጠውን የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር ባላስታውሰውም የይሖዋ ምሥክሮቹ ያደረጉልኝን ሞቅ ያለ አቀባበልና ያሳዩኝን ፍቅር ፈጽሞ አልረሳውም። በሐዘኔታ ዓይን እየተመለከቱ አላሳቀቁኝም። ከዚህ ይልቅ በደስታ ስለተቀበሉኝ ባይተዋርነት አልተሰማኝም።
ያን ዕለት በጣም ስለተደሰትኩ ከመንግሥት አዳራሽ መቅረት እንደሌለብኝ ተገነዘብኩ። በመሆኑም በስብሰባዎች ላይ አዘውትሬ መገኘት ጀመርኩ።እንደ ተራራ ያለን መሰናክል መወጣት
የአምላክን ቃል ማጥናቴ በሕይወቴ ላይ አስደናቂ ለውጥ አምጥቷል። ለእኔ የደረቀ አትክልት እንደገና መለምለም የጀመረ ያህል ነበር። ሞተው ተቀብረዋል ብዬ ያሰብኳቸው ስሜቶች ሲያቆጠቁጡ ይሰማኝ ጀመር። እንደገና ሕያው እንደሆንኩ ተሰማኝ። ያመንኩበትን ግሩም ተስፋ ለሌሎች የማካፈል ምኞት አደረብኝ። (ማቴዎስ 24:14) ይሁንና መስበክ የምችለው እንዴት ነው? ይሖዋ ይህን ምኞቴን እንዳሳካ የሚያስችለኝን መንገድ እንዲያሳየኝ አጥብቄ ለመንኩት።
በመስከረም ወር 1991 አንድ አቅኚ (የሙሉ ጊዜ አገልጋይ) በጉባኤያችን እንዲያገለግል ተመደበ። አንድ ቀን እርሱ ቤት ሳለን የመስበክ ፍላጎት እንዳለኝ አጫወትኩት። በትክክል መናገር ስለሚያቅተኝ በታይፕ ተጠቅሜ ደብዳቤ እንድጽፍ ተነጋገርን። ነገር ግን ሽባ የሆኑት እጆቼ እንቅፋት ሆኑብኝ። በአቅኚው ወንድም እርዳታ በርካታ ዘዴዎችን ሞከርኩ። በጥርሴ እርሳስ ይዤ በታይፑ ላይ የሚገኙትን ፊደላት ለመምታት ሞከርኩ። ከዚያ ደግሞ እላዩ ላይ እንጨት የተያያዘበት ጠንካራ ባርኔጣ አድርጌ ጭንቅላቴን በማንቀሳቀስ የታይፑን ፊደላት ለመምታት ሞከርኩ። ምንም ዓይነት ዘዴ ብሞክር ሊሳካልኝ አልቻለም።
በኋላ ላይ ከአቅኚው ጋር ስለዚሁ ችግር እየተወያየን ሳለ “በጣም ግሩም አፍንጫ አለህ” በማለት ለቀልድ ያህል ተናገረ። ወዲያውኑም በአፍንጫዬ የታይፑን ፊደላት ለመምታት የሞከርኩ ሲሆን ይህ ዘዴ እንደሚሠራ ተገነዘብኩ። በመጨረሻም መጻፍ ቻልኩ። በአፍንጫዬ የፊደል ስህተቶችን ማረም ምን ያህል አድካሚ እንደሚሆን መገመት ትችላላችሁ! ብዙም ሳይቆይ ኮምፒውተር ብጠቀም ችግሬ እንደሚቃለል ተሰማን። ይሁንና ኮምፒውተር የምገዛበት ገንዘብ ከየት ማግኘት እችላለሁ? ምቹ የሆነውን ጊዜ ጠብቄ ወላጆቼን አነጋገርኳቸው። ከጥቂት ጊዜ በኋላም በኮምፒውተር ደብዳቤ መጻፍ ጀመርኩ።
ምኞቴ ተሳካ
መጀመሪያ ለጓደኞቼና ለዘመዶቼ የጻፍኩላቸው ሲሆን ቀጥዬም እኔ ባለሁባት ከተማና በአካባቢዋ ለሚኖሩ ሰዎች ደብዳቤ መጻፍ ጀመርኩ። ብዙም ሳይቆይ በመላው ጣሊያን ከሚገኙ ሰዎች ጋር መጻጻፍ ጀመርኩ። ለደብዳቤዬ መልስ ባገኘሁ ቁጥር የሚሰማኝን የደስታ ስሜት በቃላት መግለጽ ያቅተኛል። በታኅሣሥ 1991 ላይ ያልተጠመቀ የምሥራቹ አስፋፊ እንድሆን ተፈቀደልኝ። ከዚህም በላይ በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ በየሳምንቱ በሚካሄደው ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ተመዘገብኩ። ንግግር እንዳቀርብ ክፍል ሲሰጠኝ ኮምፒውተሬን ተጠቅሜ በጥንቃቄ እዘጋጃለሁ። በስብሰባው ላይ ደግሞ ጓደኛዬ የሆነ አንድ ወንድም ወደ መድረኩ ሄዶ የተዘጋጀሁትን ንግግር ያነብባል።
ይሖዋ ላሳየኝ ፍቅር ያለኝን አድናቆት ለመግለጽ መንፈሳዊ እድገት በማድረግ ራሴን ለአምላክ መወሰንና መጠመቅ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። ራሴን እንደምንም አደፋፍሬ ውሳኔዬን ለወላጆቼ አሳወቅኋቸው። ደስተኞች ባይሆኑም እንኳ ለመጠመቅ የነበረኝ ፍላጎት ከሚሰማኝ ፍርሃት ይበልጥ ነበር። ይሖዋና ክርስቲያን ባልንጀሮቼ ባደረጉልኝ ድጋፍ አማካኝነት ነሐሴ 1992 ተጠመቅሁ። በዚህ ዕለት ወንድሜና ባለቤቱ በመገኘታቸው በጣም ተደስቻለሁ!
የአስተሳሰብ ለውጥ አደረግሁ
በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት መሠረታዊ ሥርዓቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ግልጽ እየሆኑልኝ ሲመጡ የነበሩኝን መጥፎ ባሕርያት የግድ ማስወገድ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። አካላዊ ሁኔታዬ ራስ ወዳድ እንድሆን አድርጎኝ እንደነበር ማስተዋል ጀመርኩ። ይህን ድክመቴን ለማሸነፍም መታገል ነበረብኝ። ይበልጥ ትሑት መሆንና በሌሎች ላይ ጥገኛ መሆኔ የፈጠረብኝን የማያቋርጥ ጭንቀት መቋቋም አስፈልጎኝ ነበር።
ከዚህም በላይ ለራሴ ማዘኔንና ዕድለ ቢስ እንደሆንኩ አድርጌ ማሰቤን ለማቆም ጥረት አደረግሁ። የአንዳንድ
ሁኔታዎችን አስቂኝ ገጽታ በመመልከት ደስተኛ ለመሆን ጥረት ማድረግ ጀመርኩ። አንድ ቀን ከቤት ወደ ቤት እያገለገልኩ ሳለ አንዲት ትንሽ ልጅ በሩን ከፈተች። አብረውኝ ከነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች አንዱ ወላጆቿ እቤት መኖራቸውን ጠየቃት። ከዚያም ልጅቷ ጮክ ብላ “እማዬ፣ ሁለት ሰዎችና አንድ በሽተኛ ሰው በር ላይ ቆመዋል” አለች። እናትየው ስታየኝ በጣም ከማፈሯ የተነሳ የምትለው ነገር ጠፋት። ከጓደኞቼ አንዱ “ለነገሩ ሁለት በሽተኞችና አንድ ጤነኛ ነን” አላት። ሁላችንም ሳቅን። በኋላም ከሴትየዋ ጋር ጥሩ ውይይት አደረግን።ይበልጥ የማገልገል ፍላጎት አደረብኝ
ከተጠመቅሁ በኋላ በስብከቱ ሥራ ላይ በየወሩ 60 ሰዓታት በማሳለፍ ለዘጠኝ ወራት ያህል ረዳት አቅኚ ሆኜ አገለገልኩ። ይሁን እንጂ ከዚህ በላይ ማድረግ እፈልግ ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላም በስብከቱ ሥራ ላይ ተጨማሪ ሰዓታት በማሳለፍ የዘወትር አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። አቅኚነት የጀመርኩባቸው የመጀመሪያዎቹ ወራት በጣም አስቸጋሪ ነበሩ። ብዙ ሰዎች ወደ ቤታቸው የሄድኩት ገንዘብ ልመና እንደሆነ ይሰማቸው ነበር። ይህ ደግሞ እኔንም ሆነ አብረውኝ የሚያገለግሉትን ወንድሞች ያሳቅቀን ነበር።
በተጨማሪም በጉባኤ ያሉ በርካታ ወንድሞችና እህቶች የምናገረውን ነገር ለመረዳት ይቸገሩ የነበረ ከመሆኑም በላይ በምን መንገድ እርዳታ ቢያደርጉልኝ የተሻለ ሊሆን እንደሚችልም አያውቁም ነበር። ይሁንና በይሖዋ እርዳታ እንዲሁም መንፈሳዊ ወንድሞቼና እህቶቼ በደግነት ባደረጉልኝ እገዛ ከጊዜ በኋላ ሁኔታው መሻሻል ጀመረ። አሁን ሰዎች የሚመለከቱኝ በተንቀሳቃሽ ወንበር ላይ እንዳለ ሰው ብቻ ሳይሆን ሌሎች የአምላክን ዓላማ እንዲያውቁ ለመርዳት እንደሚጣጣር አንድ የይሖዋ ምሥክር ነው።
ሐምሌ 1994 በአቅኚነት ለሚያገለግሉ የይሖዋ ምሥክሮች በሚሰጥ የሁለት ሳምንት ልዩ ኮርስ ላይ መካፈል ቻልኩ። በዚህ ኮርስ ላይ የስብከቱንም ሆነ ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ ለማከናወን የሚረዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን አጥንተናል። በተጨማሪም ለአገልግሎታችን የሚጠቅም ተግባራዊ ሥልጠና አግኝተናል። ኮርሱ የሚሰጥበት ቦታ ከመኖሪያ ቤቴ 60 ኪሎ ሜትር ያህል ይርቅ ስለነበር እዚያ ለመገኘት የተለያዩ እንቅፋቶችን ማለፍ ነበረብኝ። ከቤት ወጥቼ ማደር ፈጽሞ የማይቻል ነገር ስለሆነ ወንድሞች ተራ ገብተው ጠዋት ወደ ትምህርት ቤት የሚያመጡኝ ሲሆን ማታ ደግሞ ወደ ቤቴ ይመልሱኛል። በምሳ ሰዓት ደግሞ ከወንድሞች አንዱ ይሸከመኝና ሁላችንም ወደምንመገብበት ወደ ሁለተኛው ፎቅ ይወስደኛል።
ከባድ ኃላፊነት
መጋቢት 2003 ላይ የጉባኤ ሽማግሌ ሆኜ ተሾምኩ። ይህ ኃላፊነት ሌሎችን ለመርዳት ሲባል ጠንክሮ መሥራትን ይጠይቃል። ኢየሱስ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው” ሲል ምን ማለቱ እንደነበር አሁን ይበልጥ ተረድቻለሁ። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) በጣም ጥሩ ከሆኑ ሽማግሌዎች ጋር አብሬ የምሠራ ሲሆን ኃላፊነቴንም በሚገባ እንድወጣ ረድተውኛል። መላው ጉባኤ በተለይ ደግሞ ወጣቶቹ ለማከናውነው አገልግሎት ከፍተኛ አድናቆት አላቸው፤ እንዲሁም በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ላይ ያሳትፉኛል። ይሖዋን እንዳላገለግል የሚያደርጉኝን እንቅፋቶች እንዴት እንደተወጣኋቸው ስላዩ ችግር በሚያጋጥማቸው ጊዜ እንድረዳቸው ይጠይቁኛል።
አንድ ሰው ደስተኛ እንዲሆን የሚያደርገው ወሳኝ ነገር አካላዊ ሁኔታው እንዳልሆነ ተገንዝቤያለሁ። ዋናው ቁም ነገር የይሖዋን ሞገስ ማግኘትና ፈቃዱን መፈጸም ነው። በተለይ ደግሞ ይሖዋ በቅርቡ ከተሽከርካሪ ወንበሬ እንደሚገላግለኝ በማወቄ አመሰግነዋለሁ። አዎን፣ ‘እንደ ሚዳቋ የምዘልበትንና’ እውነተኛውን አምላክ ለዘላለም የማገለግልበትን ጊዜ በጉጉት እጠባበቃለሁ።—ኢሳይያስ 35:5, 6
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.8 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
አሁን ሰዎች የሚመለከቱኝ በተንቀሳቃሽ ወንበር ላይ እንዳለ ሰው ብቻ ሳይሆን ሌሎች የአምላክን ዓላማ እንዲያውቁ ለመርዳት እንደሚጣጣር አንድ የይሖዋ ምሥክር ነው
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአፍንጫዬ እየጻፍኩ ለጉባኤ ስብሰባ ስዘጋጅ