በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ያለፈው ዓመት “በሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ ከፍተኛ ሙቀት የተመዘገበበት” ዓመት ሲሆን “በዓለም ዙሪያ እስካሁን ከተመዘገበው የሙቀት መጠን ሁለተኛውን ደረጃ ይዟል።” “ከፍተኛ ሙቀት ከተመዘገበባቸው 10 ዓመታት ውስጥ 8ቱ የተከሰቱት ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ነው።”—ቢቢሲ ኒውስ፣ ብሪታንያ

የ2005ቱ የአትላንቲክ አውሎ ነፋስ “ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ፋታ የማይሰጥ” እንዲሁም እስካሁን በመዝገብ ከሠፈሩት አውሎ ነፋሶች ሁሉ “እጅግ በጣም አውዳሚ” ነበር። ከተመዘገቡት 14 አውሎ ነፋሶች ውስጥ ሰባቱ በሰዓት 177 ኪሎ ሜትር ፍጥነት ነበራቸው።—ዩ ኤስ ናሽናል ኦሽኒክ ኤንድ አትሞስፌሪክ አድሚኒስትሬሽን

“በ1850 በሞንታና [ዩናይትድ ስቴትስ] ውስጥ በሚገኘው የግግር በረዶ ብሔራዊ ፓርክ ከ150 የሚበልጡ ግግር በረዶዎች ነበሩ። አሁን ያሉት ግን 27 ብቻ ናቸው።”—ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል፣ ዩናይትድ ስቴትስ

“የአየር ንብረት መለወጥን በሚመለከተው ፖለቲካ ውስጥ ያፈጠጠ ሐቅ ቢኖር ይህን ተፈታታኝ ሁኔታ ለመፍታት የሚደረገው ለውጥ ኢኮኖሚን የሚነካ ከሆነ የትኛውም አገር ቢሆን የራሱን ኢኮኖሚ መሥዋዕት ለማድረግ የማይፈልግ መሆኑ ነው።”—ቶኒ ብሌየር፣ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር

ካቶሊኮች “ከቤት ወደ ቤት” እየሄዱ ሊሰብኩ?

የሳኦ ፖሎ ከተማ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ክላውዲዮ ሁሜስ እንደተናገሩት ከብራዚል ሕዝብ ውስጥ 83 በመቶ የሚያህለው ካቶሊክ የነበረ ሲሆን ይህ ቁጥር ባለፉት 14 ዓመታት ውስጥ እየቀነሰ ሄዶ 67 በመቶ ሆኗል። ሊቀ ጳጳሱ፣ ቤተ ክርስቲያኗ “በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ወንጌልን ለተጠመቁ አባሎቿ በደንብ መስበክ ባለመቻሏ” ወቅሰዋታል። ሁሜስ “በየደብሩ ብቻ ሳይሆን ከቤት ወደ ቤት፣ ወደ ትምህርት ቤቶችና ወደተለያዩ ተቋማት በመሄድ ለአማኞች መስበክ አለብን” ብለዋል። ፎልያ ኦንላይን የተሰኘው ጋዜጣ እንደገለጸው ይህ ሥራ፣ ሚስዮናውያን እንዲሆኑ በሠለጠኑ ምእመናን መካሄድ ይኖርበታል። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በብራዚልና በመላው የላቲን አሜሪካ አገሮች ከገጠሟት አበይት ችግሮች አንዱ የቀሳውስት እጥረት ነው።

በጀርመን ሕጋዊ እውቅና ማግኘት

በላይፕዚግ፣ ጀርመን የሚገኘው የፌደራል አስተዳደር ፍርድ ቤት የካቲት 10, 2006 ባጸደቀው ውሳኔ ላይ፣ የበርሊን ግዛት በጀርመን ያለውን የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ማኅበር ለሕዝብ ጥቅም እንደሚሠራ ኮርፖሬሽን አድርጎ በመቀበል እውቅና እንዲሰጠው ወስኗል። ይህ ውሳኔ የፌደራሉን ሕገ መንግሥት አጣሪ ፍርድ ቤት ጨምሮ በተለያዩ የጀርመን ፍርድ ቤቶች ለ15 ዓመታት ሲታይ የቆየው ጉዳይ መቋጫ እንዲያገኝ አድርጓል። በጀርመን የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ማኅበር ለሕዝብ ጥቅም የሚሠራ ኮርፖሬሽን እንደመሆኑ መጠን ከቀረጥ ነጻ መሆን እንዲሁም በአገሪቱ የሚገኙ ሌሎች ዋና ዋና ሃይማኖቶች ያሏቸውን መብቶች ማግኘት ይችላል።

የቻይና ወጣቶች የኢንተርኔት ጨዋታ ሱሰኛ ሆነዋል

“የኢንተርኔት ጨዋታ ሱሰኝነት በቻይና ወጣቶች ዘንድ በጣም ተስፋፍቷል” በማለት ሳውዝ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት የተሰኘው የሆንግ ኮንግ ጋዜጣ ይናገራልይህ ሁኔታ እንደ ሆንግ ኮንግ፣ ጃፓንና የኮሪያ ሪፑብሊክ ባሉት ሌሎች የሩቅ ምሥራቅ አገሮች ውስጥ በሚኖሩ ወጣቶችም ላይ እየታየ ነው። ጋዜጣው አክሎም “ልጆች በኢንተርኔት ጨዋታዎች በመጠመድ በዙሪያቸው ያለውን ነገር የመርሳት ፍላጎታቸው እየጨመረ መምጣቱ ወላጆቻቸው ብዙ የሚጠብቁባቸው መሆኑና ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ደግሞ ከፍተኛ ፉክክር መኖሩ የሚያስከትልባቸውን ከባድ ጫና አምርረው እንደሚቃወሙት የሚጠቁም ነው” በማለት ገልጿል። ስድስት ሚሊዮን የሚያህሉ ቻይናውያን ልጆች ይህን ሱስ ለማሸነፍ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተገምቷል።