የአንድ ልጅ እምነት
የአንድ ልጅ እምነት
ደስቲን፣ እናቱ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በምታጠናበት ወቅት አንዳንድ ጊዜ ጥናቱ ላይ ይገኝ ነበር። ምንም እንኳ ገና የ11 ዓመት ልጅ የነበረ ቢሆንም አስተሳሰቡ የበሰለ ከመሆኑም በላይ ቁም ነገር ያዘሉ በርካታ ጥያቄዎች ያነሳ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ቀድሞ በሚስዮናዊነት ታገለግል የነበረችው የእናቱ አስጠኚ መጽሐፍ ቅዱስን ለብቻው እንድታስጠናው ጠየቃት። ከዚያም የተማረውን ነገር አብረውት ለሚማሩ ልጆች መናገር ጀመረ።
ደስቲን በአካባቢው በሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ በሚደረገው ስብሰባ ላይ መገኘት ከመጀመሩም በላይ አድማጮች በሚሳተፉባቸው ትምህርቶች ላይ ሐሳብ መስጠት ጀመረ። ደስቲን ከታናናሾቹ ጋር በመሆን አባታቸውን ለመጠየቅ ሲሄዱ፣ አባትየው አንድ ላይ ቤተ ክርስቲያን መሄድ እንዳለባቸው አሳሰባቸው። ደስቲን ወደ መንግሥት አዳራሽ ለመሄድ የሚመርጥበትን ምክንያት ከነገረው በኋላ ግን አባትየው በጉዳዩ በመስማማት እንደሚፈቅድለት ነገረው።
አንድ ምሽት ላይ በመንግሥት አዳራሽ ከሚደረገው ስብሰባ በኋላ የደስቲን እናት ልጇን ከአጠገቧ አጣችው። ደስቲን እናቱ ሳታውቅ፣ የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የበላይ ተመልካች የሆነው ወንድም ጋር ሄዶ በትምህርት ቤቱ መካፈል እንደሚፈልግ ነገረው። እናቱም ስትሰማ በጉዳዩ ተስማማች። ስለዚህ ደስቲን የመጀመሪያ ንግግሩ እስኪሰጠው በጉጉት መጠባበቅ ጀመረ። ይሁን እንጂ በዚህ ጊዜ ዳሌው አካባቢ ኃይለኛ ሕመም ይሰማው ጀመር፤ በመሆኑም ለምርመራ ወደ ተለያዩ ሐኪሞች ተወሰደ። በመጨረሻም ደስቲን የጓጓለትን የመጀመሪያ ንግግሩን የሚያቀርብበት ቀን ደረሰ። በዚህ ወቅት ክራንች መያዝ ጀምሮ ነበር። ደስቲን ሕመሙ ያሠቃየው የነበረ ቢሆንም ምርኩዝ ሳይዝ ወደ መድረኩ ወጣ።
ብዙም ሳይቆይ ደስቲን፣ ዩዊንግስ ተብሎ በሚጠራው እምብዛም የማያጋጥም የአጥንት ካንሰር እንደተያዘ ታወቀ። በቀጣዩ ዓመት አብዛኛውን ጊዜ ያሳለፈው በካሊፎርኒያ
ግዛት ሳን ዲዬጎ በሚገኘው የልጆች ሆስፒታል ውስጥ ነው። የኬሞቴራፒና የጨረር ሕክምና ይሰጠው የነበረ ከመሆኑም በላይ ከዳሌው አጥንት ጀምሮ የቀኝ እግሩ ቢቆረጥም በይሖዋ ላይ ያለው ጠንካራ እምነት እንዲሁም ለእርሱ ያለው ፍቅር አልቀነሰም። ደስቲን ለማንበብ አቅም በሚያጣበት ወቅት አብዛኛውን ጊዜ ከጎኑ የማትጠፋው እናቱ ጮክ ብላ ታነብለት ነበር።የደስቲን ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ቢሄድም አላማረረም። በተሽከርካሪ ወንበሩ ተጠቅሞ እየተዘዋወረ አንድ የታመመ የይሖዋ ምሥክርን ጨምሮ ሌሎች ታካሚዎችንና ቤተሰቦቻቸውን በማበረታታት ራሱን በሥራ አስጠምዶ ነበር። ደስቲንና የታመመው የይሖዋ ምሥክር እምነታቸው መጽናኛ ስለሆነላቸው ከሌሎች ሕሙማን የተለዩ መሆናቸውን የሆስፒታሉ ሠራተኞች መመልከት ችለው ነበር።
በመጨረሻም ደስቲን ለመጠመቅ ፈለገ። በጣም በመድከሙ መቀመጥ ቢያስቸግረውም ሶፋ ላይ ጋደም እንዳለ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ለጥምቀት እጩዎች የሚቀርቡትን ጥያቄዎች ጠየቁት። ከዚያም ደስቲን ጥቅምት 16, 2004 በተደረገው የይሖዋ ምሥክሮች የወረዳ ስብሰባ ላይ በ12 ዓመቱ ተጠመቀ።
የጥምቀት ንግግሩ ሊጀመር ሲል ደስቲን በተሽከርካሪ ወንበሩ ላይ ሆኖ ሌሎች የጥምቀት እጩዎች ወደተቀመጡበት ቦታ ተወሰደ። ተጠማቂዎቹ ከመቀመጫቸው እንዲነሱ በተጠየቁ ጊዜ ደስቲን የወንበሩን እጀታ በመደገፍ በአንድ እግሩ ቆመ፤ በዕለቱ ምርጥ የሆነውን ልብሱን ለብሶ ነበር። የጥምቀት ጥያቄዎቹ ሲቀርቡ ድምፁን ከፍ አድርጎ ጥርት ባለ ሁኔታ መለሰ። የደስቲንን ወላጅ አባትና እንጀራ እናት ጨምሮ ሁሉም ቤተሰቡ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው ነበር። ከዚህም በላይ የሆስፒታሉ ሠራተኞችና በካንሰር የተያዙ ልጆች ያሏቸው ወላጆች ጭምር መጥተው ነበር።
ደስቲን ከጥምቀቱ ቀን በኋላ ተመልሶ ወደ ሆስፒታል እንዲገባ ተደረገ። በዚህ ጊዜ ካንሰሩ በሰውነቱ ውስጥ ባሉት አጥንቶች ሁሉ ተሠራጭቶ ነበር። ደስቲን እየደከመ ሲመጣ እንደሚሞት ስለተገነዘበ እናቱን ‘የምሞት ይመስልሻል?’ በማለት ጠየቃት። እናቱም “ለምን እንዲህ ብለህ ጠየቅኸኝ? መሞት ትፈራለህ እንዴ?” ስትል መልሳ ጠየቀችው።
“አልፈራም” በማለት መለሰላት። “አሁን ዓይኖቼን ከድኜ አረፍ እላለሁ፤ በትንሣኤ ስነሳ ከጥቂት ሴኮንዶች ያለፈ የተኛሁ አይመስለኝም። ከሥቃዬም እገላገላለሁ። የተጨነቅኩት ለቤተሰቤ ነው” አላት።
በቀጣዩ ወር ደስቲን ሞተ። በቀብሩ ሥነ ሥርዓት ላይ የይሖዋ ምሥክሮችም ሆኑ የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ የደስቲን ቤተሰቦች፣ ሐኪሞች፣ ነርሶች፣ የሆስፒታሉ ሠራተኞች ቤተሰቦች፣ አስተማሪዎችና ጎረቤቶች ተገኝተዋል። ደስቲን በቀብሩ ሥነ ሥርዓት ላይ ለሚገኙ ሁሉ ስለ እምነቱ ጥሩ ምሥክርነት እንዲሰጣቸው ጠይቆ ነበር። ደስቲን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያቀረበውን የተማሪ ክፍል የሰጠው የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የበላይ ተመልካች በቀብሩ ሥነ ሥርዓት ላይ ለተገኙት በርካታ ሰዎች በጣም ግሩም የሆነ፣ እምነት የሚገነባ ንግግር አቀረበ። በሥነ ሥርዓቱ ላይ በጣም ብዙ ሰዎች ስለተገኙ አብዛኞቹ ንግግሩን ያዳመጡት ቆመው ነበር።
ደስቲን የሚወዳቸው ሁለት ጥቅሶች ማለትም ማቴዎስ 24:14 እና 2 ጢሞቴዎስ 4:7 የታተሙበት ወረቀት በቀብሩ ሥነ ሥርዓት ላይ ለተገኙት ሰዎች ተሰጠ። ደስቲንን የሚያውቁት ሰዎች ሁሉ ጠንካራ እምነቱና ጽኑ አቋሙ አበረታቷቸዋል። ደስቲን በትንሣኤ ሲነሳ ለማየት እንናፍቃለን።—ደስቲንን መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናችው የይሖዋ ምሥክር እንደተናገረችው
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫውን ጨርሻለሁ፤ ሃይማኖትንም ጠብቄአለሁ።”—2 ጢሞቴዎስ 4:7
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከላይ:- ደስቲን ጥሩ ጤንነት በነበረው ጊዜ
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከታች:- ደስቲን በ12 ዓመቱ ሲጠመቅ