በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የውኃ ዳር ወፎች—የዓለማችን ድንቅ ተጓዦች

የውኃ ዳር ወፎች—የዓለማችን ድንቅ ተጓዦች

የውኃ ዳር ወፎች—የዓለማችን ድንቅ ተጓዦች

ስፔን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

በሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ በሚገኘው የአርክቲክ ገላጣ አካባቢ ፀሐይ ጨርሶ የማትጠልቅባቸውን ሁለት የበጋ ወራት አሳለፍክ እንበል። ክረምቱ ሲቃረብ ደግሞ ወደ ደቡብ አሜሪካ፣ አውስትራሊያ ወይም ደቡብ አፍሪካ ታቀናለህ። በቀሪው የዓመቱ ክፍል የምትወደውን ምግብ ለማግኘት በየአህጉራቱ የሚገኙ የውኃ ዳርቻዎችን ስታስስ ትከርማለህ። በዓለማችን ላይ የሚገኙት የብዙዎቹ የውኃ ዳር ወፎች ሕይወት ይህን ይመስላል።

የውኃ ዳር ወፎች የሚለው ስያሜ እነዚህ ወፎች ምግባቸውን የሚለቅሙት በውኃ ዳርቻ ላይ መሆኑን ይጠቁማል። * በሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ አየሩ ሲቀዘቅዝ እነዚህ ወፎች ሰው ዝር በማይልባቸው ደለላማ አካባቢዎች፣ የባሕር ዳርቻዎችና ማዕበል ሲኖር ለጊዜው በውኃ በሚሸፈኑ ረግረግ ቦታዎች ወይም በድንጋያማ የባሕር ዳርቻዎች ላይ ተከማችተው ይታያሉ። ጎብኚዎች ወደ ባሕር ዳርቻዎች በሚጎርፉባቸው ሞቃት ወቅቶች ደግሞ አብዛኞቹ የውኃ ዳር ወፎች ጫጩቶቻቸውን ለማሳደግ በቂ ምግብ ወደሚያገኙባቸውና ጭር ወዳሉት የአርክቲክና የከፊል አርክቲክ አካባቢዎች ለጥቂት ወራት ይሰደዳሉ።

የውኃ ዳር ወፎች ደማቅ ቀለም ባይኖራቸውም ማራኪ በሆነ መንገድ የሚበርሩ መሆናቸው፣ በክንፎቻቸው ላይ ከሚገኙት ለየት ያሉ ምልክቶች ጋር ተዳምሮ የብዙ ተመልካቾችን ቀልብ ይስባል። ሾርበርድስ—ብዩቲፉል ቢችኮምበርስ የተባለው መጽሐፍ እንደሚከተለው ይላል:- “[የውኃ ዳር ወፎች] በጣም ዝቅ ብለው በክንፎቻቸው ጫፍ ውኃውን እየዳሰሱ አሊያም ደግሞ ከ6 ኪሎ ሜትር ወይም ከዚያ በላይ ከፍ ብለው ሊበርሩ ይችላሉ። የነፋሱን አቅጣጫ ተከትለው በመብረር ረገድም ድንቅ ችሎታ አላቸው።”

በኀብረት በመሆን ከአደጋ መዳን

የውኃ ዳር ወፎች ብዙ ምግብ ባለበት ቦታ ሁሉ እጅብ ብለው ይታያሉ። ከአደጋ ለመዳን በኀብረት መሆን የሚፈልጉም ይመስላል። ፔሪግሪን እንደተባለው ጭልፊት ያሉ አዳኝ ወፎች ለማደን የሚመርጡት በኅብረት ያሉ ወፎችን ሳይሆን ነጠል ያለውን ወፍ ነው። እጅብ ብለው ያሉ በሺህ የሚቆጠሩ የውኃ ዳር ወፎች ጠላታቸው ጥቃት ከመሰንዘሩ በፊት በቀላሉ ሊያዩት ይችላሉ። በመሆኑም ይህን ዓይነቱን ጥበቃ ለማግኘት ሲሉ የተለያዩ ዝርያዎች ያሏቸው በርካታ የውኃ ዳር ወፎች አንድ ላይ ይሆናሉ።

የውኃ ዳር ወፎች እጅብ ብለው ሲተምሙ ማየት እጅግ ማራኪ የሆነ ትዕይንት ነው። በመቶዎች አንዳንዴም በሺዎች የሚቆጠሩ ወፎች በአንድ ላይ ወዲህ ወዲያ ሲተጣጠፉ እንዲሁም ከፍና ዝቅ እያሉ ሲበርሩ፣ አንድ የማይታይ ኃይል እየተቆጣጠራቸው ያለ ይመስላል። ሃንድቡክ ኦቭ ዘ በርድስ ኦቭ ዘ ወርልድ የተሰኘ መጽሐፍ እንደሚከተለው ብሏል:- “በሺዎች የሚቆጠሩ ወፎች በፍጥነት እየበረሩ ድንገት አንድ ላይ አቅጣጫቸውን ሲቀይሩ መመልከት ተአምር ነው።” የአእዋፍ አጥኚዎች ደንሊን የተባሉ ወፎችን እንቅስቃሴ የሚያሳይ ፊልም ከተመለከቱ በኋላ መገንዘብ እንደቻሉት አንድ ላይ የሚበሩት ወፎች ድንገተኛ ለውጥ የሚያደርጉት በመካከላቸው ያለች አንዲት ወፍ የምታደርገውን ለውጥ በመከተል ሊሆን ይችላል።

ምድሩን ማካለል

አንዳንድ የውኃ ዳር ወፎች ቃል በቃል መላውን ምድር ያካልላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ሬድ ኖት እና ሳንደርሊንግ የተባሉት ወፎች ከሌሎች የወፍ ዝርያዎች በተለየ መልኩ እንቁላል ጥለው የሚፈለፍሉት ወደ ሰሜን ዋልታ ይበልጥ ተጠግተው ነው። የውኃ ዳር ወፎች በየትኛውም የውኃ ዳርቻ ላይ የሚገኙ ሲሆን በዓመት እስከ 32,000 ኪሎ ሜትር ድረስ ሊበርሩ ይችላሉ።

የውኃ ዳር ወፎች በጉዟቸው ወቅት ውቅያኖሶችን ማቋረጥ የሚጠበቅባቸው ቢሆንም መዋኘት ስለማይችሉ በውቅያኖሱ ላይ አያርፉም። በመሆኑም ውቅያኖሱን ለማቋረጥ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ፣ ከምድር ሲነሳ ከጠቅላላ ክብደቱ 40 በመቶ የሚሆን ነዳጅ ከሚሸከመው ግዙፍ አውሮፕላን የሚበልጥ የኃይል ክምችት ሊኖራቸው ይገባል ማለት ነው። እነዚህ ወፎች ይህን ያህል ኃይል የሚያገኙት ከየት ነው?

ዴቪድ አተንበሮ፣ ዘ ላይፍ ኦቭ በርድስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ የሚከተለውን አስፍረዋል:- “[ኃይሉን] የሚያከማቹት በስብ መልክ በመሆኑ በውኃ ዳርቻዎች ባለው ደለል ላይ ያገኙትን ሁሉ እየተስገበገቡ ይውጣሉ። በመሆኑም በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ክብደታቸው በበጋው ወራት ከነበረው በእጥፍ ይጨምራል። በዚህ ጊዜ ያላቸው የስብ ክምችት ምናልባትም አላቸው ተብሎ ከሚነገረው አኃዝ በላይ ነው፤ ክብደታቸው ከመጠን በላይ ሳይጨምር ይህን ሁሉ ስብ ለማከማቸት እንዲችሉ አንጎላቸውንና የሆድ ዕቃቸውን ጨምሮ የሌሎቹም ብልቶቻቸው መጠን ይቀንሳል።”

ከእነዚህ ድንቅ ተጓዦች መካከል ከአላስካ ተነስቶ እስከ ሐዋይ ደሴቶች ድረስ የሚጓዘው ፓስፊክ ጎልደን ፕሎቨር የተባለው ወፍ ይገኝበታል። ይህ ወፍ ያለ አንዳች እረፍት 4,500 ኪሎ ሜትር ይጓዛል። ከዚህም በላይ በውቅያኖስ መሃል የሐዋይን አቅጣጫ ለመለየት የሚያስችል አስደናቂ ችሎታ አለው። አንድ ክትትል የተደረገበት ጎልደን ፕሎቨር ይህን ርቀት ከአራት ቀናት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሸፍኗል። አንድ ያረጀ ወፍ ደግሞ በሕይወት ዘመኑ ውስጥ ከአላስካ ወደ ሐዋይ ከ20 ጊዜ በላይ ተመላልሷል!

እነዚህ ብርቱ ተጓዦች ወደሚራቡበትና የጉዟቸው መደምደሚያ ወደሆነው ወደ አርክቲክ ክልል ሲደርሱ ደግሞ ሩጫ የተሞላበት ሕይወት ይጠብቃቸዋል። በሁለት ሳምንት ውስጥ ተጓዳኝ ማግኘት፣ ክልል ማበጀትና ጎጆ መሥራት ይኖርባቸዋል። ከዚያም በቀጣዮቹ ሦስት ሳምንታት እንቁላሎቻቸውን ይፈለፍላሉ። ከዚህ ቀጥሎ ባሉት ሦስት ሳምንታት ደግሞ ጫጩቶቻቸውን ያሳድጋሉ። በመጨረሻም በሐምሌ መገባደጃ አካባቢ ዳግመኛ ወደ ደቡብ ያቀናሉ።

በጉዟቸው ላይ የሚያጋጥሟቸው አደጋዎች

የውኃ ዳር ወፎች የሚያደርጉት ረጅም ጉዞ በአደገኛ ሁኔታዎች የተሞላ ነው። የወፎቹን ሕይወት ስጋት ላይ ከጣሉት ነገሮች መካከል የሰው ልጅ በዋነኝነት ይጠቀሳል። በ19ኛው ክፍለ ዘመን የኖሩት ጆን ጄምስ አውደቦን የተባሉ የሥነ ተፈጥሮ ተመራማሪ፣ አዳኞች በአንድ ቀን ብቻ 48,000 የሚያክሉ የአሜሪካ ጎልደን ፕሎቨሮችን እንደገደሉ ተናግረዋል። በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲታይ የእነዚህ ወፎች ቁጥር በመጠኑ እየጨመረ እንዳለ የሚገመት ቢሆንም አጠቃላይ ብዛታቸው በዚያ ቀን ከተገደሉት ወፎች ቁጥር ያነሰ ነው።

የውኃ ዳር ወፎችን የገጠማቸው ሌላው ይበልጥ አደገኛ ሁኔታ ደግሞ ረግረጋማ አካባቢዎች እየጠፉ መሄዳቸው ነው። የውኃ ዳር ወፎች ደግሞ ከእነዚህ ለውጦች ጋር ቶሎ ራሳቸውን ማስማማት አይችሉም። ሾርበርድስ—አን አይደንቲፊኬሽን ጋይድ ቱ ዘ ዌደርስ ኦቭ ዘ ወርልድ የተሰኘው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “የውኃ ዳር ወፎች የሚራቡባቸውና ክረምቱን የሚያሳልፉባቸው እንዲሁም በጉዞ ላይ እያሉ የሚያርፉባቸው የተለመዱ ቦታዎች አሏቸው። እነዚህን አካባቢዎች ለብዙ ሺህ ዓመታት ሲጠቀሙባቸው የቆዩ ሲሆን የሰው ልጆች ደግሞ ቦታዎቹን በቀላሉ ሊቀይሯቸው አሊያም ሊያበላሿቸው ይችላሉ።” በሚሊዮን የሚቆጠሩ የውኃ ዳር ወፎች ሕልውና የተመካው በጉዟቸው ወቅት የሚያርፉባቸው እነዚህ በጣት የሚቆጠሩ አስፈላጊ ቦታዎች ባሉበት ሁኔታ በመቆየታቸው ላይ ነው።

ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ የሚሆነው በደቡብ ምዕራብ ኒው ጀርሲ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ጠረፍ ላይ የሚገኘው ዴለዌር ቤይ የተሰኘ የባሕር ዳርቻ ነው። በጸደይ ወራት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሬድ ኖቶች፣ ሆርስሹ የተባለውን የሸርጣን ዝርያ እንቁላሎች ለመመገብ ወደዚህ የባሕር ዳርቻ ግር ብለው ይመጣሉ። እነዚህ ወፎች “በአእዋፍ ዓለም አሉ ከሚባሉት ረጅም ጉዞዎች መካከል አንዱ የሆነውን ጉዞ ያለ አንዳች እረፍት ተጉዘው” ገና ማረፋቸው በመሆኑ እዚህ የሚደርሱት እጅግ ተርበው ነው። ወፎቹ ከደቡብ ምሥራቅ ብራዚል ተነስተው ወደዚህ አካባቢ ለመድረስ በሁለት ሳምንት ውስጥ 8,000 ኪሎ ሜትር ያህል በርረዋል፤ በመሆኑም እዚህ ቦታ ላይ የሚደርሱት የሰውነታቸው ክብደት በግማሽ ቀንሶ ነው።

የአካባቢ ጥበቃ ባለሞያዎች የሚያደርጉት ጥረት ተጓዥ ወፎቹ የሚወዷቸው ጊዜያዊ ማረፊያዎቻቸው ተጠብቀው እንዲቆዩ እገዛ ያደርጋል። ምናልባትም በምትኖርበት አካባቢ እንዲህ ዓይነት ስፍራ ይገኝ ይሆናል። እነዚህ ወፎች እየተጠማዘዙ ሲበሩና በዙሪያህ ሲያንዣብቡ ከተመለከትክ አሊያም ደግሞ ከአእምሮ የማይጠፋ ድምፃቸውን አንዴ ካዳመጥክ በቀላሉ ልትረሳቸው አትችልም።

አርቱር ሞሪስ የተባሉ አንድ የሥነ ተፈጥሮ ተመራማሪ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “የውኃ ዳር ወፎችን መመልከት የምንወድ ሰዎችን የሚያመሳስለን አንድ ነገር አለ። ሁላችንም ሰዎች በብዛት በማይገኙባቸው የውኃ ዳርቻዎች ወይም ረግረጋማ ቦታዎች ላይ ሆነን ሳንድፓይፐር የተባሉት ወፎች ነጭና ጥቁር ክንፎቻቸውን እያርገበገቡ እጅብ ብለው ሲያንዣብቡ በተደጋጋሚ ተመልክተናል። ያም ሆኖ ይህን ትዕይንት ባየን ቁጥር በከፍተኛ አድናቆት እንዋጣለን።”

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 የውኃ ዳር ወፎች ቻራድሪ በሚባለው ሳይንሳዊ ክፍል ውስጥ የሚመደቡ ሲሆን ከ200 የሚበልጡ ዝርያዎችም አሏቸው።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ረጅም ርቀት በመጓዝ የተካኑ ወፎች

ሬድ ኖት የተባሉት ወፎች ረጅም ርቀት በመጓዝ ረገድ ተወዳዳሪ እንደሌላቸው ይገመታል። በሰሜናዊ ካናዳ ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች የሚፈለፈሉት እነዚህ ወፎች ብዙውን ጊዜ ክረምቱን የሚያሳልፉት በምዕራብ አውሮፓ ወይም በደቡብ አሜሪካ ጫፍ ላይ ባሉ ቦታዎች ነው (ከ10,000 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀው ማለት ነው)

[ምንጭ]

KK Hui

በኔዘርላንድና በሞሪቴንያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደንሊኖችን መመልከት ይቻላል

ባር-ቴልድ ጎድዊት የተባሉት ወፎች የሚራቡት በሳይቤሪያ ቢሆንም ወደ ብሪታንያ ትንንሽ ደሴቶች፣ ወደ ደቡብ አፍሪካ፣ ወደ መካከለኛው ምሥራቅና አውስትራሊያ እንዲሁም ወደ ኒው ዚላንድ ይፈልሳሉ

ሳንደርሊንግ ተብለው የሚጠሩት ወፎች በዓለም ላይ በሚገኝ በማንኛውም የውኃ ዳርቻ ላይ ሲዘዋወሩ ሊታዩ ይችላሉ። ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ ከሰሜን ዋልታ 950 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባሉ አካባቢዎች ሊራቡ ይችላሉ

[በገጽ 16 እና 17 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የውኃ ዳር ወፎች ውኃ ላይ ማረፍ ስለማይችሉ ሰፋፊ ውቅያኖሶችን ለማቋረጥ ብዙ ስብ ማከማቸት አለባቸው

[በገጽ 16 እና 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሳንደርሊንጎች ራሳቸውን ከአደጋ ለመከላከል እጅብ ብለው ይታያሉ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዩሬዥያን ኦይስተርካቸር

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዥንጉርጉር የሆነችው ሬድሻንክ ምግቧን ረግረግ ውስጥ ስትፈልግ

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከላይና ከታች ያሉት ጎላ ብለው የሚታዩት ፎቶዎች:- © Richard Crossley/VIREO