በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የገሊላው ጀልባ​—መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበትን ዘመን የሚያስታውሰን ቅርስ

የገሊላው ጀልባ​—መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበትን ዘመን የሚያስታውሰን ቅርስ

የገሊላው ጀልባ​—መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበትን ዘመን የሚያስታውሰን ቅርስ

እስራኤል የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ኢየሱስ የአገልግሎት ዘመን ከታዩት አስደናቂ ክንውኖች ውስጥ አንዳንዶቹ የተፈጸሙት በገሊላ ባሕር ላይ ነው። የአምላክ ልጅ በውኃ ላይ የሄደውና ኃይለኛ ማዕበልን ጸጥ ያሰኘው በዚህ ባሕር ላይ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በተአምር የመገበውና የታመሙትን የፈወሰውም በዚሁ ባሕር ዳርቻ ነበር።

በ1986 ከጥንቷ ቅፍርናሆም በስተ ደቡብ ምዕራብ በባሕር ወለል ላይ አንድ አስገራሚ ነገር ተገኘ። ግኝቱ ኢየሱስ በምድር ላይ ሲያገለግል በነበረበት ዘመን በገሊላ ባሕር ላይ ሲጓዝ የነበረ ጀልባ ነው። ይህ ጀልባ እንዴት ሊገኝ ቻለ? እኛስ ከዚህ ጀልባ ምን እንማራለን?

ድርቅ ያጋለጠው ጀልባ

ለብዙ ዓመታት በአካባቢው የጣለው ዝናብ ከወትሮው ያነሰ ከመሆኑም በላይ የ1985 የበጋ ወቅት በጣም ደረቅ መሆኑ በገሊላ ባሕር ላይ ከባድ ለውጥ አስከትሎ ነበር። ከዚህም በላይ ውኃው ጨዋማ ስላልሆነ ለሰብል ልማት እንዲውል በመስኖ ይጠለፍ ነበር። በዚህም የተነሳ የውኃው መጠን በአስገራሚ ሁኔታ ጎደለና ሰፊ ቦታ የሚሸፍን ደለል ተፈጠረ። በአቅራቢያው የሚኖሩ ሁለት ወንድማማቾች ይህን ክስተት የተደበቀ ሀብት ለመፈለግ ግሩም አጋጣሚ እንደሆነ አድርገው ተመለከቱት። እነዚህ ሰዎች ደለሉን አቋርጠው ሲያልፉ ጥቂት የነሐስ ሳንቲሞችና አሮጌ ምስማሮች አዩ። ከዚያም በደለሉ ላይ ሞላላ ቅርጽ ያለው ነገር ተመለከቱ፤ አንድ ጥንታዊ ጀልባ በዚያ ተቀብሮ ነበር። በእርግጥም ውድ ሀብት አግኝተዋል!

አርኪኦሎጂስቶች በገሊላ ባሕር ውስጥ የ2,000 ዓመታት ዕድሜ ያስቆጠረ ጀልባ እናገኛለን ብለው ፈጽሞ አላሰቡም። ጥቃቅን ነፍሳት ማንኛውንም ዓይነት እንጨት በልተው እንደሚጨርሱት ይገምቱ ነበር። ሆኖም ባለሙያዎቹ በካርቦን የዘመን ስሌት መለኪያ በመጠቀምና በሥፍራው የተገኙትን ሳንቲሞች በማጥናት፣ ጀልባው በአንደኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ወይም በአንደኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የነበረ ነው ብለው ደምድመዋል። ለማመን በሚያዳግት መልኩ የጀልባው አካል መዋቅር እንዳለ ቆይቷል። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?

ጀልባው ማንም በማይደርስበት አካባቢ የነበረ ይመስላል፤ በመሆኑም የታችኛው ክፍል ሙሉ በሙሉ በለስላሳ ደለል ተውጦ ነበር። ከጊዜ በኋላ ደለሉ በመጠጠሩ ይህ ታሪካዊ ቅርስ ለ2,000 ዓመታት ተጠብቆ ቆየ!

የጀልባው መገኘት ዜና ሲሠራጭ፣ የኢየሱስ ጀልባ የሚል ቅጽል ስም ወጣለት። እርግጥ ይህ ስም የተሰጠው ኢየሱስ ወይም ደቀ መዛሙርቱ በዚህ ጀልባ ይጠቀሙ ነበር ለማለት አይደለም። ሆኖም ዕድሜውና በወንጌል ታሪኮች ላይ ከተገለጹት ጀልባዎች ጋር ያለው ተመሳሳይነት የታሪክ ጸሐፊዎችንና የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራንን ትኩረት እንዲስብ አድርጎታል።

ጀልባው ርዝመቱ 8.2 ሜትር ሲሆን ስፋቱ ደግሞ 2.3 ሜትር ነው። አናጺው ጀልባውን የሠራው መጀመሪያ መዋቅር አዘጋጅቶ መዋቅሩን ጣውላ በማልበስ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ከጀልባው ሥር የሚውል የደጋን ቅርጽ ያለው እንጨት ካዘጋጀ በኋላ እንጨቱ ላይ ከጎንና ከጎን ጣውላዎችን እየመታ ወደላይ በማውጣት የጀልባውን አካል ሠራ። በሜዲትራንያን ባሕር ላይ ለመቅዘፍ የሚሠሩ ጀልባዎች እንዲህ ባለ መንገድ መሠራታቸው የተለመደ ነበር። ይሁን እንጂ የገሊላው ጀልባ በሐይቅ ላይ ለመጓዝ በሚያመች መልኩ የተሠራ ሳይሆን አይቀርም።

ጀልባው በአራቱም ማዕዘን እኩል የሆነ ሸራ ነበረው። አራት መቅዘፊያዎች ያሉት መሆኑ አራት ቀዛፊዎችንና አንድ ነጂ ያካተተ በትንሹ አምስት ሠራተኞች እንደሚያስፈልጉት ያመለክታል። ይሁን እንጂ ጀልባው የዚህን ቁጥር እጥፍ የሚሆኑ ሰዎች መጫን ይችላል። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ያዩት ሰባት ደቀ መዛሙርቱ ዓሣ ሲያጠምዱ ባገኛቸው ጊዜ ስለተጠቀሙበት ጀልባ ስናስብ ከላይ የተጠቀሰውን ጀልባ የሚያህል ሊሆን እንደሚችል መገመት እንችላለን።—ዮሐንስ 21:2-8

የገሊላው ጀልባ ከኋላ በኩል ትላልቅ የዓሣ ማጥመጃ መረቦችን ለማስቀመጥ የሚሆን ቦታ ሊኖረው እንደሚችል ጥርጥር የለውም። ከጀልባው ሳንቃ በታች የሚገኘውን እንዲህ ያለውን ገለል ያለ ቦታ ዓሣ አጥማጆች ሲደክማቸው አረፍ ለማለት ይጠቀሙበታል። ኃይለኛ ነፋስ በተነሳበት ወቅት “ኢየሱስ . . . ትራስ ተንተርሶ ከጀልባዋ በስተ ኋላ በኩል ተኝቶ” እንደነበር የሚገልጸው ዘገባ ኢየሱስ እንደዚህ ዓይነቱን ቦታ እንደተጠቀመበት የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። (ማርቆስ 4:38) “ትራስ” የሚለው አገላለጽ የጀልባውን ሚዛን ለመጠበቅ የሚጠቀሙበትን አሸዋ የተሞላ ጆንያ ሊያመለክት ይችላል። *

በገሊላ ባሕር አካባቢ የነበሩ ዓሣ አጥማጆች

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከላይ የተጠቀሰውን በሚመስል ጀልባ ላይ እንደተሳፈርክ አድርገህ አስብ። በገሊላ ባሕር ላይ ስትጓዝ ምን ልትመለከት ትችል ነበር? ብዙ ዓሣ አጥማጆችን ታይ ነበር፤ ከእነዚህም አንዳንዶቹ በትንንሽ ጀልባዎች ላይ ሆነው የሚያጠምዱ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ጥልቀት በሌለው ውኃ ውስጥ እየተንቦጫረቁ መረባቸውን ይጥላሉ። እነዚህ በሙያው የተካኑ ዓሣ አጥማጆች፣ መሃል ለመሃል ሲለኩ ርዝመታቸው ከ6 እስከ 8 ሜትር የሚደርሱትንና ክብደት ያለው ነገር የታሰረባቸውን ክብ መረቦች ለመጣል የሚጠቀሙት በአንድ እጃቸው ነው። መረቦቹ በውኃው ላይ ተስተካክለው ከተጣሉ በኋላ ወደ ውስጥ ይሰጥሙና ዓሦችን ያጠምዳሉ። አንድ ዓሣ አጥማጅ ያጠመዳቸውን ዓሦች ከመረቡ የሚያወጣቸው በተለያዩ መንገዶች ነው። መረቡ ብዙ ዓሣ ይዞ ከሆነ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ጎትቶ ያወጣዋል፤ አለዚያም ውኃው ውስጥ ይጠልቅና ዓሦቹን ከመረቡ ውስጥ በመልቀም በከረጢት አድርጎ ያወጣቸዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስምዖንና እንድርያስ መረባቸውን “ሲጥሉ” እንደነበረ የተገለጸው ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መንገድ ሳይሆን አይቀርም።—ማርቆስ 1:16

በተጨማሪም በገሊላ ባሕር ላይ ስትጓዝ ዓሣ አስጋሪዎች በቡድን ሆነው እየተንጫጩ አንድ ትልቅ መረብ ለመጣል ሲዘጋጁ ትመለከት ይሆናል። የሚጥሉት መረብ ከጫፍ እስከ ጫፍ ርዝማኔው 300 ሜትር ሊሆንና በእያንዳንዱ ጫፍ መጎተቻ ገመድ የታሠረበት ሆኖ ቀጥ ብሎ ወደ ባሕሩ ውስጥ ሲወርድ እስከ ስምንት ሜትር ድረስ የሚጠልቅ ሊሆን ይችላል። የሚያጠምዱበትን ቦታ ከመረጡ በኋላ ከፊሎቹ ዓሣ አጥማጆች አንዱን መጎተቻ ገመድ ይዘው በባሕሩ ዳር ይቆማሉ። ቀጥሎም የተጠቀለለው መረብ ሙሉ በሙሉ እስኪዘረጋ ድረስ ጀልባው ይዞት ወደ ባሕሩ መሃል ቀጥ ብሎ ይሄዳል። ከዚያም ቀስ ብሎ ወደ ባሕሩ ዳርቻ አቅጣጫ ሲመለስ መረቡ የግማሽ ክብ ቅርጽ ይሠራል። ከዚህ በኋላ በጀልባው ላይ የነበሩት ዓሣ አጥማጆች ሁለተኛውን መጎተቻ ገመድ ይዘው ይወርዳሉ። በተለያየ አቅጣጫ ያሉት ሁለቱ ቡድኖች እየተቀራረቡ ሲሄዱ መረባቸው የያዘውን ዓሣ እየጎተቱ ያወጣሉ።—ማቴዎስ 13:47, 48

በርቀት ብቻውን ሆኖ የሚታየው ዓሣ አስጋሪ መንጠቆና ገመድ ሲጠቀም ትመለከታለህ። በአንድ ወቅት ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ በዚሁ ባሕር ውስጥ መንጠቆውን እንዲጥል ነግሮት ነበር። ጴጥሮስ በመንጠቆው ያወጣውን ዓሣ አፍ ከፍቶ የብር ሳንቲም ሲያገኝ ምን ያህል እንደተገረመ አስበው። የተገኘው ገንዘብ የቤተ መቅደሱን ግብር ለመክፈል የሚበቃ ነበር።—ማቴዎስ 17:27

ቀኑ መሽቶ ለዓይን ሲይዝ በባሕሩ ላይ ጸጥታ ይሰፍናል። ዓሣ አጥማጆች በተቻለ መጠን ብዙ ውካታ ለመፍጠር ሲሉ የጀልባቸውን ወለል በእግራቸው በመምታትና በመቅዘፊያዎቻቸው ውኃውን በማንቦራጨቅ ጸጥታውን ድንገት ያደፈርሱታል። እንዲህ የሚያደርጉት ለምንድን ነው? ውኃው ውስጥ እንደ ግድግዳ ቀጥ ብሎ የሚቆም መረብ ስለጣሉ ዓሦቹ ድንገት በተፈጠረው ውካታ በርግገው በተዘጋጀላቸው ወጥመድ ውስጥ ሰተት ብለው እንዲገቡላቸው ለማድረግ ነው። ዓሦቹ እንዳያዩት በጨለማ ባሕሩ ውስጥ የሚጣለው እንዲህ ዓይነቱ መረብ በቀላሉ ተብትቦ እንዲይዛቸው ታስቦ የተሠራ ነው። መረቦቹ ሌሊቱን ሙሉ በተደጋጋሚ ይጣላሉ። ጠዋት ታጥበው እንዲደርቁ ይሰጣሉ። ‘በተአምር ብዙ ዓሦች እንደተያዙ በሚገልጸው የሉቃስ 5:1-7 ታሪክ ላይ እንዲህ ባለ መረብ ተጠቅመው ይሆን?’ ብለህ ታስብ ይሆናል።

ጀልባውን የማደስ ሥራ

አሁን ደግሞ ወደ ዘመናችን እንመለስ። ተቆፍሮ የወጣው ጀልባ እንዴት ሆነ? ከአካሉ የጎደለ ነገር ባይኖርም በውኃ ከራሰ ካርቶን የበለጠ ጥንካሬ አልነበረውም። ከተቀበረበት ጭቃ ውስጥ እንዳለ ቆፍሮ ማውጣቱ ጥሩ አማራጭ አይሆንም። ደግሞም ጀልባው ይህን ሁሉ ዘመን አሳልፎ በቁፋሮ ለማውጣት ሲሞከር ቢገነጣጠል እንዴት የሚያሳዝን ይሆን ነበር! ጀልባው ከመውጣቱ በፊት የባሕሩ ውኃ ጨምሮ ወደ ቀድሞው ቦታ እንዳይመለስ በመስጋት በሚቆፈርበት ቦታ ዙሪያ የውኃ ማገጃ ግድብ ተሠራ። በፋይበርግላስ የተሠራ ድጋፍ ከጀልባው ሥር ለማስገባት ሲባል ከታች በኩል ተምሶ መሹለኪያ ተሠራ። ከዚያም ጭቃው በጥንቃቄ እየተጠረገ የጀልባውን አካል ከአደጋ ለመከላከል የሚረዳ ፖሊዩሬቴን የሚባል አረፋ መሰል ኬሚካል በውስጥም በውጪም ተረጨበት።

ቀጣዩ ተፈታታኝ ሁኔታ ይህን ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያሻው ጀልባ የጥገና ሥራ ወደሚጀመርበት 300 ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው ቦታ ማጓጓዙ ነበር። ጀልባው የተቀባው የፖሊዩሬቴን ሽፋን ጠንካራ ቢሆንም አንድ ድንገተኛ መንገጫገጭ እንክትክቱን ሊያወጣው ይችላል። ስለዚህ የጥገና ቡድኑ አንድ መላ መዘየድ ነበረበት። የገነቡትን የውኃ ማገጃ ግድብ ከፍተው ውኃ እንዲገባ አደረጉ። ዘመናዊ ማጠንከሪያ የተቀባው ጀልባ ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በገሊላ ባሕር ላይ ተንሳፈፈ።

አሥራ አራት ዓመታት የፈጀው የጥገና ሥራ እስኪጠናቀቅ ድረስ ጀልባው የሚቀመጥበት የሲሚንቶ ገንዳ ተሠርቶለት ነበር። በገንዳው ውስጥ ያለው ውኃ በወባ ትንኝ እጮች በተሞላ ጊዜ ጀልባውን ሊጠግኑ ወደ ውኃው ለሚገቡት ሰዎች ችግር ተፈጥሮ ነበር። ይሁን እንጂ ጀልባውን የማደሱን ሥራ የሚሠራው ቡድን ከጥንት ጀምሮ ሲሠራበት የቆየ አንድ ዘዴ አገኘ። የቅዱስ ጴጥሮስ ዓሦች የተባሉ የዓሣ ዝርያዎችን ወደ ውኃው አስገቡና ዓሦቹ እጮቹን ሁሉ በልተው ውኃውን አጸዱላቸው።

ብዙም ሳይቆይ ጀልባው የሚደርቅበት ጊዜ ደረሰ። በዚህ ጊዜም ቢሆን ገና በቋፍ ስለነበረ በራሱ እንዲደርቅ መተው አይቻልም። እንጨቱን ያራሰው ውኃ በሌላ ነገር መተካት ነበረበት። በመሆኑም ቡድኑ በውኃው ምትክ እንጨቱ የቀድሞ ቅርጹን ሳይለውጥ እንዲደርቅ የሚያስችል በውኃ የሚሟሟ ሰው ሠራሽ ሰም ተጠቀመ።

ጀልባውን የመጠገኑ ሥራ ሲጠናቀቅ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አንድ አነስተኛ ጀልባ ብቅ አለ። ጀልባው የተሠራው ከ12 የተለያዩ የእንጨት ዓይነቶች ነበረ። ለምን? አንዱ ምክንያት በወቅቱ የእንጨት እጥረት ስለነበረ ሊሆን እንደሚችል ይታሰባል። ይበልጥ አሳማኝ የሚሆነው ምክንያት ግን የጀልባው ባለቤት ባለጸጋ ስላልነበረ ሊሆን ይችላል የሚለው ነው። ጀልባው የኋላ ኋላ በባሕሩ ውስጥ እንዲሰምጥ ከመተዉ በፊት ብዙ ጊዜ ተጠግኗል።

የገሊላው ጀልባ ከኢየሱስ ጋር በቀጥታ የሚያገናኘው ነገር ላይኖር ይችላል። ቢሆንም ብዙዎች እንደ ውድ ቅርስ ይመለከቱታል። ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወሳኝ ወቅት ላይ በገሊላ ባሕር አካባቢ ሕይወት ምን ይመስል እንደነበረ በዓይነ ኅሊና ለመቃኘት አጋጣሚ ይሰጣል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.12 በነሐሴ 15, 2005 መጠበቂያ ግንብ (በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ) ገጽ 8 ላይ የወጣውን “በገሊላ ባሕር ላይ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሠራተኞች በጀልባው ውስጥ የነበረውን ጭቃ በከፍተኛ ጥንቃቄ አስወገዱ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የገሊላውን ጀልባ የመጠገኑ ሥራ ተጠናቅቆ ለሕዝብ እይታ ሲቀርብ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጀልባው ፖሊዩሬቴን የተባለውን አረፋ ተቀብቶ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጀልባው ከ2,000 ዓመታት ገደማ በኋላ እንደገና በውኃ ላይ ተንሳፈፈ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጀልባው በአንደኛው መቶ ዘመን ምን ሊመስል ይችል እንደነበር የሚያሳይ ምስል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከጀልባው ምስልና ከባሕሩ በስተቀር ሁሉም ፎቶዎች የተወሰዱት:- Israel Antiquities Authority - The Yigal Allon Center, Ginosar