በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ደም ያለው ትክክለኛ ዋጋ

ደም ያለው ትክክለኛ ዋጋ

ደም ያለው ትክክለኛ ዋጋ

“የሰው ልጆች በሙሉ የሕይወት ምንጭ ደም ነው። ደም ቀለም፣ ዘር ወይም ሃይማኖት ሳይለይ በሁሉም የሰው ልጆች ውስጥ የሚገኝ የሕይወት ኃይል ነው።”—የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዚዳንት

ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት ሐሳብ በተወሰነ መጠንም ቢሆን እውነትነት እንዳለው ምንም አያጠያይቅም። ደም ለሁሉም ሰው ሕይወት በጣም አስፈላጊ ነገር ከመሆኑም በላይ እጅግ ውድ የሆነ ፈሳሽ ነው። ይሁን እንጂ ይህንን ፈሳሽ ለሕክምና ዓላማ ሲባል ለሌሎች መስጠት ምንም ችግር እንደሌለውና ትክክል እንደሆነ ይሰማሃል?

ቀደም ሲል እንደተመለከትነው በዓለም ዙሪያ ያሉት ደምን ከብክለት ለመጠበቅ የወጡት መመሪያዎች ወጥነት ስለሌላቸው በደም አማካኝነት የሚደረጉ ሕክምናዎች ብዙዎች ከሚገምቱት በላይ በጣም አደገኛ ናቸው። በተጨማሪም ሐኪሞች በትምህርት ደረጃቸው፣ በችሎታቸውና በአመለካከታቸው ምክንያት በደም አጠቃቀም ረገድ ሰፊ ልዩነት አላቸው። እንዲህም ሆኖ በርካታ ሐኪሞች ደም በመስጠት ረገድ የሚያደርጉትን ጥንቃቄ ከፍ እያደረጉ ነው። ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ዶክተሮች ደምን መጠቀም የማይጠይቁ ሕክምናዎችን እንደሚመርጡ እያሳዩ ነው።

ይህም በዚህ ተከታታይ ርዕስ የመጀመሪያ ክፍል ላይ ወደተነሳው ጥያቄ ይመልሰናል። ደም በጣም ውድ የሆነው በምን ምክንያት ነው? ደምን ለሕክምና መጠቀም ይበልጥ አጠያያቂ እየሆነ ከመጣ ለሌላ ዓላማ ይውል ይሆን?

ፈጣሪያችን ስለ ደም ያለው አመለካከት

የሰው ልጆች ሁሉ ቅድመ አያት በሆነው በኖኅ ዘመን አምላክ አንድ ለየት ያለ ሕግ አውጥቶ ነበር። ሰዎች የእንስሳትን ሥጋ የመብላት መብት ቢኖራቸውም እንኳን ደምን እንዳይመገቡ ከልክሏቸዋል። (ዘፍጥረት 9:4) ለዚህም ምክንያቱ፣ ደምን ከፍጥረቱ ነፍስ ወይም ሕይወት ጋር አንድ አድርጎ መመልከቱ እንደሆነ ገልጾላቸዋል። ቆይቶም “የፍጡር ሕይወት [ወይም ነፍስ] በደሙ ውስጥ ነው” በማለት ተናግሯል። ፈጣሪ ደምን ቅዱስ አድርጎ ይመለከተዋል። ደም፣ እያንዳንዱ ሕያው ነፍስ የተሰጠውን ውድ ስጦታ ይኸውም ሕይወቱን ይወክላል። አምላክ ይህንን መሠረታዊ ሥርዓት ደጋግሞ ገልጿል።ዘሌዋውያን 3:17፤ 17:10, 11, 14፤ ዘዳግም 12:16, 23

ከዛሬ 2,000 ዓመታት ገደማ በፊት ወይም ክርስትና ከተመሠረተ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ክርስቲያኖች ‘ከደም እንዲርቁ’ መለኮታዊ ትእዛዝ ተሰጥቷቸው ነበር። ይህ እገዳ የተጣለው ከጤና ጋር በተያያዘ ሳይሆን ደም ቅዱስ ከመሆኑ አንጻር ነው። (የሐዋርያት ሥራ 15:19, 20, 29) አንዳንዶች አምላክ የከለከለው ደም እንዳይበላ ብቻ ነው ብለው ይከራከራሉ፤ ነገር ግን “እንድትርቁ” የሚለው አነጋገር ራሱ የሚገልጸው ነገር አለ። አንድ ሐኪም ከአልኮል መጠጥ እንድንርቅ ቢነግረን በደም ሥራችን በኩል ወደ ሰውነታችን ማስገባት እንችላለን ብለን እንደማናስብ የተረጋገጠ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ደም እጅግ ቅዱስ ስለሆነበት ምክንያት ተጨማሪ ማብራሪያ ይሰጣል። ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሲል የሰጠውን ሰብዓዊ ሕይወት የሚወክለው የፈሰሰው ደሙ ለክርስቲያናዊ ተስፋ ቁልፍ ነው። የእርሱ ደም የኃጢአት ይቅርታ እንድናገኝና የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንዲኖረን መሠረት ጥሏል። አንድ ክርስቲያን ከደም መራቁ፣ በእውነት ነፃ ሊያወጣውና ሕይወቱን ሊያድነው የሚችለው የፈሰሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ደም እንደሆነ እምነት እንዳለው ያሳያል።ኤፌሶን 1:7

የይሖዋ ምሥክሮች እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዞች በጥብቅ በመከተል ረገድ በሰፊው ይታወቃሉ። ሙሉውን ደም ወይም ደግሞ ቀይ የደም ሕዋስ፣ ፕላዝማ፣ ነጭ የደም ሕዋስና ፕሌትሌት የሚባሉትን አራት ዋና ዋና የደም ክፍሎች ከመውሰድ ይቆጠባሉ። ከእነዚህ ዋና ዋና ክፍሎች የሚገኙትን ጥቃቅን ክፍልፋዮችና እነዚህ ክፍልፋዮች የሚጨመሩባቸውን ሌሎች መድኃኒቶች በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ነገር የለም። ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ እያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክር የራሱን ውሳኔ ያደርጋል። የይሖዋ ምሥክሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እንዲህ የመሰለ አቋም አላቸው ሲባል መታከም አይፈልጉም ወይም ለጤንነታቸውና ለሕይወታቸው ግድ የላቸውም ማለት ነው? በጭራሽ!—“የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ጤንነት ያላቸው አመለካከት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች አጥብቀው መከተላቸው በሕክምና ረገድ ጥቅም እንዳስገኘላቸው በርካታ ዶክተሮች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተገንዝበዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በቅርብ ጊዜ አንድ የአከርካሪ ቀዶ ሐኪም ለሕመምተኞች ደም በመስጠት ከሚደረግ ሕክምና ይልቅ ሌሎች አማራጮችን መጠቀም እንደሚሻል በግልጽ ተናግረዋል። እንዲህ ብለዋል:- “ለይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም ሰው አማራጭ ዘዴዎችን መጠቀም በጣም አስተማማኝ ነው።”

ከባድ ውሳኔ ማድረግን የሚጠይቁ የጤና ጉዳዮች ከፍተኛ የአእምሮ ውጥረት ሊፈጥሩ የሚችሉ ከመሆኑም በላይ በአብዛኛው ውሳኔ ላይ ለመድረስ ያስቸግራሉ። የሳንባና የመተንፈሻ አካላት ሐኪም እንዲሁም ሜዲካል ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ዴቭ ዊልያምስ የተለመደውን ለሕመምተኞች ደም የመስጠት ሕክምና አስመልክተው የተናገሯቸውን ቃላት ተመልከት:- “የሰዎችን ፍላጎት ማክበራችን በጣም አስፈላጊ ነው፤ . . . በተጨማሪም ወደ ሰውነታችን የምናስገባውን ነገር በተመለከተ በጣም መጠንቀቅ አለብን።” እነዚህ ቃላት ከመቼውም በበለጠ በአሁኑ ጊዜ እውነትነት አላቸው።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ከሄሞግሎቢን የተሠራ ኦክስጅን ተሸካሚ ምንድን ነው?

በእያንዳንዱ ቀይ የደም ሕዋስ ውስጥ ወደ 300 ሚሊዮን የሚጠጉ የሄሞግሎቢን ሞለኪውሎች ይገኛሉ። እድገቱን በጨረሰ ቀይ የደም ሕዋስ ውስጥ አንድ ሦስተኛ ገደማ የሚሆነው ሄሞግሎቢን ነው። እያንዳንዱ ሞለኪውል ውስጥ ግሎቢን የሚባል ፕሮቲንና በውስጡ ብረት ያለው ሄም የሚባል ማቅለሚያ ይገኛል። ቀይ የደም ሕዋስ በሳንባዎች ውስጥ ሲያልፍ የኦክስጅን ሞለኪውሎች ሕዋሱ ውስጥ ይገቡና ከሄሞግሎቢን ሞለኪውሎች ጋር ይጣበቃሉ። ከጥቂት ሴኮንዶች በኋላ ኦክስጅኑ ሕብረ ሕዋሳት ውስጥ በመግባት ሕዋሶቹ በሕይወት እንዲቆዩ ይረዳል።

በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ መድኃኒት አምራቾች ከሰዎች ወይም ከከብቶች ቀይ የደም ሕዋሳት ውስጥ ሄሞግሎቢንን ለይተው ማውጣት ጀምረዋል። ሄሞግሎቢኑ ተለይቶ ከወጣ በኋላ በውስጡ ያሉትን ቆሻሻዎች ለማስወገድ ይጣራል፤ ከዚያም በኬሚካል አማካኝነት እንዲሻሻልና እንዲነፃ ከተደረገ በኋላ ከፈሳሽ ጋር ተቀላቅሎ ይታሸጋል። የዚህ ሂደት የመጨረሻው ውጤት ከሄሞግሎቢን የተሠራ ኦክስጅን ተሸካሚ (hemoglobin-based oxygen carrier [HBOC]) የሚባል ሲሆን እስከ አሁን ድረስ በርካታ አገሮች ጥቅም ላይ እንዲውል አልፈቀዱም። ደም ደማቅ ቀይ ቀለም እንዲኖረው የሚያደርገው ሄም በመሆኑ፣ ከሄሞግሎቢን የተሠራ ኦክስጅን ተሸካሚ ዋነኛ መገኛውን ይኸውም ቀይ የደም ሕዋስን የሚመስል መልክ አለው።

ቀይ የደም ሕዋስ ማቀዝቀዣ ውስጥ መቀመጥና ከጥቂት ሳምንታት በኋላ መጣል የሚኖርበት ሲሆን ከሄሞግሎቢን የተሠራ ኦክስጅን ተሸካሚ ግን ማቀዝቀዣ ውስጥ መግባት የማያስፈልገው ከመሆኑም በላይ ከወራት በኋላም ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል። በተጨማሪም ይህንን ከሄሞግሎቢን የተሠራ ኦክስጅን ተሸካሚ ለሕክምና መጠቀም ዓይነቱ የማይመሳሰል ደም በመውሰድ ምክንያት የሚመጡ ከባድ ችግሮች ያስከትላል ብሎ መስጋት አያስፈልግም፤ ምክንያቱም ከሄሞግሎቢን የተሠራው ኦክስጅን ተሸካሚ ጸረ እንግዳ አካላትን የሚይዘው የሕዋስ ሽፋን የለውም። የሆነ ሆኖ ከሄሞግሎቢን የተሠራ ኦክስጅን ተሸካሚ ከሌሎች የደም ክፍልፋዮች ጋር ሲነጻጸር አምላክ ስለ ደም ያወጣውን ሕግ ማክበር የሚፈልጉ ክርስቲያኖችን ሕሊና የሚፈታተኑ በርካታ ጎኖች አሉት። ለምን? ከሄሞግሎቢን የተሠራ ኦክስጅን ተሸካሚ ከደም የተገኘ እንደመሆኑ መጠን ሁለት አጠያያቂ ጉዳዮች ሊነሱ ይችላሉ። አንደኛ፣ ከሄሞግሎቢን የተሠራ ኦክስጅን ተሸካሚ የሚያከናውነው ሥራ ዋነኛ የደም ክፍል የሆነው ቀይ የደም ሕዋስ የሚፈጽመውን ቁልፍ ተግባር ነው። ሁለተኛ፣ ከሄሞግሎቢን የተሠራ ኦክስጅን ተሸካሚን ያስገኘው ሄሞግሎቢን በዚህ ፈሳሽ ውስጥ በብዛት ይገኛል። ስለዚህ ክርስቲያኖች ይህንንና ሌሎች ተመሳሳይ የደም ውጤቶችን በተመለከተ ውሳኔ ሲያደርጉ በጣም መጠንቀቅ ያስፈልጋቸዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ደም ቅድስና በተገለጹት መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ በጥንቃቄና በጸሎት ማሰላሰል ይገባቸዋል። እያንዳንዱ ክርስቲያን ከይሖዋ ጋር የመሠረተውን ጥሩ ወዳጅነት ጠብቆ ለማቆየት ካለው ጽኑ ፍላጎት በመነሳት በመጽሐፍ ቅዱስ በሠለጠነ ሕሊናው መመራት አለበት።ገላትያ 6:5

[ሥዕል]

የሄሞግሎቢን ሞለኪውል

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ተፈላጊነቱ እየጨመረ የመጣ የሕክምና ዘዴ

“በርካታ ሆስፒታሎች ‘ያለ ደም’ የሚደረግን የቀዶ ሕክምና እንደ አማራጭ እያቀረቡ ነው” ሲል ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል። አክሎም እንዲህ ብሏል:- “በመጀመሪያ የይሖዋ ምሥክሮችን ለመርዳት የተፈለሰፈው ይህ ዘዴ . . . ሰፊ ተቀባይነት በማግኘቱ በርካታ ሆስፒታሎች ደም አልባ የቀዶ ሕክምና ፕሮግራም እንዳላቸው ለሁሉም ሰው እያስተዋወቁ ነው።” በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሆስፒታሎች ለሕመምተኞች ደም የመስጠትን አስፈላጊነት የሚቀንሱ ሌሎች የሕክምና ዘዴዎችን ተግባራዊ ማድረግ፣ በተለይ ለታካሚዎች በርካታ ጥቅሞችን እንደሚያስገኝ እየተገነዘቡ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሺዎች የሚቆጠሩ ዶክተሮች ያለ ደም ሕመምተኞችን በማከም ላይ ናቸው።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ጤንነት ያላቸው አመለካከት

ሐኪሞችና ነርሶች የሆኑትን ጨምሮ ሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች ሙሉውን ደምም ሆነ ዋና ዋና የደም ክፍሎችን እንደማይወስዱ በመላው ዓለም የታወቀ ነው። ደም ላለመውሰድ ተመሳሳይ አቋም የያዙት በሰው ሠራሽ መሠረተ ትምህርት ምክንያት ወይም አንድ ሰው እምነት ካለው ከሕመም ይድናል የሚል አስተሳሰብ ስላላቸው ነው? እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ከእውነታው የራቀ ነው።

የይሖዋ ምሥክሮች ሕይወትን ከአምላክ የተገኘ ስጦታ እንደሆነ አድርገው ስለሚመለከቱ ከፍ ያለ ዋጋ ይሰጡታል፤ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ ‘የእግዚአብሔር መንፈስ እንዳለበት’ የሚያምኑ በመሆኑ በውስጡ ባሉት መመሪያዎች መሠረት ለመኖር አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ያደርጋሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17፤ ራእይ 4:11) መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ አገልጋዮች ጤናን ከሚጎዱ ወይም ሕይወትን ለአደጋ ከሚያጋልጡ ድርጊቶችና ልማዶች እንዲርቁ ምክር ይሰጣል፤ ከእነዚህም መካከል ከልክ በላይ መብላት፣ ትንባሆ ማጨስ ወይም ማኘክ፣ አልኮልን አላግባብ መጠቀም፣ መድኃኒቶችንና ዕፆችን ለመዝናናት ሲባል መውሰድ እንዲሁም ጫት መቃም ይገኙባቸዋል።ምሳሌ 23:20፤ 2 ቆሮንቶስ 7:1

አካላችንንና አካባቢያችንን በንጽሕና በመያዝ እንዲሁም ለጤንነት ስንል መጠነኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በሚስማማ መንገድ እንመላለሳለን። (ማቴዎስ 7:12፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:8) የይሖዋ ምሥክሮች ሲታመሙ የሕክምና እርዳታ በመፈለግና በርካታ የሕክምና አማራጮችን በመቀበል ምክንያታዊ እንደሆኑ ያሳያሉ። (ፊልጵስዩስ 4:5 NW) አዎን፣ ደም መውሰድን የማይጠይቁ ሕክምናዎችን ለማግኘት በመጣጣር ‘ከደም ራቁ’ የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ ያከብራሉ። (የሐዋርያት ሥራ 15:29) እንዲህ ለማድረግ መምረጣቸው በአብዛኛው ከፍተኛ ጥራት ያለው ሕክምና እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።