በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በዕፅዋት ላይ የሚታዩ አስደናቂ ንድፎች

በዕፅዋት ላይ የሚታዩ አስደናቂ ንድፎች

በዕፅዋት ላይ የሚታዩ አስደናቂ ንድፎች

ብዙ ዕፅዋት የሚያድጉት ክብ ቅርጽ ይዘው እንደሆነ አስተውለህ ታውቃለህ? ለምሳሌ አንድ አናናስ በአንድ አቅጣጫ የሚሄዱ 8 የቅርፊት ዙሮች፣ በተቃራኒው አቅጣጫ የሚሄዱ ደግሞ 5 ወይም 13 ዙሮች ሊኖሩት ይችላል። (ሥዕል 1ን ተመልከት።) በሱፍ አበባ ላይ ያሉትን ፍሬዎች ብትመለከት 55 እና 89 ወይም ከዚያ የሚበልጡ ዙሮች አንዳቸው ሌላውን አቋርጠው ትመለከት ይሆናል። እንዲያውም በአበባ ጎመን ላይ ሳይቀር ዙሮች ልትመለከት ትችላለህ። ዕፅዋት ዙሮች እንዳላቸው ካወቅህበት ጊዜ አንስቶ ወደ አትክልትና ፍራፍሬ መደብሮች የምትሄደው ለየት ያለ አመለካከት በመያዝ ይሆናል። ዕፅዋት በዚህ ሁኔታ የሚያድጉት ለምንድን ነው? የዙሮቹ ቁጥር የተለየ ትርጉም ይኖረው ይሆን?

ዕፅዋት የሚያድጉት እንዴት ነው?

አብዛኞቹ ዕፅዋት እንደ ግንድ፣ ቅጠልና አበባ የመሰሉትን አዳዲስ ክፍሎች የሚያወጡት አደግ (ሜሪስቴም) ከሚባል ማዕከላዊ ቦታ ነው። ፕሪሞርዲየም የሚባለው የተክሉ እያንዳንዱ አዲስ ክፍል ከማዕከላዊው ቦታ ወጥቶ በአዲስ አቅጣጫ በማደግ ከእርሱ በፊት ከተሠራው የተክሉ ክፍል ጋር ሲቀናጅ ማዕዘን ይሠራል። * (ሥዕል 2ን ተመልከት።) አብዛኞቹ ዕፅዋት አዳዲስ ክፍሎች የሚያወጡት ክብ ቅርጽ በሚያስገኝ ለየት ያለ ማዕዘን ነው። ይህ ማዕዘን ምንድን ነው?

እስቲ ለሚከተለው ሁኔታ መፍትሄ ለማግኘት ሞክር:- ምንም ቦታ ሳታባክን አዳዲስ የተክል ክፍሎችን የመብቀያው ቦታ ላይ አጠጋግተህ ለመደርደር እየሞከርክ እንደሆነ አስብ። እያንዳንዱ አዲስ ፕሪሞርዲየም ከእርሱ በፊት ካደገው ጋር ሲነጻጸር የሙሉ ክብ ሁለት አምስተኛ በሚያክል ማዕዘን ላይ እንዲያድግ አደረግህ እንበል። ይህ ሁኔታ ችግር የሚያስከትል ሲሆን ይህም እያንዳንዱ አምስተኛ ፕሪሞርዲየም ከተመሳሳይ ቦታና በተመሳሳይ አቅጣጫ የሚያድግ መሆኑ ነው። በመደዳ የሚቀመጡ ፕሪሞርዲየሞች ስለሚኖሩ በመስመሮቹ መሃል ያለው ቦታ ይባክናል። (ሥዕል 3ን ተመልከት።) ማንኛውም የክቡ ሙሉ ክፍልፋይ ወይም ፍራክሽን መስመሮች እንዲፈጠሩ ስለሚያደርግ የሚባክን ቦታ መኖሩ አይቀርም። ቦታ ሳይባክን ጥቅጥቅ ብለው የሚያድጉበት ሁኔታ የሚፈጠረው “ወርቃማ ማዕዘን” በሚባለው 137.5 ዲግሪ ገደማ ላይ ብቻ ነው። (ሥዕል 5ን ተመልከት።) ይህን ማዕዘን ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?

ወርቃማው ማዕዘን በጣም ተስማሚ የሆነው የአንድ ዙር ሙሉ ክፍልፋይ ሊሆን ስለማይችል ነው። የአንድ ሙሉ ዙር 5/8 ወደ እርሱ የተጠጋ ነው፣ 8/13ኛው ደግሞ ይበልጥ የተጠጋ ሲሆን 13/21ኛው ደግሞ ከዚያ ይበልጥ በጣም የሚቀርበው ቢሆንም የአንድ ዙር ወርቃማውን መጠን በትክክል ሊገልጽ የሚችል ክፍልፋይ ግን የለም። ስለዚህ በአደግ ላይ አንድ አዲስ ቅጠል ከእርሱ በፊት ካደገው ቅጠል በ137.5 ዲግሪ ማዕዘን ላይ ካደገ ሁለት ቅጠሎች ፈጽሞ በአንድ አቅጣጫ ሊያድጉ አይችሉም። (ሥዕል 4ን ተመልከት።) በዚህም ምክንያት ፕሪሞርዲያው እንደ ጨረር የሚወጣ ከመሆን ይልቅ ጥምዝ ቅርጽ ይኖረዋል።

በኮምፒውተር እገዛ የተሠራ ከአንድ ማዕከላዊ ቦታ የሚነሳ የፕሪሞርዲያ እድገት የሚያሳዩ ሥዕሎች ተለይተው የሚታዩ ዙሮች የሚኖሯቸው በአዳዲስ እድገቶች መካከል የሚኖረው ማዕዘን ትክክል ሲሆን ብቻ ነው። ከወርቃማው ማዕዘን በአንድ አሥረኛ ዲግሪ እንኳን ዝንፈት ቢፈጠር ተመሳሳይ ውጤት ሊገኝ አይችልም።—ሥዕል 5ን ተመልከት።

በአንድ አበባ ላይ የሚኖሩ መልካ አበቦች ስንት ናቸው?

በወርቃማ ማዕዘን ላይ የተመሠረተ እድገት በሚኖርበት ጊዜ የመልካ አበቦች ቁጥር የፊቦናቺ ሥርዓት የሚባለውን ሕግ ይከተላል። ይህ ሥርዓት ለመጀመሪያ ጊዜ የተገለጸው በ13ኛው መቶ ዘመን ይኖር በነበረው ሊዮናርዶ ፊቦናቺ በተባለ የሂሣብ ሊቅ ነው። በዚህ ሥርዓት መሠረት ከ1 በኋላ ያለው እያንዳንዱ ቁጥር ከፊቱ ያሉት ሁለት ቁጥሮች ድምር ሲሆን ይህም እንደሚከተለው ነው—1, 1, 2, 3, 5, 8, 13, 21, 34, 55 ወዘተ።

ክብ ቅርጽ ይዘው የሚያድጉ የብዙ ዕፅዋት አበቦች አብዛኛውን ጊዜ የፊቦናቺን ሥርዓት የተከተለ የመልካ አበቦች ቁጥር አሏቸው። የዕፅዋቱን ባሕርይ የሚከታተሉ አንዳንዶች እንዳሉት በአብዛኛው የቀጋ አበቦች 5 መልካ አበቦች፣ ብለድሩትስ የተባለው አበባ 8፣ ፋየርዊድስ 13፣ ኤስተርስ 21፣ በየቦታው የሚገኘው ዴይዚ 34 እንዲሁም ማይክልማስ ዴይዚ 55 ወይም 89 መልካ አበቦች አሏቸው። (ሥዕል 6ን ተመልከት።) ፍራፍሬዎችና አትክልቶች በአብዛኛው የፊቦናቺን ሥርዓት የሚከተል ገጽታ አላቸው። ለምሳሌ ሙዝ ከመሃል ተቆርጦ ሲታይ አምስት ጎኖች አሉት።

‘ሁሉንም ነገር ውብ አድርጎ ሠራው’

የሥነ ጥበብ ሰዎች እንደ ወርቃማው ማዕዘን ለዓይናችን እጅግ አምሮ የሚታይ ሥርዓት እንደሌለ ከተገነዘቡ ብዙ ጊዜ ሆኗል። ዕፅዋት ይህን ምሥጢራዊ ማዕዘን ተከትለው እንዲያድጉ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው? ብዙ ሰዎች ይህ አንድ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ያለው ንድፍ አውጪ መኖሩን የሚያረጋግጥ ተጨማሪ ማስረጃ እንደሆነ ያምናሉ።

ብዙዎች የሕያዋን ነገሮችን አፈጣጠርና እኛም በእነዚህ ፍጥረታት ለመደሰት በመቻላችን ላይ ሲያሰላስሉ በሕይወት እንድንደሰት የሚፈልግ ፈጣሪ መኖሩን ይገነዘባሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፈጣሪያችን ሲናገር “ሁሉንም ነገር በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው” ይላል።—መክብብ 3:11

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 የሚገርመው ነገር፣ በሱፍ አበባ ላይ የሚያድጉ ወደ ሱፍ ፍሬነት የሚለወጡ ትንንሽ አበቦች ክብ ቅርጽ መሥራት የሚጀምሩት ከመካከል ሳይሆን ከዳር መሆኑ ይህን አበባ ከሌሎቹ ዕፅዋት የተለየ ያደርገዋል።

[በገጽ 24, 25 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

ሥዕል 1

(ጽሑፉን ተመልከት)

ሥዕል 2

(ጽሑፉን ተመልከት)

ሥዕል 3

(ጽሑፉን ተመልከት)

ሥዕል 4

(ጽሑፉን ተመልከት)

ሥዕል 5

(ጽሑፉን ተመልከት)

ሥዕል 6

(ጽሑፉን ተመልከት)

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አደግ (ሜሪስቴም) ጎልቶ ሲታይ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

R. Rutishauser, University of Zurich, Switzerland

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ነጭ አበባ:- Thomas G. Barnes @ USDA-NRCS PLANTS Database