በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በፈጣሪ የምናምንበት ምክንያት

በፈጣሪ የምናምንበት ምክንያት

በፈጣሪ የምናምንበት ምክንያት

በተለያዩ የሳይንስ ዘርፎች የተሰማሩ በርካታ ሊቃውንት ፍጥረት ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ የሚጠይቅ ንድፍ እንደተንጸባረቀበት ያምናሉ። በምድር ላይ የሚኖሩ ሕያዋን ፍጥረታት እንዲያው በአጋጣሚ የተገኙ ናቸው ብሎ ማመን ምክንያታዊ መስሎ አይታያቸውም። በዚህም ምክንያት በርካታ ሳይንቲስቶችና ተመራማሪዎች በፈጣሪ ያምናሉ።

ከእነዚህ አንዳንዶቹ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ አምላክ የግዑዙ ጽንፈ ዓለም ንድፍ አውጪና ፈጣሪ እንደሆነ አሳማኝ ምክንያት አግኝተዋል። እነዚህ ሰዎች እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረሱት ለምንድን ነው? ንቁ! መጽሔት አንዳንዶቹን አነጋግሯቸዋል። የሰጡትን አስተያየት ለማወቅ መፈለግህ አይቀርም። *

‘ሕይወት ለመረዳት የሚከብድ ውስብስብነት አለው’

ቮልፍ-ኤከሃርት ሎኒግ

አጭር የሕይወት ታሪክ:- ላለፉት 28 ዓመታት በዕፅዋት ጄኔቲክ ሚውቴሽን መስክ ሳይንሳዊ ጥናት ሳካሂድ ቆይቻለሁ። ከእነዚህ ውስጥ 21ዱን ዓመታት የሠራሁት ኮሎኝ፣ ጀርመን በሚገኘው የማክስ ፕላንክ ዕፅዋትን የማዳቀል ምርምር ተቋም ውስጥ ነው። በተጨማሪም ለሠላሳ ዓመታት ያህል በክርስቲያን የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኜ አገልግያለሁ።

በጄኔቲክስ የጥናት መስክ ያካሄድኩት በሙከራ ላይ የተመሠረተ ምርምርም ሆነ እንደ ፊዚዮሎጂና ሞርፎሎጂ ባሉት የባዮሎጂ ትምህርት ዘርፎች ያደረግሁት ጥናት ሕይወት ለመረዳት የሚከብድ ውስብስብነት ያለው መሆኑን እንዳስተውል ረድቶኛል። በእነዚህ ዘርፎች ላይ ያደረግሁት ጥናት ሌላው ቀርቶ ሕይወት የተገነባባቸው በጣም ረቂቅ ነገሮች እንኳ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ያለው ሠሪ ሊኖራቸው እንደሚገባ ያለኝን እምነት አጠንክሮልኛል።

የሳይንሱ ማኅበረሰብ ሕይወት የተገነባባቸው ነገሮች በጣም ውስብስብ መሆናቸውን በሚገባ ያውቃል። ይሁን እንጂ እነዚህ አስደናቂ ሐቆች የሚቀርቡት የዝግመተ ለውጥን ንድፈ ሐሳብ እንደሚደግፉ ተደርገው ነው። በእኔ አስተያየት ግን የመጽሐፍ ቅዱስን የፍጥረት ዘገባ ለማጣጣል ከሚቀርቡት የመከራከሪያ ነጥቦች መካከል በጣም ጠንካራ የሚባለው እንኳን በሳይንሳዊ መመዘኛ ሲለካ ሚዛን የሚደፋ ሆኖ አይገኝም። እነዚህን የመከራከሪያ ነጥቦች ለበርካታ ዓመታት መርምሬያለሁ። ሕይወት ያላቸውን ፍጥረታት ባሕርይ በጥንቃቄ ካጠናሁና ጽንፈ ዓለሙ የሚገዛባቸው ሕግጋት ሕይወት በምድር ላይ እንዲኖር ሁኔታዎችን እንዴት እንደሚያመቻቹ ከመረመርኩ በኋላ በፈጣሪ ለማመን ተገድጃለሁ።

‘የምመለከታቸው ነገሮች በሙሉ ያለ ምክንያት የተገኙ አይደሉም’

ባይረን ሊዮን ሜዶስ

አጭር የሕይወት ታሪክ:- የምኖረው በዩናይትድ ስቴትስ ሲሆን የምሠራው በብሔራዊ የበረራና ሕዋ አስተዳደር [NASA] በሌዘር ፊዚክስ የጥናት ዘርፍ ውስጥ ነው። በአሁኑ ጊዜ የዓለምን የአየር ሁኔታና ሌሎች ፕላኔታዊ ክስተቶችን ለመቆጣጠርና ለማጥናት የሚያስችለውን ቴክኖሎጂ ለማሻሻል እየተደረገ ባለው ጥናት እካፈላለሁ። እንዲሁም በቨርጂንያ አካባቢ በሚገኘው በኪልማርኖክ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኜ በማገልገል ላይ ነኝ።

በምርምር ሥራዬ ብዙውን ጊዜ የፊዚክስ ሕግጋትን አጠናለሁ። አንዳንድ ነገሮች እንዴትና ለምን እንደሚከሰቱ ለመረዳት እፈልጋለሁ። በተሰማራሁበት የጥናት መስክ የምመለከታቸው ነገሮች በሙሉ ያለ ምክንያት የተገኙ እንዳልሆኑ የሚያረጋግጥልኝ ግልጽ መረጃ አገኛለሁ። በሳይንሳዊ መሥፈርት ሲመዘን በተፈጥሮ ያሉትን ነገሮች በሙሉ አምላክ እንደፈጠራቸው ማመኑ ምክንያታዊ እንደሆነ ይሰማኛል። የተፈጥሮ ሕግጋት ፈጽሞ ዝንፍ የማይሉ መሆናቸው ግሩም የማደራጀት ችሎታ ያለው ፈጣሪ ያወጣቸው መሆኑን እንዳምን ያስገድደኛል።

እንዲህ ያለው መደምደሚያ ግልጽ ሆኖ ሳለ በጣም ብዙ ሳይንቲስቶች በዝግመተ ለውጥ የሚያምኑት ለምንድን ነው? የዝግመተ ለውጥ አማኞች መረጃዎቹን የሚመዝኑት አስቀድመው ከደረሱበት መደምደሚያ አንጻር ስለሆነ ይሆን? ሳይንቲስቶች እንዲህ ማድረጋቸው እንግዳ ነገር አይደለም። ይሁን እንጂ በግልጽ የሚታይ ነገር ምንም ያህል አሳማኝ ቢሆን ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ ያስችላል ማለት አይቻልም። ለምሳሌ ያህል፣ በሌዘር ፊዚክስ ላይ ጥናት የሚያደርግ ሰው ብርሃን ብዙውን ጊዜ የሞገድነት ባሕርይ ስለሚታይበት ልክ እንደ ድምፅ ሞገድ ነው ብሎ ሊከራከር ይችላል። ይሁን እንጂ ብርሃን ፎቶንስ የሚባሉ ቅንጣቶች እንዳሉት የሚያሳይ ባሕርያትም ስላሉት ይህ መደምደሚያው የተሟላ አይሆንለትም። በተመሳሳይም ዝግመተ ለውጥ እውነት እንደሆነ አድርገው የሚከራከሩ ሰዎች እዚህ መደምደሚያ ላይ የሚደርሱት ቁንጽል ሐቅ ይዘው ነው። በአእምሯቸው የያዙት ግምታዊ ሐሳብ መረጃዎቹን በሚመዝኑበት መንገድ ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድር ይፈቅዳሉ።

የዝግመተ ለውጥ “ሊቃውንት” ራሳቸው ዝግመተ ለውጥ በተከናወነበት መንገድ ላይ እርስ በርሳቸው እየተወዛገቡ ባሉበት በዚህ ጊዜ ንድፈ ሐሳቡን ተጨባጭ ሐቅ እንደሆነ አድርጎ የሚቀበል ሰው መኖሩ በጣም ያስገርመኛል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ሊቃውንት 2 ሲደመር 2 አራት እንደሆነ ሲናገሩ ሌሎች ግን 3 ወይም 6 ነው ብለው ቢከራከሩ ሒሳብ የተረጋገጠ ሐቅ ነው ብለህ ትቀበል ነበር? የሳይንስ ሚና በማስረጃ፣ በሙከራ እንዲሁም በሠርቶ ማሳያ ሊረጋገጥ የሚችለውን ብቻ መቀበል ከሆነ ሕይወት ያለው ነገር ሁሉ በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት ከአንድ የጋራ ቅድመ አያት ተገኝቷል የሚለው ንድፈ ሐሳብ ሳይንሳዊ ሐቅ አይደለም።

“እንዲሁ በራሱ ሊገኝ የሚችል ምንም ነገር የለም”

ኬኔት ሎይድ ታናካ

አጭር የሕይወት ታሪክ:- ጂኦሎጂስት ስሆን በአሁኑ ጊዜ ፍላግስታፍ፣ አሪዞና የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ የምድር ጥናት ተቋም ባልደረባ ነኝ። ለሠላሳ ዓመታት ለማለት ይቻላል፣ ሌሎች ፕላኔቶችን ጨምሮ በተለያዩ የምድር ጥናት መስኮች ላይ በሚደረጉ ሳይንሳዊ ምርምሮች ተካፍያለሁ። በርካታ የጥናት ጽሑፎቼና የማርስ ጂኦሎጂያዊ ካርታዎቼ እውቅ በሆኑ ሳይንሳዊ መጽሔቶች ላይ ወጥተዋል። የይሖዋ ምሥክር እንደመሆኔ መጠን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያነቡ በማበረታታት በየወሩ 70 ሰዓት ያህል አሳልፋለሁ።

በዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ እንዳምን የሚያደርግ ትምህርት የተሰጠኝ ቢሆንም ጽንፈ ዓለምን ለማስገኘት የሚያስፈልገው ብርቱ ኃይል እጅግ ኃያል ከሆነ ፈጣሪ ካልሆነ በስተቀር በራሱ ሊገኝ ይችላል ብዬ እንዳምን አላደረገኝም። እንዲሁ በራሱ ሊገኝ የሚችል ምንም ነገር የለም። በተጨማሪም የፈጣሪን መኖር የሚያሳምን ጠንካራ ማረጋገጫ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አግኝቻለሁ። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ከተሰማራሁበት የሳይንስ ዘርፍ ጋር የሚስማሙ ምድር ክብ መሆኗንና “በባዶው ላይ” እንደተንጠለጠለች የሚገልጹ ሳይንሳዊ ሐቆችን አግኝቻለሁ። (ኢዮብ 26:7፤ ኢሳይያስ 40:22) እነዚህ ሐቆች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፉት ሰዎች በምርምር ከማረጋገጣቸው ከረዥም ዘመናት በፊት ነው።

እስቲ የገዛ ራሳችንን አፈጣጠር እንመልከት። የስሜት ሕዋሳት፣ ማንነትን የማወቅ ችሎታ፣ ረቂቅ ነገሮችን የማስተዋል ችሎታ፣ ሐሳባችንን የመግለጽ ችሎታና የተለያዩ ስሜቶች አሉን። በተለይ ደግሞ የመውደድና የመወደድ እንዲሁም ሌሎች ስላሳዩን ፍቅር አድናቆታችንን የመግለጽ ችሎታ አለን። አስደናቂ የሆኑት እነዚህ የሰው ልጅ ችሎታዎች ከየት እንደተገኙ ከዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ማብራሪያ ማግኘት አንችልም።

‘የዝግመተ ለውጥን ንድፈ ሐሳብ ይደግፋሉ ተብለው የሚጠቀሱት የመረጃ ምንጮች ምን ያህል ተአማኒነት አላቸው?’ እያልን ራሳችንን እንጠይቅ። ከምድር ጥናት የተገኙት መረጃዎች ያልተሟሉና የተወሳሰቡ ከመሆናቸውም በላይ ግራ የሚያጋቡ ናቸው። የዝግመተ ለውጥ አማኞች ተከናውኗል የሚሉትን ይህን ሒደት ሳይንሳዊ ዘዴዎችን ተጠቅመው በቤተ ሙከራ ሊያረጋግጡልን አልቻሉም። ሳይንቲስቶች በአብዛኛው መረጃዎችን በሚያሰባስቡበት ጊዜ ጥሩ የምርምር ዘዴዎችን የሚጠቀሙ ቢሆንም እነዚህን መረጃዎች በሚተነትኑበትና በሚተረጉሙበት ጊዜ ግን ራስ ወዳድነት ያሸንፋቸዋል። መረጃዎቹ አጠራጣሪ ወይም ተቃራኒ በሚሆኑበት ጊዜ ደግሞ የራሳቸውን አስተሳሰብ ማራመድ እንደሚቀናቸው የታወቀ ነው። ከፍተኛ ቦታ የሚሰጡት ለተሰማሩበት የሥራ መስክና ለግል ዝናቸው ነው።

ሳይንቲስትና የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ እንደመሆኔ መጠን ትክክለኛ ግንዛቤ ላይ ለመድረስ እንድችል በግልጽ ከታወቁና ከተረጋገጡ ሐቆች ጋር ሙሉ በሙሉ የሚስማማውን እውነት ለማግኘት እጥራለሁ። እኔ በበኩሌ ከሁሉም ይበልጥ ምክንያታዊ ሆኖ ያገኘሁት በፈጣሪ ማመን ነው።

“በእያንዳንዱ ሴል ውስጥ የሚታየው አስደናቂ ንድፍ”

ፓውላ ኪንቸሎ

አጭር የሕይወት ታሪክ:- በሴልና በሞለኪውል ባዮሎጂ እንዲሁም በማይክሮባዮሎጂ የምርምር ዘርፎች የበርካታ ዓመታት ልምድ አለኝ። በአሁኑ ጊዜ የምሠራው አትላንታ፣ ጆርጅያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የኤመሪ ዩኒቨርሲቲ ነው። በተጨማሪም ለሩሲያ ቋንቋ ተናጋሪ ማኅበረሰቦች መጽሐፍ ቅዱስ የማስተማር ነጻ አገልግሎት እሰጣለሁ።

በባዮሎጂ የጥናት ዘርፍ በሴልና በሴል ክፍሎች ላይ ብቻ አራት ዓመት የፈጀ ትምህርት ወስጃለሁ። ስለ ዲ ኤን ኤ፣ አር ኤን ኤ፣ ፕሮቲኖችና፣ ኬሚካላዊ ሂደቶች ባወቅሁ መጠን ሴሎች ስላላቸው ውስብስብነት፣ የተቀናጀ አሠራርና ትክክለኝነት ያለኝ አድናቆት ይጨምራል። የሰው ልጅ ስለ ሴሎች የደረሰበት የእውቀት ደረጃ በእጅጉ ቢያስደንቀኝም ገና ብዙ ያላወቃቸው ነገሮች እንዳሉ ይሰማኛል። በአምላክ መኖር እንዳምን ያስገደደኝ በእያንዳንዱ ሴል ውስጥ የሚታየው አስደናቂ ንድፍ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴ የፈጣሪን ማንነት አሳውቆኛል፤ ይህ ፈጣሪ ይሖዋ አምላክ ይባላል። እርሱ ጥበበኛ ንድፍ አውጪ ብቻ ሳይሆን ለእኔ የሚያስብ ደግና አፍቃሪ አባት እንደሆነም ጭምር አሳምኖኛል። መጽሐፍ ቅዱስ የሕይወት ዓላማ ምን እንደሆነ ከመግለጹም በላይ የወደፊቱ ጊዜ አስደሳች እንደሚሆን ተስፋ ይሰጣል።

በትምህርት ቤት ስለ ዝግመተ ለውጥ በመማር ላይ የሚገኙ ወጣቶች በምን ማመን እንደሚኖርባቸው ለመወሰን ይቸገሩ ይሆናል። እንዲህ ያለው ጊዜ ግራ የሚያጋባ ሊሆንባቸው ይችላል። በአምላክ የሚያምኑ ከሆነ ስለዚህ ንድፈ ሐሳብ ሲማሩ እምነታቸው ፈተና ላይ ይወድቃል። ይሁን እንጂ ይህን ፈተና በዙሪያችን ባለው ተፈጥሮ ውስጥ የሚንጸባረቁትን አስደናቂ ነገሮች በመመርመርና ስለ ፈጣሪና ስለ ባሕርያቱ ያላቸውን እውቀት በማሳደግ ሊወጡት ይችላሉ። እኔ በግሌ እንዲህ ስላደረግሁ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፍጥረት የሚናገረው ዘገባ ትክክል እንደሆነ እንዲሁም ከእውነተኛ ሳይንስ ጋር እንደማይጋጭ ለማመን ችያለሁ።

‘የተፈጥሮ ሕጎች ያልተወሳሰቡና ግልጽ ናቸው’

ኤንሪኬ ኤርናንዴስ-ላሙስ

አጭር የሕይወት ታሪክ:- በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ነኝ። በተጨማሪም በሜክሲኮ ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ የፊዚክስ ንድፈ ሐሳቦች ተመራማሪ ነኝ። በአሁኑ ጊዜ ከዋክብት እንዲያድጉ የሚያደርገውን ግራቮተርማል ካታስትሮፍ የሚባለውን ክስተት እንቆቅልሽ የሚፈታ የቴርሞዳይናሚክስ ማብራሪያ ለማግኘት በሚደረገው ጥናት ላይ እካፈላለሁ። በተጨማሪም ዲ ኤን ኤ ምን ያህል ውስብስብ እንደሆነ ጥናት አካሂጃለሁ።

በአጭሩ ሕይወት በጣም ውስብስብ በመሆኑ እንዲያው በአጋጣሚ ሊገኝ አይችልም። ለምሳሌ ያህል፣ በዲ ኤን ኤ ሞለኪውል ውስጥ የሚገኘውን በጣም ሰፊ የመረጃ ክምችት እንመልከት። አንዲት ክሮሞዞም በራስዋ ልትገኝ የምትችልበት አጋጣሚ ቢበዛ ከ9 ትሪሊዮን አንድ በመሆኑ ፈጽሞ ሊሆን አይችልም ማለት ይቀላል። ምንም ዓይነት የማሰብ ችሎታ የሌላቸው ኃይሎች አንድን ክሮሞዞም ብቻ ሳይሆን በሕያዋን ፍጥረታት ውስጥ የሚገኙትን በጣም ውስብስብ አሠራሮች በሙሉ አስገኙ ብሎ ማመን ሞኝነት እንደሆነ ይሰማኛል።

በተጨማሪም በአጉሊ መነጽር ብቻ ሊታይ ከሚችለው አነስተኛ የቁስ አካል ቅንጣት አንስቶ በሕዋ ውስጥ በሚንቀሳቀሱት በጣም ግዙፍ የደመና አካላት ውስጥ የሚታየውን እጅግ የተወሳሰበ ባሕርይ ሳጠና እነዚህ እንቅስቃሴዎች የሚመሩባቸው ሕጎች ያልተወሳሰቡና ግልጽ መሆናቸው ያስደንቀኛል። ለእኔ እነዚህ ሕግጋት የአንድ ታላቅ የሒሳብ ሊቅ ብቻ ሳይሆን ታላቅ የሥነ ጥበብ ሊቅ የሥራ ውጤቶች መሆናቸውን ያረጋግጡልኛል። ብዙውን ጊዜ ሰዎች የይሖዋ ምሥክር መሆኔን ስነግራቸው ይደነቃሉ። አንዳንድ ጊዜ እንዴት በአምላክ ታምናለህ ብለው ይጠይቁኛል። አብዛኞቹ ሃይማኖቶች አማኞቻቸው ስለሚማሯቸው ነገሮች ማስረጃ እንዲሰጣቸው እንዲጠይቁ ወይም ስለ እምነታቸው ምርምር እንዲያደርጉ ስለማያበረታቱ እንዲህ ቢሰማቸው አያስደንቅም። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ‘የማስተዋል ችሎታችንን’ እንድንጠቀም ያበረታታል። (ምሳሌ 3:21) ተፈጥሮ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ የሚጠይቅ ንድፍ የተንጸባረቀበት መሆኑን የሚያረጋግጡት ማስረጃዎች መጽሐፍ ቅዱስ ከያዘው ማስረጃ ጋር ተዳምረው አምላክ እንዳለ ብቻ ሳይሆን ይህ አምላክ ጸሎቶቻችንን በትኩረት የሚያዳምጥ መሆኑን እንዳምን አድርገውኛል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ሊቃውንት የሰጡት አስተያየት የራሳቸውን እንጂ የሚሠሩበትን ተቋም አመለካከት የሚያንጸባርቅ አይደለም።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

በስተ ጀርባ የሚታየው የማርስ ምስል:- Courtesy USGS Astrogeology Research Program, http://astrogeology.usgs.gov