በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ሕይወትን የፈጠረው በዝግመተ ለውጥ ነው?

አምላክ ሕይወትን የፈጠረው በዝግመተ ለውጥ ነው?

አምላክ ሕይወትን የፈጠረው በዝግመተ ለውጥ ነው?

“ጌታችንና አምላካችን ሆይ፤ ክብርና ሞገስ፣ ኀይልም ልትቀበል ይገባሃል፤ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና፤ በፈቃድህም ተፈጥረዋልና፤ ሆነዋልምና።” —ራእይ 4:11

ቻርልስ ዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳቡን ለዓለም ካስተዋወቀ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሃይማኖታዊ ቡድኖች በአምላክ ላይ ያላቸውን እምነት ከዚህ ንድፈ ሐሳብ ጋር ማስታረቅ የሚችሉበትን መንገድ መፈለግ ጀመሩ።

በዛሬው ጊዜ ክርስቲያን እንደሆኑ ከሚናገሩት ታዋቂ ሃይማኖታዊ ቡድኖች መካከል አብዛኞቹ አምላክ ሕይወትን ለማስገኘት በሆነ መንገድ ዝግመተ ለውጥን ተጠቅሟል የሚለውን ሐሳብ የሚቀበሉ ይመስላል። አንዳንዶች አምላክ ጽንፈ ዓለሙን ሲፈጥር ሕይወት ከሌላቸው ኬሚካሎች ሕይወት እንዲጀምር በማድረግ የኋላ ኋላ በዚሁ ሂደት አማካኝነት የሰው ልጅ እንዲገኝ አድርጓል ብለው ያስተምራሉ። ቴየስቲክ ኢቮሉሽን የሚባለውን ይህን ትምህርት የሚቀበሉ ቡድኖች አምላክ አንድ ጊዜ ሂደቱን ካስጀመረ በኋላ እጁን ጣልቃ አላስገባም ብለው ያምናሉ። ሌሎች ደግሞ አምላክ አብዛኞቹ የዕፅዋትና የእንስሳት ዝርያዎች በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት እንዲገኙ ያደረገ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ሂደቱን ለማፋጠን ጣልቃ ይገባ እንደነበረ ይሰማቸዋል።

ሁለቱን ትምህርቶች ማስታረቅ ይቻላል?

የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር በእርግጥ ሊስማማ ይችላል? የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ እውነት ከሆነ ስለ መጀመሪያው ሰው ስለ አዳም አፈጣጠር የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ  የሞራል ትምህርት ከመስጠት የበለጠ ፋይዳ የሌለው ቃል በቃል ሊወሰድ የማይችል ታሪክ ይሆናል ማለት ነው። (ዘፍጥረት 1:26, 27፤ 2:18-24) ኢየሱስ ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንዲህ ያለ አመለካከት ነበረው? እንዲህ ብሎ ነበር:- “ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አድርጎ እንደ ፈጠራቸው አላነበባችሁምን? እንዲህም አለ፤ ‘ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣመራል፣ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’ የተባለው በዚህ ምክንያት አይደለምን? ከእንግዲህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው።”—ማቴዎስ 19:4-6

ኢየሱስ እዚህ ላይ የጠቀሰው በዘፍጥረት ምዕራፍ 2 ላይ የተገለጸውን የፍጥረት ታሪክ ነው። ኢየሱስ የመጀመሪያው ጋብቻ የፈጠራ ታሪክ እንደሆነ አድርጎ ቢያምን ኖሮ ጋብቻ ቅዱስ መሆኑን ለማስረዳት ማስረጃ አድርጎ ይጠቅሰው ነበር? በፍጹም። ኢየሱስ በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ የሚገኘውን ታሪክ የጠቀሰው እውነተኛ ታሪክ መሆኑን ያውቅ ስለነበረ ነው።—ዮሐንስ 17:17

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም በተመሳሳይ ስለ ፍጥረት በሚናገረው የዘፍጥረት መጽሐፍ ዘገባ ያምኑ ነበር። ለምሳሌ ሉቃስ በጻፈው ወንጌል ላይ የኢየሱስ የትውልድ ሐረግ ወደኋላ እየተቆጠረ እስከ አዳም ድረስ ተዘርዝሯል። (ሉቃስ 3:23-38) አዳም ሐሳብ የወለደው ሰው ከሆነ ይህ የትውልድ ሐረግ ከተጨባጭ ሐቅ ወደ ፈጠራ የተሸጋገረው የት ላይ ነው? የዚህ የዘር ሐረግ መነሻ ፈጠራ ቢሆን ኖሮ ኢየሱስ ከዳዊት የትውልድ ሐረግ የተገኘ መሲሕ ለመሆኑ ማረጋገጫ ሆኖ ሊጠቀስ ይችል ነበር? (ማቴዎስ 1:1) የወንጌል ጸሐፊ የሆነው ሉቃስ “ሁሉን ከመሠረቱ በጥንቃቄ [መረመርሁ]” ብሏል። እርሱም በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ በሚገኘው የፍጥረት ታሪክ ያምን እንደነበረ ግልጽ ነው።—ሉቃስ 1:3

ሐዋርያው ጳውሎስ በኢየሱስ ላይ የነበረው እምነት በዘፍጥረት ዘገባ ላይ የተመሠረተ ነበር። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሞት በአንድ ሰው በኩል እንደ መጣ፣ የሙታንም ትንሣኤ በአንድ ሰው በኩል ሆኖአልና። ሰዎች ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ፣ እንደዚሁም ሰዎች ሁሉ በክርስቶስ ሕያዋን ይሆናሉ።” (1 ቆሮንቶስ 15:21, 22) ኃጢአትም ሆነ የኃጢአት ውጤት የሆነው ሞት ወደ ዓለም ለመግባታቸው ምክንያት የሆነው አዳም የሰው ዘር የመጀመሪያ አባት ባይሆን ኖሮ ኢየሱስ በውርስ የሚተላለፈውን ኃጢአት ለማስወገድ የሚሞትበት ምን ምክንያት ይኖራል?—ሮሜ 5:12፤ 6:23

ሰዎች ዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ በሚገኘው የፍጥረት ታሪክ ላይ ያላቸውን እምነት ለማዳከም መሞከር የክርስትናን እምነት መሠረት ከመናድ ተለይቶ አይታይም። የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብና የክርስቶስ ትምህርት ፈጽሞ ሊጣጣሙ አይችሉም። እነዚህን እምነቶች ለማስታረቅ የሚደረገው ማንኛውም ጥረት ‘በማዕበል ወደ ፊትና ወደ ኋላ የሚነዳና በትምህርት ነፋስ ወዲያና ወዲህ የሚንገዋለል’ ደካማ እምነት ከማስገኘት ሌላ ምንም ፋይዳ የለውም።—ኤፌሶን 4:14

በጠንካራ መሠረት ላይ የተመሠረተ እምነት

መጽሐፍ ቅዱስ ለበርካታ መቶ ዓመታት የትችትና የጥቃት ዒላማ ሆኖ ቆይቷል። ይሁንና የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ትክክል መሆኑ በተደጋጋሚ ጊዜያት ተረጋግጧል። መጽሐፍ ቅዱስ ከታሪክ፣ ከጤናና ከሳይንስ ጋር በተያያዘ የሚያነሳቸው ጉዳዮች በሙሉ እምነት የሚጣልባቸው መሆኑ በተደጋጋሚ ተረጋግጧል። ስለ ሰዎች የእርስ በርስ ግንኙነት የሚሰጠው ምክር አስተማማኝና ዘመን የማይሽረው ነው። ሰብዓዊ ፍልስፍናዎችና ንድፈ ሐሳቦች አንድ ሰሞን ብቅ ብሎ ወዲያው እንደሚጠወልግ ሣር ናቸው፤ የአምላክ ቃል ግን “ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”—ኢሳይያስ 40:8

የዝግመተ ለውጥ ትምህርት በሳይንሳዊ ንድፈ ሐሳብነት ብቻ ተወስኖ አልቀረም። ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ሲያብብና ሲስፋፋ የቆየ ሰብዓዊ ፍልስፍና ነው። ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተፈጥሮ የተራቀቀ ንድፍ አውጪ እንዳለው የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች እየበዙ በመምጣታቸው ለእነዚህ ማስረጃዎች ምላሽ ለመስጠት ሲባል የዳርዊን ንድፈ ሐሳብ ራሱ አዝጋሚ ለውጥ እያደረገ ነው። ይህን ጉዳይ በይበልጥ እንድትመረምር እንጋብዝሃለን። በዚሁ እትም ውስጥ የሚገኙትን ሌሎች ርዕሶች በማንበብ ይህን ማድረግ ትችላለህ። በተጨማሪም በዚህና በ32ኛው ገጽ ላይ የተጠቀሱትን መጻሕፍት ማንበብ ትችላለህ።

በዚህ ጉዳይ ላይ ምርምር ካደረግክ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቀድሞዎቹ ዘመናት በሚናገራቸው ነገሮች ላይ ያለህ እምነት መጠናከሩ አይቀርም። ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ በሚሰጠው ተስፋ ላይ ያለህ እምነት ይጠናከራል። (ዕብራውያን 11:1) በተጨማሪም ‘የሰማይና የምድር ፈጣሪ’ የሆነውን ይሖዋን ለማወደስ ትገፋፋ ይሆናል።—መዝሙር 146:6

ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት

ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛነት የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች በዚህ ብሮሹር ውስጥ ተገልጸዋል

Is There a Creator Who Cares About You? አንዳንድ ሳይንሳዊ ማስረጃዎችን በመመርመር አሳቢ የሆነው አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደበትን ምክንያት ለማወቅ ጥረት አድርግ

ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? “አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?” የሚለው ጥያቄ በዚህ መጽሐፍ በምዕራፍ 3 ላይ ተብራርቷል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ኢየሱስ ስለ ፍጥረት በሚናገረው የዘፍጥረት መጽሐፍ ዘገባ ያምን ነበር። ታዲያ እርሱ ተሳስቶ ነበር?

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ዝግመተ ለውጥ ምንድን ነው?

ዝግመተ ለውጥ ተብሎ የሚተረጎመው “ኢቮሉሽን” የሚለው እንግሊዝኛ ቃል “በአንድ አቅጣጫ የሚጓዝ የለውጥ ሂደት” የሚል ፍቺ አለው። ይሁን እንጂ ቃሉ በተለያዩ መንገዶችም ይሠራበታል። ለምሳሌ ያህል ሕይወት የሌላቸው ነገሮች የሚያደርጉትን ከፍተኛ ለውጥ ያመለክታል፤ በጽንፈ ዓለም ውስጥ የሚታየው እድገት ለዚህ እንደ አብነት ይጠቀሳል። በተጨማሪም ቃሉ ሕይወት ያላቸው ነገሮች ማለትም ዕፅዋትና እንስሳት ከአካባቢያቸው ጋር ለመላመድ የሚያደርጉትን ዓይነት ለውጥ ያመለክታል። ይሁን እንጂ ቃሉ አብዛኛውን ጊዜ ሕይወት የተገኘው ሕይወት ከሌላቸው ኬሚካሎች እንደሆነ የሚገልጸውን ንድፈ ሐሳብ ለማመልከትም ይሠራበታል፤ በዚህ ንድፈ ሐሳብ መሠረት እነዚህ ኬሚካሎች የመባዛት ችሎታ ያላቸው ሴሎች አስገኙና ሴሎቹ ይበልጥ ውስብስብ ወደሆኑ ፍጥረታት እየተሻሻሉ ሄዱ። በመጨረሻም ከሁሉ የበለጠ የማሰብ ችሎታ ያለው ሰው ተገኘ። በዚህ መጽሔት ውስጥ “ዝግመተ ለውጥ” የሚለው ሐረግ የተሠራበት በዚህ በሦስተኛ ትርጉሙ ነው።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

የሕዋ ፎቶ:- J. Hester and P. Scowen (AZ State Univ.), NASA