በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአንድ ባዮኬሚስት ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ

ከአንድ ባዮኬሚስት ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ

ከአንድ ባዮኬሚስት ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ

በአሁኑ ጊዜ በፔንስልቬንያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ሊሃይ ዩኒቨርሲቲ የባዮኬሚስትሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ማይክል ቤሄ በ1996 ዳርዊንስ ብላክ ቦክስ—ዘ ባዮኬሚካል ቻሌንጅ ቱ ኢቮሉሽን (የዳርዊን እንቆቅልሽ—ባዮኬሚካላዊ ግኝቶች በዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ላይ ያስከተሉት ፈተና) የተባለ መጽሐፍ አሳትመው ነበር። የነሐሴ 1998 ንቁ! መጽሔት እትም “ምድር ላይ የተገኘነው ተፈጥረን ነው ወይስ በአጋጣሚ?” በሚል ዋና ርዕስ ሥር ተከታታይ ጽሑፎችን ይዞ ወጥቶ የነበረ ሲሆን እዚያ ላይ የማይክል ቤሄ መጽሐፍ ተጠቅሷል። ዳርዊንስ ብላክ ቦክስ የተባለው መጽሐፍ ከወጣ ወዲህ ባሳለፍናቸው አሥር ዓመታት ውስጥ የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብን የሚደግፉ ሳይንቲስቶች ቤሄ ያነሱትን የመከራከሪያ ነጥብ ለማስተባበል ተረባርበዋል። ተቺዎች ቤሄ ሃይማኖታዊ እምነታቸው (የሮማ ካቶሊክ አማኝ ናቸው) ሳይንሳዊ የማመዛዘን ችሎታቸውን አጨልሞባቸዋል ሲሉ ከስሰዋቸዋል። ሌሎች ደግሞ የሚያቀርቡት የመከራከሪያ ነጥብ ሳይንሳዊ አይደለም ብለዋል። ንቁ! እኚህ ሰው የሰነዘሩት ሐሳብ ይህን ያህል አወዛጋቢ የሆነበትን ምክንያት ለመረዳት ራሳቸውን አነጋግሯቸዋል።

ንቁ!:- ሕይወት ያላቸው ነገሮች ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ የሚጠይቅ ንድፍ የተንጸባረቀባቸው ናቸው ብለው እንዲያምኑ ያደረጎት ምንድን ነው?

ፕሮፌሰር ቤሄ:- የተለያዩ ክፍሎች ያሉትና ውስብስብ ሥራ የሚያከናውን መሣሪያ በምንመለከትበት ጊዜ ሠሪ ወይም ንድፍ አውጪ እንዳለው እንረዳለን። ለአብነት ያህል፣ በየቀኑ ጥቅም ላይ የሚውሉ እንደ ሣር ማጨጃ ማሽንና መኪና ያሉትን ወይም የእነዚህን ያህል ውስብስብነት የሌላቸውን መሣሪያዎች እንመልከት። ብዙውን ጊዜ እንደ ምሳሌ የምጠቅሰው የአይጥ ወጥመድን ነው። የተለያዩ ክፍሎች አንድ ላይ ተቀናጅተው አይጥ የመያዝ ተግባራቸውን ሲፈጽሙ ስለምታይ ይህን ነገር የሠራ አንድ ሰው መኖር አለበት ብለህ ታስባለህ።

በአሁኑ ጊዜ ሳይንስ ሴልን የመሳሰሉትን የሕይወት መሠረታዊ ክፍሎች ለይቶ ለማወቅ በሚያስችለው የእድገት ደረጃ ላይ ደርሷል። በጣም የሚያስደንቀው ደግሞ እነዚህ መሠረታዊ ክፍሎች እንደ አንድ ውስብስብ ማሽን የተራቀቀ አሠራር እንዳላቸው ሳይንቲስቶች ደርሰውበታል። ለምሳሌ ያህል፣ በሴሎች ውስጥ አስፈላጊ ነገሮችን ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላው ጫፍ የሚያጓጉዙ “የጭነት ተሽከርካሪዎች” አሉ። እንዲሁም እነዚህ “ተሽከርካሪዎች” የሚታጠፉበትን ትክክለኛ አቅጣጫ የሚያመለክቱ ሞለኪውል የሚባሉ ጥቃቅን “ጠቋሚ ምልክቶች” አሉ። አንዳንድ ሴሎች በፈሳሽ ውስጥ እንዲጓዙ የሚያስችላቸው ውጪያዊ “መቅዘፊያ ሞተር” አላቸው። በማንኛውም ጊዜ ቢሆን ሰዎች እንዲህ ያሉ የተወሳሰቡ መሣሪያዎችን ሲመለከቱ እነዚህን ነገሮች የሠራ አንድ ንድፍ አውጪ መኖር አለበት ብለው መደምደማቸው አይቀርም። የዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ምንም ይበል ምን፣ ውስብስብ ለመሆናቸው ሌላ ምክንያት ልንሰጥ አንችልም። እንዲህ ያለ ውስብስብ ነገር ሲያጋጥመን ሠሪ አለው ብለን መደምደማችን የተለመደ በመሆኑ ይህ ውስብስብ የሞለኪውሎች ቅንብርም የረቀቀ ችሎታ ያለው አንድ ንድፍ አውጪ አለው ብለን ማሰባችን ተገቢ ነው።

ንቁ!:- አብዛኞቹ ባልደረቦችዎ በእርስዎ አመለካከት የማይስማሙት ለምን ይመስልዎታል?

ፕሮፌሰር ቤሄ:- ብዙ ሳይንቲስቶች በእኔ አመለካከት የማይስማሙት፣ ሕይወት ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ የሚጠይቅ ንድፍ ተንጸባርቆበታል የሚለው ሐሳብ ከሳይንሳዊ አስተሳሰብ ጋር እንደሚጋጭ ስለሚሰማቸውና ከተፈጥሮ ኃይሎች በላይ ወደሆነ አካል ሊያመለክት ይችላል ብለው ስለሚያስቡ ነው። ብዙዎችን እንዲህ ያለው መደምደሚያ ያስፈራቸዋል። ይሁን እንጂ ሳይንስ ማስረጃዎቹ ወደሚጠቁሙት አቅጣጫ መሄድ እንዳለበት የታወቀ ነው። በእኔ አመለካከት ተቀባይነት የሌለው ፍልስፍና ይሆናል በሚል ስሜት ጠንካራ ማስረጃ ያለውን መደምደሚያ ከመቀበል ወደኋላ ማለት ፈሪነት ነው።

ንቁ!:- ተፈጥሮ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ የሚጠይቅ ንድፍ ተንጸባርቆበታል የሚለው አስተሳሰብ ድንቁርናን ያስፋፋል ለሚሉ ተቺዎች ምን መልስ ይሰጣሉ?

ፕሮፌሰር ቤሄ:- በተፈጥሮ ውስጥ የረቀቀ ንድፍ ተንጸባርቋል የሚለው መደምደሚያ ከድንቁርና የመነጨ አይደለም። ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ካለማወቅ የመነጨ ሳይሆን በማወቃችን የደረስንበት መደምደሚያ ነው። ዳርዊን ከ150 ዓመት በፊት ዚ ኦሪጅን ኦቭ ስፒሽስ የተባለውን መጽሐፉን ባወጣ ጊዜ ሕይወት ይህን ያህል የተወሳሰበ መስሎ አይታይም ነበር። ሳይንቲስቶች ሴል በጣም ተራ ነገር በመሆኑ ባሕር ውስጥ ካለ ጭቃ በድንገት ሊገኝ እንደሚችል ይሰማቸው ነበር። ከዚያ ወዲህ ግን ሳይንስ፣ ሴል በጣም ውስብስብ እንዲያውም በዚህ በ21ኛው መቶ ዘመን ከተሠሩ መሣሪያዎች ሁሉ ይበልጥ የረቀቀ መሆኑን ደርሶበታል። ሴል ውስብስብ መሆኑ በዓላማ እንደተነደፈ ይጠቁማል።

ንቁ!:- ዝግመተ ለውጥ በተፈጥሯዊ ምርጦሽ (NATURAL SELECTION) አማካኝነት እንዲህ ያለውን ውስብስብ የሞለኪውሎች ቅንብር ሊያስገኝ እንደሚችል ሳይንስ ማስረጃ ማቅረብ ችሏል?

ፕሮፌሰር ቤሄ:- ሳይንሳዊ ጽሑፎችን ብትመረምር ሥራዬ ብሎ እንዲህ ያለ ሙከራ ያደረገ ሰው እንደሌለ ትገነዘባለህ። ይህንን ስል እንደ ሴል ያሉ ውስብስብ ነገሮች በዳርዊን ንድፈ ሐሳብ መሠረት እንዴት ሊገኙ እንደሚችሉ የሚያሳይ መጠነኛ ሙከራም ሆነ ዘርዘር ያለ ሳይንሳዊ ጥናት አልተደረገም ማለቴ ነው። የእኔ መጽሐፍ ከወጣ በኋላ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ እንደ ብሔራዊ የሳይንስ አካዳሚ እና የአሜሪካ ሳይንሳዊ እድገት ማኅበር ያሉት በርካታ ሳይንሳዊ ድርጅቶች፣ አባሎቻቸው የሕይወት ውስብስብነት ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ የሚጠይቅ ንድፍ ተንጸባርቆበታል የሚለውን ሐሳብ ለማስተባበል የተቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ አስቸኳይ ጥሪ ቢያስተላልፉም እንኳ የተገኘ ውጤት የለም።

ንቁ!:- ምንም ጥቅም የሌላቸው የሚመስሉ የዕፅዋት ወይም የእንስሳት አካል ክፍሎች መኖራቸው የንድፍ ጉድለት መኖሩን ይጠቁማል ለሚሉ ሰዎች ምን መልስ ይሰጣሉ?

ፕሮፌሰር ቤሄ:- የአንድ ፍጡር የአካል ክፍል ምን ተግባር እንደሚያከናውን ስላላወቅን ብቻ ምንም ጥቅም የለውም ማለት አንችልም። ለምሳሌ ያህል፣ ምንም ጥቅም እንደሌላቸው ተደርገው የሚታዩ አንዳንድ ትናንሽ ብልቶች የሰውና የሌሎች ፍጥረታት አካላት የአሠራር ጉድለት ያለባቸው መሆኑን ያረጋግጣሉ ተብሎ ይታሰብ ነበር። ለአብነት ያህል፣ በአንድ ወቅት ትርፍ አንጀትና እንጥል ምንም ጥቅም እንደሌላቸው ተደርጎ ይታሰብ ስለነበረ ተቆርጠው ይወጡ ነበር። አሁን ግን እነዚህ ብልቶች በሽታን በመከላከል ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱ ስለተደረሰበት ጥቅም እንደሌላቸው ተደርገው መታየታቸው ቀርቷል።

ሊዘነጋ የማይገባው ሌላው ነገር በባዮሎጂ በአጋጣሚ የሚከሰቱ አንዳንድ ነገሮች መኖራቸው ነው። መኪናዬ ስርጉድ ያለ ነገር ስላለው ወይም ጎማው ስለሚተነፍስ ብቻ መኪናው ወይም ጎማው ታስቦበት አልተሠራም ለማለት አይቻልም። በተመሳሳይም በባዮሎጂ በአጋጣሚ የሚከሰቱ አንዳንድ ነገሮች መኖራቸው ሕይወትን የመሰለው ውስብስብ ነገር በአጋጣሚ ተገኘ ለማለት አያስደፍርም። እንዲህ ያለው ክርክር ፈጽሞ ምክንያታዊ አይደለም።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በእኔ አመለካከት ተቀባይነት የሌለው ፍልስፍና ይሆናል በሚል ስሜት ጠንካራ ማስረጃ ያለውን መደምደሚያ ከመቀበል ወደኋላ ማለት ፈሪነት ነው