በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

“ጥልቁ ባሕር፣ በፕላኔታችን ላይ በትልቅነቱ ከፍተኛውን ደረጃ የሚይዝ ሕይወት ያላቸው ነገሮች መኖሪያ ሲሆን ለመኖር በጣም አስቸጋሪ ከሚባሉት ውስጥ ይመደባል። ሆኖም በደረስንበት ሁሉ፣ አንዳንድ ጊዜም ብዛታቸው በጣም አስገራሚ የሆነ ሕይወት ያላቸው ፍጥረታት እናገኛለን።”—ኒው ሳይንቲስት፣ ብሪታንያ

በሃሪስበርግ፣ ፔንሲልቬኒያ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው የፌደራል ፍርድ ቤት ዳኛ በቅርቡ “በሕዝብ ትምህርት ቤቶች የሳይንስ ክፍለ ጊዜ ላይ በዝግመተ ለውጥ ምትክ [የማሰብ ችሎታ ያለው ንድፍ አውጪ እንዳለ] ማስተማር ሕገ መንግሥቱን የሚፃረር” እንደሆነ በይነዋል።—ኒው ዮርክ ታይምስ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

በ2005 በተካሄደ አንድ የሕዝብ አስተያየት ጥናት መሠረት “51 በመቶ የሚሆኑት አሜሪካውያን የዝግመተ ለውጥን ንድፈ ሐሳብ አይቀበሉትም።”—ኒው ዮርክ ታይምስ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

በብሪስቤን፣ አውስትራሊያ የአራዊት መጠበቂያ ውስጥ ሃሪየት በመባል የምትጠራና የ175 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ የሆነች ግዙፍ የጋላፓጎስ ኤሊ ትገኛለች። አንድ መቶ ሃምሳ ኪሎ ግራም የምትመዝነው ይህቺ ኤሊ “በሕይወት ካሉ እንስሳት መካከል በዕድሜ ባለጸጋነቷ በዓለም የታወቀች” ናት።—የአውስትራሊያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን

የስዊዘርላንድ ተመራማሪዎች አንዳንድ የበቆሎ ዝርያዎች፣ ሩትዎርም የተባለው የጥንዚዛ ዝርያ እጭ እንዳያጠቃቸው ራሳቸውን ለመከላከል ምን እንደሚያደርጉ እንደደረሱበት ገልጸዋል። እነዚህ የበቆሎ ዝርያዎች የጥንዚዛውን እጭ የሚገድሉ ትናንሽ ትሎችን የሚስብ መዓዛ ወደ መሬት ይለቅቃሉ።—ዲ ቬልት፣ ጀርመን

ግዙፉን ስኩዊድ ፎቶግራፍ ማንሳት ተቻለ

የሳይንስ ሊቃውንት ከጃፓን በስተ ደቡብ በሚገኙት የቦኒን ደሴቶች አቅራቢያ፣ በሕይወት ያለ ግዙፍ ስኩዊድ ለመጀመሪያ ጊዜ ፎቶግራፍ አንስተዋል። ይህን የባሕር እንስሳ ለመሳብ በመንጠቆ ላይ አንድ ትንሽ ስኩዊድ እና የትንንሽ ዓሣዎች ሥጋ አደረጉና ከበላዩ ካሜራ አንጠለጠሉ። በ900 ሜትር ጥልቀት ላይ የታየው ግዙፉ ስኩዊድ ርዝመቱ 8 ሜትር እንደሚሆን ተገምቷል።

“ዳይነሶር ሣር ይበላ” ነበር

የሳይንስ ሊቃውንት “ዳይነሶር ሣር ይበላ እንደነበር” ማወቃቸው “በጣም አስደንቋቸዋል” በማለት አሶሺየትድ ፕሬስ ገልጿል። እዚህ ግኝት ላይ የተደረሰው በሕንድ የተገኘው የዳይነሶር ቅሪተ አካል ፍግ ሲጠና ነበር። ታዲያ የሳይንስ ሊቃውንቱ የተደነቁት ለምን ነበር? “ሣር መብቀል የጀመረው ዳይነሶሮች ከጠፉ ከረጅም ዘመን በኋላ ነው” ተብሎ ይታመን ስለነበረ መሆኑን ዘገባው ገልጿል። በተጨማሪም እነዚያ ፍጥረታት “የሚኮሰኩሱ ሣር ቅጠሎችን ለማድቀቅ የሚያስፈልገው ዓይነት ጥርስ አልነበራቸውም” ተብሎም ይታመን ነበር። የፔሊዮቦታኒ (ወደ ቅሪተ አካልነት የተለወጡ ተክሎች ጥናት) ባለሞያና ግኝቱን የደረሰበት ቡድን መሪ የሆኑት ካሮሊን ስትሮምበርግ የተባሉ ሴት “አብዛኞቹ ሰዎች [ዳይነሶሮች] ሣር ይበላሉ ብለው አስበው አያውቁም” ብለዋል።

ንቦች የሚበሩት እንዴት ነው?

በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ሲታይ ንቦች መብረር እንደማይችሉ መሐንዲሶች ማረጋገጣቸውን እንደ ቀልድ ሲነገር ይሰማል። ከክንፋቸው መጠን አንጻር ሲታዩ “ከባድ” የሆኑትና ክንፋቸውን በፍጥነት የሚያርገበግቡት እነዚህ ነፍሳት ለመብረር የሚያስችል አቅም የሚኖራቸው አይመስልም። መሐንዲሶቹ ነፍሳቱ ለመብረር ያስቻላቸውን ምስጢር ለማወቅ “ንቦቹ እየበረሩ እያለ በአንድ ሴኮንድ ውስጥ 6,000 ምስል” እንዳነሱ ኒው ሳይንቲስት ይናገራል። ከዚህም በመነሳት ንቦቹ ለመብረር የሚጠቀሙበት ዘዴ “ያልተለመደ” እንደሆነ ተገልጿል። “ክንፋቸው ወደኋላ 90 ዲግሪ ቅስት ከሄደ በኋላ በሚመለስበት ጊዜ ይገለበጣል፤ በዚህ ዓይነት በአንድ ሴኮንድ ውስጥ 230 ጊዜ ይርገበገባል። . . . ክንፋቸው የሚርገበገብበት ሁኔታ ምላጩም ጭምር ከሚሾር ውልብልቢት (ፕሮፔለር) ጋር ይመሳሰላል” በማለት የምርምር ቡድኑ አባል የሆነ ሰው ያስረዳል። የተገኘው የምርምር ውጤት መሐንዲሶች ለውልብልቢቶች የሚሆን አዲስ ንድፍ እንዲያወጡና በቀላሉ ወደተለያየ አቅጣጫ መታጠፍ የሚችል አውሮፕላን እንዲሠሩ ይረዳቸው ይሆናል።

የሚዘምሩ አይጦች

“አይጦች መዘመር ይችላሉ፤ የወደፊቱ ተጓዳኛቸው እንዲሆን ያሰቡትን አይጥ ለማስደሰት የሚዘምሩት መዝሙር ከወፎች ዝማሬ ባልተናነሰ መልኩ የረቀቀ ነው” በማለት ኒው ሳይንቲስት ዘግቧል። የአይጦች ዝማሬ የሰው ጆሮ ሊሰማው ከሚችለው በላይ በሚርገበገብ የድምፅ ሞገድ የሚፈጠር ሲሆን እስከዛሬ ሰዎች ልብ ሳይሉት የቀሩትም በዚሁ ምክንያት ሊሆን ይችላል። በሴንት ሉዊስ፣ ሚዙሪ ዩናይትድ ስቴትስ ጥናት ያካሄዱ ተመራማሪዎች የወንዱ አይጥ ድምፅ አወጣጥ “የሙዚቃ ቃና ባላቸው ተከታታይ ሐረጎችና በየመሃሉ በሚደጋገም አዝማች የተቀናበረ በመሆኑ ‘መዝሙር’ ሊባል ይችላል” የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። ይህም አይጦችን ለየት ባለ ቡድን ውስጥ እንዲመደቡ አድርጓቸዋል። ከሰው ዘር ውጪ እንደሚዘምሩ የሚታወቁት ሌሎች አጥቢ እንስሳት ዓሣ ነባሪዎች፣ ዶልፊኖችና አንዳንድ የሌሊት ወፍ ዝርያዎች ናቸው።