በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምታምንበት ነገር ለውጥ ያመጣል?

የምታምንበት ነገር ለውጥ ያመጣል?

የምታምንበት ነገር ለውጥ ያመጣል?

ሕይወት ዓላማ ያለው ይመስልሃል? የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ እውነት ከሆነ ሳይንቲፊክ አሜሪካን በተባለው መጽሔት ላይ የወጣው “በዚህ ዘመን ስለ ዝግመተ ለውጥ ያለን ግንዛቤ . . . ይህ ነው የሚባል የሕይወት ዓላማ እንደሌለ ይጠቁማል” የሚለው ሐሳብ ትክክል ነው ማለት ነው።

እነዚህ ቃላት ምን አንድምታ እንደሚኖራቸው እንመልከት። ይህ ነው የሚባል የሕይወት ዓላማ ከሌለ በሕይወትህ ውስጥ አንዳንድ በጎ ሥራዎችን ለመሥራት ከመጣጣር ምናልባትም በዘር የሚተላለፉ ባሕርያትን ለቀጣዩ ትውልድ ከማስተላለፍ የዘለለ ዓላማ የለህም ማለት ነው። አንድ ጊዜ ከሞትክ በኋላ ለዘላለም ጠፍተህ ትቀራለህ። የማሰብ፣ ምክንያቶችን የማገናዘብና በሕይወት ትርጉም ላይ የማሰላሰል ችሎታ ያለው አንጎልህ ተፈጥሮ በአጋጣሚ ያስገኘው ነገር ይሆናል።

ይህ ብቻ ሳይሆን በዝግመተ ለውጥ የሚያምኑ ብዙ ሰዎች ወይ አምላክ የለም፣ ቢኖርም በሰው ልጆች ጉዳይ እጁን ጣልቃ አያስገባም ይላሉ። እንደ ሁለቱም ሐሳቦች ከሆነ የወደፊት ዕጣችን በፖለቲከኞች፣ በምሑራንና በሃይማኖት መሪዎች እጅ የወደቀ ይሆናል። የእነዚህ ቡድኖች ያለፈ ታሪክ ሲታይ ሰብዓዊውን ማኅበረሰብ እንደ ነቀዝ እየበላው ያለው ምስቅልቅል፣ ግጭትና ሙስና መቀጠሉ አይቀርም። በእርግጥም የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ እውነት ቢሆን ኖሮ “ነገ ስለምንሞት፣ እንብላ፣ እንጠጣ” የሚለውን አደገኛ መርህ የምንከተልበት በቂ ምክንያት ይኖረን ነበር።—1 ቆሮንቶስ 15:32

ሆኖም ስለ አንድ ነገር እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። የይሖዋ ምሥክሮች ከላይ በተገለጹት አባባሎች አይስማሙም። ከዚህም ሌላ ለእነዚህ አባባሎች ምንጭ የሆነውን የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ አይቀበሉም። በአንጻሩ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንደሆነ ያምናሉ። (ዮሐንስ 17:17) ስለሆነም “የሕይወት ምንጭ ከአንተ [ከአምላክ] ዘንድ ነው” በማለት እንዴት እንደተፈጠርን የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ያምናሉ። (መዝሙር 36:9) እነዚህ ቃላት ከፍተኛ አንድምታ አላቸው።

ሕይወት በእርግጥ ትርጉም አለው። ፈጣሪያችን ከፈቃዱ ጋር ተስማምተው ለመኖር ለሚመርጡ ሁሉ ፍቅራዊ ዓላማ አለው። (መክብብ 12:13) ይህ ዓላማ ከምስቅልቅል፣ ከግጭትና ከሙስና ሌላው ቀርቶ ከሞት እንኳ ሙሉ በሙሉ በጸዳ ዓለም የመኖር ተስፋን ይጨምራል። (ኢሳይያስ 2:4፤ 25:6-8) በመላው ዓለም የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አምላክ መማርና የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ከምንም በላይ ሕይወት ትርጉም እንዲኖረው እንደሚያደርግ መመሥከር ይችላሉ።—ዮሐንስ 17:3

የምታምንበት ነገር የአሁኑን ደስታህን ብቻ ሳይሆን የወደፊት ሕይወትህን ጭምር ስለሚነካ በእርግጥም የሚያመጣው ለውጥ አለ። ምርጫው ለአንተ የተተወ ነው። የምታምነው ተፈጥሮ የረቀቀ ችሎታ ባለው አንድ ንድፍ አውጪ እንደተሠራ የሚያረጋግጡትን እየጨመሩ የመጡ ማስረጃዎች ማስተባበል ባልቻለው ንድፈ ሐሳብ ነው? ወይስ ምድርና በምድር ላይ የሚኖሩት ሕያዋን ፍጥረታት በሙሉ ‘ሁሉን የፈጠረው’ የይሖዋ አምላክ አስደናቂ የእጅ ሥራ መሆናቸውን በሚናገረው በመጽሐፍ ቅዱስ?—ራእይ 4:11