በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ተጨባጭ ሐቅ ነው?

የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ተጨባጭ ሐቅ ነው?

የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ተጨባጭ ሐቅ ነው?

እውቅ የዝግመተ ለውጥ ሳይንቲስት የሆኑት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ዶውከንዝ “ዝግመተ ለውጥ የፀሐይን ትኩሳት ያህል የተረጋገጠ ሐቅ ነው” ብለዋል። ፀሐይ የምታቃጥል መሆኗን በሙከራም ሆነ ቀጥታ በመመልከት ማረጋገጥ እንደሚቻል የታወቀ ነው። ይሁንና በሙከራ አማካኝነትም ሆነ ቀጥታ በመመልከት የዝግመተ ለውጥ ትምህርት ተጨባጭ ሐቅ መሆኑን በማያዳግም ሁኔታ ማረጋገጥ ይቻላል?

ይህን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት አንድ ነገር ግልጽ ሊሆንልን ይገባል። በርካታ ሳይንቲስቶች የእንስሳትም ሆኑ የዕፅዋት ዝርያዎች በጊዜ ሂደት መጠነኛ ለውጥ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ደርሰውበታል። ቻርልስ ዳርዊን ይህን ሂደት “በተከታታይ ለውጥ ያደረገ ዝርያ” በማለት ጠርቶታል። ዕፅዋትንና እንስሳትን የሚያዳቅሉ ሰዎች እንዲህ ያለውን ለውጥ ማየታቸው የተለመደ ከመሆኑም በላይ በሙከራ ሲያረጋግጡትና ዘዴውን ሲጠቀሙበት ቆይተዋል። * በመሆኑም እንዲህ ያለው ለውጥ ተጨባጭነት ያለው ሐቅ ተደርጎ ሊታይ ይችላል። ይሁን እንጂ፣ ሳይንቲስቶች እንዲህ ያለውን ትንንሽ ለውጥ “ማይክሮኢቮሉሽን” በማለት ይጠሩታል። ስያሜውም ራሱ እንደሚያመለክተው በርካታ ሳይንቲስቶች እነዚህ ትንንሽ ለውጦች ማክሮኢቮሉሽን ወደሚባል ማንም በዓይኑ ወዳላየው በጣም ትልቅ ለውጥ እንደሚሸጋገሩ ማስረጃ ይሆናሉ ብለው ያምናሉ።

ይሁንና ዳርዊን ሊታዩ በሚችሉ በእነዚህ ለውጦች ብቻ አልተወሰነም። ዚ ኦሪጅን ኦቭ ስፒሽስ በተባለው ዝነኛ መጽሐፉ ላይ “እንደ እኔ አመለካከት ሕይወት ያላቸው ነገሮች ሁሉ የተለያዩ ፍጡራን ሳይሆኑ በቁጥር ጥቂት የሆኑ ሕያዋን ነገሮች ዝርያዎች ናቸው” ሲል ጽፏል። በተጨማሪም ውስብስብ እንዳልሆኑ ተደርገው የሚታሰቡት ‘እነዚህ ጥቂት ሕያዋን ነገሮች’ በጣም ረዥም በሆነ የጊዜ ሂደት “በጣም ጥቃቅን በሆኑ ለውጦች” አማካኝነት ቀስ በቀስ እየተለወጡ በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ የሚገኙትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ የዕፅዋትና የእንስሳት ዝርያዎች እንዳስገኙ ተናግሯል። የዝግመተ ለውጥ አስተማሪዎች እነዚህ ጥቃቅን ለውጦች ሲጠራቀሙ ትልልቅ ለውጦችን በማስገኘታቸው ዓሣዎች በየብስና በባሕር ወደሚኖሩ እንስሳት፣ ዝንጀሮዎች ደግሞ ወደ ሰው እንደተለወጡ ይናገራሉ። እንዲህ ያለው ትልቅ ለውጥ ማክሮኢቮሉሽን ተብሎ ይጠራል። ብዙዎች ይህ ሁለተኛ አባባል ምክንያታዊ እንደሆነ ይሰማቸዋል። በዚህም ምክንያት ‘በአንድ ዝርያ (species) ውስጥ ጥቃቅን ለውጦች የሚከሰቱ ከሆነ ዝግመተ ለውጥ በረዥም የጊዜ ሂደት ውስጥ ትላልቅ ለውጦችን ሊያስገኝ የማይችልበት ምን ምክንያት ይኖራል?’ በማለት ይጠይቃሉ። *

የማክሮኢቮሉሽን ትምህርት በሦስት ዋና ዋና ግምታዊ ሐሳቦች ላይ የተመሠረተ ነው:-

1. የሚውቴሽን ሂደት አዳዲስ ዝርያዎችን ለመፍጠር የሚያስፈልገውን ጥሬ ዕቃ ያስገኛል። *

2. አዳዲስ ዝርያዎች የሚገኙት በተፈጥሯዊ ምርጦሽ (natural selection) ምክንያት ነው።

3. ወደ አለትነት በተለወጡ ቅሪተ አካላት ውስጥ ዕፅዋትና እንስሳት ያደረጉትን ማክሮኢቮሉሽናዊ ለውጥ የሚያሳይ መረጃ ይገኛል።

ማክሮኢቮሉሽን ተጨባጭ ሐቅ ነው ለማለት የሚያስችል በቂ ማስረጃ አለ?

የሚውቴሽን ሂደት አዳዲስ ዝርያዎችን ሊያስገኝ ይችላል?

የአንድ ተክል ወይም እንስሳ ዝርዝር ባሕርይ በአብዛኛው የሚወሰነው በእያንዳንዱ ሴል ኒውክሊየስ ውስጥ የሚገኘው ጂን በሚሰጠው መመሪያ ነው። * በእነዚህ የጂን ባሕርያት ላይ በየጊዜው የሚደርሰው ሚውቴሽን ወይም ድንገተኛ ለውጥ በእንስሳቱ ወይም በዕፅዋቱ የወደፊት ዝርያዎች ላይ ለውጥ እንደሚያስከትል ተመራማሪዎች ደርሰውበታል። የሚውቴሽን ጄኔቲክስ ጥናት መሥራችና የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ኸርማን ሙለር በ1946 “ከስንት አንዴ የሚከሰቱት እነዚህ ጥቃቅን ለውጦች ተጠራቅመው እንስሳትንና ዕፅዋትን በሰው ሠራሽ ዘዴዎች ለማሻሻል ከማስቻላቸውም በላይ በተፈጥሯዊ ምርጦሽ አማካኝነት ተፈጥሯዊው ዝግመተ ለውጥ እንዲካሄድ መንገድ ጠርገዋል” በማለት ተናግረዋል።

በእርግጥም የማክሮኢቮሉሽን ትምህርት ሚውቴሽን አዳዲስ ዝርያዎችን (species) ብቻ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ አዲስ የሆኑ የዕፅዋትና የእንስሳት ቤተሰቦችን (families) ሊያስገኝ ይችላል በሚል እምነት ላይ የተመሠረተ ነው። ታዲያ ይህን የድፍረት አነጋገር በሙከራ ማረጋገጥ የሚቻልበት መንገድ ይኖራል? ለ100 ዓመት ያህል በጄኔቲክስ የምርምር መስክ የተደረገ ጥናት ያስገኘውን ውጤት እንመልከት።

በ1930ዎቹ ዓመታት መጨረሻ ላይ ሳይንቲስቶች ተፈጥሯዊ ምርጦሽ በሚውቴሽን አማካኝነት አዳዲስ የዕፅዋት ዝርያዎችን ማስገኘት ከቻለ ሰዎች በምርጫቸው የሚያካሂዱት ሚውቴሽን ወይም ለውጥ ይበልጥ ውጤታማ መሆን አለበት የሚል ስሜት አድሮባቸው ነው። ጀርመን ውስጥ የማክስ ፕላንክ ዕፅዋትን የማዳቀል ምርምር ተቋም ባልደረባ የሆኑት ቮልፍ ኢከሃርት ሎኒግ ከንቁ! መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “አብዛኞቹ ባዮሎጂስቶች፣ በተለይ ደግሞ የጄኔቲክስ ተመራማሪዎችና አዳቃዮች በደስታ ፈንጥዘው” ነበር ብለዋል። እንዲህ ያስፈነጠዛቸው ምን ነበር? ለ28 ዓመታት በዕፅዋት ሚውቴሽን የጄኔቲክስ መስክ የተሰማሩት ሎኒግ “እነዚህ ተመራማሪዎች ከዚያ በፊት ይሠራበት የነበረውን ዕፅዋትንና እንስሳትን የማዳቀል ዘዴ ሙሉ በሙሉ መለወጥ የሚችሉበት ጊዜ ላይ የደረሱ መስሏቸው ነበር። ሚውቴሽኖችን በማካሄድና ጠቃሚ የሆኑትን በመምረጥ አዳዲስና የተሻሉ የዕፅዋትና የእንስሳት ዝርያዎችን ማግኘት የሚችሉ መስሏቸው ነበር” ብለዋል። *

በዩናይትድ ስቴትስ፣ በእስያና በአውሮፓ የሚገኙ ሳይንቲስቶች የዝግመተ ለውጥን ሂደት እንደሚያፋጥኑ የታመነባቸውን ዘዴዎች በመጠቀም ከፍተኛ ገንዘብ የፈሰሰባቸው የምርምር ፕሮግራም ማካሄድ ጀመሩ። ከአርባ ለሚበልጡ ዓመታት ጥልቅ ምርምር ከተደረገ በኋላ ምን ውጤት ተገኘ? ፒተር ፎን ዜንግቡሽ የተባሉት ተመራማሪ “ምርምሩን ለማካሄድ በጣም ብዙ ገንዘብ ቢፈስም በጨረር አማካኝነት የጂኖችን ባሕርይ ለውጦ የተሻሉ ዝርያዎችን ለማግኘት የተደረገው ጥረት በአብዛኛው ስኬታማ ሳይሆን ቀርቷል” ብለዋል። ሎኒግም እንዲሁ “በ1980ዎቹ ዓመታት፣ የዓለም ሳይንቲስቶች የነበራቸው ተስፋና ደስታ መጨረሻው ውድቀት ሆኗል። በምዕራባውያን አገሮች በሚውቴሽን አማካኝነት ማዳቀል ራሱን የቻለ የምርምር ዘርፍ መሆኑ ቀረ። በሚውቴሽን የተገኙ ዝርያዎች በሙሉ ለማለት ይቻላል ‘የማይፈለጉ ባሕርያት’ በማሳየት ወዲያው ሞተዋል ወይም ከተፈጥሮ ዝርያዎች የበለጡ ደካሞች ሆነው ተገኝተዋል” በማለት ተናግረዋል። *

ያም ሆኖ ግን ስለ ሚውቴሽን በጥቅሉ ለማጥናት በፈጀው 100 ዓመትና በሚውቴሽን አማካኝነት ለማዳቀል የሚያስችል ምርምር ለማድረግ በወሰደው 70 ዓመት ጊዜ ውስጥ የተሰበሰበው መረጃ ሳይንቲስቶች ሚውቴሽን አዳዲስ ዝርያዎችን ለማስገኘት ስላለው ችሎታ አንድ ዓይነት ድምዳሜ ላይ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል። ሎኒግ መረጃዎቹን ከመረመሩ በኋላ እንዲህ የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል:- “ሚውቴሽን ነባሩን [የተክል ወይም የእንስሳ] ዝርያ ሙሉ በሙሉ አዲስ ወደሆነ ዝርያ ሊለውጥ አይችልም። ይህ መደምደሚያ በ20ኛው መቶ ዘመን ከተደረጉ የሚውቴሽን ምርምሮች ከተገኙት ተሞክሮዎችና ውጤቶች እንዲሁም ከሒሳብ ሕግ ጋር ይስማማል። በመሆኑም ይህ ሕግ (ሎው ኦቭ ሪከረንት ቬሪዬሽን) በግልጽ የታወቀ የጂን ባሕርይ ያላቸው ዝርያዎች በድንገተኛ ሚውቴሽን ምክንያት ሊፈርስ ወይም ሊጣስ የማይችል ድንበር እንዳላቸው ይጠቁማል።”

ከላይ የሠፈሩት ሐቆች ምን አንድምታ እንደሚኖራቸው እንመልከት። ከፍተኛ ሥልጠና የተሰጣቸው ሳይንቲስቶች በሰው ሠራሽ ዘዴዎች ተጠቅመውና የተሻሉ የሚውቴሽን ውጤቶችን መርጠው አዳዲስ ዝርያዎችን ማስገኘት ካልቻሉ ምንም ዓይነት የማሰብ ችሎታ የሌለው ሂደት የተሻለ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው? ሚውቴሽን አንድን ዝርያ ሙሉ በሙሉ አዲስ ወደሆነ ሌላ ዝርያ መለወጥ እንደማይችል በምርምር ከተረጋገጠ ማክሮኢቮሉሽን ተካሄደ ተብሎ የሚታሰበው እንዴት ነው?

ተፈጥሯዊ ምርጦሽ አዳዲስ ዝርያዎችን ያስገኛል?

ዳርዊን ናቹራል ሴሌክሽን ወይም ተፈጥሯዊ ምርጦሽ በማለት የጠራው ሂደት ከአካባቢያቸው ጋር በሚገባ የተላመዱትን ዝርያዎች ሲጠቅም ያልተላመዱት ግን ቀስ በቀስ ሞተው እንዲያልቁ ያደርጋል ብሎ ያምን ነበር። በዘመናችን ያሉ የዝግመተ ለውጥ ምሁራን፣ ዝርያዎች በሚሰራጩበትና በተወሰኑ አካባቢዎች ተለይተው መኖር በሚጀምሩበት ጊዜ ተፈጥሯዊ ምርጦሽ ለአዲሱ አካባቢ ይበልጥ ምቹ የሆነ የጂን ለውጥ ያደረጉ ዝርያዎችን ብቻ ይመርጣል ብለው ያስተምራሉ። ከዚህም በላይ እነዚህ ዝርያዎች ሙሉ በሙሉ አዲስ ወደሆኑ ዝርያዎች ቀስ በቀስ እንደሚቀየሩ ያምናሉ።

ቀደም ሲል እንደተገለጸው የሚውቴሽን ሂደት ሙሉ በሙሉ አዲስ የሆኑ የዕፅዋትና የእንስሳት ዝርያዎችን ሊያስገኝ እንደማይችል በምርምር የተገኙ መረጃዎች አረጋግጠዋል። ይሁን እንጂ ተመራማሪዎቹ ተፈጥሯዊ ምርጦሽ ጠቃሚ ሚውቴሽኖችን እየመረጠ አዳዲስ ዝርያዎችን ያስገኛል ለሚለው ሐሳባቸው ምን ማስረጃ ማቅረብ ይችላሉ? የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የሳይንስ አካዳሚ በ1999 ያወጣው አንድ ብሮሹር “አዳዲስ ዝርያዎች እንደሚገኙ አሳማኝ ማስረጃ የሚሆነን በአሁኑ ጊዜ የዳርዊን ፊንቾች በሚባሉትና ዳርዊን በጋላፓጎስ ደሴቶች ላይ ጥናት ባካሄደባቸው 13 የድንቢጥ ዝርያዎች ላይ የታየው ሁኔታ ነው” በማለት ተናግሯል።

በ1970ዎቹ ዓመታት በፒተርና በሮዝሜሪ ግራንት የሚመራ የምርምር ቡድን ፊንች በሚባሉት በእነዚህ የአእዋፍ ዝርያዎች ላይ ባደረገው ጥናት ከአንድ ዓመት የድርቅ ዘመን በኋላ ትናንሽ መንቆር ወይም አፍ ካላቸው ፊንቾች ይልቅ ትላልቅ መንቆር ያላቸው ፊንቾች ድርቁን መቋቋም እንደቻሉ ተገነዘበ። የዚህ ወፍ አሥራ ሦስቱ ዝርያዎች ተለይተው ከሚታወቁባቸው መንገዶች አንዱ የመንቆራቸው መጠንና ቅርጽ በመሆኑ ይህ ግኝት ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል ተብሎ ታስቦ ነበር። ብሮሹሩ በመቀጠል “ፒተርና ሮዝሜሪ በደሴቶቹ ላይ በየአሥር ዓመቱ ድርቅ ቢከሰት አዲስ የፊንች ዝርያ ሊገኝ የሚችለው በ200 ዓመታት ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ እንደሆነ የሚገልጽ ግምታዊ ሐሳብ ሰንዝረዋል” በማለት አስፍሯል።

ይሁን እንጂ ብሔራዊ የሳይንስ አካዳሚው ያዘጋጀው ብሮሹር ከዚህ ጋር የሚጋጩ አንዳንድ ሐቆችን ሳይጠቅስ አልፏል። ከድርቁ በኋላ ባሉት ዓመታት፣ ትናንሽ መንቆር ያላቸው ፊንቾች ትላልቅ መንቆር ካላቸው ይልቅ በዝተው ታይተዋል። በዚህም ምክንያት ፒተር ግራንት እና የድኅረ ምረቃ ተማሪ የሆነው ላይል ጊብስ ኔቸር በተባለው የሳይንስ መጽሔት ላይ በ1987 “ምርጫው ወደኋላ ሲመለስ” እንደተመለከቱ ጽፈዋል። ግራንት በ1991 “ተፈጥሯዊ ምርጦሽ የተደረገባቸው አእዋፍ ብዛት” የአየሩ ሁኔታ በተለወጠ ቁጥር “ሲለዋወጥ ኖሯል” ሲሉ ጽፈዋል። በተጨማሪም ተመራማሪዎቹ የተለያዩ የፊንች “ዝርያዎች” እርስ በርስ ተዋልደው ችግር የመቋቋም አቅም ያላቸው ዝርያዎች እንዳስገኙ አስተውለዋል። ፒተርና ሮዝሜሪ ግራንት እነዚህ ዝርያዎች እርስ በርስ መዳቀላቸውን ቢቀጥሉ በ200 ዓመት ጊዜ ውስጥ ሁለት “ዝርያዎች” አንድ ይሆናሉ ሲሉ ደምድመዋል።

የዝግመተ ለውጥ ባዮሎጂስት የሆኑት ጆርጅ ክሪስቶፈር ዊልያምስ በ1966 “መጀመሪያውኑም ቢሆን የተፈጥሯዊ ምርጦሽ ንድፈ ሐሳብ ለዝግመተ ለውጥ ማስረጃ ተደርጎ መቅረቡ አሳዛኝ ነገር ይመስለኛል። የበለጠ ማስረጃ የሚሆነው ሕያዋን ፍጥረታት ከአካባቢያቸው ጋር ለመላመድ ሲሉ ለሚያደርጉት ለውጥ ነው” በማለት ጽፈዋል። በ1999፣ የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ አስተማሪ የሆኑት ጀፍሪ ሽዋርዝ፣ ዊልያም የደረሱበት መደምደሚያ ትክክል ከሆነ ተፈጥሯዊ ምርጦሽ ዝርያዎች በአካባቢያቸው የሚከሰተውን ለውጥ እንዲቋቋሙ ይረዳቸዋል እንጂ “ምንም ዓይነት አዲስ ነገር አይፈጥርም” ሲሉ ጽፈዋል።

በእርግጥም የዳርዊን ፊንቾች ወደ “አዲስ ነገር” አልተለወጡም። አሁንም ቢሆን ያው ፊንቾች ናቸው። እርስ በርስ መዋለዳቸው ደግሞ አንዳንድ የዝግመተ ለውጥ አማኞች የዝርያዎችን (species) አመጣጥ ለማብራራት በሚሞክሩበት ዘዴ ላይ ጥርጣሬ እንዲፈጠር አድርጓል። በተጨማሪም ትልቅ ግምት የሚሰጣቸው የሳይንስ ተቋማት እንኳ ሳይቀሩ መረጃዎችን አዛብተው ከማቅረብ ወደኋላ እንደማይሉ ይጠቁማሉ።

ቅሪተ አካላት የማክሮኢቮሉሽን ማስረጃዎችን ይዘዋል?

ብሔራዊ የሳይንስ አካዳሚ ያዘጋጀው ከላይ የተጠቀሰው ብሮሹር አንባቢያን፣ ሳይንቲስቶች ያገኟቸው ቅሪተ አካላት የማክሮኢቮሉሽንን ሂደት በሚገባ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ይዘዋል የሚል ግንዛቤ እንዲያድርባቸው የሚያደርግ ሐሳብ ይዟል። እንዲህ ይላል:- “በዓሦች እና በየብስና በባሕር ሊኖሩ በሚችሉ ፍጥረታት፣ በየብስም ሆነ በባሕር ሊኖሩ በሚችሉት እንስሳትና በተሳቢ እንስሳት፣ በተሳቢ እንስሳት እና በአጥቢ እንስሳት እንዲሁም በዝንጀሮ መሰል እንስሳት የተለያዩ ትውልዶች መካከል ያሉ በርካታ የመሸጋገሪያ እንስሳት ዝርያዎች በመገኘታቸው ከአንዱ ዝርያ ወደ ሌላው ሽግግር የተደረገበትን ጊዜ በትክክል ለመለየት አስቸጋሪ ሆኗል።”

እንዲህ ያለው የድፍረት አነጋገር በእጅጉ የሚያስገርም ነው። ለምን? ናሽናል ጂኦግራፊክ መጽሔት በ2004 ቅሪተ አካላት ይዘውታል የሚባለው መረጃ “ከ1,000 የፊልም ጥብጣቦች ውስጥ 999ኙ በማቀናበሪያ ክፍል ውስጥ ከጠፉበት የዝግመተ ለውጥ ፊልም” ጋር እንደሚመሳሰል ገልጿል። ታዲያ ቀሪው አንድ “ጥብጣብ” የማክሮኢቮሉሽንን ሂደት በትክክል መዝግቦ ይዟል ለማለት ይቻላል? የቅሪተ አካላት መረጃ ምን ያሳያል? ዝግመተ ለውጥን በጥብቅ የሚደግፉት ናይልስ ኤልድሪጅ ለብዙ ዘመናት “በአብዛኞቹ ዝርያዎች ላይ ምንም ዓይነት አዝጋሚ ለውጥ አልታየም ለማለት ይቻላል” በማለት መረጃው የሚያመለክተውን ሳይሸሽጉ ተናግረዋል።

እስከዛሬ ድረስ በመላው ዓለም የሚኖሩ ሳይንቲስቶች 200 ሚሊዮን የሚያህሉ ትላልቅ ቅሪተ አካላትንና በቢሊዮን የሚቆጠሩ ጥቃቅን ቅሪተ አካላትን ቆፍረው በማውጣት መዝግበው ይዘዋል። ብዙ ተመራማሪዎች ይህ እጅግ ትልቅና ዝርዝር ጉዳዮችን ያካተተ መዝገብ ዋነኞቹ የእንስሳት ዝርያዎች በሙሉ ድንገት በአንድ ጊዜ እንደተገኙና ምንም ዓይነት ለውጥ ሳይታይባቸው እንደኖሩ፣ ብዙ ዝርያዎች ደግሞ በተገኙበት ቅጽበት በድንገት መጥፋታቸውን እንደሚያረጋግጥ ይስማማሉ። ጆናታን ዌልስ የተባሉት ባዮሎጂስት የቅሪተ አካላትን ማስረጃ ከመረመሩ በኋላ “በኪንግደም፣ በፋይለምና በክላስ ደረጃ ከአንድ የጋራ ቅድመ አያት የመጣ የለውጥ ሂደት መኖሩን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ የለም። ቅሪተ አካላትንና ሞለኪውላዊ መረጃዎችን መሠረት አድርገን ስንመለከተው ጥሩ ድጋፍ ያለው ንድፈ ሐሳብ ነው ለማለት እንኳን አይቻልም” ብለዋል።

የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ተጨባጭ ሐቅ ነው ወይስ ፈጠራ?

ብዙ እውቅ የዝግመተ ለውጥ አማኞች ማክሮኢቮሉሽን የተረጋገጠ ሐቅ ነው በማለት ሽንጣቸውን ገትረው የሚሟገቱት ለምንድን ነው? ከፍተኛ ተደማጭነት ያላቸው የዝግመተ ለውጥ አማኝ የሆኑት ሪቻርድ ለዎንተን የሪቻርድ ዶውከንዝን አንዳንድ ማብራሪያዎች ከተቹ በኋላ ብዙ ሳይንቲስቶች ምክንያታዊ ያልሆኑ ሳይንሳዊ ድምዳሜዎችን የሚቀበሉት “በቁስ አካላዊነት (materialism) ለማመን ቃል ስለገባን ነው” ሲሉ ጽፈዋል። * ለዎንተን “መለኮታዊ እግር በራችን እንዲደርስ መፍቀድ አንችልም” ሲሉ መጻፋቸው ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ያለው ንድፍ አውጪ መኖሩን ማሰብ እንኳን እንደማይፈልጉ ያሳያል።

በዚህ ረገድ፣ ሮድኔይ ስታርክ የተባሉት ሶሽዮሎጂስት በሳይንቲፊክ አሜሪካን ላይ “ሳይንሳዊ ሰው ለመሆን የምትፈልግ ከሆነ ከሃይማኖት ሰንሰለት ነጻ መውጣት አለብህ የሚለው አመለካከት ለሁለት መቶ ዓመታት ሲለፈፍ ቆይቷል” ሲሉ ጽፈዋል። አክለውም ምርምር በሚያካሂዱ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ “ሃይማኖተኛ የሆኑ ሰዎች ሃይማኖት አልባ በሆኑ ሰዎች ሲናቁ በመቆየታቸው አፋቸውን ዘግተው ለመኖር መርጠዋል” ብለዋል። ስታርክ እንዳሉት “[በሳይንሱ ማኅበረሰብ] ቁንጮዎች ዘንድ ሃይማኖት የሌላቸውን ሰዎች የመሸለም ዘይቤ አለ።”

የማክሮኢቮሉሽን ትምህርት እውነት ነው ብለህ የምትቀበል ከሆነ አምላክ የለሽ የሆኑ ሳይንቲስቶች ሳይንሳዊ ግኝቶችን በሚተረጉሙበት ጊዜ የግል እምነታቸው ተጽዕኖ አያደርግባቸውም ብለህ ማመን ይኖርብሃል። በቢሊዮን በሚቆጠሩ የሚውቴሽን ሂደቶች ላይ አንድ መቶ ዓመት ለሚያክል ጊዜ በተካሄደው ጥናት ሚውቴሽን አንድን ነባር ዝርያ ሙሉ በሙሉ አዲስ ወደሆነ ሌላ ዝርያ ሊለውጥ አለመቻሉ በሚገባ ቢረጋገጥም ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ በሚውቴሽንና በተፈጥሯዊ ምርጦሽ የተገኙ ናቸው ብለህ ማመን ይኖርብሃል። የቅሪተ አካላት መረጃዎች ዋነኞቹ የዕፅዋትና የእንስሳት ዝርያዎች ድንገት በአንድ ጊዜ የተገኙ እንጂ ሕልቆ መሳፍርት በሌላቸው ዘመናት ውስጥ ከአንዱ ዝርያ ወደ ሌላው የተለወጡ አለመሆናቸውን አበክረው ቢያመለክቱም ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ ከአንድ የጋራ ቅድመ አያት እየተሻሻሉ የመጡ ናቸው ብለህ ማመን አለብህ። ታዲያ እንዲህ ያለው እምነት በተጨባጭ ሐቅ ላይ የተመሠረተ ይመስልሃል? ወይስ ተረት ነው?

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 ውሻ የሚያዳቅሉ ሰዎች የሚፈልጉትን እየመረጡ በማዳቀል ከጊዜ በኋላ አጠር ያሉ እግሮች ወይም ረዘም ያለ ፀጉር ያላቸው ውሾች እንዲወለዱ ማድረግ ይችላሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች የሚያስገኙት ለውጥ አንዳንድ ጂኖችን ከጥቅም ውጭ በማድረጋቸው ምክንያት የመጣ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ዳክስሁንድ የሚባለው የውሻ ዝርያ በጣም ድንክዬ የሆነው ለስላሳ አጥንቶቹ (cartilage) ተገቢውን እድገት ማድረግ ስላልቻሉ ነው።

^ አን.4 በዚህ ርዕስ ውስጥ “ዝርያ” የሚለው ቃል በተደጋጋሚ ጊዜያት ቢጠቀስም ቃሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው የዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ እንደማይገኝ ልብ ሊባል ይገባዋል። በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰው ከዚህ ሰፋ ያለ ትርጉም ያለው ‘ወገን’ የሚለው ቃል ነው። ብዙውን ጊዜ ሳይንቲስቶች በዝግመተ ለውጥ አዳዲስ ዝርያዎች ተገኝተዋል የሚሉት መጽሐፍ ቅዱስ ‘ወገን’ በሚለው ውስጥ ያለውን ልዩነት በማየት ነው።

^ አን.6 “ሕይወት ያላቸው ነገሮች በተለያዩ ክፍሎች የሚመደቡት እንዴት ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

^ አን.11 የአንድን ሕያው አካል ቅርጽና ተግባር በመወሰን ረገድ የአንድ ሴል ሳይቶፕላዝም፣ የውጭ ሽፋንና ሌሎች ነገሮች የየራሳቸው ድርሻ እንዳላቸው ተመራማሪዎች አረጋግጠዋል።

^ አን.13 በዚህ ጽሑፍ ላይ የተጠቀሰው የሎኒግ አስተያየት የራሳቸው እንጂ የማክስ ፕላንክን የምርምር ተቋም የሚወክል አይደለም።

^ አን.14 በሚውቴሽን ላይ የተደረጉት ሙከራዎች በተደጋጋሚ እንዳረጋገጡት በሚውቴሽን አማካኝነት አዳዲስ ባሕርያት ያላቸውን ዝርያዎች የማግኘቱ አጋጣሚ በጣም እየቀነሰ ሲሄድ ተመሳሳይ የባሕርይ ለውጥ ያደረጉ ዝርያዎችን የማግኘቱ አጋጣሚ ግን እየጨመረ መጥቷል። ሎኒግ ከዚህ ክስተት በመነሳት “ሎው ኦቭ ሪከረንት ቬሪዬሽን” (ተደጋግሞ የሚከሰት ልዩነት ደንብ) የሚባል ሕግ አውጥተዋል። በተጨማሪም ከዕፅዋት ሚውቴሽን ውጤቶች ውስጥ ለቀጣይ ምርምር ብቁ ሆነው የተገኙት ከ1 በመቶ ያነሱ ሲሆኑ ከእነዚህም መካከል የንግድ ጠቀሜታ እንዳላቸው የታመነባቸው ከ1 በመቶ ያነሱ ናቸው። እንስሳትን በሚውቴሽን በማዳቀል የተገኘውም ውጤት ከዚህ እጅግ የከፋ በመሆኑ ዘዴው ሥራ ላይ እንዳይውል ተደርጓል።

^ አን.29 ቁስ አካላዊነት የሚለው ቃል በዚህ አገባቡ ‘ብቸኛው ወይም መሠረታዊው ነባራዊ ሁኔታ የሚታየው ቁስ አካል ነው፤ ሕይወት ያላቸውን ነገሮች ጨምሮ በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ ያሉት ነገሮች በሙሉ ወደ ሕልውና የመጡት ከተፈጥሮ ውጭ የሆነ ኃይል ፈጽሞ ጣልቃ ሳይገባባቸው ነው’ የሚለውን ንድፈ ሐሳብ ያመለክታል።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ሚውቴሽን አንድን ነባር [የተክል ወይም የእንስሳ] ዝርያ ሙሉ በሙሉ አዲስ ወደሆነ ሌላ ዝርያ ሊለውጥ አይችልም”

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በዳርዊን ፊንቾች ላይ የተደረገው ምርምር ግፋ ቢል ዝርያዎች ከአየሩ ጠባይ ጋር ለመላመድ ራሳቸውን እንደሚለዋውጡ ቢያሳይ ነው

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ቅሪተ አካላት በያዙት መረጃ መሠረት ዋነኞቹ የእንስሳት ዝርያዎች ድንገት በአንድ ጊዜ የተገኙ ሲሆን ምንም ዓይነት ለውጥ ሳይታይባቸው ኖረዋል

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት )

ሕይወት ያላቸው ነገሮች በተለያዩ ክፍሎች የሚመደቡት እንዴት ነው?

ሕይወት ያላቸው ነገሮች ከዝርያ (species) ተነስቶ እስከ ኪንግደም በሚደርስ እያደር እየሰፋ በሚሄድ ክፍል ይመደባሉ። * ለምሳሌ ያህል፣ ከዚህ በታች የተዘረዘረውን የሰውንና የትንኝን አመዳደብ ተመልከት።

ሰው ትንኝ

ስፒሽስ ሳፒየንስ ሜላኖጋስተር

ጂነስ ሆሞ ድሮሶፊላ

ፋሚሊ ሆሚኒድስ ድሮሶፊሊድስ

ኦርደር ፕራይሜትስ ዲፕተራ

ክላስ ማማልስ ኢንሴክትስ

ፋይለም ኮርዴትስ አርትሮፖድስ

ኪንግደም አኒማልስ አኒማልስ

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.49 ማሳሰቢያ:- ዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ዕፅዋትና እንስሳት “እንደየወገናቸው” ዘራቸውን እንደሚተኩ ይገልጻል። (ዘፍጥረት 1:12, 21, 24, 25) ይሁን እንጂ “ወገን” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ሳይንሳዊ ስያሜ ባለመሆኑ “ስፒሽስ” ከሚለው ቃል ጋር አንድ እንደሆነ ተደርጎ መወሰድ የለበትም።

[ምንጭ]

ሰንጠረዡ ጆናታን ዌልስ ባዘጋጁት የዝግመተ ለውጥ ዋና ዋና ንድፈ ሐሳቦች—ሳይንሳዊ ናቸው ወይስ ተረት? ስለ ዝግመተ ለውጥ የምንሰጠው አብዛኛው ትምህርት ስህተት የሆነበት ምክንያት በተባለው መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ላይ የተመሠረተ ነው

[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የሚውቴሽን ውጤት የሆነች ትንኝ (ከላይ) የአካል ጉድለት ይኑራት እንጂ ያው ትንኝ ነች

[ምንጭ]

© Dr. Jeremy Burgess/Photo Researchers, Inc.

[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በዕፅዋት ላይ የተደረጉ የሚውቴሽን ሙከራዎች በተደጋጋሚ እንዳመለከቱት አዳዲስ ባሕርያት ያላቸውን ዝርያዎች የማግኘቱ አጋጣሚ በጣም እያነሰ ሲሄድ ተመሳሳይ ባሕርይ ያላቸው ዝርያዎች ቁጥር ግን ጨምሯል

(የሚውቴሽን ውጤት የሆነው ይህ ተክል ትላልቅ አበቦች አሉት)

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

From a Photograph by Mrs. J. M. Cameron/ U.S. National Archives photo

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

የፊንች ራሶች:- © Dr. Jeremy Burgess/ Photo Researchers, Inc.

[በገጽ 17 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]

ዳይነሶር:- © Pat Canova/Index Stock Imagery; ቅሪተ አካላት:- GOH CHAI HIN/AFP/Getty Images