በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሃሎዊንን የማላከብረው ለምንድን ነው?

ሃሎዊንን የማላከብረው ለምንድን ነው?

ሃሎዊንን የማላከብረው ለምንድን ነው?

በካናዳ የሚኖረው የ14 ዓመቱ ማይክል፣ ባለፈው ዓመት ጎረቤቶቹ ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ጋር ተያያዥነት ያለውንና በአንዳንድ አካባቢዎች እጅግ ታዋቂ የሆነውን የሃሎዊንን ዓመት በዓል ለማክበር ጉድ ጉድ ሲሉ እርሱ ደግሞ በበኩሉ አንድ ሐሳብ በአእምሮው ውስጥ ይጉላላ ነበር። ማይክል ለትምህርት ቤቱ ባዘጋጀው ድርሰት ላይ ሁኔታውን እንደሚከተለው ሲል ገልጾታል:-

‘ምሽቱ የሃሎዊን ዋዜማ ነው። በመስኮት አሻግሬ ስቃኝ የጎረቤቶቻችን ግቢ መቃብር ላይ በሚሠራ ዓይነት ሐውልትና በዓፅም ተሞልቶ፣ መስኮቶቻቸው ደግሞ በጃኮላንተርን አሸብርቀው ተመለከትኩ። * ወላጆች የልጆቻቸውን የበዓል ልብሶች ያሰማምራሉ፤ ልጆች ደግሞ በማግስቱ ስለሚሰበስቡት ከረሜላ ያልማሉ።

‘የእኛ ቤተሰብ ሁኔታ ግን የተለየ ነበር። ግቢያችን አላጌጠም፤ መስኮታችንም ቢሆን በመብራት አላሸበረቀም። ሰዎች ሃሎዊንን የማላከብረው ለምን እንደሆነ ይጠይቁኛል። በመሠረቱ የይሖዋ ምሥክሮች ይህን በዓል የማያከብሩት የበዓሉ አመጣጥ ጥሩ ስላልሆነ ነው። *

‘የሚገርመው፣ ሃሎዊን የሚከበርበትን ወቅት እወደዋለሁ። “ለምን?” ትሉኝ ይሆናል። ምክንያቱም እንዳሰላስል ምቹ አጋጣሚ ይፈጥርልኛል። አንዳንድ ነገሮችን ላለማድረግ የወሰንኩት ለምን እንደሆነ እንዳስብ ያደርገኛል። የአንድን ወግ አመጣጥ ማወቅ አለማወቅ ለውጥ ያመጣል ወይም አያመጣም በሚለው ጉዳይ ላይ እያንዳንዱ ሰው የራሱ አመለካከት ሊኖረው ይችላል። እኔ ግን ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ ይሰማኛል። ለምሳሌ ያህል፣ ብዙ ሰዎች ጎረቤቶቻቸው የናዚዎችን የደንብ ልብስ አድርገው ቢመለከቱ መበሳጨታቸው አይቀርም። ለምን? ይህ የሆነበት ምክንያት አብዛኞቹ ሰዎች የደንብ ልብሶቹ አመጣጥም ሆነ የሚወክሉት ነገር መጥፎ እንደሆነ ስለሚሰማቸው ነው። እኔም ብሆን ዲያብሎስን፣ ክፉ መናፍስትንና አስማተኞችን የሚወክሉ ነገሮች መጥፎ መሆናቸውን አውቃለሁ፤ እንዲሁም ከእነዚህ ነገሮች ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ እንዲኖረኝ አልፈልግም። በሕይወታችን ውስጥ ስለምናደርጋቸው ውሳኔዎችና ለውሳኔያችን ምክንያት ስለሆኑት ጉዳዮች መለስ ብለን ማሰብም ሆነ ብዙኃኑን ተከትለን ሳይሆን በመሠረታዊ ሥርዓቶች ተመርተን ውሳኔዎችን ማድረግ ጠቃሚ እንደሆነ አምናለሁ። ይህን ወቅት የምወደውም ለዚህ ነው። ከሌሎች የተለየሁ በመሆኔና ባመንኩበት ነገር መጽናት በመቻሌ ኩራት ይሰማኛል።’

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 ጃኮላንተርን የሚሠራው የሰው ፊት እንዲመስል ውስጡ ተቦርቡሮ የአፍንጫ፣ የአፍና የዓይን ቀዳዳ በተበጁለት ዱባ ሲሆን በውስጡም ሻማ ወይም ብርሃን የሚሰጥ ሌላ ነገር ይቀመጣል።

^ አን.4 ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የጥቅምት 8, 2001 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ከገጽ 5-10 ተመልከት።