በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለዘመናት ሐዘንና ደስታ ሲፈራረቅባቸው የኖሩት ሮማዎች

ለዘመናት ሐዘንና ደስታ ሲፈራረቅባቸው የኖሩት ሮማዎች

ለዘመናት ሐዘንና ደስታ ሲፈራረቅባቸው የኖሩት ሮማዎች

ዝግጅቱ በተለምዶ የሚደረገውን ትልቅ የሠርግ ሥነ ሥርዓት ይመስላል። ምግብና መጠጥ እንደ ልብ ቀርቧል፤ ቤቱ ውስጥ ሙዚቃው ያስተጋባል። ወዳጅ ዘመድ ሁሉ ዓይን አፋር የሆነውን ሙሽራና በደስታ የምትፍለቀለቀውን ሙሽሪት እንኳን ለወግ ለማዕረግ አበቃችሁ ለማለት ይተረማመሳል። ሆኖም ይህ የሠርግ ዝግጅት ሳይሆን በዋዜማው የሚደረግ የቀለበት ሥነ ሥርዓት ነው። በዚህ የቀለበት ሥነ ሥርዓት ላይ ከ600 በላይ እድምተኞች ተገኝተዋል። የሙሽራው ቤተሰቦች ለወደፊት አማቾቻቸው የሚሆን ጥሎሽ የሚሰጡት በዚህ ጊዜ ነው። በቀጣዩ ቀን ሙሽራውና ቤተሰቡ ሙሽሪትን አጅበው ወደ ሙሽራው ቤት ይወስዷታል፤ በዚያም ዋናው የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ይከናወናል።

የአዲሶቹ ተጋቢዎች ወዳጅ ዘመዶች በሙሉ የሚናገሩት በየትኛውም አካባቢ እንደ ባዕድ ቋንቋ ተደርጎ የሚቆጠረውን ሮማኒ የተባለ ቋንቋ ነው። የተለያዩ ቀበሌኛዎች ያሉት ይህ ቋንቋ ከበርካታ ጥንታዊ ባሕሎችና የጋብቻ ወጎች ጋር ተዳምሮ፣ የራሳቸው አገርና አገዛዝ ሳይኖራቸው በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ ሕዝቦች የጋራ ውርስ ነው። እነዚህ ሕዝቦች ሮማዎች ይባላሉ። *

ሮማዎች እነማን ናቸው?

የሮማዎችን ቋንቋ፣ ባሕልና የዘር ሃረግ አስመልክተው የተደረጉ ጥናቶች እነዚህ ሰዎች ከዛሬ 1,000 ዓመት በፊት በሰሜን ሕንድ አካባቢ ይኖሩ እንደነበር ይጠቁማሉ። ከቅርብ ጊዜያት በኋላ ሰርገው ከገቡት አንዳንድ አዳዲስ ቃላት ውጭ ቋንቋቸው ከሕንድ የተገኘ መሆኑን በግልጽ ማየት ይቻላል። ሕንድን ለቅቀው የሄዱበት ምክንያት በውል አይታወቅም። አንዳንድ ምሑራን የሮማውያን ቅድመ አያቶች በጦርነት ሳቢያ ከትውልድ አገራቸው የተፈናቀሉ ሲሆኑ በጦር ሠራዊት ውስጥ በዕደ-ጥበብና ወታደሮችን በማዝናናት ሥራ ላይ የተሠማሩ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያምናሉ። ያም ሆነ ይህ ሮማዎች ከ1300 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ቀደም ብለው ፋርስንና ቱርክን አቋርጠው እስከ አውሮፓ ድረስ ዘልቀዋል።

አውሮፓውያን፣ ሮማዎችን በተመለከተ ፍጹም ተቃራኒ የሆኑ ሁለት አመለካከቶች አሏቸው። በአንድ በኩል በአንዳንድ ድርሰቶችና ፊልሞች ላይ እንግዳ ተቀባዮች፣ ስለ ምንም ነገር የማይጨነቁ፣ በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥመውን ደስታም ሆነ ሐዘን በሙዚቃና በጭፈራ የሚገልጹ ነጻ ሰዎች እንደሆኑ ተደርገው ተወድሰዋል። በሌላ በኩል ደግሞ የማይታመኑ፣ ድብቅ፣ ተጠራጣሪ፣ ውስጣቸው የማይታወቅ፣ ከሰው የማይቀላቀሉ እንዲሁም ከማኅበረሰቡ የተገለሉ እንደሆኑ ስለሚገለጽ ስማቸው ጎድፏል። በብዙ ሰዎች ዘንድ እንዲህ ዓይነቱ ግንዛቤ እንዲኖር ምክንያት የሆነው ምን እንደሆነ ለማወቅ እንድንችል፣ ትኩረት የሚስበውን የሮማዎች ታሪክ መለስ ብለን እንቃኝ።

የዘር መድልዎ የነገሠበት ዘመን

በመካከለኛው ዘመን ይኖሩ የነበሩት አብዛኞቹ አውሮፓውያን ከመንደራቸው ወይም ከከተማቸው ውጪ ስለ ሌላው ዓለም ያላቸው እውቀት ውስን ነበር። በመሆኑም የመጀመሪያዎቹ የሮማ ቤተሰቦች ወደ መንደሮቻቸው ሲመጡ ምን ተሰምቷቸው ሊሆን እንደሚችል ገምት። ስደተኞቹ የሚያደርጉት እያንዳንዱ እንቅስቃሴ የመንደርተኞቹን ትኩረት መሳቡ አይቀርም። ከመልካቸው፣ ከዓይናቸውና ከጸጉራቸው ጥቁረት ባሻገር አለባበሳቸው፣ ወጋቸውና ቋንቋቸውም ቢሆን አውሮፓውያኑ ከሚያውቁት ፈጽሞ የተለየ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ሮማዎች የመደብ ልዩነት በስፋት ከሚታይበት ከሕንድ መምጣታቸው ባሳደረባቸው ተጽዕኖ ሳቢያ ሳይሆን አይቀርም፣ ራሳቸውን ከኅብረተሰቡ የማግለል ባሕርይ ይታይባቸው ነበር። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ የአውሮፓውያኑ የአግራሞት ስሜት በጥርጣሬ ተተካ።

ሮማዎች ቃል በቃል ከኅብረተሰቡ እንዲገለሉ ብሎም ከመንደሮች ርቀው በሚገኙ ቦታዎች እንዲሰፍሩ ተደረገ። ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ አስፈላጊ ነገሮችን ለመሸመትም ሆነ ውኃ ለመቅዳት እንኳ ወደ መንደሮቹ እንዳይገቡ ተከለከሉ። “ልጆችን ይሰርቃሉ፤ እንዲያውም ይበሏቸዋል!” የሚል ወሬም ይናፈስ ነበር። በመሆኑም በአንዳንድ አካባቢ ሮማዎች የሚበሉት ምን እንደሆነ ለማወቅ የፈለገ ሰው መመልከት እንዲችል ምግባቸውን ከቤት ውጪ እንዲያበስሉ የሚያዝ ሕግ ወጣ። አብዛኛውን ጊዜ፣ የሚያበስሉት ምን እንደሆነ ለማወቅ የፈለጉ ሰዎች የዕለት ምግባቸውን መሬት ላይ ይደፉባቸው ነበር። በመሆኑም አንዳንድ ሮማዎች ሕይወታቸውን ለማቆየት ሲሉ ምግብ መስረቅ መጀመራቸው አያስገርምም።

ሮማዎች የሚደርስባቸውን የዘር መድልዎ መቋቋም የቻሉት አንድነታቸውን በማጠናከር ነበር። በቤተሰባቸው መካከል ያለው ይህ ጥብቅ ትስስር ለብዙ ዓመታት የድጋፍና የደስታ ምንጭ ሆኖላቸዋል። ሮማ ወላጆች ለልጆቻቸው ልዩ እንክብካቤ የማድረግ፣ ልጆች ደግሞ ወላጆቻቸውን የመጦር ባሕል አላቸው። አብዛኞቹ ሮማዎች ሲወርድ ሲዋረድ የመጡ የሥነ ምግባር ደንቦችን በጥብቅ ይከተላሉ።

ከቦታ ቦታ መንከራተት

ሮማዎች በሚጓዙባቸው በአብዛኞቹ አካባቢዎች ተገቢ አቀባበል ስለማይደረግላቸው ከቦታ ወደ ቦታ መንከራተት ግድ ይሆንባቸዋል። ይህ ዓይነቱ አኗኗር የብረታ ብረት ሥራ፣ ንግድና ሰዎችን ማዝናናትን የመሳሰሉ የተለያዩ ሙያዎች በኅብረተሰባቸው ዘንድ እንዲስፋፉ አስተዋጽኦ አድርጓል። በሰዎች ዘንድ ተፈላጊነት ያላቸውን እንደ እነዚህ ያሉ ሥራዎችን መሥራታቸው ቢያንስ ቢያንስ ለቤተሰባቸው የዕለት ጉርስ የሚሆን ገቢ ያስገኝላቸዋል። ሮማዎች ምትሃታዊ ኃይል አላቸው ተብሎ የሚነገር ሲሆን አንዳንድ የሮማ ሴቶች ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ እንዲህ ዓይነት ችሎታ ያላቸው ያስመስሉ ነበር። ከቦታ ቦታ መዘዋወራቸው ከጋድጄ ማለትም “ሮማ ካልሆኑ ሰዎች” ጋር የቅርብ ግንኙነት በመመሥረታቸው ሳቢያ ሊከሰት የሚችለውን የባሕል ወይም የሥነ ምግባር መበከል በመጠኑም ቢሆን ቀንሶታል። *

ቆየት ብሎም፣ የዘር መድልዎው ወደ ስደት ተቀየረ። ሮማዎች ከአንዳንድ የአውሮፓ አካባቢዎች ተባረሩ። በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ለበርካታ ዘመናት በባርነት ሲማቅቁ ኖረዋል። በ1860ዎቹ ይህ የባርነት ዘመን ማብቃቱም ቢሆን በርካታ ሮማዎች ወደ ምዕራብ አውሮፓና ወደ አሜሪካ እንዲፈልሱ ምክንያት ሆኗል። እነዚህ ሕዝቦች የትም ይሂዱ የት ቋንቋቸውን፣ ባሕላቸውንና ሙያቸውን አይተዉም ነበር።

ሮማዎች በግፍ በሚደቆሱበት ጊዜም ቢሆን ባላቸው የጥበብ ተሰጥኦ ይደሰቱ ነበር። በስፔን የሮማዎች ባሕል ከሌሎች ባሕሎች ጋር ተደባልቆ የፍላሚንኮን ሙዚቃና ጭፈራ አስገኝቷል፤ በምሥራቅ አውሮፓ ደግሞ ሮማ ሙዚቀኞች የአካባቢውን ባሕላዊ ሙዚቃ ከራሳቸው ለየት ያለ ስልት ጋር አዋህደውታል። የሮማዎች ስሜት ቀስቃሽ የሙዚቃ ስልት ቤትሆቨንን፣ ብራምዝን፣ ድቮርዣክን፣ ሃይድንን፣ ሊስትን፣ ሞዛርትን፣ ራኽማኒኖፍን፣ ራቬልን፣ ሮሲኒን፣ ሳን-ሳንንና ሳራሳቴን በመሳሰሉ የክላሲካል ሙዚቃ ደራሲዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል።

ሮማዎች በዘመናችን

በዛሬው ጊዜ ከሁለት እስከ አምስት ሚሊዮን፣ አንዳንዶች እንደሚሉት ከሆነ ደግሞ ከዚህ ቁጥር በላይ የሚሆኑ ሮማዎች በሁሉም የምድር ክፍል ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ የሚኖሩት በአውሮፓ ነው። ብዙዎቹ የተረጋጋ ሕይወት የሚመሩ ሲሆን እንዲያውም አንዳንዶቹ የናጠጡ ሀብታሞች ናቸው። ይሁንና ሮማዎች በብዙ አካባቢዎች አሁንም ድሆችና ችግረኞች ከመሆናቸውም በላይ የሚኖሩትም በደሳሳ ጎጆ ውስጥ ነው።

ኮሚኒዝም በሰፈነበት ዘመን የምሥራቅ አውሮፓ የፖለቲካ ጽንሰ ሐሳብ የሁሉንም ሰዎች እኩልነት ይደነግግ ነበር። መንግሥታቱ፣ ሮማዎችን ሥራ በማስያዝና በመንግሥት መኖሪያ ቤቶች ውስጥ እንዲኖሩ በማድረግ ከቦታ ቦታ መዘዋወራቸውን ለማስቀረት ያደረጉት ሙከራ በተወሰነ መልኩ ተሳክቶላቸዋል። አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ጤና ነክ በሆኑ ጉዳዮችና በአኗኗራቸው ላይ መሻሻል እንዲታይ ምክንያት ሆኗል። የሆነ ሆኖ፣ ይህ ሁሉ በሮማዎችና ሮማ ባልሆኑ ሰዎች መካከል ለዘመናት የኖረውን አሉታዊ ስሜትና አመለካከት ሊፍቀው አልቻለም።

በ1990ዎቹ በምሥራቅ አውሮፓ የተካሄዱት ፖለቲካዊ ለውጦች ተስፋ የሚሰጡ መስለው ይታዩ ነበር። ይሁን እንጂ እነዚህ ለውጦች የሮማዎች የቆየ ቁስል እንዲያመረቅዝ ምክንያት ሆነዋል። ለኅብረተሰቡ የሚደረጉት ድጎማዎች መቀነሳቸውና የዘር መድልዎን የሚቃወሙ ሕጎችን ለማስፈጸም የሚደረገው ጥረት መለዘቡ በርካታ ሮማዎችን ለከፋ ማኅበረሰባዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ዳርጓቸዋል።

ተስፋና የተሻለ ሕይወት ማግኘት

ሐር የመሰለ ጸጉር ያላት አንድሪያ በምሥራቅ አውሮፓ በሚገኝ ትምህርት ቤት ውስጥ ስትማር የነበረው ሁኔታ ከላይ የተጠቀሰውን ይመስል ነበር። በክፍሏ ውስጥ ካሉት ተማሪዎች መካከል የሮማ ዝርያ ያላት እርሷ ብቻ ነበረች። መንፈሰ ጠንካራ ብትሆንም በጊዜው ይደርስባት የነበረውን ስድብና መገለል ባስታወሰች ቁጥር ዓይኖቿ እንባ ያቀራሉ። አንድሪያ እንዲህ ትላለች:- “አንድ ዓይነት ጨዋታ ለመጫወት በምንመዳደብበት ጊዜ እኔን የሚመርጡኝ ሌላ ሰው ሲያጡ ብቻ ነበር። በዚህ ጊዜ ተቀባይነት ላገኝ ወደምችልበት ወደ ሕንድ በረሽ ሂጂ የሚል ስሜት ይመጣብኛል። እንዲያውም በአንድ ወቅት አንድ ልጅ ጓደኛዬን ‘ወደ ሕንድ ሂዱልን!’ ብሎት ነበር። እርሱም በምላሹ ‘ገንዘብ የለኝም እንጂ እሄድልህ ነበር’ ማለቱን አስታውሳለሁ። የትኛውም አካባቢ ቢሆን እንደ ቤትህ ሆኖ አይሰማህም፤ ባይተዋርነት ይሰማን ነበር።” የውዝዋዜ ተሰጥኦ ያላት አንድሪያ ዝነኛ በመሆን በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት የማግኘት ሕልም ነበራት። ሆኖም በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለች ከዚህ የተሻለ ነገር አገኘች።

አንድሪያ እንደሚከተለው ብላለች:- “አንድ ቀን ፓይሮስካ የተባለች አንዲት ወጣት የይሖዋ ምሥክር ቤታችን መጣች። አምላክ የሰውን ዘር በጠቅላላ ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱን ሰው በግለሰብ ደረጃ እንደሚወደው ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳየችኝ። ፈቃደኛ ከሆንኩ ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረት እንደምችል አስረዳችኝ። ይህ ደግሞ በአምላክ ፊት ውድ እንደሆንኩ እንዲሰማኝ አደረገኝ። ሁሉም ሰዎች በእርሱ ፊት እኩል መሆናቸውን ማወቄ በራስ የመተማመን መንፈሴን ይበልጥ አጠንክሮልኛል።

“ፓይሮስካ ወደ ይሖዋ ምሥክሮች መሰብሰቢያ ወሰደችኝ። በዚያም ከሮማዎችና ሮማዎች ካልሆኑ ሰዎች ጋር የተዋወቅሁ ሲሆን በመካከላቸውም ፍጹም አንድነት መኖሩን ተገነዘብኩ። ሮማዎች ከሆኑትም ይሁን ካልሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ጥሩ ወዳጅነት መመሥረት ቻልኩ። ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል ከፓይሮስካ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ካጠናሁ በኋላ እኔም የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።” በአሁኑ ጊዜ አንድሪያና ባለቤቷ የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን ሲሆኑ አምላክ ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ፍቅር እንዳለው ለሰዎች ያስተምራሉ።

“ሁሉም ሰው ከሌሎች እኩል አድርጎ ይመለከተኝ ነበር”

ሃይሮ የተባለ ሮም፣ በልጅነቱ ያሳለፈውን ጊዜ መለስ ብሎ በማስታወስ እንዲህ ይላል:- “ሕግ ከማያከብሩ መጥፎ ልጆች ጋር መግጠሜ በተደጋጋሚ ለችግር ዳርጎኛል። አንድ ጊዜ፣ ከእነዚሁ ልጆች ጋር ሆኜ ስሰርቅ ፖሊሶች ያዙኝ። ወደ ቤቴ ይዘውኝ በሚሄዱበት ጊዜ በጣም ያስፈራኝ በፖሊሶች መያዜ ሳይሆን የእናቴ ቁጣ ነበር። ብዙዎቹ የሮም ቤተሰቦች እንደሚያደርጉት ሁሉ እኔም መስረቅ ትክክል አለመሆኑን ተምሬአለሁ።”

ሃይሮ ካደገ በኋላ እርሱና ቤተሰቡ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኙ። ሃይሮ፣ የአምላክ መንግሥት ጭፍን ጥላቻንና የዘር መድልዎን ጨምሮ በሰው ልጆች ላይ የሚደርስ ማንኛውንም ችግር እንደሚያስወግድ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ሲያውቅ ልቡ ተነካ። ሃይሮ እንደሚከተለው ይላል:- “ሮማዎች እንክብካቤ የሚያደርግላቸው የራሳቸው መንግሥት ኖሯቸው አያውቅም። በመሆኑም ሮማዎች የአምላክ መንግሥት ለሁሉም ሰው የሚያስገኘውን ጥቅም ከማንም የበለጠ እንደሚረዱትና ለዚህም አመስጋኝ እንደሚሆኑ አምናለሁ። አሁንም ቢሆን ተጠቃሚዎች ሆነናል። ለመጀመሪያ ጊዜ በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ከተገኘሁበት ጊዜ አንስቶ ‘እግዚአብሔር ለማንም እንደማያዳላ በእርግጥ ተረድቻለሁ፤ ነገር ግን እርሱን የሚፈሩትንና ጽድቅን የሚያደርጉትን ሁሉ ከየትኛውም ወገን ቢሆኑ ይቀበላቸዋል’ በማለት እንደተናገረው እንደ ሐዋርያው ጴጥሮስ ዓይነት ስሜት ይሰማኛል። (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35) ሁሉም ሰው ከሌሎች እኩል አድርጎ ይመለከተኝ ነበር። ሮም ያልሆነ አንድ ሰው በሮማኒ ቋንቋ ፕራላ ማለትም ‘ወንድም’ ብሎ ሲጠራኝ ስሰማ ጆሮዬን ማመን አልቻልኩም!

“በመጀመሪያ፣ ከቤተሰባችን ውስጥ አንዳንዶቹ ክፉኛ ተቃውመውኝ ነበር። ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምቼ ለመኖር ስል የማደርጋቸውን ለውጦች መረዳት አስቸግሯቸው ነበር። አሁን ግን ዘመዶቻችንም ሆኑ መላው የሮማ ማኅበረሰብ የአምላክን የአቋም ደረጃዎች ጠብቄ መመላለሴ ምን ያህል ደስተኛ እንዳደረገኝና መልካም ፍሬዎችን እንዳስገኘልኝ መመልከት ችለዋል። ብዙዎቹም ሕይወታቸውን ለማሻሻል ይፈልጋሉ።” በአሁኑ ወቅት ሃይሮ ክርስቲያን ሽማግሌና የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል። ሮም ያልሆነችው ባለቤቱ ሜገንም ብትሆን መጽሐፍ ቅዱስ አሁንና ወደፊት ደስታ የሰፈነበት ሕይወት እንዲመሩ ሊረዳቸው የሚችለው እንዴት እንደሆነ ለሮማዎችም ሆነ ለሌሎች በማስተማር ላይ ትገኛለች። ሜገን “የባለቤቴ ቤተሰቦችም ሆኑ መላው ማኅበረሰብ ሙሉ በሙሉ ተቀብለውኛል። ሮም ያልሆነ ሰው እነርሱን ለመቅረብ መፈለጉ ያስደስታቸዋል” ብላለች።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 ሮማዎች በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ውስጥ በተለያዩ መጠሪያዎች የሚታወቁ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ጂፕሲ፣ ኪታኖስ፣ ቲሲጎይኒ፣ ቲሲጋኒ እና ሲጋኒ የሚሉት ይገኙበታል። እነዚህ መጠሪያዎች አሉታዊ አንድምታ ያላቸው ናቸው። ሮም (ብዙ ቁጥሩ ደግሞ ሮማ) የሚለው ቃል በእነርሱ ቋንቋ ትርጉሙ “ሰው” ማለት ሲሆን አብዛኞቹ ሮማዎች ራሳቸውን በዚህ ስም ይጠራሉ። እንደ ሲንቲ ያሉ አንዳንድ ሮማኒ ተናጋሪ ኅብረተሰቦች ደግሞ ሌሎች መጠሪያዎችን ይጠቀማሉ።

^ አን.12 አንዳንድ ሮማዎች የጥንት ባሕላቸውን አጥብቀው የሚይዙ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ ግን በአካባቢያቸው የሚኖሩትን ሰዎች ሃይማኖት ይከተላሉ።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በዛሬው ጊዜ ሮማዎች በሁሉም የምድር ክፍል ይገኛሉ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በአውሮፓ ውስጥ የናዚ አገዛዝ በሰፈነበት ጊዜ ሂትለር የአይሁዶችን፣ የይሖዋ ምሥክሮችንና የሌሎችንም ሕይወት በቀጠፈባቸው ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ 400,000 ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑ ሮማዎችም ተገድለዋል። የሂትለር የዘር ማጥፋት ዘመቻ ባልተስፋፋበት በ1940 የሮም ዝርያ ያለው የፊልም ተዋናይ ቻርሊ ቻፕሊን ሂትለርንና የናዚ ንቅናቄን የሚነቅፍ ዘ ግሬት ዲክታተር የተሰኘ ፊልም ሠርቷል። የሮማ ዝርያ እንዳላቸው ከሚነገርላቸው ታዋቂ አርቲስቶች መካከል ዩል ብሪነር፣ የፊልም ተዋናይ የሆነችው ሪታ ሄይዎርዝ (ከታች)፣ ሠዓሊው ፓብሎ ፒካሶ (ከታች)፣ የጃዝ ሙዚቀኛ የሆነው ጃንጎ ራይንሃርትና መቄዶናዊዋ አቀንቃኝ ኤስማ ሬድጄፖቫ ይገኙበታል። ከዚህም በተጨማሪ ሮማዎች የሆኑ ዶክተሮች፣ መሃንዲሶች፣ ፕሮፌሰሮችና የምክር ቤት አባሎችም ይገኛሉ።

[ምንጮች]

AFP/Getty Images

Photo by Tony Vaccaro/Getty Images

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ሮማ የይሖዋ ምሥክሮች

ከሮማዎች መካከል ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ የጉባኤ ሽማግሌዎችና የዘወትር አቅኚዎች ሆነው ያገለግላሉ። የመንግሥት ባለ ሥልጣናትም ሆኑ ሮማዎች ያልሆኑ ሌሎች ሰዎች፣ የይሖዋ ምሥክር የሆኑት ሮማዎች ጥሩ አርዓያ እንደሆኑ ይመሠክራሉ። በስሎቫኪያ የሚኖር አንድ ሮም የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ብሏል:- “አንድ ቀን ሮም ያልሆነ አንድ ጎረቤታችን በራችንን አንኳኳ። ከዚያም ‘በትዳሬ ውስጥ ችግር አጋጥሞኛል፣ ሆኖም እናንተ ልትረዱኝ እንደምትችሉ አምናለሁ’ አለን። እኛም ‘እነርሱ ይረዱኛል ብለህ ለምን አሰብክ?’ በማለት ጠየቅነው። እርሱም በምላሹ ‘የምታመልኩት አምላክ እናንተን ሮማዎችን ሕይወታችሁን እንድታሻሽሉ ከረዳችሁ እኛንም ሊረዳን ይችላል’ አለን። እኛም በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ ስለ ቤተሰብ ሕይወት የሚናገር አንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ ሰጠነው።

“ትንሽ ቆየት ብሎ አሁንም በራችን ተንኳኳ፤ ሁኔታውን ያላወቀችው ቀደም ሲል መጥቶ የነበረው ግለሰብ ባለቤትም ተመሳሳይ ጥያቄ አቀረበችልን። ‘ከእናንተ በቀር በዚህ መኖሪያ ሕንጻ ውስጥ ሊረዳን የሚችል ማንም ሰው የለም’ አለችን። ለእርሷም እንዲሁ ለባለቤቷ የሰጠነውን መጽሐፍ ሰጠናት። ሁለቱም ወደ እኛ ቤት መምጣታቸውን ለትዳር ጓደኛቸው እንዳንናገር ጠይቀውን ነበር። ከአንድ ወር ከግማሽ በኋላ ከእነዚህ ባልና ሚስት ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመርን። ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር ተስማምተን መኖራችን ሰዎች ስለ እኛ መልካም አመለካከት እንዲኖራቸውና መንፈሳዊ እርዳታ ለማግኘት ወደ እኛ እንዲመጡ ምክንያት ሆኗል።”

[ሥዕል]

ናርቦኒ፣ ፈረንሳይ

ግራናዳ፣ ስፔን

“ሮማዎች የአምላክ መንግሥት ለሁሉም ሰው የሚያስገኘውን ጥቅም ከማንም የበለጠ እንደሚረዱትና ለዚህም አመስጋኝ እንደሚሆኑ አምናለሁ።”—ሃይሮ

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፖላንድ

[ምንጭ]

© Clive Shirley/Panos Pictures

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሮማዎች በእንግሊዝ፣ በ1911

[ምንጭ]

By courtesy of the University of Liverpool Library

[በገጽ 22 እና 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስሎቫኪያ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መቄዶንያ

[ምንጭ]

© Mikkel Ostergaard/Panos Pictures

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሩማንያ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መቄዶንያ

[በገጽ 24 እና 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቼክ ሪፑብሊክ

[በገጽ 24 እና 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስፔን

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድሪያ ጎበዝ ተወዛዋዥ በመሆን ታዋቂነትና ተቀባይነት የማግኘት ሕልም ነበራት

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ሩማንያ:- © Karen Robinson/Panos Pictures; መቄዶንያ:- © Mikkel Ostergaard/Panos Pictures; ቼክ ሪፑብሊክ:- © Julie Denesha/Panos Pictures