በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሥር የሰደደ የአመጋገብ ችግር ይኖርብኝ ይሆን?

ሥር የሰደደ የአመጋገብ ችግር ይኖርብኝ ይሆን?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

ሥር የሰደደ የአመጋገብ ችግር ይኖርብኝ ይሆን?

“አንዳንድ ጊዜ ምግብ ፊት ስቀርብ በጣም ከመረበሼ የተነሳ ሰውነቴ መንቀጥቀጥ ይጀምራል። ክብደት እንዳልጨምር እፈራለሁ። ‘ገና ሁለት ኪሎ መቀነስ አለብኝ’ ብዬ አስባለሁ።”—ሜሊሳ *

“ማራኪ ሆኜ መታየት ስለምፈልግ እንዳልወፍር እፈራለሁ። ሆኖም ምግብ ከበላሁ በኋላ ሆነ ብዬ እንደማስመልስ ማንም እንዲያውቅብኝ አልፈልግም። እንዲህ ያለው ነገር በጣም አሳፋሪ ነው።”—አምበር

“‘ዛሬ፣ ማሻሻል አለብኝ። . . .’ ብዬ ለራሴ ቃል እገባለሁ። በኋላ ላይ ግን ሁኔታው ከቁጥጥሬ ውጪ ይሆንና ከመጠን በላይ እበላለሁ። ወዲያውኑ የጥፋተኝነት ስሜት ስለሚሰማኝ ሞቴን እመኛለሁ።”—ጄኒፈር

ማራኪ ሆነሽ ለመታየት እንደምትፈልጊ እሙን ነው፤ እንዲህ ያለው ስሜት ተፈጥሯዊ ነው። የመረበሽ ወይም የጭንቀት ስሜት ሲሰማሽ የሚያጽናናሽ ትፈልጊያለሽ፤ ይህም ቢሆን ምንም ስህተት የለውም። እዚህ ላይ ከተጠቀሱት ወጣቶች መካከል እንደ አንዷ የምታደርጊ ከሆነ ግን ችግር ሊኖርብሽ ይችላል። ችግር ቢኖርብሽ አንቺ የመጀመሪያዋ አይደለሽም። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች በተለይ ደግሞ ወጣት ሴቶች ሥር የሰደደ የአመጋገብ ችግር አለባቸው። *

እስቲ አኖሬክሲያ፣ ቡሊሚያ እና ቢንጅ ኢቲንግ (ከመጠን በላይ የመብላት ችግር) ስለተባሉት ችግሮች አንዳንድ ሐሳቦችን እንመልከት። የእያንዳንዱ ሕመም ምልክት ለየቅል ቢሆንም ሁሉም ሰዎች ስለ ምግብ ካላቸው የተዛባ አመለካከት ጋር የተያያዙ ናቸው። ከታች ከሰፈሩት መግለጫዎች መካከል አንዱ ከአንቺ ሁኔታ ጋር እንደሚመሳሰል ከተገነዘብሽ እርዳታ በማግኘት ከችግርሽ መላቀቅ እንደምትችዪ እርግጠኛ ሁኚ!

አጭር መግለጫ

አኖሬክሲያ። ይህ ችግር ያለባት ሴት ምንም ያህል ቀጭን ብትሆን ራሷን በመስተዋት ስትመለከት የሚታያት ወፍራም እንደሆነች ነው። ውፍረት ለመቀነስ ስትል በምግብ ላይ ከመጠን ያለፈ ገደብ ትጥላለች። በዚህ ሕመም የምትሰቃይ አንዲት ወጣት “በምበላው ምግብ ውስጥ ምን ያህል ካሎሪ እንዳለ የመከታተል ልማድ ተጠናወተኝ” ብላለች። አክላም “በሳምንቱ ውስጥ የምበላውን የምግብ ዓይነት አስቀድሜ እወስናለሁ። ብዙ ካሎሪ ያለው ምግብ እንደተመገብኩ ከተሰማኝ ደግሞ በቀን ውስጥ ቁርስ ወይም ምሳ አሊያም እራት ሳልበላ እቀራለሁ፤ እንዲሁም ከባድ ስፖርት እሠራለሁ። በቀን ውስጥ ስድስት የሚያህሉ የሚያስቀምጡ መድኃኒቶችን እወስዳለሁ” ስትል ተናግራለች።

ብዙም ሳይቆይ የአኖሬክሲያ ችግር መኖሩን የሚጠቁሙት ምልክቶች መታየት ይጀምራሉ። የተለመደው ምልክት ክብደት መቀነስ ሲሆን ሕመምተኛዋ እንደ ፀጉር መርገፍ፣ የቆዳ ድርቀት፣ ድካምና የአጥንት መልፈስፈስ የመሳሰሉ ምልክቶች ሊታዩባት ይችላሉ። የወር አበባዋ ጊዜውን ጠብቆ ላይመጣ ሌላው ቀርቶ ለበርካታ ወራት ሊቀር ይችላል።

እነዚህ ምልክቶች ምንም ጉዳት የሌላቸው ይመስሉ ይሆናል፤ ሆኖም የሚከተለውን ሐቅ መዘንጋት አይኖርብሽም:- አኖሬክሲያ ለሕይወት አስጊ ነው። አንድ ጥናት እንዳመለከተው ይህ ችግር ካለባቸው ሰዎች መካከል 10 በመቶ የሚያህሉት አብዛኛውን ጊዜ ከሰውነት ክፍላቸው አንዱ መሥራት በማቆሙ ወይም ደግሞ የተመጣጠነ ምግብ ባለመውሰዳቸው ምክንያት ሕይወታቸውን ያጣሉ።

ቡሊሚያ። ይህ ችግር ያለባት ሴት ምግብ ከመተው ይልቅ በሁለት ሰዓታት ውስጥ ብቻ 15,000 የሚያህል ካሎሪ ያለበት ምግብ ትበላለች! ከዚያም አብዛኛውን ጊዜ እንዲያስመልሳት በማድረግ ወይም የሚያስቀምጡ አሊያም የሚያሸኑ መድኃኒቶችን በመውሰድ የበላችውን ታስወግዳለች።

የቡሊሚያ ችግር ያለባቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ የሚበሉት በድብቅ ነው። አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች:- “ከትምህርት ቤት ስመለስ ቤት ውስጥ ማንም ከሌለ አብዛኛውን ጊዜ ከመጠን በላይ እበላለሁ። እንዲሁም ያደረግሁት ነገር እንዳይታወቅብኝ እጠነቀቃለሁ።” ይሁን እንጂ ከበላች በኋላ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማታል። “ስለ ራሴ መጥፎ ስሜት ይሰማኛል። ሆኖም ያደረግኋቸውን ነገሮች መቀልበስ እንደምችል አውቃለሁ። ወደ ፎቅ እሄድና የበላሁትን አስወጣዋለሁ። በዚህ ጊዜ እፎይታ ብቻ ሳይሆን ነገሮችን በቁጥጥሬ ሥር እንዳደረግሁ ጭምር ይሰማኝ ነበር” ብላለች።

የበሉትን ማስወጣት ጥቅም ያለው ቢመስልም አደገኛ ነው። የሚያስቀምጡ መድኃኒቶችን አላግባብ መውሰድ የአንጀትን የውስጥ ግድግዳ ስለሚያሳሳ ለአንጀት እብጠት አሊያም ቁስለት ሊዳርግ ይችላል። ደጋግሞ ማስመለስ ደግሞ ድርቀት፣ የጥርስ መበስበስ፣ የምግብ መውረጃ ቧንቧ መጎዳት ሌላው ቀርቶ የልብ ድካም ሊያስከትል ይችላል።

ቢንጅ ኢቲንግ ወይም ከመጠን በላይ መብላት። በቡሊሚያ እንደሚሠቃዩት ሰዎች ሁሉ ይህ ችግር ያለባት ሴትም በጣም ብዙ ምግብ ትመገባለች። ልዩነቱ የበላችውን ምግብ መልሳ የማታስወጣ መሆኑ ነው። በዚህም ምክንያት ከልክ በላይ ልትወፍር ትችላለች። ይሁን እንጂ ይህ ችግር እንዳለባቸው አንዳንድ ሰዎች ሁሉ እርሷም ብዙ ከበላች በኋላ ለረጅም ጊዜ ምንም ሳትበላ ትቆያለች፤ ወይም ደግሞ ከባድ ስፖርት ትሠራለች። አንዳንድ ጊዜ ክብደቷን በዚህ መንገድ ልትቆጣጠረው ስለምትችል ቤተሰቦቿ ወይም ጓደኞቿ ችግር እንዳለባት እንኳ ሳይረዱላት ሊቀሩ ይችላሉ።

የአኖሬክሲያና የቡሊሚያ ችግር እንዳለባቸው ሰዎች ሁሉ እነዚህም ስለ ምግብ ያላቸው አመለካከት የተዛባ ነው። አንዲት ወጣት ስለራሷም ሆነ በዚህ ችግር ስለሚሠቃዩ ሌሎች ሰዎች ስትናገር “ምግብ የምስጢር ጓደኛችን ነው። ምናልባትም ብቸኛው ወዳጃችን ሳይሆን አይቀርም” ብላለች። ሌላዋ ወጣት ደግሞ “ከመጠን በላይ እየበላችሁ እያለ ከምግብ ሌላ አስፈላጊ ነገር እንደሌለ ይሰማችኋል። . . . ምግብ ሐሳብ ይቀንሳል። ከበላችሁ በኋላ ግን በጥፋተኝነት ስሜትና በጭንቀት ትዋጣላችሁ” ብላለች።

አንድ ሰው የበላውን ምግብ የማያስወግድ ቢሆንም እንኳ ያለ ልክ መብላት በራሱ አደገኛ ነው። ለስኳር በሽታ፣ ለደም ግፊት፣ ለልብ ችግርና ለሌሎች በርካታ በሽታዎች ሊያጋልጥ ይችላል። ከዚህም በላይ ከፍተኛ የስሜት ቀውስ ሊያስከትል ይችላል።

አንቺስ ሊያጋጥምሽ ይችላል?

እርግጥ ነው፣ ሰውነታቸው እንዲቀንስ ወይም የተስተካከለ የሰውነት ቅርጽ እንዲኖራቸው የሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ሥር የሰደደ የአመጋገብ ችግር አለባቸው ማለት አይደለም። ያም ሆኖ ግን ከላይ የተሰጡትን ሐሳቦች ከመረመርሽ በኋላ ወደዚህ ችግር እያመራሽ መሆኑን አስተውለሽ ይሆናል። እስቲ እንዲህ እያልሽ ራስሽን ጠይቂ:-

▪ ከምግብ ጋር በተያያዘ ያሉኝ ልማዶች ያሳፍሩኛል?

▪ የአመጋገብ ልማዴን ሌሎች ሰዎች እንዳያውቁብኝ እጠነቀቃለሁ?

▪ ከምግብ የበለጠ ምንም ነገር እንደሌለ ይሰማኛል?

▪ በቀን ከአንድ ጊዜ በላይ ክብደቴን እለካለሁ?

▪ ክብደት ለመቀነስ ስል አደገኛ የሆኑ እርምጃዎችን እወስዳለሁ?

▪ ሆነ ብዬ በማስመለስ የበላሁትን አስወጣለሁ? የሚያስቀምጡና የሚያሸኑ መድኃኒቶችንስ እወስዳለሁ?

▪ የአመጋገብ ልማዴ ማኅበራዊ ሕይወቴን ነክቶብኛል? ለምሳሌ፣ ተደብቄ ለመብላት ወይም ለማስመለስ ስል ብቻዬን መሆን እመርጣለሁ?

ለእነዚህ ጥያቄዎች የሰጠሻቸው መልሶች ችግር እንዳለብሽ የሚጠቁሙ ከሆነ እንዲህ እያልሽ ራስሽን ጠይቂ:-

▪ በዚህ መልክ የምመራው ሕይወት በእርግጥ ያስደስተኛል?

ሁኔታውን ለማስተካከል ምን ማድረግ እችላለሁ?

አሁኑኑ እርምጃ ውሰጂ!

በቅድሚያ መውሰድ የሚገባሽ እርምጃ ችግር እንዳለብሽ ማመን ነው። ዳንየል እንዲህ ብላለች:- “በጉዳዩ ላይ በደንብ ካሰብኩበት በኋላ የአኖሬክሲያ ችግር ያለባቸው ወጣቶች ዓይነት ስሜትና ልማድ እንዳለኝ ተገነዘብኩ። እነርሱ የሚያደርጉትን ነገር እኔም የማደርግ መሆኔን አምኖ መቀበሉ አስፈርቶኝ ነበር።”

የሚቀጥለው እርምጃሽ ስለ ጉዳዩ አንስተሽ ወደ ይሖዋ መጸለይ ነው። * ይህን የጤና ችግር ማሸነፍ እንድትችዪ መንስኤውን ለማወቅ የሚያስችልሽን ማስተዋል እንዲሰጥሽ ለምኚው። እንደ ዳዊት እንዲህ ብለሽ መጸለይ ትችያለሽ:- “እግዚአብሔር ሆይ፤ መርምረኝ፤ ልቤንም ዕወቅ፤ ፈትነኝ፤ ሐሳቤንም ዕወቅ፤ የክፋት መንገድ በውስጤ ቢኖር እይ፤ በዘላለምም መንገድ ምራኝ።”—መዝሙር 139:23, 24

በሌላ በኩል ግን ከችግርሽ ለመላቀቅ ታመነቺ ይሆናል። ልክ እንደ ሱስ ሆኖብሽ ያለዚያ መኖር እንደማትችይ ሊሰማሽ ይችላል። ልትጸልዪበት የሚገባው ሌላው ጉዳይ ይህ ነው። ዳንየል እንዲህ ማድረግ ግድ ሆኖባት ነበር። “መጀመሪያ ላይ ከችግሬ ለመላቀቅ ፍላጎቱ አልነበረኝም። በመሆኑም ፍላጎቱ እንዲያድርብኝ መጸለይ ነበረብኝ” በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች።

በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ከወላጅሽ ወይም ሊረዳሽ ከሚችል ሰው ጋር ተነጋገሪ። የሚያስቡልሽ ሰዎች እንድትሸማቀቂ አያደርጉሽም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋን ለመምሰል ይጥራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “እርሱ የተጨነቀውን ሰው ጭንቀት፣ አልናቀም፤ ቸልም አላለምና፤ ፊቱንም ከእርሱ አልሰወረም፤ ነገር ግን ድረስልኝ ብሎ ሲጮኽ ሰማው።”—መዝሙር 22:24

ከዚህ ችግር ለመላቀቅ የሚደረገው ጥረት ቀላል እንዳልሆነ አይካድም። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ የባለሙያ እርዳታ ሊያስፈልግ ይችላል። * ትልቁ ቁም ነገር እርምጃ የመውሰዱ ጉዳይ ነው። የቡሊሚያ ችግር ያለባት አንዲት ወጣት ለማድረግ የወሰነችው ነገር ይኸው ነበር። “አንድ ቀን፣ በልቶ የማስመለስ ልማድ እንደተጠናወተኝ ተገነዘብኩ። ይሁን እንጂ ይህን ልማድ ማቆም እንደምችል እርግጠኛ አልነበርኩም። መጨረሻ ላይ፣ አድርጌው የማላውቀውን አንድ ከባድ ነገር አደረግሁ፤ ይኸውም እርዳታ ጠየቅሁ።”

አንቺም እንዲህ ማድረግ ትችያለሽ!

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “የወጣቶች ጥያቄ . . .” የሚሉትን ተከታታይ ርዕሶች ማግኘት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.6 አብዛኛውን ጊዜ ሥር የሰደደ የአመጋገብ ችግር የሚያጋጥማቸው ሴቶች በመሆናቸው በዚህ ርዕስ ውስጥ የምንጠቀመው በአንስታይ ፆታ ነው። ይሁን እንጂ የሚብራሩት አብዛኞቹ መሠረታዊ ሐሳቦች ለወንዶችም ይሠራሉ።

^ አን.32 ስትጨነቂ በሚከተሉት ጥቅሶች ላይ ካሰላሰልሽ የይሖዋን እንክብካቤ እንደምታገኚ እርግጠኛ መሆን ትችያለሽ:- ዘፀአት 3:7፤ መዝሙር 9:9፤ 34:18፤ 51:17፤ 55:22፤ ኢሳይያስ 57:15፤ 2 ቆሮንቶስ 4:7፤ ፊልጵስዩስ 4:6, 7፤ 1 ጴጥሮስ 5:7፤ 1 ዮሐንስ 5:14

^ አን.35 ክርስቲያኖች የሚወስዱት ማንኛውም ዓይነት ሕክምና ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የማይጋጭ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

▪ ሥር የሰደደ የአመጋገብ ችግር እንዳለብሽ ይሰማሻል? ከሆነ፣ እርዳታ ለማግኘት ወደ ማን መሄድ ትችያለሽ?

▪ ጓደኛሽ ሥር የሰደደ የአመጋገብ ችግር ካለባት እንዴት ልትረጃት ትችያለሽ?

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“ችግር ያለብሽ ይመስለኛል”

አንድ የቤተሰብሽ አባል ወይም ጓደኛሽ እንዲህ ቢልሽ ችግር እንዳለብሽ ላለመቀበል የሚታገልሽን ስሜት ለማሸነፍ ጥረት አድርጊ። አንዲት ጓደኛሽ ከኋላሽ የቀሚስሽ ዝምዝማት እየተፈታ እንደሆነ አስተዋለች እንበል። ሙሉ በሙሉ ከመልቀቁ በፊት ብትነግርሽ አታመሰግኛትም? መጽሐፍ ቅዱስ “ከወንድም አብልጦ የሚቀርብ ጓደኛም አለ” ይላል። (ምሳሌ 18:24) አንድ ሰው ችግርሽ አሳስቦት ወደ አንቺ ቢመጣ በእርግጥም የቅርብ ጓደኛሽ መሆኑን እያስመሠከረ ነው!

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

‘መቅጠን እፈልግ ነበር’

“ክብደት መቀነስ ጀመርኩ። የመንጋጋ ጥርሴን ሳስነቅል ደግሞ ምግብ መብላት አቃተኝ። በዚህም ምክንያት አኖሬክሲያ ጀመረኝ። ስለ መልክና ቁመናዬ በጣም እጨነቅ ጀመር። የፈለግሁትን ያህል መቅጠን እንዳልቻልኩ ይሰማኝ ነበር። በጣም የከሳሁ ጊዜ የነበረኝ ክብደት አስደንጋጭ ነበር። ሰውነቴን በጣም ጎዳሁት! አሁን ጥፍሮቼን ማሳደግ አልችልም። በሰውነቴ ውስጥ ያለውን የተፈጥሮ ሥርዓት (internal clock) አዛብቼዋለሁ። አራት ጊዜ ያስወረደኝ ሲሆን ያለ ዕድሜዬ የወር አበባዬ ቆመ። የሰውነቴ የምግብ መፈጨትና መዋሃድ ሂደት ጨርሶ ቆሟል ለማለት ይቻላል። በተጨማሪም የአንጀት ችግር አለብኝ። ይህ ሁሉ የሆነው መቅጠን እፈልግ ስለነበረ ነው።”—ኒኮል

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ችግሩ ካገረሸብሽ

የገጠመሽን ሥር የሰደደ የአመጋገብ ችግር አሸንፈሽውም እንኳ ከተወሰኑ ሳምንታት ወይም ወራት በኋላ እንደገና ያገረሽብሽ ይሆናል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ከገጠመሽ ተስፋ አትቁረጪ። መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቅ ሰባት ጊዜ እንኳ ቢወድቅ ይነሣል” የሚል ማረጋገጫ ይሰጣል። (ምሳሌ 24:16) ችግሩን ለማሸነፍ በምታደርጊው ጥረት እንቅፋት አጋጠመሽ ማለት ከዚያ በኋላ ማሸነፍ አትችይም ማለት አይደለም። እንዲያውም ይህ ቁርጥ ውሳኔሽን ማጠናከር፣ ችግሩ ሊያገረሽ እንደሚችል የሚጠቁሙ ምልክቶችን ለይተሽ ማወቅና ሊረዱሽ የሚችሉ ሰዎችን ምክር መጠየቅ እንዳለብሽ የሚያሳይ ማስጠንቀቂያ ነው።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ስለ ጉዳዩ በደንብ አንብቢ

ሥር በሰደደ የአመጋገብ ችግር የምትሠቃዪ ከሆነ ጉዳዩን በተመለከተ በደንብ ብታነቢ ጥሩ ይሆናል። ስለ ችግሩ በደንብ ባወቅሽ መጠን ለማሸነፍ ይበልጥ ቀላል ይሆንልሻል። የጥር 22, 1999 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ ከ3-12 እንዲሁም የሚያዝያ 22, 1999 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ ከ13-15 ላይ የሚገኙትን መረጃዎች ብትመረምሪ ጥቅም እንደምታገኚ እሙን ነው።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ለወላጆች የተሰጠ ማሳሰቢያ

ልጃችሁ ሥር የሰደደ የአመጋገብ ችግር ካለባት ምን ማድረግ ትችላላችሁ? በመጀመሪያ በዚህ ርዕስ ውስጥም ሆነ በገጽ 20 ላይ በተገለጹት ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙትን ሐሳቦች በጥንቃቄ መርምሩ። ልጃችሁ ለዚህ ችግር የተጋለጠችው ለምን እንደሆነ ለመረዳት ጥረት አድርጉ።

ሥር የሰደደ የአመጋገብ ችግር ያለባቸው ብዙ ሰዎች ለራሳቸው ዝቅተኛ አመለካከት ያላቸው ከመሆኑም በላይ ከራሳቸው ፍጽምናን ወይም ምክንያታዊ ያልሆኑ ነገሮችን የመጠበቅ ዝንባሌ እንዳላቸው ተስተውሏል። ልጃችሁ እንዲህ ያለ ባሕርይ እንዲኖራት አስተዋጽኦ እንዳታበረክቱ ጥንቃቄ አድርጉ። ልጃችሁ በራሷ እንድትተማመን አበረታቷት። (ኢሳይያስ 50:4) እንዲሁም ፍጽምናን የመጠበቅ ዝንባሌን መዋጋት እንድትችሉ ‘ምክንያታዊነታችሁ በሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን።’—ፊልጵስዩስ 4:5 NW

ከዚህም በላይ እናንተ ራሳችሁ ለምግብና ለውፍረት ያላችሁን አመለካከት በሚገባ መርምሩ። ሳይታወቃችሁ እነዚህን ነገሮች በቃልም ሆነ በድርጊት የማጋነን ዝንባሌ አላችሁ? ወጣቶች ከልክ በላይ ስለ ቁመናቸው እንደሚጨነቁ አትዘንጉ። ልጃችሁ ስትወፍር ወይም ፈጣን አካላዊ እድገት ስታደርግ የምታሾፉባት ከሆነ በአእምሮዋ ውስጥ መጥፎ ሐሳብ ሊቀረጽ ይችላል።

በጉዳዩ ላይ በደንብ ካሰባችሁበት በኋላ ከልጃችሁ ጋር በግልጽ ተነጋገሩ።

ምንና መቼ እንደምትናገሩ አስቀድማችሁ ወስኑ።

▪ ያሳሰባችሁ ጉዳይ ምን እንደሆነና እርሷን ለመርዳት ያላችሁን ፍላጎት በግልጽ ንገሯት።

▪ መጀመሪያ ላይ ችግር የለብኝም ብላ ብትከራከር አትደነቁ።

▪ በትዕግሥት አዳምጧት።

ከሁሉም በላይ ልጃችሁ ችግሯን ለማሸነፍ በምታደርገው ጥረት ተባበሯት። ችግሯን እንደ ቤተሰቡ ችግር አድርጋችሁ በመቁጠር ከሕመሟ እንድታገግም ጥረት አድርጉ!

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከችግርሽ የመላቀቅ ፍላጎት እንዲያድርብሽ መጸለይ ትችያለሽ