በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ስውር አስተማሪ” የሆነው ቴሌቪዥን

“ስውር አስተማሪ” የሆነው ቴሌቪዥን

“ስውር አስተማሪ” የሆነው ቴሌቪዥን

ቴሌቪዥን ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድር አስተማሪ ሊሆን ይችላል። ያሉበት ቦታ ድረስ ሄደን ልንጎበኛቸው የማንችላቸውን አገሮችና ሕዝቦች ያሳየናል። በቴሌቪዥን አማካኝነት፣ በሐሩራማ አካባቢዎች ወደሚገኙ ደኖችና በምድር ዋልታዎች ላይ ወደሚገኙት ግግር በረዶ ያለባቸው ቦታዎች እንዲሁም ወደ ታላላቅ ተራራዎችና ጥልቅ ውቅያኖሶች “መጓዝ” እንችላለን። አስደናቂ የሆኑትን አቶሞችም ሆነ የከዋክብትን ዓለም እናይበታለን። በሌላው የምድር ክፍል እየተከናወኑ ያሉትን ነገሮች በዚያው ሰዓት በዜና እንመለከታቸዋለን። ስለ ፖለቲካ፣ ስለ ታሪክ፣ ስለ ወቅታዊ ጉዳዮችና ስለ ባሕል በጥልቀት ማወቅ እንችላለን። ቴሌቪዥን ሰዎች የሚያጋጥማቸውን አሳዛኝም ሆነ አስደሳች ሁኔታ ቀርጾ ያቀርብልናል። ያዝናናል፣ ትምህርት ይሰጣል አልፎ ተርፎም መንፈስን ያነቃቃል።

ይሁን እንጂ በቴሌቪዥን የሚቀርበው አብዛኛው ፕሮግራም ጤናማና ትምህርት ሰጪ አይደለም። ምናልባትም በቴሌቪዥን ላይ ኃይለኛ ትችት የሚሰነዝሩት ዓመጽና ወሲብ በብዛትና በይፋ መቅረቡን አጥብቀው የሚቃወሙት ወገኖች ሳይሆኑ አይቀሩም። በዩናይትድ ስቴትስ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከሦስት የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ውስጥ ሁለቱ የዓመጽ ትዕይንቶችን የሚያሳዩ ሲሆኑ ይህም በአማካይ በአንድ ሰዓት ውስጥ ስድስት የዓመጽ ትዕይንቶች ይተላለፋሉ ማለት ነው። አንድ ወጣት ለአካለ መጠን እስኪደርስ ድረስ በሺህ የሚቆጠሩ የዓመጽና የግድያ ድርጊቶች በቴሌቪዥን ሲቀርቡ ይመለከታል። ወሲባዊ ይዘት ያለው ፕሮግራምም እንደዚሁ በብዛት ይቀርባል። በአጠቃላይ በቴሌቪዥን ከሚተላለፉት ፕሮግራሞች ውስጥ ሁለት ሦስተኛ በሚሆኑት ላይ ስለ ወሲብ የሚወራ ሲሆን 35 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያለው ድርጊት ምንም አደጋ እንደማያስከትል፣ በአጋጣሚ ካገኙት ሰው ጋር እና ባልተጋቡ ጥንዶች መካከል ሊፈጸም እንደሚችል አድርገው ያቀርቡታል። *

ወሲብንና ዓመጽን የሚያሳዩ ፕሮግራሞች በመላው ዓለም ከፍተኛ ተፈላጊነት አላቸው። በአሜሪካ የሚዘጋጁ እንዲህ ያሉ ፊልሞች የኋላ ኋላ በቴሌቪዥን ሲተላለፉ በቀላሉ ወደ ውጭ ገበያዎች ይሸጋገራሉ። እንደዚህ ያሉት ፊልሞች ጥሩ ትወና ወይም በደንብ የተዘጋጁ የድራማ ጽሑፎች አያስፈልጓቸውም። የተመልካቹን ቀልብ ለመሳብ ድብድብ፣ ግድያና ወሲብ የሚያቀርቡ ሲሆን ልዩ ቅንብሮችንም ይጠቀማሉ። ይሁን እንጂ ረዘም ላለ ጊዜ የሰዎችን ትኩረት ማርኮ ለማቆየት ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋል። ተመልካቾች አንድን ነገር ደጋግሞ ማየት ቶሎ ስለሚሰለቻቸው ስሜት ቀስቃሽ የነበረው ትዕይንት ብዙም ሳይቆይ እንደ ተራ ይቆጠራል። ስለዚህ አዘጋጆቹ የተመልካችን ስሜት ይዘው ለማቆየት ሲሉ በዓመጽ የተሞላ፣ ወሲባዊ ድርጊት የበዛበትና በግልጽ የሚታይበት እንዲሁም በሌሎች ላይ በሚደርሰው ሥቃይ ደስታ የሚገኝበት ፊልም በመሥራት በጣም ዘግናኝና ስሜት ቀስቃሽ ትዕይንቶችን ያቀርባሉ።

ቴሌቪዥን የሚያሳድረውን ተጽዕኖ በተመለከተ የተነሳው ውዝግብ

ተመልካቾች በቴሌቪዥን የሚቀርበውን ዓመጽና ወሲብ ሁልጊዜ መመልከታቸው ምን ተጽዕኖ ያሳድርባቸዋል? ተቺዎች በቴሌቪዥን የሚቀርብ ዓመጽ ሰዎች ጠበኞች እንዲሆኑና በገሃዱ ዓለም የዓመጽ ሰለባዎች ለሆኑ ሰዎች እንዳያዝኑ እንደሚያደርግ ሲናገሩ ይሰማል። በተጨማሪም ወሲብን ማሳየት ሴሰኝነትን እንደሚያበረታታና የሥነ ምግባር አቋምን እንደሚሸረሽር ይገልጻሉ።

ይሁን እንጂ ቴሌቪዥን መመልከት በእርግጥ ይህን ሁሉ ያስከትላል? ይህ ጥያቄ ለአሥርተ ዓመታት የጦፈ ክርክር ሲደረግበት የቆየ ሲሆን በጉዳዩ ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጥናቶች ተካሂደዋል፤ እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ መጻሕፍትና መጣጥፎች ቀርበውበታል። በውዝግቡ ላይ ከተነሱት ነጥቦች ዋነኛው ለችግሩ መንስኤ የሆነውን ነገር በእርግጠኝነት የማወቁ ጉዳይ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ገና በልጅነት በቴሌቪዥን የሚቀርበውን ዓመጽ መመልከት የኋላ ኋላ ጠበኛ እንደሚያደርግ ማረጋገጥ አልተቻለም። ቴሌቪዥን መመልከት ዓመጸኝነትን እንደሚያስፋፋ ማረጋገጡ አንዳንድ ጊዜ አስቸጋሪ ነው። በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ መድኃኒት ወሰድክ እንበል። በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ሰውነትህ ሽፍ አለ። እንዲህ ባለው ሁኔታ አለርጂ የሆነብህ መድኃኒቱ ነው ብሎ መደምደም ቀላል ነው። ይሁንና አንዳንድ ጊዜ አንድ ነገር አለርጂ የሚሆነው ቀስ በቀስ ነው። አለርጂ የሚያስከትሉ በርካታ ምክንያቶች ስላሉ በዚህ ጊዜ በሰውነትህ ላይ የተከሰተውን ለውጥ ያስከተለውን መድኃኒት መለየቱ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል።

በተመሳሳይም በቴሌቪዥን የሚቀርበው ዓመጽ ወንጀልንና ከማኅበረሰቡ ጋር የሚያጋጩ ባሕርያትን እንዳስከተለ ማረጋገጥ አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል። ብዙ ጥናቶች እነዚህ ነገሮች ተያያዥነት እንዳላቸው ያመለክታሉ። ከዚህም በላይ አንዳንድ ወንጀለኞች ዝንባሌያቸውና የዓመጸኝነት ባሕርያቸው በቴሌቪዥን ያዩትን ነገር የተከተለ እንደሆነ ተናግረዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ለብዙ ተጽዕኖዎች ይጋለጣሉ። ዓመጽ የሚካሄድባቸው የቪዲዮ ጨዋታዎች፣ ከጓደኞችና ከቤተሰብ የሚወረሱ ማኅበራዊ እሴቶች እንዲሁም አጠቃላዩ የኑሮ ሁኔታና የመሳሰሉት ነገሮች ሰዎች ጠበኞች እንዲሆኑ ሊያደርጉ ይችላሉ።

በዚህ ጉዳይ ላይ ተቃራኒ አመለካከቶች መኖራቸው እምብዛም አያስደንቅም። አንድ ካናዳዊ የሥነ አእምሮ ሊቅ “በሳይንስ የተገኘው ማስረጃ፣ ዓመጽ ሲፈጸም መመልከት ሰዎች ዓመጸኞች እንዲሆኑ እንደሚያደርግ ወይም ስሜታቸውን እንደሚያደነዝዘው አያሳይም” በማለት ጽፈዋል። ይሁን እንጂ አሜሪካን ሳይኮሎጂካል አሶሲዬሽን ኮሚቲ ኦን ሚድያ ኤንድ ሶሳይቲ እንዲህ ብሏል:- “በቴሌቪዥን የሚቀርቡ የዓመጽ ድርጊቶችን አዘውትረው የሚመለከቱ ሰዎች የጠበኝነት ባሕርይን በቸልታ የማየት ዝንባሌ እንደሚኖራቸውና ይበልጥ ጠበኛ እንደሚሆኑ ምንም አያጠራጥርም።”

ቴሌቪዥን በአመለካከትህ ላይ ስለሚያሳድረው ተጽዕኖ ማሰብ

ባለሙያዎቹ እየተከራከሩ ያሉት ማስረጃ ማቅረብ መቻል አለመቻሉን በተመለከተ መሆኑን አስታውስ። ይኸውም ዓመጽን መመልከት ጠበኛ ያደርጋል ወይስ አያደርግም የሚለውን ለማረጋገጥ ስለመቻሉ ነው። ይሁንና አብዛኞቹ ሰዎች ቴሌቪዥን በአስተሳሰባችንና በጠባያችን ላይ ምንም ተጽዕኖ የለውም ብለው አይከራከሩም። እስቲ አስበው:- አንድን ፎቶግራፍ ማየት ብቻ እንኳ እንድንናደድ፣ እንድናለቅስ ወይም እንድንደሰት ሊያደርገን ይችላል። ሙዚቃም በከፍተኛ ደረጃ ስሜታችንን ሊቀሰቅስ ይችላል። በወረቀት ላይ የታተሙ ቃላትም እንኳ ሳይቀሩ እንድናስብ፣ አንድ ነገር እንዲሰማንና እርምጃ እንድንወስድ ያደርጋሉ። ታዲያ የሚንቀሳቀሱ ምስሎች፣ ሙዚቃና ቃላት አንድ ላይ በብልሃት ተቀናብረው ሲቀርቡ እንዴት ያለ ኃይል ይኖራቸው! እንግዲያው ቴሌቪዥን መስህብ ያለው መሆኑ አያስደንቅም! ደግሞም በብዙ ቦታዎች የሚገኝ ነው። አንድ ጸሐፊ “የሰው ልጅ ሐሳቡን በጽሑፍ ማስፈር ከቻለበት ጊዜ አንስቶ ሐሳብ ለማስተላለፍ ከተጠቀመባቸው ዘዴዎች ውስጥ [የቴሌቪዥንን ያህል] በሥልጣኔ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረ አዲስ ዘዴ የለም” ብለዋል።

የንግድ ድርጅቶች፣ ተመልካቾች የሚያዩትና የሚሰሙት ነገር ተጽዕኖ እንደሚያደርግባቸው ስለሚያውቁ ሸቀጣቸውን ለማስተዋወቅ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያወጣሉ። ማስታወቂያ ለማሠራት ይህን ያህል ገንዘብ የሚያወጡት ውጤታማ ሊሆን ይችላል ብለው ስለሚያስቡ አይደለም። ማስታወቂያው ለውጥ እንደሚያመጣ ስለሚያውቁ ነው። ማስታወቂያው ምርታቸውን ያሸጥላቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በ2004 የኮካ ኮላ ኩባንያ ምርቶቹን በመላው ዓለም በጽሑፍ፣ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ለማስተዋወቅ 2.2 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር አውጥቷል። ታዲያ ለማስታወቂያ የዋለው ገንዘብ ጥቅም ነበረው? ኩባንያው በዚያ ዓመት ወደ 22 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ትርፍ አግኝቷል። ማስታወቂያ የሚሠሩ ሰዎች አንድ ነጠላ ማስታወቂያ ብቻውን በሰዎች ባሕርይ ላይ ለውጥ እንደማያመጣ ይገነዘባሉ። ከዚህ ይልቅ ተደጋግሞ የሚነገር ማስታወቂያ በጊዜ ሂደት በሰዎች አመለካከት ላይ ተጽዕኖ የማሳደር ኃይል እንዳለው ስለሚያውቁ ይህን መሠረት በማድረግ ሥራቸውን ያከናውናሉ።

የ30 ሴኮንድ ማስታወቂያ በዝንባሌያችንና በባሕርያችን ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ከሆነ ለሰዓታት ቴሌቪዥን መመልከትም ሊነካን እንደሚችል እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ቴሌቪዥን—አን ኢንተርናሽናል ሂስትሪ የተሰኘው መጽሐፍ ደራሲ “ቴሌቪዥን ነጋ ጠባ በሚቀርቡት ወይም አነስተኛ በሆኑ መዝናኛዎቹ አማካኝነት ስውር አስተማሪ ሆኖ ያገለግላል” ብለዋል። ኤ ፒክቶሪያል ሂስትሪ ኦቭ ቴሌቪዥን የተሰኘው መጽሐፍም “ቴሌቪዥን አስተሳሰባችንን እየለወጠው ነው” ብሏል። እንግዲያስ ራሳችንን ‘የማየው ነገር በአስተሳሰቤ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው በምፈልገው መንገድ ነው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል።

በተለይ አምላክን ለሚያገለግሉ ሰዎች ይህ ጥያቄ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው። በቴሌቪዥን የሚቀርበው አብዛኛው ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምራቸው የላቁ መሠረታዊ ሥርዓቶችና የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር የሚቃረን ነው። ቅዱሳን ጽሑፎች የሚያወግዟቸው የአኗኗር ዘይቤዎችና ድርጊቶች ተቀባይነት እንዳላቸው፣ እንደተለመዱና የወቅቱን ፋሽን የተከተሉ እንደሆኑ ተደርገው ይቀርባሉ። እግረ መንገዱንም ክርስቲያናዊ እሴቶችና በእነዚህ እሴቶች እንደሚመሩ ሆነው የቀረቡት ሰዎች ብዙውን ጊዜ በቴሌቪዥን ችላ ሲባሉ፣ ሲሾፍባቸው ወይም መሣቂያ ሲሆኑ ይታያል። አንድ ደራሲ “መጥፎ የሆነው ባሕርይ ተቀባይነት እንዳለው ተደርጎ መቆጠሩ ሳያንስ ተቀባይነት ያለው ባሕርይ መጥፎ እንደሆነ ተደርጎ ይቀርባል” በማለት በምሬት ተናግረዋል። ብዙ ጊዜ እንደሚታየው ‘ስውር የሆነው አስተማሪ’ “ክፉን መልካም፣ መልካሙን ክፉ” እንደሆነ የሚያስመስል ሐሳብ ያስተላልፋል።—ኢሳይያስ 5:20

እንግዲያውስ የምንመለከተው ነገር በአስተሳሰባችን ላይ ተጽዕኖ ስለሚያሳድር ስለምናየው ነገር ጠንቃቆች መሆን አለብን። መጽሐፍ ቅዱስ “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጕዳት ያገኘዋል” ይላል። (ምሳሌ 13:20) አዳም ክላርክ የተባሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንደሚከተለው በማለት ተናግረዋል:- “ከአንድ ሰው ጋር መሄድ ፍቅርና ቅርበትን የሚያመለክት ሲሆን የምንወዳቸውን ሰዎች አለመምሰል ደግሞ የማይቻል ነገር ነው። ‘ጓደኛህን ንገረኝና ማንነትህን እነግርሃለሁ’ የሚባለውም ለዚህ ነው። የአንድን ሰው ጓደኞች ካወቅን፣ ግለሰቡ ምን ዓይነት ሥነ ምግባር እንዳለው በቀላሉ መገመት ይቻላል።” ከላይ እንደተመለከትነው አብዛኞቹ ሰዎች ጠቢብ ካልሆኑ የቴሌቪዥን ተዋንያን ጋር በጣም ሰፊ ጊዜ ያሳልፋሉ፤ አንድ ቅን ክርስቲያን ግን እነዚህን ተዋንያን ፈጽሞ ቤቱ ሊጋብዛቸው አያስብም።

ሐኪም አንድ ኃይለኛ መድኃኒት ቢያዝልህ ይህን መድኃኒት መውሰድ ያለውን ጥቅምና ጉዳት በጥንቃቄ ማመዛዘንህ አይቀርም። ትክክለኛ ያልሆነ መድኃኒት መውሰድ አሊያም ትክክለኛ የሆነውን መድኃኒትም እንኳ ከተገቢው መጠን በላይ መውሰድ ጤንነትህን ሊጎዳው ይችላል። ቴሌቪዥን በመመልከት ረገድም ቢሆን ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። እንግዲያስ ስለምንመለከተው ነገር በጥሞና ማሰባችን ጥበብ ነው።

ሐዋርያው ጳውሎስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት በጻፈው ደብዳቤ ላይ ክርስቲያኖች እውነት የሆነውን፣ ክቡር የሆነውን፣ ትክክል የሆነውን፣ ንጹሕ የሆነውን፣ ተወዳጅ የሆነውን፣ መልካም የሆነውን፣ በጎ የሆነውንና ምስጋና ያለበትን ነገር እንዲያስቡ አበረታቷቸዋል። (ፊልጵስዩስ 4:6-8) ይህን ምክር ተግባራዊ ታደርጋለህ? የምታደርግ ከሆነ ደስተኛ ትሆናለህ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 የአሜሪካ ቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና ፊልሞች በመላው ዓለም ስለሚሠራጩ በዩናይትድ ስቴትስ የቀረቡት አኃዛዊ መረጃዎች በሌሎች አገሮች ካሉት ጋር ተመሳሳይ ናቸው።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ቴሌቪዥን ሳሎንህ ውስጥ ቁጭ ብለህ፣ ቤትህ ልትጋብዛቸው በማትፈልጋቸው ሰዎች እንድትዝናና የሚያስችልህ የፈጠራ ውጤት ነው።”—ዴቪድ ፍሮስት፣ ብሪታንያዊ ዜና አቅራቢ

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የጾታ ግንኙነትንና ዓመጽን አስመልክቶ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው ሐሳብ በቴሌቪዥን ከሚታየው በምን ይለያል?

በቴሌቪዥን በሚታየውና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው ስለ ዓመጽና ስለ ጾታ ግንኙነት የሚገልጽ ሐሳብ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ እነዚህ ድርጊቶች የተገለጸው ለማስተማር እንጂ ለማዝናናት ታስቦ አይደለም። (ሮሜ 15:4) የአምላክ ቃል ታሪካዊ ክንውኖችን በጽሑፍ አስፍሮልናል። ይህ የታሪክ መዝገብ አምላክ ለነገሮች ያለውን አመለካከት እንድንረዳና ከሌሎች ስህተት እንድንማር ይረዳናል።

በቴሌቪዥን ማስታወቂያ በሚቀርብባቸው በአብዛኞቹ አገሮች የወሲብና የዓመጽ ድርጊቶች የሚተላለፉት ለማስተማር ተብሎ ሳይሆን ለገንዘብ ማግኛ ነው። ማስታወቂያ አቅራቢዎች በተቻለ መጠን ብዙ ሰው ለመሳብ የሚፈልጉ ሲሆን ከወሲብና ከዓመጽ ጋር የተያያዙ ነገሮች ደግሞ የተመልካቾችን ትኩረት ይስባሉ። ይህም ማስታወቂያዎቹን እንዲመለከቱና በማስታወቂያው ላይ ያዩትን ነገር እንዲገዙ ያደርጋቸዋል። ዜና አንባቢዎች “አሰቃቂ የሆነ ታሪክ ርዕሰ ዜና ነው” የሚለውን ሥርዓት ይከተላሉ። በአጠቃላይ ሲታይ ስለ ወንጀል፣ ስለ አደጋና ስለ ጦርነት የሚዘግቡ ዘግናኝ ታሪኮች እምብዛም ከማይመስጡ ዜናዎች የበለጠ ተመራጭነት አላቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዓመጽ የሚዘግቡ ታሪኮችን ቢይዝም ሰዎች ሰላማዊ ሕይወት እንዲኖሩ ይኸውም በቀልን እንዳይሹና ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ያበረታታል። መጽሐፉ ከጾታ ግንኙነት ጋር በተያያዘ መልካም ሥነ ምግባርን በማበረታታት ረገድ የማይለዋወጥ አቋም አለው። በተቃራኒው በቴሌቪዥን ከሚተላለፈው መልእክት መካከል አብዛኛው ሰላምንና መልካም ሥነ ምግባርን አያበረታታም።—ኢሳይያስ 2:2-4፤ 1 ቆሮንቶስ 13:4-8፤ ኤፌሶን 4:32

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ቴሌቪዥንና ትንንሽ ልጆች

“በሳይንስና በሕዝብ ጤና እንክብካቤ መስኮች የተሠማሩ ሰዎች ለብዙ አሥርተ ዓመታት የተደረጉትን ጥናቶች መሠረት በማድረግ የደረሱበት መደምደሚያ ዓመጽ የሚንጸባረቅባቸውን [የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች] መመልከት በልጆች ላይ ጎጂ ውጤት እንዳለው ያሳያል።” —ዘ ሄንሪ ጆን ኬይሰር ፋምሊ ፋውንዴሽን

“የአሜሪካው የሕፃናት ጤና አካዳሚ ‘ሁለት ዓመትና ዕድሜያቸው ከዚያ በታች የሆኑ ሕፃናት [ቴሌቪዥን ማየት] እንደሌለባቸው’ በሰጠው ሐሳብ [እንስማማለን።] አንጎላቸው ከፍተኛ እድገት በሚያደርግበት ወቅት ላይ የሚገኙት እነዚህ ሕፃናት እድገታቸው እንዲፋጠንና አካላዊም ሆነ ማኅበራዊ ክህሎታቸው እንዲዳብር እነሱም የሚሳተፉበት ዓይነት ጨዋታ ያስፈልጋቸዋል፤ እንዲሁም በገሃዱ ዓለም ካሉ ሰዎች ጋር መቀላቀል ይኖርባቸዋል።”— ዘ ናሽናል ኢንስቲትዩት ኦን ሚድያ ኤንድ ዘ ፋምሊ

[በገጽ 6, 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቴሌቪዥን የማየው ነገር አስተሳሰቤን እየለወጠው ያለው በምፈልገው መንገድ ነው?