በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታወር ብሪጅ—የለንደን ከተማ መግቢያ

ታወር ብሪጅ—የለንደን ከተማ መግቢያ

ታወር ብሪጅ—የለንደን ከተማ መግቢያ

ብሪታንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ዚህ ቀደም ወደ እንግሊዝ የመሄድ ዕድሉ ያልነበራቸው የውጭ አገር ዜጎች እንኳ በቀላሉ ሊለዩት ይችላሉ። በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ይጎበኙታል። የለንደን ነዋሪዎች ልብ ብለው ሳይመለከቱት ወይም ስለ አሠራሩ ሳያስቡ በየዕለቱ ይመላለሱበታል። ታወር ብሪጅ የተባለው ይህ ድልድይ ለንደን ውስጥ ከሚገኙ እጅግ ታዋቂ ቦታዎች መካከል አንዱ ነው።

ከለንደን ታወር ጋር ተመሳሳይነት ያለው ታወር ብሪጅ በአቅራቢያው ካለው ከለንደን ብሪጅ የተለየ ነው። በ1872 የእንግሊዝ ፓርላማ፣ የቴምዝን ወንዝ ለማቋረጥ የሚያገለግል ሌላ ድልድይ የመሥራት ሐሳብ ቀረበለት። በዚህ ጊዜ የለንደኑ ታወር ገዥ ሐሳቡን ቢቃወሙም፣ ፓርላማው ከለንደን ታወር ንድፍ ጋር ተመሳሳይ እስከሆነ ድረስ ድልድዩን ለመገንባት የቀረበለትን ሐሳብ ለማጽደቅ ወሰነ። በዘመናችን ያለው ታወር ብሪጅ የተሠራው ከዚህ ዕቅድ በመነሳት ነው።

በ18ኛውና በ19ኛው ክፍለ ዘመን የቴምዝን ወንዝ ለማቋረጥ የሚያገለግሉ በርካታ ድልድዮች የተሠሩ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ እጅግ ዝነኛ የሆነው ጥንታዊው የለንደን ብሪጅ ወይም ድልድይ ይገኝበታል። በ1750 ይህ ድልድይ በጣም ከማርጀቱም በላይ ጠባብ በመሆኑ የትራፊክ መጨናነቅ ያስከትል ነበር። ከተለያዩ የምድር ክፍሎች የመጡ መርከቦች ከድልድዩ ሥር በሚገኘው የተጨናነቀ ወደብ ላይ ቦታ ለማግኘት ይጋፉ ነበር። በዚያን ጊዜ በወደቡ ላይ በርካታ መርከቦች ተጠጋግተው ይቆሙ ስለነበር አንድ ሰው ከአንዱ መርከብ ወደ ሌላው እየተሸጋገረ ከመርከቦቹ ላይ ሳይወርድ በርካታ ኪሎ ሜትሮች መጓዝ ይችል እንደነበር ይነገራል።

የከተሞች ንድፍ አውጪ የሆነው ሆረስ ጆንስ፣ የለንደን ከተማ አስተዳደር ያቀረበውን ጥያቄ መሠረት በማድረግ ከለንደን ብሪጅ በላይ ወደ ወንዙ መነሻ ቀረብ ብሎ የጎቲክ-ስታይል ያለው (በመካከለኛው ዘመን ይዘወተሩ የነበሩትን ንድፎች የተከተለ) ተካፋች ድልድይ ለመሥራት ሐሳብ አቀረበ። በቴምዝ ወንዝ ላይ በምዕራብ አቅጣጫ ወደ ወደቦቹ የሚያቀኑት መርከቦች በዚህ ድልድይ ሥር ሊያልፉ ይችላሉ። ይህ ንድፍ ብዙዎች አዲስ የፈጠራ ውጤት እንደሆነ የሚናገሩለት ልዩ ገጽታ አለው። 

ለየት ያለ ንድፍ

ጆንስ በብዙ ቦታዎች የተዘዋወረ ሲሆን በኔዘርላንድ ቦዮች ላይ የተመለከታቸው ትንንሽ ተካፋች ድልድዮች፣ መሃል ለመሃል ተከፍለው ወደ ላይ ሊነሱ የሚችሉ ሁለት ተካፋቾች ያሉት ድልድይ ለመሥራት እንዲያስብ አደረጉት። ዘመናዊ ንድፍ በመጠቀም በብረት ፍሬሞች ከተገነባ በኋላ በኮንክሪት የተሸፈነው ዝነኛው ታወር ብሪጅ የተሠራው የጆንስ የሥራ ባልደረቦች ባዘጋጁት ንድፍ መሠረት ነው።

ታወር ብሪጅ ሁለት ትላልቅ ማማዎች ያሉት ሲሆን ከመኪና መንገዱ 34 ሜትር፣ ወንዙ በጣም ሲሞላ ከሚደርስበት አማካይ ከፍታ ደግሞ 42 ሜትር ያህል ከፍ ብሎ የሚገኝ የእግረኛ መንገድ እነዚህን ማማዎች ያገናኛቸዋል። የመኪና መንገዱ ከመሃል ላይ ተከፍሎ ሁለቱ ተካፋቾች ወደ ላይ ይነሳሉ። እነዚህ ግዙፍ የሆኑ ተካፋቾች እያንዳንዳቸው 1,219,256 ኪሎ ግራም ገደማ የሚመዝኑ ሲሆን በ86 ዲግሪ ቅስት ወደ ላይ ቀጥ ብለው መቆም ይችላሉ። በድልድዩ ሥር እስከ 10,000 ቶን የሚደርስ መጠን ያላቸው መርከቦች ያላንዳች ችግር ማለፍ ይችላሉ።

የድልድዩ ተካፋቾች ወደ ላይ እንዲነሱ የሚያደርጋቸው ኃይል

የድልድዩ ተካፋቾች ወደ ላይ የሚነሱት፣ የእግረኞች አሳንሰር ከመኪና መንገዱ ወደ እግረኞች መንገድ ሽቅብ የሚወጣውም ሆነ ድልድዩ ሊከፈት መሆኑን የሚጠቁሙት የማስጠንቀቂያ ምልክቶች የሚሠሩት በሃይድሮሊክ ኃይል ነበር። አዎን፣ ድልድዩ የሚንቀሳቀሰው በውኃ ኃይል ነበር! ያም ሆኖ ከሚፈለገው በሁለት እጥፍ የሚበልጥ ኃይል ማግኘት ይቻል ነበር።

በድልድዩ በስተ ደቡብ ጫፍ ላይ በከሰል የሚሠሩ አራት ማሞቂያዎች ያሉ ሲሆን እነርሱም በእያንዳንዱ ካሬ ሴንቲ ሜትር ከ5 እስከ 6 ኪሎ ግራም በሚሆን ግፊት እንፋሎት በማመንጨት ሁለት ግዙፍ ፓምፖችን ያንቀሳቅሳሉ። ፓምፖቹ ደግሞ በተራቸው በእያንዳንዱ ካሬ ሴንቲ ሜትር 60 ኪሎ ግራም በሚሆን ግፊት ውኃ ይስባሉ። ከዚያም የድልድዩ ተካፋቾች እንዲንቀሳቀሱ የሚያደርገው ኃይለኛ ግፊት ያለው ውኃ በስድስት ትላልቅ ማጠራቀሚያዎች ውስጥ ይከማቻል። ይህ ደግሞ ተካፋቾቹን ለሚያንቀሳቅሱት ስምንት ሞተሮች ኃይል ይሰጣቸዋል። አንዴ ሞተሮቹ እንዲንቀሳቀሱ ከተደረገ የድልድዩ ሁለት ተካፋቾች 50 ሴንቲ ሜትር ስፋት ባላቸው ደጋፊ ቋሚዎች ላይ ሽቅብ ይነሳሉ። የድልድዩ ተካፋቾች ሙሉ በሙሉ ወደ ላይ ተነስተው ለመቆም የሚፈጅባቸው ጊዜ አንድ ደቂቃ ብቻ ነው።

ዘመናዊውን ታወር ብሪጅ መጎብኘት

በአሁኑ ወቅት በእንፋሎት የሚገኘው ኃይል በኤሌክትሪክ ኃይል ተተክቷል። ሆኖም ልክ እንደ ጥንቱ አሁንም ታወር ብሪጅ ወደ ላይ ሲነሳ መኪኖችም ሆኑ በድልድዩ ላይ የሚደረገው ማንኛውም እንቅስቃሴ ለጊዜው ይቆማል። እግረኞች፣ ጎብኚዎችና ሌሎችም በድልድዩ እንቅስቃሴ እጅግ ይደነቃሉ።

ድልድዩ ሊከፈት ሲል የማስጠንቀቂያ ድምጽ መሰማት ይጀምራል፣ የመኪና መንገዶች በኬላ ይዘጋሉ፣ ኬላው ከመዘጋቱ በፊት ካለፉት መኪኖች የመጨረሻው ከሄደ በኋላ በድልድዩ ላይ ያሉት መቆጣጠሪያዎች ድልድዩ ነጻ መሆኑን ይጠቁማሉ። ከዚያም የድልድዩ ተካፋቾች የተቆላለፉባቸው ብረቶች ያላንዳች ድምጽ ይላቀቁና ተካፋቾቹ ወደ ላይ መነሳት ይጀምራሉ። በዚህ ጊዜ የሁሉም ሰው ትኩረት ወደ ወንዙ ይሆናል። በድልድዩ ሥር የሚያልፈው ጎታች ጀልባም ይሁን ለመዝናኛ የሚያገለግል የሞተር ጀልባ አሊያም ማንኛውም መርከብ የሁሉም ዓይን በመተላለፊያው ላይ ይተከላል። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ የማስጠንቀቂያው ምልክት ይቀየራል። ወደ ላይ የተዘረጉት ተካፋቾች ሲወርዱ መኪና መንገዱን የዘጉት ኬላዎች ደግሞ ወደ ላይ ይነሳሉ። ብስክሌተኞች ተራቸውን ከሚጠባበቁት መኪኖች ቀደም ብለው ድልድዩን በፍጥነት ያቋርጣሉ። ከጥቂት ሴኮንዶች በኋላ ታወር ብሪጅ ሌላ የማስጠንቀቂያ ደወል እስኪሰማ ድረስ ወደ ወትሮው እንቅስቃሴ ይመለሳል።

ተጨማሪ ነገር መመልከት የፈለገ አንድ ጎብኚ እንዲህ ካለው ተደጋጋሚ እንቅስቃሴ ባሻገር ሌሎች ነገሮችንም ማየት ይችላል። በስተ ሰሜን ወደሚገኘው ማማ በመሄድ ከሌሎች ሰዎች ጋር ሆኖ በአሳንሰር በመውጣት በተንቀሳቃሽ ሞዴል የታጀበውንና ስለ ድልድዩ ታሪክ ዝርዝር መረጃዎችን የያዘውን “ታወር ብሪጅ ኤክስፒሪያንስ” የተሰኘ ኤግዚቢሽን መመልከት ይችላል። በዚህ ኤግዚቢሽን ውስጥ የድልድዩን ድንቅ የምህንድስና ሥራና በደመቀ ሁኔታ የተካሄደውን የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት የሚያሳዩ በሸራ ላይ የተሠሩ ሥዕሎች ይገኛሉ። ከዚህም በተጨማሪ የድሮ ፎቶግራፎችና ሌሎች መረጃዎችን የያዙት ሰሌዳዎች የታወር ብሪጅን አስደናቂ አሠራር ያሳያሉ።

ከፍ ብሎ የሚገኘው የእግረኛ መንገድ፣ ጎብኚዎች የለንደንን ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች እንዲያዩ ምቹ አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል። በምዕራብ በኩል የሴንት ፖልን ካቴድራል፣ የባንክ ሕንጻዎችንና ከርቀት ደግሞ ፖስታ ቤቱን ማየት ይቻላል። አንድ ሰው በስተ ምሥራቅ በኩል የመርከብ ወደቦችን አያለሁ ብሎ ሊያስብ ይችላል፤ ሆኖም ወደቦቹ ከመሃል ከተማ ተነስተው ወደ ወንዙ መነሻ አካባቢ ስለተዛወሩ እነርሱን ለማየት አይችልም። ከዚህ ይልቅ ዶክላንድስ ተብሎ በሚጠራው የከተማ ልማት ፕሮጀክት በሚከናወንበት አካባቢ በአዲስ መልክ የሚገነቡትን አስደናቂ ንድፍ ያላቸውን ሕንጻዎች መመልከት ይችላል። በእርግጥም፣ ጉልህ ስፍራ በሚሰጠው የለንደን ዝነኛ ቦታ ላይ ሆነን የምናያቸው ነገሮች ድንቅ፣ ማራኪና ቀልብ የሚስቡ ናቸው።

ወደ ለንደን ከሄድክ ይህን ታሪካዊ ድልድይ ለምን አትጎበኝም? ጉብኝትህ ከአእምሮህ የማይጠፋ ግሩም የምህንድስና ውጤት ለማየት ያስችልሃል።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአንድ ወቅት በእንፋሎት ኃይል በመንቀሳቀስ ለሞተሮቹ ኃይል ሲሰጡ ከነበሩት ሁለት ፓምፖች አንዱ

[ምንጭ]

Copyright Tower Bridge Exhibition

[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የድልድዩ ተካፋቾች ሙሉ በሙሉ ወደ ላይ ተነስተው ለመቆም የሚፈጅባቸው ጊዜ ከአንድ ደቂቃ ያነሰ ነው

[ምንጭ]

©Alan Copson/Agency Jon Arnold Images/age fotostock

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል ምንጭ]

© Brian Lawrence/SuperStock