በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቴሌቪዥን የማየት ልማድን መቆጣጠር የሚቻልባቸው መንገዶች

ቴሌቪዥን የማየት ልማድን መቆጣጠር የሚቻልባቸው መንገዶች

ቴሌቪዥን የማየት ልማድን መቆጣጠር የሚቻልባቸው መንገዶች

ቴሌቪዥን የማየት ልማድን መቆጣጠር የሚቻልባቸው መንገዶች “አንዴ ቴሌቪዥኑ ከተከፈተ የቀረበውን ፕሮግራም ሁሉ እንመለከታለን” በማለት ክላውዲን ተናግራለች። “ወደ መኝታችን እስክንሄድ ድረስ ቴሌቪዥኑን አንዘጋውም።” አንዳንዶች “ዓይኔን ከቴሌቪዥኑ ላይ ማንሳት አልችልም” ሲሉ ሌሎች ደግሞ “ይህን ሁሉ ሰዓት ቴሌቪዥን መመልከት ባልፈልግም እንዲህ ማድረጌን ማቆም ግን አልቻልኩም” ይላሉ። አንተስ ቴሌቪዥን በመመልከት ብዙ ሰዓት ታጠፋለህ? ቴሌቪዥን በቤተሰብህ ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተጽዕኖ ያሳስብሃል? ቴሌቪዥን የመመልከት ልማድህን ለመቆጣጠር ሊረዱህ የሚችሉ ሐሳቦች ከዚህ በታች ቀርበዋል።

1. ቴሌቪዥን በመመልከት ምን ያህል ሰዓት እንደምታጠፋ ለማወቅ ሞክር። ምሳሌ 14:15 “አስተዋይ . . . ርምጃውን ያስተውላል” ይላል። ለውጥ ማድረግ ያስፈልግህ እንደሆነ ለማወቅ ቴሌቪዥን የመመልከት ልማድህን መመርመርህ ብልህነት ነው። ለአንድ ሳምንት ያህል ቴሌቪዥን በማየት ምን ያህል ጊዜ እንደምታሳልፍ በየዕለቱ መዝግብ። ያየሃቸውን ፕሮግራሞች፣ የተማርካቸውን ነገሮችና በፕሮግራሞቹ ምን ያህል እንደተደሰትክ ጭምር ልትመዘግብ ትችላለህ። ዋናው ነገር በቴሌቪዥን ፊት ተቀምጠህ የምታሳልፈው ጊዜ ምን ያህል እንደሆነ ማስላትህ ነው። ቴሌቪዥን በመመልከት የምታጠፋውን ሰዓት ጠቅላላ ድምር ስታውቅ ትገረም ይሆናል። ከሕይወትህ ውስጥ ምን ያህሉ ጊዜ ቴሌቪዥን በመመልከት እንደባከነ ማወቅህ ብቻ እንኳ ለውጥ እንድታደርግ ሊያነሳሳህ ይችላል።

2. ቴሌቪዥን የምትመለከትበትን ጊዜ ቀንስ። በሳምንት ውስጥ አንድ ቀን፣ አንድ ሙሉ ሳምንት ወይም አንድ ወር ቴሌቪዥን ሳታይ ለማሳለፍ ሞክር። በሌላ በኩል ደግሞ በየቀኑ ቴሌቪዥን በምትመለከትበት ጊዜ ላይ ገደብ ለማበጀት ትፈልግ ይሆናል። በየቀኑ ቴሌቪዥን ለማየት ከምታውለው ጊዜ ላይ ግማሽ ሰዓት ብትቀንስ በየወሩ 15 ተጨማሪ ሰዓት ታገኛለህ። ይህን ጊዜ መንፈሳዊ ነገሮች ለማድረግ፣ አንድ ጥሩ መጽሐፍ ለማንበብ ወይም ከቤተሰብህና ከጓደኞችህ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ እንዲሁም እንደነዚህ ያሉ ጠቃሚ እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን ተጠቀምበት። ለረጅም ሰዓት ቴሌቪዥን ከሚያዩት ይልቅ ጥቂት ሰዓት ብቻ የሚያዩት ሰዎች በሚመለከቱት ነገር ይበልጥ እንደሚደሰቱ ጥናቶች አመልክተዋል። ቴሌቪዥን የምትመለከትበትን ጊዜ ለመቀነስ የሚረዳህ አንዱ መንገድ ቴሌቪዥኑን ከመኝታ ቤትህ ማውጣት ነው። በመኝታ ክፍላቸው ውስጥ ቴሌቪዥን ያላቸው ልጆች በመኝታ ክፍላቸው ውስጥ ቴሌቪዥን ከሌላቸው ልጆች ጋር ሲወዳደሩ በየቀኑ ቴሌቪዥን በማየት የሚያጠፉት ጊዜ የአንድ ሰዓት ተኩል ብልጫ አለው። ከዚህም በላይ ቴሌቪዥኑ በልጆቹ ክፍል የሚገኝ ከሆነ ወላጆች ልጃቸው ምን እንደሚያይ ማወቅ አይችሉም። ወላጆችም ሆኑ ባልና ሚስቶች ቴሌቪዥኑን ከመኝታ ቤታቸው አውጥተው ወደ ሌላ ክፍል ካዛወሩት አብረው የሚያሳልፉት ተጨማሪ ጊዜ እንደሚኖራቸው ተገንዝበዋል። አንዳንዶች ደግሞ እስከ ጭራሹ ቴሌቪዥን እንዳይኖራቸው ወስነዋል።

3. በቴሌቪዥን ለምታየው ነገር የተወሰነ ፕሮግራም ይኑርህ። እርግጥ ነው፣ በቴሌቪዥን የሚቀርቡ ብዙ ጥሩ ፕሮግራሞች አሉ። ስለዚህ ለማየት የምትፈልገው ፕሮግራም እንዳለ ለማወቅ የቴሌቪዥን ጣቢያዎቹን በየተራ ከመቃኘት ወይም የቀረበውን ነገር ሁሉ ከመመልከት ይልቅ ልታየው የምትፈልገውን ፕሮግራም ለመምረጥ አስቀድመህ ምን እንደሚተላለፍ አጣራ። የምትፈልገው ፕሮግራም ሲጀምር ብቻ ቴሌቪዥኑን ከፍተህ ሲያበቃ ደግሞ አጥፋው። ወይም ደግሞ አንድን ፕሮግራም በሚተላለፍበት ወቅት በመመልከት ፈንታ በኋላ ለማየት እንድትችል ልትቀዳው ትፈልግ ይሆናል። ይህም በሚመችህ ጊዜ ፕሮግራሙን ለማየትና ማስታወቂያዎቹን እያሳለፍክ ለመመልከት ያስችልሃል።

4. መራጭ ሁን። መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናችን ሰዎች “ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉ፤ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክሕተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ለዕርቅ የማይሸነፉ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በከንቱ በትዕቢት የተወጠሩ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ” እንደሚሆኑ አስቀድሞ ተንብዮአል። ምናልባት አንተም ብዙዎቹ የቴሌቪዥን ተዋንያን ከላይ እንደተጠቀሰው ዓይነት ባሕርይ አላቸው ቢባል ሳትስማማ አትቀርም። መጽሐፍ ቅዱስ “ከእነዚህ ራቅ” በማለት ይመክራል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) እንዲሁም “አትሳቱ፤ መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል” የሚል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶናል።—1 ቆሮንቶስ 15:33

መራጭ መሆን ራስን መግዛትን ይጠይቃል። ለጥቂት ደቂቃዎች አንድ ድራማ ወይም ፊልም ከተመለከትህ በኋላ እየቀረበ ያለው ነገር መጥፎ መሆኑን ብትገነዘብም ቀጥሎ የሚሆነውን ለማየት ብለህ ሙሉውን ፊልም አይተህ ታውቃለህ? ብዙዎች እንደዚህ አድርገዋል። ይሁን እንጂ ጊዜህን ሌላ ነገር ለመሥራት እንድትጠቀምበት ብለህ ቴሌቪዥኑን ለማጥፋት የሚያስችል ቆራጥነት ካለህ ቀጥሎ ምን እንደሚቀርብ ለማየት ግድ እንደማይኖርህ ትገነዘባለህ።

ቴሌቪዥን ከመፈልሰፉ ከረዥም ጊዜ በፊት መዝሙራዊው “በዐይኔ ፊት፣ ክፉ ነገር አላኖርም” በማለት ጽፎ ነበር። (መዝሙር 101:3) እኛም በቴሌቪዥን የምንመለከተውን ነገር በምንመርጥበት ጊዜ መዝሙራዊው የተናገረውን ማስታወሳችን መልካም ነው! አንዳንዶች እንደ ክላውዲን ቴሌቪዥን እንዳይኖራቸው ወስነዋል። እንዲህ ብላለች:- “ቴሌቪዥን መመልከት ምን ያህል እንዳደነዘዘኝ ፈጽሞ አልተገነዘብኩም ነበር። አሁን ቴሌቪዥን ለማየት አጋጣሚ ሳገኝ ከዚህ በፊት ሳያቸው ምንም የማይመስሉኝ ነገሮች ያስደነግጡኛል። በማየው ነገር ረገድ መራጭ የሆንኩ ይመስለኝ ነበር፤ አሁን ግን መራጭ እንዳልነበርኩ ተገንዝቤያለሁ። አሁን ጤናማ የሆኑ ነገሮችን ስመለከት ከበፊቱ ይበልጥ እደሰትባቸዋለሁ።”

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቴሌቪዥን በመመልከት ምን ያህል ሰዓት እንደምታጠፋ ጻፍ

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቴሌቪዥን በመመልከት ፈንታ ሌሎች ጠቃሚ እንቅስቃሴዎችን አከናውን

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቴሌቪዥኑን ለማጥፋት አታመንታ!