ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
▪ “በመገናኛ ብዙኃን በሚተላለፉ የዓመጽ ድርጊቶችና [በጎረምሶች] የጠበኝነት ባሕርይ መካከል ያለው ቁርኝት ሲጋራ በማጨስና በሳንባ ካንሰር መካከል ካለው ጥብቅ ትስስር የማይተናነስ ነው።”—ዘ ሜዲካል ጆርናል ኦቭ አውስትራሊያ
▪ በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች የሚኖሩ ሰዎች የሚበሏቸው የሌሊት ወፍ ዝርያዎች “የኢቦላ ቫይረስ መራቢያ ሊሆኑ እንደሚችሉ” መረጃዎች ያሳያሉ።—ማክሌንስ የተባለ መጽሔት፣ ካናዳ
▪ የሜክሲኮ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ ቢያንስ 130,000 የሚያህሉ ሜክሲካውያን ልጆች ታፍነው ተወስደዋል። እንዲህ የሚደረገው ልጆቹን ለመሸጥ፣ በጾታ ተግባር ወይም በጉልበት ሥራ ላይ አሰማርቶ ጥቅም ለማግኘት አሊያም የአካል ክፍሎቻቸውን አውጥቶ ለመሸጥ ሲባል ነው።—ሚሌኒዮ የተባለ ጋዜጣ፣ ሜክሲኮ
ለአሥራ ሁለት ዓመት በእስር ቤት የቆዩት ለምንድን ነው?
በሳዋ፣ ኤርትራ ሦስት የይሖዋ ምሥክሮች ላለፉት 12 ዓመታት በእስር ቤት ቆይተዋል። እነዚህ ሰዎች ክስ ያልተመሠረተባቸው ከመሆኑም በላይ ፈጽሞ ለፍርድ አልቀረቡም። ከዚህም በላይ የቤተሰቦቻቸውን አባላት ጨምሮ ማንም ሰው እንዲጠይቃቸው አይፈቀድላቸውም። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? የውትድርና አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ስላልሆኑ ነው። የኤርትራ ሕግ በውትድርና ለመካፈል ሕሊናቸው ለማይፈቅድላቸው ሰዎች ቦታ የለውም። ወጣት ወንዶች ሲያዙ ወደ ወታደሮች ካምፕ የሚወሰዱ ሲሆን እዚያም ብዙውን ጊዜ ክፉኛ ይገረፋሉ እንዲሁም የተለያየ ዓይነት ሥቃይ ይደርስባቸዋል።
በእርግጥ ኢንተርኔት ለዱር እንስሳት ጠር ሆኗል?
ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ “ኢንተርኔት፣ በአፍሪካ ለሚገኙት ዝሆኖች መመናመን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይሆን?” የሚል ጥያቄ አቅርቧል። አንዳንድ የእንስሳት ደኅንነት ተከራካሪዎች ለጥያቄው የአዎንታ መልስ የሰጡ ከመሆኑም በላይ ሌሎች በርካታ የእንስሳት ዝርያዎችም አደጋ እንደተጋረጠባቸው ይሰማቸዋል። የኢንተርኔት ድረ ገጾች እየበዙ በሄዱ ቁጥር በኢንተርኔት የሚደረገው ሕገ ወጥ ንግድ እንደጨመረ ይነገራል። በእንግሊዝኛ ቋንቋ አገልግሎት በሚሰጡ ድረ ገጾች ላይ ለሦስት ወራት የተደረጉት ምርምሮች እንዳሳዩት “ከ6,000 የሚበልጡ ሕገ ወጥ ወይም ሕገ ወጥ ሊሆኑ የሚችሉ ከዱር እንስሳት አካላት የሚሠሩ ዕቃዎች ለሽያጭ ቀርበዋል።” ከእነዚህም መካከል ኤሊን የሚሸፍናት ድንጋይ፣ ከዝሆን አጥንት የተሠሩ ቅርጻ ቅርጾች አልፎ ተርፎም በሕይወት ያሉ ጥቋቁር ነብሮች ይገኙበታል።
አየር የማይበክል ማሞቂያ
ኤል ፓይስ የተባለው የስፔን ጋዜጣ “በወይራ ፍሬ የሚሠራ ማሞቂያ በሥራ ላይ ዋለ” የሚል ሪፖርት አወጣ። በዚህ የኃይል ምንጭ አማካኝነት በማድሪድ ለሚገኙ ቢያንስ 300 ለሚያህሉ ቤቶች ሙቀትና ሙቅ ውኃ ማሰራጨት ተጀምሯል። የወይራ ፍሬ ዋጋው ከነዳጅ ዘይት 60 በመቶ ከድንጋይ ከሰል ደግሞ 20 በመቶ ስለሚያንስ ከነዳጅ አንጻር ሲታይ ርካሽ ነው። ይህ ፍሬ በሚቀጣጠልበት ጊዜ የሚወጣው ካርቦን ዳይኦክሳይድ በተፈጥሯዊ ሁኔታ በሚበሰብስበት ጊዜ ከሚወጣው መጠን ጋር ተመጣጣኝ ስለሆነ አካባቢ አይበክልም። ሌላው ጥሩ ጎኑ ደግሞ በቀላሉ የሚገኝ መሆኑ ነው። የወይራ ፍሬ ዘይቱ ከተጨመቀ በኋላ የሚቀረው ዝቃጭ ነው፤ ስፔን ደግሞ ከዓለም ቁጥር አንድ የወይራ ዘይት አምራች እንደሆነች ይታሰባል።
አራት ሺህ ዓመታት ያስቆጠሩ ፓስታዎች
ሳይንቲስቶች “ከዓለም እጅግ ረጅም ዘመን ያስቆጠሩ ፓስታዎች” ማግኘታቸውን እንደተናገሩ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል። ፓስታዎቹ ቀጭን፣ ቢጫና 50 ሴንቲ ሜትር ርዝመት ያላቸው ሲሆኑ በቻይና ከሚበቅል የማሽላ ዝርያ የተሠሩ ናቸው። እነዚህ ፓስታዎች ከሸክላ በተሠራ ጎድጓዳ ሳህን ውስጥ ታሽገው የተገኙት በሰሜን ምዕራብ ቻይና ኽዋንግ ወንዝ አቅራቢያ 3 ሜትር ጥልቀት ባለው ደለል ውስጥ ነው። ይህ አካባቢ የወደመው ከዛሬ 4,000 ዓመታት ገደማ በፊት በመሬት መንቀጥቀጥና “በውኃ መጥለቅለቅ” ሊሆን እንደሚችል ኔቸር የተባለው መጽሔት ዘግቧል። ሳህኑን ካገኙት ተመራማሪዎች መካከል አንዱና የቻይና የሳይንስ አካዳሚ ባልደረባ የሆኑት ሆዩአን ሉ ፓስታ መሥራት የተጀመረው በጣሊያን፣ በመካከለኛው ወይም በሩቅ ምሥራቅ ስለመሆኑ የተነሳውን ክርክር በሚመለከት “ይህ ጥናት፣ ፓስታ መመረት የተጀመረው በቻይና መሆኑን ያረጋግጥልናል” ማለታቸውን ታይምስ ዘግቧል።