በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሕይወት በሞት ሸለቆ

ሕይወት በሞት ሸለቆ

ሕይወት በሞት ሸለቆ

በ1848 በካሊፎርኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ሳክረሜንቶ ከተማ አካባቢ ወርቅ ተገኝቶ ነበር። በቀጣዩ ዓመት 80,000 የሚያክሉ ሀብት ፈላጊዎች ቶሎ እንከብራለን በሚል ጉጉት ወደ ካሊፎርኒያ ተመሙ። ታኅሣሥ 25, 1849 መቶ የጭነት ሠረገላዎችን እየነዱ ከሳልት ሌክ ሲቲ ወደ ምዕራብ ሲጓዙ ከነበሩ ሰዎች መካከል የተወሰኑት በአሁኑ ጊዜ ዴዝ ቫሊ ወይም የሞት ሸለቆ ወደሚባለው በረሃ ገቡ። እነዚህ ሰዎች በካሊፎርኒያ-ነቫዳ ጠረፍ አቅራቢያ የሚገኘው ይህ በረሃማ ሸለቆ አቋራጭ መንገድ እንደሚሆን አስበው ነበር።

በዚያን ወቅት ሸለቆው ቀዝቀዝ ያለ ቢሆንም የመሬቱ አቀማመጥ ግን እጅግ አደገኛ ነበር። በመሆኑም በቡድን ሆነው ሲጓዙ የነበሩት ሰዎች በትንንሽ ቡድኖች ተከፋፈሉና በተለያዩ መንገዶች መሄድ ጀመሩ። ከእነዚህ ውስጥ ሴቶችንና ሕጻናትን ያቀፈ አንድ ቡድን ሸንተረሮቹን አቋርጦ ከሸለቆው በመውጣት ወደ ምዕራብ ለመሻገር ያደረገው ሙከራ ሳይሳካለት ይቀራል። በመሆኑም በድካም የዛሉትና ስንቃቸው የተመናመነባቸው እነዚህ ተጓዦች በአሁኑ ጊዜ ፈርነስ ክሪክ ተብሎ በሚጠራው የውኃ ምንጭ አካባቢ ለትንሽ ጊዜ ካረፉ በኋላ የቤኔት ዌል በሚባል አንድ ኩሬ አጠገብ ሰፈሩ። በዚህ ጊዜ ዊሊያም ማንሊና ጆን ሮጀርስ የተባሉ ሁለት የሃያ ዓመት ወጣቶች ሌሎቹን ባሉበት ትተው እርዳታ ለማግኘት ጉዞ ጀመሩ።

ማንሊና ሮጀርስ በጥቂት ቀናት ውስጥ ሎስ አንጀለስ ከተማ እንደርሳለን የሚል ሐሳብ ነበራቸው። ሎስ አንጀለስ ከተማ እነርሱ ካሉበት ወደ ደቡብ ምዕራብ 300 ኪሎ ሜትር እንደሚርቅ አላወቁም ነበር። እነዚህ ወጣቶች በእግራቸው ለሁለት ሳምንት ከተጓዙ በኋላ በሎስ አንጀለስ ከተማ ሰሜናዊ ጫፍ ላይ ወደሚገኘው ሰን ፈርናንዶ ሸለቆ ደረሱ። ከዚያም የሚያስፈልጓቸውን ቁሳቁሶች ይዘው ወዲያውኑ ወደመጡበት ተመለሱ።

ከ25 ቀናት ቆይታ በኋላ ሌሎቹን ትተው ወደሄዱበት ስፍራ ሲደርሱ ማንም ሰው ባለማግኘታቸው ማንሊ ሽጉጥ አውጥቶ ወደ ላይ ተኮሰ። በዚህ ጊዜ አንድ ሰው ከቆሙት ሠረገላዎች ሥር ወጣ። ቆየት ብሎ ማንሊ ሁኔታውን አስመልክቶ ሲጽፍ “ሰውየው እጆቹን ወደ ላይ ዘርግቶ ‘ልጆቹ መጥተዋል! ልጆቹ መጥተዋል!’ ሲል ጮኸ” ብሏል። ሌሎቹም ሰዎች ስሜታቸው በጥልቅ በመነካቱ መናገር አቅቷቸው ነበር። ለማንሊና ሮጀርስ ምስጋና ይግባቸውና ሸለቆውን ብቻውን ለማቋረጥ ከሞከረ አንድ ሰው በቀር ሁሉም ተጓዦች ሕይወታቸው ሊተርፍ ችሏል። በኋላም ተጓዦቹ ሸለቆውን ለቅቀው ሲወጡ አንዲት ሴት ወደ ኋላዋ መለስ ብላ ከተመለከተች በኋላ ‘ደህና ሁን፣ የሞት ሸለቆ!’ እንዳለች ይነገራል። ይህም የሸለቆው መጠሪያ ሆነ።

በጣም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ያሉበት ምድር

ሁለት መቶ ሃያ አምስት ኪሎ ሜትር ርዝመትና ከ8 እስከ 24 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ስፋት ያለው የሞት ሸለቆ በሰሜን አሜሪካ ውስጥ ካሉት አካባቢዎች ሁሉ በጣም ደረቅ፣ እጅግ ሞቃታማና የመጨረሻው ዝቅተኛ ቦታ ነው። በፈርነስ ክሪክ የአየሩ ሙቀት 57 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ፣ ከታች መሬት ላይ ያለው ሙቀት ደግሞ 94 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የደረሰበት ጊዜ ነበር። ይህም በባሕር ወለል ልክ በሚገኝ ቦታ ላይ ውኃ ከሚፈላበት የሙቀት መጠን በ6 ሴንቲ ግሬድ ብቻ ያነሰ ነው! *

ዓመታዊው አማካኝ የዝናብ መጠን ከ5 ሴንቲ ሜትር የሚያንስ ሲሆን አካባቢው ጭራሹኑ ዝናብ የማያገኝባቸው ዓመታትም አሉ። በምዕራቡ ንፍቀ ክበብ ከሚገኙ አካባቢዎች በሙሉ ዝቅተኛው ስፍራ የሚገኘው በሸለቆው ውስጥ ባለ ባድዎተር የተሰኘ ጨዋማ ኩሬ አቅራቢያ ሲሆን ቦታው ከባሕር ወለል በታች 86 ሜትር ዝቅ ይላል። ከዚህ ቦታ 140 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ 4,418 ሜትር ከፍታ ያለውና አላስካን ሳይጨምር በመላው ዩናይትድ ስቴትስ በከፍታው ተወዳዳሪ የሌለው የዊትኒ ተራራ ይገኛል።

በ1850 በሸለቆው ውስጥ ባለ ሳልት ስፕሪንግ በተሰኘ ስፍራ ትንሽ ወርቅ ተገኘ። ከዚህም በተጨማሪ ማዕድን አሳሾች በአካባቢው ብር፣ መዳብና ሊድ ማግኘት ቻሉ። በዚህ ሳቢያ በመላው ሸለቆ ውስጥ ቡልፍሮግ፣ ግሪንዎተር፣ ራዮላይት፣ ስኪዱ የሚሉትን የመሳሰሉ አስገራሚ ስም ያላቸው የማዕድን ማውጫ ከተሞች በፍጥነት ተቆረቆሩ። ይሁንና ማዕድናቱ ሲመናመኑ በሕዝብ ተጨናንቀው የነበሩት እነዚህ ከተሞች ወና ይሆኑ ጀመር። በ1880 ግን በሞት ሸለቆ ውስጥ ቦራክስ የተባለ ሳሙናንና ሌሎች ነገሮችን ለመሥራት የሚያገለግል ነጭ ማዕድን ተገኘ፤ ይህም በሸለቆው ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ስኬታማ የማዕድን ማውጣት እንቅስቃሴ እንዲጀመር በር ከፈተ። እስከ 1888 ድረስ በቡድን የተደራጁ ሰዎች ቦራክስ የተሸከሙና አምስት ሜትር ርዝመት ያላቸው ሁለት የተያያዙ የጭነት ሠረገላዎችን በ18 በቅሎዎችና በ2 ፈረሶች እያስጎተቱ 270 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው ሞሃቪ ከተማ አድካሚ ጉዞ ያደርጉ ነበር። ይሁንና ከሰኔ እስከ መስከረም ባሉት ወራት ሙቀቱ ለሰዎቹም ሆነ ለእንስሳቱ በጣም ከባድ ስለሚሆን ማዕድኑን ማመላለሳቸውን ያቆሙ ነበር።

በ1933 የሞት ሸለቆ ብሔራዊ ቅርስ እንዲሆን ተወሰነ። ይህ ክልል ቀስ በቀስ እየሰፋ ሄዶ በአሁኑ ጊዜ 1.3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ይሸፍናል። በ1994 ቦታው ዴዝ ቫሊ ናሽናል ፓርክ ወይም የሞት ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ በመባል የተሰየመ ሲሆን በዩናይትድ ስቴትስ ካሉት ትላልቅ ፓርኮች መካከል አንዱ ነው።

በሕያዋን ፍጥረታት የተሞላው የሞት ሸለቆ

አንድ ሰው የሞት ሸለቆ ሕይወት አልባ ነው ብሎ ቢያስብ አያስገርምም። ይሁን እንጂ በዚህ አካባቢ በመቶዎች የሚቆጠሩ የእንስሳት ዝርያዎች ለጊዜው ወይም በዘላቂነት ይኖራሉ። ከእነዚህ ውስጥ ብዙዎቹ በሙቀቱ ምክንያት የሚንቀሳቀሱት በሌሊት ነው። በአካባቢው ከሚገኙት አጥቢ እንስሳት መካከል ትልቁ በሸለቆው አቅራቢያ ካሉት ተራራማ አካባቢዎች ተሻግሮ ወደዚህ ሸለቆ አልፎ አልፎ የሚመጣው ግርማ የተላበሰው ባለ ትልቅ ቀንድ የበረሃ በግ ነው። በዚህ ሸለቆ ውስጥ ከሚኖሩት ሌሎች እንስሳት መካከል ሽኮኮ፣ የሌሊት ወፍ፣ የዱር ድመት፣ ተኩላ፣ ቀበሮ፣ ካንጋሮ የተባሉ የአይጥ ዝርያዎች፣ ግስላ፣ ጃርት፣ ጥንቸል፣ ሸለምጥማጥ፣ የዱር አህያ፣ እንሽላሊት፣ እባብና የበረሃ ኤሊ ይገኙበታል። በተጨማሪም ኩት፣ ጭልፊት፣ ሳቢሳ፣ ድርጭት፣ ቁራ፣ ሳንድፓይፐርና ጥንብ አንሳን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሌሎች የወፍ ዝርያዎች በዚህ አካባቢ ይኖራሉ።

ከእነዚህ ፍጥረታት መካከል ችግርን በመቋቋም ረገድ ካንጋሮ አይጦችን የሚወዳደራቸው የለም። እነዚህ አይጦች አንዲት ጠብታ ውኃ ሳይቀምሱ ዕድሜያቸውን በሙሉ መኖር ይችላሉ! አንድ መጽሔት እንዳለው ከሆነ እነዚህ ፍጥረታት “በሕይወት ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን ውኃ የሚያገኙት በሚመገቡት ደረቅ አዝርዕት ውስጥ ካለው ስኳርና ስብ ነው።” የእነዚህ እንስሳት ኩላሊት ቆሻሻ ለማስወገድ የሚያስፈልገው የውኃ መጠን የሰው ኩላሊት ከሚያስፈልገው ውኃ አምስት ጊዜ ያነሰ ነው። መሬት ውስጥ ጉድጓድ በመቆፈር የሚኖሩት እነዚህ ትንንሽ የአይጥ ዝርያዎች ምግብ ፍለጋ የሚወጡት በምሽት ስለሆነ የቀኑ ኃይለኛ ትኩሳት አያገኛቸውም።

በሞት ሸለቆ ውስጥ ከሺህ የሚበልጡ የዕፅዋት ዝርያዎች ይበቅላሉ። በዚህ ስፍራ ከአንድ ሺህ ዓመት በላይ የኖሩት ሾሾኒ የተባሉ የሕንድ ዝርያዎች በአካባቢው የሚገኙትን ዕፅዋት ለምግብነትና የቤት ቁሳቁስ ለመሥራት ይጠቀሙባቸዋል። እነዚህ ሰዎች፣ ‘ምን መፈለግ እንዳለብህ ካወቅክ በሞት ሸለቆ ውስጥ የተትረፈረፈ ምግብ ማግኘት ትችላለህ’ ይላሉ።

በረሃው ሲያብብ

አልፎ አልፎ የሞት ሸለቆ እጅግ አስደናቂ በሆኑ የበረሃ አበቦች ያጌጣል። አበቦቹ የሚያድጉት በአፈሩ ውስጥ ተቀብረው ከሚገኙ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ዘሮች ሲሆን ዘሮቹ ለመብቀል የሚያስችላቸውን ተስማሚ የዝናብና የሙቀት መጠን እስከሚያገኙ ድረስ አንዳንድ ጊዜ ለብዙ አሥርተ ዓመታት ይጠብቃሉ። የብሔራዊ ፓርኩ የሥነ ዕፅዋት ተመራማሪ የሆኑት ቲም ክሮሶንት “ምንም አበባ ሳናይ ብዙ ዓመታት ያልፋሉ” ብለዋል።

ይሁንና በ2004 መጨረሻና በ2005 መጀመሪያ ላይ በሞት ሸለቆ ውስጥ ከወትሮው ሦስት እጥፍ የሚበልጥና ከዚያ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ዝናብ ዘነበ። በዚህም ምክንያት ላርክስፐር፣ ላይላክ፣ ኦርኪድ፣ ፓፒ፣ ፕሪምሮዝ፣ የሱፍ አበባና ቨርቢና የተባሉትን ጨምሮ ከ50 በላይ አበባዎች ፈኩ። አንዲት ጎብኚ ሸለቆው የአበባ መሸጫ ቤቶች ዓይነት መዓዛ እንደነበረው ተናግረዋል። የፈኩት አበባዎች የንቦችንና የሌሎች ነፍሳትን ትኩረት መሳባቸው አልቀረም። ስለሆነም የሞት ሸለቆ ሲያብብ አካባቢው ቁጥር ስፍር የሌላቸው ትንንሽ ነፍሳት ሲበሩ በሚፈጥሩት ድምፅ ይሞላል።

ልዩ ልዩ ነገሮች የሚገኙበትን ይህን ሸለቆ ለመጎብኘት ካሰብክ አስተማማኝ መኪናና ብዙ ውኃ መያዝ እንዳለብህ አትዘንጋ። አካባቢውን የምትጎበኘው ንቦች በሚመጡበት ጊዜ ከሆነ ደግሞ ካሜራህን መያዝ ይኖርብሃል። ወደ ቤትህ ስትመለስ ፎቶውን የምታሳያቸው ወዳጅ ዘመዶችህ፣ የሞት ሸለቆ በበርካታ ሕያዋን ፍጥረታት የተሞላ መሆኑን ሲመለከቱ መገረማቸው አይቀርም።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7 በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ካሉት እጅግ ሞቃታማ ቦታዎች መካከል ከፍተኛ ሙቀት የተመዘገበው በ1922 በሊቢያ ሲሆን የሙቀቱ መጠንም 58.0 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ነበር። በሞቃታማ ወራት አጠቃላይ የሙቀት መጠን ግን በምድር ላይ የሞት ሸለቆን የሚተካከል ስፍራ የለም።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ አካባቢዎች ሁሉ በጣም ደረቅ፣ እጅግ ሞቃታማና የመጨረሻ ዝቅተኛ የሆነው ስፍራ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

የበረሃ ዓሣ!

በሞት ሸለቆ ዴዘርት ፐፕፊሽ የሚባሉ አስደናቂ የሆኑ አራት ትንንሽ የዓሣ ዝርያዎች ይገኛሉ። በቀዝቃዛው ወራት እነዚህ 6 ሴንቲ ሜትር ርዝመትና ብርማ ቀለም ያላቸው ፍጥረታት በጅረቶችና ኩሬዎች ሥር በሚገኘው ጭቃ ውስጥ ተደብቀው ይቆዩና የፀደይ ፀሐይ ውኃውን ማሞቅ ስትጀምር መንቀሳቀስና መራባት ይጀምራሉ። የወንዶቹ ቀለም ወደሚያብረቀርቅ ደማቅ ሰማያዊነት ይቀየራል፤ ከዚያም ወሰናቸውን ከሌሎች ወንድ ዓሦች ለመከላከል ከባድ ፍልሚያ ውስጥ ይገባሉ። ይሁንና ብዙም ሳይቆይ በሞቃታማው ወራት የሚኖረው ጠራራ ፀሐይ አብዛኛውን ውኃ ስለሚያደርቀው ብዙዎቹ ፐፕፊሾች ይሞታሉ። በሕይወት የተረፉት ዓሦች ደግሞ ከፍተኛ የጨው መጠን ባለውና ሙቀቱ ወደ 44 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሊደርስ በሚችለው ውኃ ውስጥ ለመኖር ይገደዳሉ።

[ምንጭ]

ከላይ ያሉት ዓሦች:- © Neil Mishalov--www.mishalov.com; ከታች ያለው ዓሣ:- Donald W. Sada, Desert Research Institute

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካ

ካሊፎርኒያ

የሞት ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

በቅሎዎች:- Courtesy of The Bancroft Library/University of California, Berkeley

[በገጽ 16 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]

አህዮች:- ©Joseph C. Dovala/age fotostock; ከላይ ያለው ፎቶግራፍ:- © Neil Mishalov--www.mishalov.com; አበቦች:- Photo by David McNew/Getty Images