በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የሕዝብ መዝናኛ

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የሕዝብ መዝናኛ

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የሕዝብ መዝናኛ

በደቡባዊ ጣሊያን የሚገኙ የሁለት ጎረቤት ከተሞች ተፎካካሪ የስፖርት ደጋፊዎች ያስነሱት ረብሻ በብዙዎች ላይ የመቁሰል አደጋ እንዲደርስ ከማድረጉም በላይ የተወሰኑ ልጆችን ጨምሮ ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል። በዚህ አሳዛኝ ክስተት ምክንያት ባለ ሥልጣናት አምፊቲያትሩ ለአሥር ዓመታት እንዲዘጋ ትእዛዝ አስተላልፈዋል።

ዛሬው ጊዜ እንደዚህ ስለመሰለው የሕዝብ ረብሻ ከጋዜጦች ላይ ማንበብ አዲስ ነገር አይደለም። ሆኖም ከላይ የተገለጸው ሁኔታ የተከሰተው ከ2,000 ዓመታት ገደማ በፊት በንጉሠ ነገሥት ኔሮ የግዛት ዘመን ነበር። በፖምፔ አምፊቲያትር በተደረገ የግላድያተሮች ግጥሚያ ላይ በፖምፔ ነዋሪዎችና ከምትጎራበታቸው ከተማ ከኑኬሪያ በመጡ የስፖርት ደጋፊዎች መካከል ስለተነሳው ስለዚህ ረብሻ ሮማዊው ታሪክ ጸሐፊ ታሲተስ ዘግቧል።

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሕዝቡ ለመዝናኛ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጥ ነበር። በሮም ግዛት የሚገኙ ትልልቅ ከተሞች ቲያትር ቤቶች፣ አምፊቲያትሮችና ሰርከስ ማሳያዎች የነበሯቸው ሲሆን በአንዳንዶቹ ከተሞች ደግሞ ሦስቱም የመዝናኛ ቦታዎች ይገኙ ነበር። “ውድድሮቹ ዘግናኝ በሆኑ አደጋዎች የተሞሉ ከመሆናቸውም ሌላ የሚያሰቅቁ ነበሩ። . . . [እንዲሁም] ሆን ተብሎ ደም ለማፋሰስ የታቀዱ ነበሩ” በማለት አትላስ ኦቭ ዘ ሮማን ወርልድ የተባለው መጽሐፍ ይናገራል። ሰረገላ ነጂዎቹ አንዳቸው ከሌላው የሚለዩበት ቀለም ያለው ልብስ የሚለብሱ ሲሆን እያንዳንዱ ቡድን ማኅበራዊ ወይም ፖለቲካዊ የሆነን አንድ የኅብረተሰብ ክፍል ይወክላል። ደጋፊዎች የሚወዱት ቡድን ብቅ ሲል በከፍተኛ ጩኸት ስሜታቸውን ይገልጻሉ። ሰረገላ ነጂዎቹ በጣም ተወዳጅ በመሆናቸው ሕዝቡ ቤቱን በእነርሱ ምስል ከማስጌጡም ሌላ ዳጎስ ያለ ገንዘብ ይከፈላቸው ነበር።

ከተሞች ደም መፋሰስ የሚታይባቸውን የግላዲያተሮች ግጥሚያ እንዲሁም በሰዎችና በአራዊት መካከል የሚደረግ ትግል የሚታይባቸውን ትርኢቶች ያስተናግዱ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ሰዎቹ ከአውሬ ጋር የሚታገሉት ምንም መሣሪያ ሳይዙ ነው። ታሪክ ጸሐፊው ዊል ዱራንት እንደገለጹት ከሆነ “ሞት የተፈረደባቸው ወንጀለኞች፣ አንዳንድ ጊዜም እንስሳ እንዲመስሉ የእንስሳ ቆዳ ለብሰው ሆን ተብሎ እንዲራቡ ወደተደረጉ አራዊት ይወረወራሉ፤ በዚህ መንገድ የሚሞቱ ወንጀለኞች ከፍተኛ ሥቃይ ይደርስባቸዋል።”

እንዲህ በመሰለው አምላክን የሚያሳዝን መዝናኛ የሚደሰቱ ሰዎች ‘ልቦናቸው የጨለመና ኅሊናቸው የደነዘዘ’ ናቸው። (ኤፌሶን 4:17-19) በሁለተኛው መቶ ዘመን ተርቱሊያን እንዲህ ሲል ጽፏል:- “[በክርስቲያኖች] መካከል፣ በሰርከስ ቦታዎች የሚታየውን ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ባሕርይም ሆነ፣ በቲያትር ቤቶች የሚቀርበውን አስነዋሪ ትርኢት [እንዲሁም] በመወዳደሪያ ቦታዎች የሚፈጸመውን አረመኔያዊ ድርጊት የመሰለ ነገር ተነግሮ ወይም ታይቶ አሊያም ተሰምቶ አይታወቅም።” በዛሬው ጊዜ የሚገኙ እውነተኛ ክርስቲያኖችም ይሖዋ “ዐመፃን የሚወዱትን” እንደሚጠላ በማስታወስ በጽሑፍ፣ በቴሌቪዥን ወይም በኮምፒውተር ጨዋታዎች አማካኝነት ዓመጽ ለተሞላበት መዝናኛ እንዳይጋለጡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋሉ።—መዝሙር 11:5

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሠረገላ ውድድር ድል ያደረገ ሰው ምስል

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ሰው ከእንስት አንበሳ ጋር ሲታገል የሚያሳይ ሥዕል

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረ የሮም ቲያትር ቤት

[የሥዕል ምንጭ]

Ciudad de Mérida

[በገጽ 30 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]

ከላይና ከታች በስተ ግራ:- Museo Nacional de Arte Romano, Mérida