በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በጨለማ የሚያበሩ “ትንንሽ ባቡሮች”

በጨለማ የሚያበሩ “ትንንሽ ባቡሮች”

በጨለማ የሚያበሩ “ትንንሽ ባቡሮች”

ጸጥ እረጭ ባለ ምሽት በብራዚል ገጠራማ ክልል ከሚገኝ ጫካ ውስጥ፣ ከብስባሹ ሥር አንድ ትንሽ “ባቡር” ብቅ ይላል። ይህ ባቡር መንገዱን የሚያበሩለት ሁለት ቀያይ “የፊት መብራቶች”፣ ከጎንና ከጎኑ ደግሞ ወደ ቢጫነት ያደሉ 11 ጥንድ አረንጓዴ ፋኖሶች አሉት። መቼም ይህ እውነተኛ ባቡር እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ከዚህ ይልቅ 70 ሚሊ ሜትር ርዝመት ያለው በደቡብና በሰሜን አሜሪካ የሚገኝ የአንድ ጥንዚዛ ዝርያ እጭ ነው። በእጭነት ደረጃ የሚቆዩት እንስት ጥንዚዛዎች የውስጥ መብራት አብርቶ የሚሄድ የባቡር ፉርጎ ስለሚመስሉ አብዛኛውን ጊዜ የባቡር ሃዲድ ትሎች ተብለው ይጠራሉ። ብራዚላውያን የገጠር ሰዎች ደግሞ ትንንሽ ባቡሮች ብለው ይጠሯቸዋል።

ቀን ቀን፣ ደብዘዝ ያለ ቡናማ ቀለም ያለውን ይህን እጭ ከሌሎች ነገሮች መለየት አስቸጋሪ ነው። ምሽት ላይ ግን በሚያወጣቸው አስደናቂ ብርሃኖች አማካኝነት በእርግጥ መኖሩን ይጠቁማል። እነዚህ ብርሃኖች የሚመነጩት ሉሲፈሬስ የሚባል ኢንዛይም በሚያወጣው ተፈጥሯዊ ንጥረ ነገር አማካኝነት ሲሆን ብርሃን ከመስጠት በስተቀር የሚፈጥሩት ምንም ሙቀት የለም። ከብርሃኖቹ ቀለማት መካከል ቀይ፣ ብርቱካንማ፣ ቢጫና አረንጓዴ ይገኙበታል።

ቀያዮቹ የፊት መብራቶች በቋሚነት ይበራሉ ማለት ይቻላል። የጎን መብራቶቹ ግን ሁልጊዜ አይበሩም። ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ የፊት መብራቶቹ እጩ መቶ እግር የተባለውን ተወዳጅ ምግቡን ለማደን ይረዱታል። በሌላ በኩል ደግሞ የጎን መብራቶቹን እንደ ጉንዳን፣ እንቁራሪትና ሸረሪት ያሉ አዳኞቹን ለማባረር የሚጠቀምባቸው ይመስላል። መብራቶቹ “ጣፋጭ አይደለሁም፣ ዞር በል!” የሚል መልእክት የሚያስተላልፉ ያህል ነው። በመሆኑም የጎን መብራቶቹ የሚበሩት እጩ አዳኝ እንደመጣበት ሲሰማው ነው። እንዲሁም ትል በሚያድንበት ብሎም እንስቷ በእንቁላሎቿ ዙሪያ በምትጠቀለልበት ወቅት ይበራሉ። በሌላ ወቅት ግን የጎን መብራቶቹ ቦግ ብለው ከበሩ በኋላ በጥቂት ሴኮንዶች ውስጥ ድርግም ብለው ይጠፋሉ፤ ይህ ሂደት እንደ አስፈላጊነቱ ይደጋገማል።

አዎን፣ አንድ ሰው ከጫካ ብስባሽ ሥር እንኳ አስደናቂ ውበት ማግኘት ይችላል። ይህም መዝሙራዊው ፈጣሪን ለማወደስ “ምድርም በፍጥረትህ ተሞላች” ሲል የተናገረውን ቃል ያስታውሰናል።—መዝሙር 104:24

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Robert F. Sisson / National Geographic Image Collection