በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታላቁን የሜኮንግ ወንዝ ይጎብኙ

ታላቁን የሜኮንግ ወንዝ ይጎብኙ

ታላቁን የሜኮንግ ወንዝ ይጎብኙ

የሜኮንግ ወንዝ ስድስት የእስያ አገሮችን አቆራርጦ የሚጓዝ ሲሆን ወደ 100 በሚጠጉ የተለያዩ ጎሣዎች ውስጥ ለሚገኙ 100 ሚሊዮን የሚያህሉ የየአካባቢው ተወላጆች ሕልውና መሠረት ነው ለማለት ይቻላል። በየዓመቱ ከዚህ ወንዝ 1.3 ሚሊዮን ቶን የሚሆን ዓሣ ይወጣል፤ ይህ ደግሞ ከሰሜን ባሕር ከሚገኘው በአራት እጥፍ ይበልጣል! በደቡብ ምሥራቅ እስያ ከሚገኙት ወንዞች ሁሉ ረዥም የሆነው ይህ ወንዝ 4,350 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው። ወንዙ በርካታ አገሮችን አቋርጦ ስለሚጓዝ በየቦታው የተለያየ ስያሜ ተሰጥቶታል። ይበልጥ የሚታወቀው ሜኮንግ በተባለው ስያሜ ሲሆን ይህ ስም ሜ ናም ኮንግ የሚለው የታይ ቋንቋ ስያሜ አጭር አጠራር ነው።

የሜኮንግ ወንዝ ከሂማልያ ተራሮች ተነስቶ በከፍተኛ ኃይል ቁልቁል እየተምዘገዘገ በመውረድ ጥልቀት ያላቸውን ሸለቆዎች እያቆራረጠ ይፈሳል። ላንሳንግ ተብሎ በሚጠራበት በቻይና የሚያደርገውን ጉዞ ሲጨርስ የአጠቃላይ ርዝመቱን ግማሽ ያህሉን የተጓዘ ሲሆን እዚህ ቦታ ላይ ሲደርስ መነሻው ላይ ከነበረው ከፍታ 4,500 ሜትር ወርዶ ይፈሳል። ከዚህ በኋላ ከፍታው ዝቅ የሚለው በ500 ሜትር ብቻ ነው። በዚህም ምክንያት ከግማሽ በኋላ ያለው የወንዙ ክፍል የሚፈሰው ጸጥና ዝግ ብሎ ነው። ከቻይና እንደወጣ ማያንማርና ላኦስ ለተባሉት አገሮች የጋራ ድንበር ሆኖ ይፈሳል። እንዲሁም ላኦስን ከታይላንድ በአብዛኛው የሚያዋስነው ይህ ወንዝ ነው። ሜኮንግ ካምቦዲያ ከደረሰ በኋላ ለሁለት ይከፈልና ወደ ቬትናም ይገባል። ከዚያም በብዙ አቅጣጫዎች ተከፋፍሎ ይፈስና በስተ መጨረሻ ወደ ደቡብ ቻይና ባሕር ይገባል።

በ1860ዎቹ መገባደጃ ላይ ፈረንሳውያን የሜኮንግን ወንዝ ሽቅብ በመቅዘፍ ቻይና ሊገቡ አስበው ነበር። ይሁን እንጂ ክራትዬ፣ ካምቦዲያ ሲደርሱ በዓለቶች ላይ ቁልቁል የሚጋልበው ውኃ እንዲሁም በደቡብ ላኦስ የሚገኙት ኮኔ የተባሉት ተከታትለው የሚወርዱ ኃይለኛ ፏፏቴዎች ተስፋቸውን አጨለሙባቸው። በኮኔ ፏፏቴዎች ላይ የሚጎርፈው ውኃ በየትኛውም የዓለም ክፍል ካሉት ፏፏቴዎች የሚበልጥ ሲሆን ሌላው ቀርቶ ካናዳን ከዩናይትድ ስቴትስ የሚያዋስነውን ኒያጋራ ፏፏቴ እንኳ በእጥፍ ይበልጠዋል።

የሕይወት ወንዝ

ሜኮንግ ለደቡብ እስያ አገሮች ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ነው። የላኦስ ዋና ከተማ ቪየንቲያን እና የካምቦዲያ ዋና ከተማ ፕኖም ፔን በወንዙ ላይ የተመሠረቱ የወደብ ከተሞች ናቸው። ወደታች ስንወርድ ደግሞ ወንዙ ቬትናማውያን የዕለት ጉርስ እንዲያገኙ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ቬትናም ከገባ በኋላ በሰባት አቅጣጫዎች የሚፈስ ሲሆን 3,200 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው የውኃ ላይ የመጓጓዣ መስመሮችንና 40,000 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ደለላማ ምድር ይፈጥራል። ወንዙ ይዞት የሚመጣው ከፍተኛ መጠን ያለው ውኃ እርሻዎችን ከማጠጣቱና በሩዝ ማሳዎች ላይ ከመተኛቱም በላይ ለምነት ያለው አፈር ይዞ ስለሚመጣ የቬትናም ገበሬዎች በዓመት ሦስት ጊዜ ሩዝ እንዲያመርቱ አስችሏቸዋል። በዚህም ምክንያት ቬትናም የብዙዎች የዕለት ተዕለት ምግብ የሆነውን ሩዝ ወደ ውጪ አገር በመላክ ከታይላንድ ቀጥላ በዓለም ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

በሜኮንግ ውስጥ 1,200 የሚያህሉ የዓሣ ዝርያዎች እንዳሉ ይገመታል። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹና ሽሪምፕ የተባሉት ትንንሽ የባሕር ፍጥረታት በእርባታ ጣቢያዎች ውስጥ ይረባሉ። ትሬ ሪያል የሚባል አንድ ተወዳጅ የዓሣ ዝርያ ለየት ባለ ምክንያት ታዋቂ ለመሆን በቅቷል። “ሪያል” በመባል የሚታወቀው የካምቦዲያ ገንዘብ መጠሪያውን ያገኘው ከዚህ ዓሣ ነው። በተጨማሪም በሜኮንግ ወንዝ ውስጥ ርዝመቱ እስከ 2.75 ሜትር የሚደርስ ካትፊሽ የሚባል ሊጠፋ የተቃረበ የዓሣ ዝርያ ይኖራል። በ2005 ዓሣ አስጋሪዎች በመረብ ያጠመዱት ካትፊሽ 290 ኪሎ ግራም ይመዝን ነበር። ምናልባትም ይህ ዓሣ በዓለም ላይ ካሉ ጨው አልባ ውኃዎች ውስጥ ከተያዙ ዓሣዎች ትልቁ ሊሆን ይችላል! ሜኮንግ ውስጥ ከሚገኙ እንስሳት መካከል የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበት ሌላው የዓሣ ዝርያ ደግሞ ኢራዋዲ ዶልፊን ነው። ተመራማሪዎች እንደሚሉት ከሆነ በወንዙ ውስጥ የቀሩት ዶልፊኖች 100 እንኳ ላይሞሉ ይችላሉ።

ሜኮንግ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከመመገቡም በላይ የተለያየ መጠን ላላቸው መጓጓዣዎች፣ ለምሳሌ ያህል መንገደኞችን ለሚያጓጉዙ ትናንሽ ጀልባዎች፣ ሸቀጥ ለሚጭኑ ትላልቅ ጀልባዎችና ከውቅያኖስ ለሚመጡ የጭነት መርከቦች እንደ አውራ ጎዳና ሆኖ ያገለግላል። ከዚህም በላይ ይህ ወንዝ ትልቅ የቱሪስት መስህብ ነው። አብዛኞቹ ቱሪስቶች ከኮኔ ፏፏቴዎች ባሻገር ተጉዘው ቪየንቲያንን መጎብኘት ያስደስታቸዋል። ይህች ከተማ በሰው ሠራሽ ቦዮችዋ፣ ፓጎዳ በሚባሉ ቤተ መቅደሶቿና ውኃ ላይ በተሠሩ ቤቶቿ የምትታወቅ ከመሆኗም ሌላ ከ1,000 ለሚበልጡ ዓመታት የንግድ፣ የፖለቲካና የሃይማኖት ማዕከል ሆና ቆይታለች። ሁኔታው አደገኛ ቢሆንም እንኳ አንድ ሰው ከቪየንቲያን ተነስቶ ወደ ወንዙ መነሻ ሽቅብ ቢጓዝ ሉዋንግፐረባንግ ይደርሳል። ይህች የወደብ ከተማ በአንድ ወቅት የታይ-ላኦ ሰፊ ግዛት ዋና ከተማ የነበረች ሲሆን የፈረንሳይን የቅኝ ግዛት ዘመን ጨምሮ ለተወሰኑ ዓመታት የላኦስ ነገሥታት መቀመጫ ሆናም አገልግላለች። ይህች ታሪካዊ ከተማ አሁንም ድረስ የፈረንሳይን ቅኝ አገዛዝ የሚያንጸባርቁ ነገሮች ይታዩባታል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሜኮንግ ላይ አስጊ የሆኑ ለውጦች እየታዩ ነው። ከእነዚህም መካከል አውዳሚ የሆነ ዓሣ የማስገር ልማድ፣ የደን ምንጠራና ትላልቅ የኃይል ምንጭ ግድቦች ግንባታ ይገኙበታል። ብዙ ታዛቢዎች ይህ ሁኔታ ከቁጥጥር ውጪ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ ሁኔታው ፈጽሞ ተስፋ ቢስ አይደለም።

አፍቃሪው ፈጣሪያችን በመንግሥቱ አማካኝነት በሰው ልጆች ጉዳይ በቅርቡ ጣልቃ እንደሚገባ መጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ሰጥቷል። (ዳንኤል 2:44፤ 7:13, 14፤ ማቴዎስ 6:10) ፍጹም በሆነው በዚህ ዓለም አቀፋዊ አገዛዝ ሥር መላዋ ምድር ትታደሳለች እንዲሁም በምሳሌያዊ አነጋገር ወንዞች ከደስታቸው የተነሳ ‘በእጃቸው ያጨበጭባሉ።’ (መዝሙር 98:7-9) ታላቁ ሜኮንግም በደስታ ‘የሚያጨበጭብበትን’ ጊዜ ለማየት እንናፍቃለን።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ቻይና

ማያንማር

ላኦስ

ታይላንድ

ካምቦዲያ

ቬትናም

የሜኮንግ ወንዝ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሩዝ የተዘራበት የሜኮንግ ወንዝ ደለላማ መሬት

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሜኮንግ ወንዝ ውስጥ ወደ 1,200 የሚጠጉ የዓሣ ዝርያዎች ይገኛሉ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የውኃ ላይ ገበያ በቬትናም

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

የሩዝ ማሳ:- ©Jordi Camí/age fotostock; ዓሣ አስጋሪ:- ©Stuart Pearce/World Pictures/age fotostock; የበስተ ጀርባው ምስል:- © Chris Sattlberger/Panos Pictures

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ገበያ:- ©Lorne Resnick/age fotostock; ሴት:- ©Stuart Pearce/​World Pictures/​age fotostock