በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?

አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?

አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?

አንዳንድ ጊዜ ሰዎች “ለምን?” የሚለውን ጥያቄ የሚያነሱት መጽናኛ አልፎ ተርፎም መልስ ስለሚፈልጉ ነው። በተለይ ደግሞ ይህን ጥያቄ ያነሱት ከባድ መከራ ደርሶባቸው ከሆነ መጽናኛ እንደሚያስፈልጋቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለውን መጽናኛ ይሰጣል? ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ አስፈላጊ የሆኑ ሦስት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን እንመልከት።

አንደኛ:- አምላክ መከራ እንዲኖር ለምን ፈቀደ? ብሎ መጠየቅ ስህተት አይደለም። አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ያለ ጥያቄ ማንሳት በአምላክ ላይ እምነት ማጣት ወይም ለእርሱ አክብሮት አለማሳየት እንደሆነ አድርገው በማሰብ ስጋት ያድርባቸዋል። ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ብዙ ጥሩ ሰዎች ከቅን ልብ ተነሳስተው ይህን ጥያቄ ይጠይቃሉ። ታማኙ ነቢይ ዕንባቆም አምላክን “ስለ ምን በደልን እንዳይ አደረግኸኝ? እንዴትስ ግፍ ሲፈጸም ትታገሣለህ? ጥፋትና ግፍ በፊቴ አለ፤ ጠብና ግጭት በዝቶአል” በማለት ጠይቆታል። (ዕንባቆም 1:3) ዕንባቆም እንዲህ ያለ ጥያቄ በመጠየቁ ይሖዋ አምላክ አልገሠጸውም። ከዚህ ይልቅ ሁላችንም እንድናነብበው ሲል የዚህ ታማኝ ሰው ጥያቄዎች ተመዝግበው እንዲቀመጡ አድርጎልናል።—ሮሜ 15:4

ሁለተኛ:- አምላክ ሥቃይህ እንደሚሰማው መረዳትህ አስፈላጊ ነው። እርሱ የማይቀረብና ምስጢራዊ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አምላክ “ፍትሕን ይወዳል” እንዲሁም ክፋትንና በክፋት ምክንያት እየደረሰ ያለውን መከራ ይጠላል። (መዝሙር 37:28፤ ምሳሌ 6:16-19) በኖህ ዘመን የነበረውን ሁኔታ ብንመለከት አምላክ በምድር ላይ ተንሰራፍቶ በነበረው ዓመጽ ምክንያት ‘ልቡ እጅግ አዝኗል።’ (ዘፍጥረት 6:5, 6) አምላክ አልተለወጠም፤ በአሁኑ ጊዜ እየተፈጸሙ ስላሉ ሁኔታዎችም ያለው ስሜት ያኔ ከተሰማው የተለየ አይደለም።—ሚልክያስ 3:6

ሦስተኛ:- የክፋት ድርጊቶች ምንጭ አምላክ አይደለም። ይህን ጉዳይ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ግልጽ ያደርገዋል። ለግድያና ለሽብርተኝነት ተጠያቂው አምላክ ነው የሚሉ ሰዎች ስሙን እያጠፉ ነው። ኢዮብ 34:10 ምን እንደሚል ተመልከት:- “ክፋትን ማድረግ ከእግዚአብሔር ዘንድ፣ በደልንም መፈጸም ሁሉን ከሚችል አምላክ ይራቅ።” በተመሳሳይም ያዕቆብ 1:13 “ማንም ሲፈተን፣ ‘እግዚአብሔር ፈተነኝ’ አይበል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንም፤ እርሱም ማንንም አይፈትንም” ይላል። ስለዚህ ከፍተኛ መከራ ከደረሰብህ አምላክ እንዳላመጣብህ እርግጠኛ ሁን።

ዓለምን የሚገዛው ማን ነው?

ከላይ የተጠቀሱት ሐሳቦች እንዳሉ ሆነው አምላክ አፍቃሪ፣ ፍትሐዊና ኃያል ከሆነ ዙሪያችን በመከራ የተሞላው ለምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት ያስፈልገናል። በመጀመሪያ ግን በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ አንድ የተሳሳተ ግንዛቤ መስተካከል ይኖርበታል። ብዙ ሰዎች ሁሉን ነገር የሚቆጣጠረውና ይህን ዓለም የሚገዛው ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ነው ብለው ያምናሉ። የአንድ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ፕሬዚዳንት “እርሱ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ያለች አንዲት አቶም ወይም ሞለኪውል የምታደርገውን እንቅስቃሴ እንኳ ይቆጣጠራል” በማለት ተናግረዋል። በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ብሎ ያስተምራል?

በፍጹም። ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የዓለም ገዥ ማን እንደሆነ የሚናገረውን ሐሳብ ሲያውቁ በጣም ይገረማሉ። ለምሳሌ ያህል 1 ዮሐንስ 5:19 ‘መላው ዓለም በክፉው ሥር እንደሆነ’ ይናገራል። ክፉው የተባለው ማን ነው? ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ክፉው “የዚህ ዓለም ገዥ” በማለት የጠራውን ሰይጣን ዲያብሎስን እንደሚያመለክት በግልጽ ተናግሯል። (ዮሐንስ 14:30) ታዲያ ይህን ማወቃችን በዚህ ዓለም ላይ ክፋትና መከራ የበዛበትን ምክንያት ግልጽ አያደርግልንም? ሰይጣን ጨካኝ፣ አታላይና በጥላቻ የተሞላ ነው፤ ዛሬ በሰው ልጆች ላይ እየደረሰ ላለው ሥቃይ መንሥኤዎቹ እነዚህ ባሕርያት ናቸው። ይሁንና አምላክ፣ ሰይጣን ይህን ዓለም እንዲገዛ ለምን ፈቀደለት?

በኤደን ገነት የተነሳው አወዛጋቢ ጉዳይ

አፍቃሪ የሆነና ቤተሰቡን በብቃት የሚያስተዳድር አንድ ወላጅ ልጆቹን ዋሽቷቸዋል፣ በእነርሱ ላይ ሥልጣኑን ያላግባብ ተጠቅሟል እንዲሁም ልጆቹን የሚጠቅማቸውን መልካም ነገር ነፍጓቸዋል ተብሎ በአደባባይ ቢከሰስ ምን ይሰማዋል? ይህ ወላጅ በከሳሹ ላይ የኃይል እርምጃ ቢወስድ የተነሱት ክሶች ሐሰት መሆናቸውን ማረጋገጥ ይችላል? በፍጹም አይችልም! እንዲያውም እንዲህ ያለውን እርምጃ መውሰዱ ክሶቹ ትክክል እንደሆኑ ሊያስመስል ይችላል።

ይህ ምሳሌ ይሖዋ አምላክ በሰው ልጅ ታሪክ መጀመሪያ ላይ ኤደን በተባለ ቦታ በእርሱ ላይ ለተነሳው ግድድር መልስ ለማስገኘት ጉዳዩን የያዘበትን መንገድ ለማብራራት ይጠቅመናል። አምላክ ምድራዊ ልጆቹ ለሆኑት ለመጀመሪያዎቹ ሰዎች ማለትም ለአዳምና ለሔዋን ዓላማውን አሳውቋቸዋል። ዓላማው ምድርን እንዲሞሉና እንዲገዙ ብሎም መላውን ምድር ወደ ገነትነት እንዲለውጡ ነበር። (ዘፍጥረት 1:28) ከዚህም በላይ እልፍ አእላፋት የሆኑ የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች አጓጊ በሆነው በዚህ ዓላማው በጣም ተደስተው ነበር።—ኢዮብ 38:4, 7፤ ዳንኤል 7:10

ይሖዋ ለጋስ የሆነ አምላክ እንደመሆኑ መጠን ለአዳምና ለሔዋን ጣፋጭ ፍራፍሬ የሞላበት በጣም ውብ የሆነ የአትክልት ቦታ መኖሪያ እንዲሆናቸው ሰጣቸው። ነገር ግን ከአንድ ዛፍ ማለትም “መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ” ብቻ እንዳይበሉ አዘዛቸው። አዳምና ሔዋን ከዚህ ዛፍ ባለመብላት ይሖዋ ክፉና መልካም ምን እንደሆነ ለልጆቹ የመወሰን መብት እንዳለው አምነው በመቀበል በአባታቸው ላይ እንደሚታመኑ ማሳየት ይችሉ ነበር።—ዘፍጥረት 2:16, 17

የሚያሳዝነው ግን ከአምላክ መንፈሳዊ ልጆች መሃል አንዱ የመመለክ ምኞት ስላደረበት ለሔዋን ከተከለከለው ፍሬ ቢበሉ ‘እንደማይሞቱ’ ነገራት። (ዘፍጥረት 2:17፤ 3:1-5) በዚህ መንገድ ይህ ክፉ መልአክ ማለትም ሰይጣን አምላክን ውሸታም ነው በማለት በግልጽ ተቃወመ! ከዚህም በተጨማሪ ሰይጣን፣ አምላክ ለአዳምና ለሔዋን ጠቃሚ የሆነ እውቀት ደብቋቸዋል በማለት ከሰሰው። ሰይጣን ሰዎች ለራሳቸው ምን ነገር ጥሩ ወይም መጥፎ እንደሆነ መወሰን ይችላሉ ባይ ነው። ነጥቡን በቀላሉ ለማስቀመጥ ያህል ሰይጣን አምላክን ጥሩ ገዥ እንዲሁም አባት የመሆን ብቃት የለውም ብሎ ከስሶታል፤ ይህን ሲል እርሱ ቢሆን ኖሮ የተሻለ ማድረግ እንደሚችል በተዘዋዋሪ መንገድ መናገሩ ነበር።

መሰሪና ተንኮል ያዘሉ ውሸቶች በመናገር ይህ መልአክ ራሱን ሰይጣን ዲያብሎስ አደረገ። ሰይጣን እና ዲያብሎስ የሚሉት ስሞች “ተቃዋሚ” እና “ስም አጥፊ” የሚል ፍቺ አላቸው። አዳምና ሔዋንስ ምን አደረጉ? ለአምላክ ጀርባቸውን በመስጠት ለሰይጣን ወገኑ።—ዘፍጥረት 3:6

ይሖዋ ዓመጸኞቹን ወዲያውኑ ሊያጠፋቸው ይችል ነበር። ነገር ግን ከላይ በምሳሌው ላይ እንደተመለከትነው የተነሳው ጥያቄ መፍትሔ የሚያገኘው የአጸፋ እርምጃ በመውሰድ አይደለም። ከዚህም በተጨማሪ ሰይጣን ይህን ጥያቄ ሲያስነሳ በሚሊዮን የሚቆጠሩ መላእክት መስማታቸውን መዘንጋት አይኖርብንም። እንዲያውም ቁጥራቸው ባይገለጽም በርካታ መላእክት ከጊዜ በኋላ ሰይጣንን በዓመጹ የተባበሩት ሲሆን በዚህ ተግባራቸው ራሳቸውን አጋንንት አድርገዋል።—ማርቆስ 1:34፤ 2 ጴጥሮስ 2:4፤ ይሁዳ 6

አምላክ ጣልቃ ያልገባው ለምንድን ነው?

ሰይጣን አዳምና ሔዋንን አታሎ ያለ ፈጣሪያቸው እርዳታ ራሳቸውን ለማስተዳደር እንዲመርጡ አደረጋቸው። በውጤቱም እውነተኛ ነጻነት ያለው ሳይሆን በራሱ በሰይጣን አመራር ሥር የወደቀ ቤተሰብ ተመሠረተ። የዚህ ቤተሰብ አባላት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ‘አባታቸው’ በሆነው በዲያብሎስ ተጽዕኖ ሥር ሆነው የራሳቸውን ግቦችና የሥነ ምግባር ደንቦች መከተል ጀመሩ። (ዮሐንስ 8:44) ነገር ግን የመረጡት የሕይወት መንገድ እውነተኛ ነጻነትና ዘላቂ ደስታ አስገኝቶላቸዋል? ይሖዋ ይህ እንደማይሆን በሚገባ ያውቅ ነበር። ያም ሆኖ በኤደን የተነሳው ጥያቄ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መልስ ማግኘት የሚችለው በዚህ መንገድ ብቻ በመሆኑ ይሖዋ ዓመጸኞቹ የመረጡትን ጎዳና እንዲሞክሩት ፈቀደላቸው።

የሰው ልጅ ከ6,000 ለሚበልጡ ዓመታት የተለያዩ አገዛዞችንና የሥነ ምግባር ደንቦችን በመሞከር አሁን ያለውን ዓለም አስገኝቷል። በውጤቱ ደስተኛ ነህ? የሰው ልጅ እውነተኛ ደስታ፣ ሰላምና አንድነት አግኝቷል? በግልጽ ማየት እንደሚቻለው መልሱ አላገኘም ነው። ከዚህ ይልቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደተገለጸው ጦርነቶች፣ ረሃብ፣ የተፈጥሮ አደጋዎች፣ በሽታና ሞት የሰውን ልጅ ‘በከንቱነት’ ስሜት፣ ‘በሥቃይና’ “በመቃተት” እንዲኖር አድርገውታል።—ሮሜ 8:19-22፤ መክብብ 8:9

ይሁን እንጂ አንዳንዶች ‘አምላክ መጥፎ ነገሮች እንዳይደርሱ ያላደረገው ለምንድን ነው?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። እንደ እውነቱ ከሆነ እንዲህ ማድረጉ ፍትሐዊ የማይሆን ከመሆኑም በላይ በአምላክ ላይ ማመጽ ምንም ዓይነት መዘዝ የማያስከትል እንደሆነ ስለሚያስመስል የተነሳውን አወዛጋቢ ጉዳይ ያድበሰብሰው ነበር። ስለዚህ ይሖዋ፣ ሰዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እርሱን ባለመታዘዛቸው ምክንያት የመጡትን መከራዎችና አሳዛኝ ሁኔታዎች ለማስቀረት በስውር የወሰደው ምንም እርምጃ የለም። * ይሖዋ፣ ‘የሰይጣን ዓለም ደስታ የሚገኝበትን ቁልፍ ስለሚያውቅ ሊሳካለት ይችላል’ የሚለውን ጎጂ ውሸት ፍጽሞ አይደግፍም። የሆነ ሆኖ ይሖዋ አሁን እየተከሰቱ ላሉት ነገሮች ግድ የለሽ አይደለም። እንዲያውም ከዚህ በታች እንደምንመለከተው ይሖዋ እርምጃ እየወሰደ ነው።

‘አባቴ እየሠራ ነው’

እነዚህ ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት አምላክ እጁን አጣጥፎ የሚከሰቱትን ሁኔታዎች እየተመለከተ እንዳልሆነ ያሳያሉ። (ዮሐንስ 5:17) ከዚህ ይልቅ በኤደን ዓመጽ ከተቀሰቀሰ ጀምሮ በትጋት እየሠራ ነው። ለምሳሌ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ወደፊት የሚነሳው ‘ዘር’ ሰይጣንንና የእርሱን ታማኝ ደጋፊዎች እንደሚቀጠቅጣቸው የሰጠውን ተስፋ እንዲጽፉ አድርጓል። (ዘፍጥረት 3:15) በተጨማሪም በዘሩ አማካኝነት አምላክ መስተዳድር ማለትም ታዛዥ የሰው ልጆችን የሚባርክ ብሎም ሁሉንም የመከራ ምንጮች ሌላው ቀርቶ ሞትን እንኳ የሚያስወግድ ሰማያዊ መንግሥት አቋቁሟል።—ዘፍጥረት 22:18፤ መዝሙር 46:9፤ 72:16፤ ኢሳይያስ 25:8፤ 33:24፤ ዳንኤል 7:13, 14

ይሖዋ እነዚህ አስደሳች ተስፋዎች ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙ ሲል የመንግሥቲቱ ዋነኛ ገዥ የሚሆነውን ወደ ምድር ላከ። እርሱም የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ገላትያ 3:16) ኢየሱስ ከተላከበት ዓላማ ጋር በሚስማማ መልኩ ትምህርቱ ያተኮረው በአምላክ መንግሥት ላይ ነበር። (ሉቃስ 4:43) እንዲያውም ክርስቶስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ በሚመጣበት ወቅት የሚያከናውናቸውን ነገሮች ለናሙና ያህል አሳይቷል። በሺህ የሚቆጠሩ የተራቡ ሰዎችን መግቧል፣ በሽተኞችን ፈውሷል፣ የሞቱትን አስነስቷል አልፎ ተርፎም ኃይለኛ ማዕበል ጸጥ በማሰኘት በተፈጥሮ ኃይሎች ላይ ያለውን ሥልጣን አሳይቷል። (ማቴዎስ 14:14-21፤ ማርቆስ 4:37-39፤ ዮሐንስ 11:43, 44) መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን አስመልክቶ “በእግዚአብሔር የተሰጡ ተስፋዎች ሁሉ፣ ‘አዎን’ የሚሆኑት በእርሱ ነው” በማለት ይናገራል።—2 ቆሮንቶስ 1:20

ኢየሱስን ሰምተው “ከዓለም” ማለትም ከአምላክ ከራቀውና ሰይጣን ከሚገዛው ዓለም ተለይተው የሚወጡ ሰዎችን የይሖዋ ቤተሰብ በደስታ ይቀበላቸዋል። (ዮሐንስ 15:19) ይህ የእውነተኛ ክርስቲያኖች ዓለም አቀፋዊ ቤተሰብ፣ በፍቅር የሚመራና ለሰላም ያደረ ከመሆኑም በላይ የጭፍን ጥላቻንና የዘረኝነትን ርዝራዥ ነቅሎ ለማውጣት ባለው ቁርጥ አቋም ተለይቶ ይታወቃል።—ሚልክያስ 3:17, 18፤ ዮሐንስ 13:34, 35

እውነተኛ ክርስቲያኖች ይህን ዓለም ከመደገፍ ይልቅ ኢየሱስ በማቴዎስ 24:14 ላይ የተናገረውን ትእዛዝ በመከተል የአምላክን መንግሥት ይደግፋሉ እንዲሁም ይሰብካሉ። እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች አስብባቸው:- ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ በዓለም ዙሪያ እየሰበኩ ያሉት እነማን ናቸው? ዓለም አቀፋዊ የወንድማማች አንድነት ስላላቸው በጦርነትና በሚከፋፍሉ ብሔራዊና የጎሳ ግጭቶች ለመካፈል ፈቃደኛ ያልሆኑ እነማን ናቸው? እንዲሁም የሚከተሏቸው የሥነ ምግባር ደንቦች በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ይኑራቸውም አይኑራቸው አኗኗራቸውን የአምላክ ቃል እንዲመራላቸው የሚፈቅዱ እነማን ናቸው? (1 ዮሐንስ 5:3) ብዙዎች የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ያለ አቋም እንዳላቸው ተመልክተዋል። ማስረጃዎቹን ራስህ እንድትመረምራቸው እናበረታታሃለን።

የአምላክን አገዛዝ ምረጥ!

ከአምላክ የራቀውና በሰይጣን እየተመራ ያለው የሰው ልጅ፣ መከራና ሥቃይ የበዛበት እንዲሁም ተስፋ የቆረጠ ዓለም ገንብቷል። ምድር ራሷም ብትሆን እየተበላሸች ነው! በሌላ በኩል ይሖዋ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት መለወጥ የቻለና ለብዙዎች እውነተኛ ተስፋ የሚሰጥ ሰማያዊ መንግሥት አቋቁሟል። (1 ጢሞቴዎስ 4:10) አንተ የትኛውን ትመርጣለህ?

ለመምረጥ ጊዜው አሁን ነው። አምላክ ሰይጣንም ሆነ ይህ ክፉ ዓለም ለዘላለም እንዲቀጥሉ አይፈቅድም። አምላክ ይህችን ምድር ገነት ለማድረግ ያለው የመጀመሪያ ዓላማ አልተለወጠም። ይህን ዓላማውን ከግብ ለማድረስ የእርሱ መንግሥትና ደጋፊዎቹ ከዕለት ወደ ዕለት እየተጠናከሩ ይሄዳሉ፤ በተቃራኒው በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም አምላክ በቃ እስኪለው ድረስ ‘በምጥ’ ጣር ውስጥ ይኖራል። (ማቴዎስ 24:3, 7, 8) ስለዚህ ከቅን ልቦና ተነሳስተህ “ለምን?” ብለህ ወደ አምላክ ጮኸህ ከሆነ መጽናኛና ተስፋ በያዘው የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በመተማመን ለእርሱ ጆሮህን ክፈት። ሌላው ቀርቶ አሁን እንኳ የሐዘን እንባህ ወደ ደስታ እንባ ሊለወጥ ይችላል።—ማቴዎስ 5:4፤ ራእይ 21:3, 4

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.19 አምላክ በሰው ልጆች ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ በመግባት አንዳንድ እርምጃዎች የወሰደባቸው ጊዜያት ቢኖሩም ይህን ያደረገው አሁን ያለውን ዓለም ለመደገፍ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ እነዚህ እርምጃዎች ዓላማውን ከሚያስፈጽምበት መንገድ ጋር የተያያዙ ናቸው።—ሉቃስ 17:26-30፤ ሮሜ 9:17-24

[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የሰው አገዛዝ ባስገኘው ውጤት ረክተሃል?

[ምንጭ]

ልጅ:- © J. B. Russell/Panos Pictures; የምታለቅሰው ሴት:- © Paul Lowe/Panos Pictures

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ገነትን መልሶ ያቋቁማል፤ አልፎ ተርፎም ሙታንን ያስነሳል