በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ላይ በየቀኑ 5.7 ሚሊዮን የማታለል ሙከራዎች ይደረጋሉ።—መጋዚን፣ ስፔን

“በጃፓን እስከ 2005 ባሉት ስምንት ተከታታይ ዓመታት ውስጥ የራሳቸውን ሕይወት ያጠፉ ሰዎች ቁጥር በየዓመቱ ከ30,000 በላይ እንደሆነ ተመዝግቧል።” ጃፓን በዓለም ላይ ከፍተኛ ቁጥር ከተመዘገበባቸው አገሮች አንዷ ናት።—ማይንቺ ዴይሊ ኒውስ፣ ጃፓን

“የሰው ልጆች እንቅስቃሴ ባለፉት 500 ዓመታት 844 የሚሆኑ የዱር እንስሳት ከምድር ገጽ እንዲጠፉ ምክንያት ሆኗል።”—አይ ዩ ሲ ኤን፣ የዓለም የአካባቢ ጥበቃ ማኅበር፣ ስዊዘርላንድ

መንግሥት ባወጣው አኃዝ መሠረት 6 በመቶ የሚሆኑት ብሪታንያውያን ወንዶችና ሴቶች፣ ተመሳሳይ ጾታ ካላቸው ሰዎች ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ይፈጽማሉ። በ2005 የጸደቀው ሕግ “ተመሳሳይ ጾታ ያላቸው ሰዎች ‘እንዲጋቡ’ የሚፈቅድ ሲሆን” ከማንኛውም ወንድና ሴት ባለትዳር ያልተለየ መብት ይሰጣቸዋል።—ዘ ዴይሊ ቴሌግራፍ፣ እንግሊዝ

የበረዶ ግግሮች በፍጥነት እየተንሸራተቱ ነው

ሳይንስ መጽሔት እንደዘገበው ከሆነ “በግሪንላንድ ያሉት በርካታ ግግር በረዶዎች የሚንሸራተቱበት ፍጥነት በመጨመሩ የበረዶው ንጣፍ እያነሰ ሄዷል።” ባለፉት አምስት ዓመታት በግሪንላንድ ያሉ በርካታ የበረዶ ግግሮች የሚንሸራተቱበት ፍጥነት በእጥፍ ያህል በመጨመሩ በየዓመቱ ከ12 ኪሎ ሜትር በላይ እየተንሸራተቱ እንደሆነ የሳተላይት መረጃዎች ይጠቁማሉ። ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ የበረዶ ግግሮቹ በየዓመቱ የሚቀንሱበት መጠን ከ90 ወደ 220 ኪሎ ሜትር ኩብ ጨምሯል። በመሆኑም ሳይንቲስቶች “ወደፊት የባሕር ወለል አሁን ከሚገመተው የበለጠ ከፍ ሊል እንደሚችል” ይጠቁማሉ።

አብያተ ክርስቲያናት የዳርዊንን ልደት አከበሩ

በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኙ ወደ 450 የሚጠጉ ክርስቲያን ነን የሚሉ አብያተ ክርስቲያናት የቻርልስ ዳርዊንን 197ኛ የልደት በዓል በየካቲት 2006 አክብረዋል። ክብረ በዓሉ፣ የዳርዊን “የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ከክርስትና እምነት ጋር የሚጣጣም እንደሆነና ክርስቲያኖች ከሃይማኖትና ከሳይንስ የግድ አንዱን መምረጥ እንደማያስፈልጋቸው ለማሳየት ታስበው የተዘጋጁ ፕሮግራሞችንና ስብከቶችን” ያካተተ ነበር። ባዮሎጂስት እንዲሁም በዊስኮንሲን-ኦሽኮሽ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍና ሳይንስ ማዕከል ኃላፊና የዝግጅቱ አስተባባሪ የሆኑት ማይክል ዚመርማን “[ከሃይማኖትና ከሳይንስ] የግዴታ አንዱን መምረጥ አስፈላጊ አይደለም፤ በሁለቱም ማመን ይቻላል” ማለታቸውን ቺካጎ ትሪቡን ዘግቧል።

በሥራ ቦታ የሚያጋጥም ጨዋነት የጎደለው ምግባር

ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል የተባለው መጽሔት “በሥራ ቦታ የሚያጋጥም ጨዋነት የጎደለው ምግባር የሠራተኞችን ጊዜ፣ ጉልበትና ተሰጥኦ በማባከን አንድን ድርጅት ለኪሳራ ሊዳርግ ይችላል” በማለት ዘግቧል። ወደ ሦስት ሺህ በሚጠጉ ሰዎች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው 90 በመቶ የሚሆኑት “በመሥሪያ ቤታቸው ውስጥ ጨዋነት የጎደለው ምግባር አጋጥሟቸዋል።” ከእነዚህ ውስጥ 50 በመቶ የሚሆኑት “ስለተፈጠረው ችግር በማብሰልሰል የሥራ ሰዓታቸውን እንዳባከኑ” ሲገልጹ “25 በመቶዎቹ ደግሞ የሥራ ትጋታቸው እንደቀነሰ” ተናግረዋል፤ ከዚህም በተጨማሪ ከስምንቱ ሰዎች አንዱ በዚህ ምክንያት ሥራውን እንደለቀቀ ተዘግቧል። ጆርናል መጽሔት የሳውዘርን ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ አስተዳዳሪ ፕሮፌሰር የሆኑትን ክርስቲን ፖርዝን በመጥቀስ እንዲህ ሲል አትቷል:- “ሠራተኞች የሥራ ትጋታቸው መቀነሱ፣ ከሥራ መቅረታቸው ሌላው ቀርቶ ስርቆት መኖሩም ጭምር በድርጅቱ ውስጥ ጨዋነት የጎደለው ምግባር በተደጋጋሚ እንደሚያጋጥማቸው ይጠቁማል።”

በውቅያኖስ ላይ የሚንሳፈፍ የቆሻሻ ጥርቅም

በ2006 መጀመሪያ አካባቢ፣ በውቅያኖስ ላይ የሚንሳፈፍ ከፍተኛ መጠን ያለው የቆሻሻ ጥርቅም “በማዕበል ተገፍቶ በስተ ደቡብ ወደ ሐዋይ በመወሰዱ በደሴቲቱ የባሕር ዳርቻዎች ላይ የተጣሉ የዓሣ ማስገሪያ ቁሳቁሶችና የፕላስቲክ ቆሻሻዎች ተከማችተዋል” በማለት ዘ ሆነሉሉ አድቨርታይዘር ዘግቧል። በሰሜን ፓስፊክ ላይ የተጣሉት ብዙዎቹ ተንሳፋፊ ቆሻሻዎች በባሕር ማዕበል እየተገፉ ጸጥተኛ ወደሆነው የባሕሩ ክፍል ይወሰዳሉ፤ ይሁንና በአንዳንድ የአየር ሁኔታ ለውጥ ምክንያት ቆሻሻዎቹ መንገዳቸውን ቀይረው ወደ ሐዋይ እያመሩ ነው። በ2005 “ከ2,000 በላይ ቁርጥራጭ ቆሻሻ” እንዲሁም ከ100 በላይ የዓሣ ማስገሪያ መረቦች ተገኝተዋል። ይህ ቆሻሻ ለባሕር እንስሳት ጠንቅ ነው። የአልጋሊታ የባሕር ምርምር ተቋም መሥራች የሆኑት ቻርልስ ሞር “በውቅያኖስ ውስጥ በተፈጥሮ የሚገኙ ምግቦችን ብቻ የተመገቡ ዓሦችን ማግኘት አይቻልም፤ ሁሉም ዓሦች የፕላስቲክ ቁርጥራጮችን ይበላሉ” ብለዋል።