በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘የምግብ ሰዓት ይበልጥ እንድንቀራረብ አድርጎናል’

‘የምግብ ሰዓት ይበልጥ እንድንቀራረብ አድርጎናል’

‘የምግብ ሰዓት ይበልጥ እንድንቀራረብ አድርጎናል’

ቤተሰብህ በቀን ቢያንስ አንድ ጊዜ አብሮ ይመገባል? ጥድፊያ በሞላበት በዛሬው ጊዜ ብዙ ቤተሰቦች ምግብ የሚመገቡት በተናጠል፣ በፈለጉበት ጊዜና እንዳመቻቸው ሆኗል። ሆኖም በቤተሰብ ደረጃ አብሮ መመገብ፣ የረሃብን ስሜት ከማስታገስ በተጨማሪ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ፍላጎቶች ለማሟላት ይኸውም ሞቅ ያለ ውይይት ለማድረግና የጠበቀ የቤተሰብ ትስስር ለመመሥረት የሚያስችል አጋጣሚ ይፈጥራል።

ኤልጊርዴስ፣ ከባለቤቱ ከሪሜ እና ከሦስት ሴቶች ልጆቹ ጋር በሰሜን አውሮፓ በምትገኘው በሊቱዌኒያ ይኖራል። ኤልጊርዴስ እንዲህ ይላል:- “ሰብዓዊ ሥራ የምሠራና ሴቶች ልጆቼ ተማሪዎች ቢሆኑም እንኳ አንድ ላይ ሆነን እራት መብላት እንድንችል ፕሮግራማችንን አስተካክለናል። በምግብ ሰዓት ሁላችንም በቀኑ ውስጥ ያጋጠሙንን ነገሮች አንስተን በነጻነት እንነጋገራለን። ከዚህም በተጨማሪ ያጋጠሙንን ችግሮች፣ የሚያሳስቡንን ሁኔታዎች፣ እቅዳችንን እንዲሁም የምንወዳቸውንና የምንጠላቸውን ነገሮች እያነሳን እናወራለን። በዚህ ወቅት መንፈሳዊ ነገሮችንም ጭምር እንወያያለን። የምግብ ሰዓት ይበልጥ እንድንቀራረብ እንዳደረገን ምንም ጥርጥር የለውም።”

ሪሜ ደግሞ እንዲህ ትላለች:- “ከሴቶች ልጆቼ ጋር አንድ ላይ ሆነን ምግብ ማዘጋጀታችን የልባችንን አውጥተን እንድንወያይ አስችሎናል። ልጆቼም ወጥ ቤት ውስጥ አብረን መሥራታችን የሚያስደስታቸው ከመሆኑም ሌላ የሚጠቅማቸውን ሙያ ይማራሉ። በመሆኑም እየሠራን አስደሳች ጊዜ ማሳለፍ ችለናል።”

ኤልጊርዴስ፣ ሪሜና ሴቶች ልጆቻቸው አንድ ላይ ሆነው ለመመገብ ጊዜ በመመደባቸው በርካታ ጥቅሞችን እያገኙ ነው። እናንተም እንዲህ የማታደርጉ ከሆነ በቤተሰብ አንድ ላይ ሆናችሁ ቢያንስ በቀን አንዴ የምትመገቡበትን ሁኔታ ለምን አታመቻቹም? ነጠላ ወላጅ ብትሆኑም እንኳ ይህን ማድረግ ትችላላችሁ። በቤተሰብ አንድ ላይ ለመመገብ ስትሉ ምንም ያህል መሥዋዕትነት ብትከፍሉ የምታገኙት ጥቅም ከዚያ በጣም የላቀ ነው።