የኩዌከሮች “ቅዱስ ሙከራ”
የኩዌከሮች “ቅዱስ ሙከራ”
ሐምሌ 1656 ከዌስት ኢንዲስ ባርቤዶስ የተነሳች ስዋሎው የተባለች መርከብ በቦስተን፣ ማሳቹሴትስ አሁን ዩናይትድ ስቴትስ በምትባለው አገር መልሕቋን ጣለች። የማሳቹሴትስ ግዛት ምክትል አስተዳዳሪ የሆኑት ሪቻርድ ቤሊንግሃም፣ ሜሪ ፊሸር እና አን ኦስተን የተባሉት ሴቶች ከመርከቧ ሳይወርዱ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ትእዛዝ አስተላለፉ። ከእነዚህ ሴቶች ንብረቶች መሃል “በካይ፣ የተወገዙና አምላክን የሚያዋርዱ ትምህርቶች” ይዘዋል የተባሉ 100 መጻሕፍት ይገኙ ነበር።
እነዚህ መጻሕፍት በአንድ የገበያ ስፍራ ላይ ተቃጠሉ። ከዚያም ሁለቱ ሴቶች ታሠሩ፣ እንዲሁም ጠንቋዮች መሆናቸውን የሚጠቁም ምልክት በሰውነታቸው ላይ ለማግኘት ልብሳቸውን አስወልቀው መረመሯቸው። ሴቶቹ የታሰሩበት ክፍል መስኮት እንዲታሸግና ለአምስት ሳምንታት በጨለማ ውስጥ እንዲቆዩ ተደረገ። እነርሱን ለማነጋገር የሞከረ ሰው አምስት ፓውንድ መቀጮ ይከፍል ነበር። በመጨረሻም ሜሪ ፊሸር እና አን ኦስተን ወደመጡበት ወደ ባርቤዶስ ተላኩ።
በወቅቱ የነበረ አንድ ታሪክ ጸሐፊ “ድንበራችሁ በታላቅ ሰራዊት የተወረረ ይመስል የሁለቱ ሴቶች መምጣት ይህን ያህል ያሸበራችሁ ለምንድን ነው?” በማለት ዳኞቹን ጠይቋቸው ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ “አደገኛ” የተባሉት እነዚህ ሁለት ሴቶች ወደ ሰሜን አሜሪካ የመጡ የመጀመሪያዎቹ የኩዌከሮች ሚስዮናውያን ነበሩ። ኩዌከሮች እነማን ነበሩ? ይህን ያህል ስጋት የፈጠሩትስ ለምን ነበር?
ሶሳይቲ ኦቭ ፍሬንድስ
ኩዌከሮች ወይም ሪሊጅየስ ሶሳይቲ ኦቭ ፍሬንድስ የተነሱት በ17ኛው ክፍለ ዘመን፣ በእንግሊዝ አገር ነበር። የዚህ ሃይማኖት መሥራች የሆነው ጆርጅ ፎክስ (1624-1691) የተወለደው በሌስተርሻየር ሲሆን የሸማኔ ልጅ ነበር። ፎክስ እንደተናገረው ከሆነ አንድ ተዓምራዊ ድምፅ ከሰማ በኋላ የማንም መካከለኛነት ሳያስፈልገው ከአምላክ ጋር በቀጥታ መገናኘትና የእውቀት ብርሃን መቀበል እንደሚችል ሆኖ ተሰምቶታል። ኤ ሪሊጅየስ ሂስትሪ ኦቭ ዚ አሜሪካን ፒፕል የተባለው መጽሐፍ “ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ሶሳይቲ ኦቭ ፍሬንድስ በ1652 እንደተመሠረተ ሲታመን ቆይቷል” በማለት ይገልጻል።
ሶሳይቲ ኦቭ ፍሬንድስ፣ ኩዌከሮች (ኩዌክ የሚለው የእንግሊዘኛ ቃል መንቀጥቀጥ የሚል ትርጉም አለው) ተብለው የተጠሩት ለምን ነበር? አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ “መለኮታዊ ራእይ ከመቀበላቸው በፊት ስለሚንዘፈዘፉ” መሆኑን ገልጿል። ሌላ ሳይክሎፒዲያ ደግሞ “ለአምላክ ወደር የለሽ ቅድስናና ግርማ ካላቸው ጥልቅ አክብሮት የተነሳ ስለሚንቀጠቀጡ” እንደሆነ ተናግሯል። የኩዌከሮች ዓላማ ሃይማኖታዊ እውነትን ማግኘትና የቀድሞውን ክርስትና መልሶ ማቋቋም ነበር።
እነዚህ ሰዎች አመራር ለማግኘት በመንፈስ ቅዱስ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጠቀሱት ነቢያት፣ በክርስቶስ ሐዋርያትና መንፈሳዊ እውነት ያስገኛል በሚሉት ውስጣዊ “ብርሃን” ወይም “ድምፅ” እንደሚታመኑ ይናገራሉ። በመሆኑም *
ስብሰባዎች ሰዎች በቡድን ሆነው በጸጥታ የሚቀመጡባቸውና እያንዳንዱ ሰው በግለሰብ ደረጃ የአምላክን መመሪያ ለማግኘት የሚጥርባቸው ቦታዎች ነበሩ። መለኮታዊ መልእክት የተቀበለ ማንኛውም ሰው መናገር ይችላል።ኩዌከሮች ፍጹም ሐቀኛና ሰላማዊ በመሆን፣ ቀላል ኑሮ በመምራት እንዲሁም በፍትሕ ያምናሉ። ከዚህም በተጨማሪ ሴቶችን ጨምሮ ሁሉም ክርስቲያኖች በሃይማኖታዊ አገልግሎት ውስጥ መካፈል አለባቸው የሚል አቋም አላቸው። ኩዌከሮች በሃይማኖት ድርጅት አስፈላጊነት አለማመናቸው፣ በድምቀት በሚከበሩ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች አለመካፈላቸውና በቀሳውስት ሳይሆን በውስጣችን ባለ ድምፅ እንመራለን ማለታቸው በሌሎች ዘንድ ፍርሃትና ጥርጣሬ ማሳደሩ አልቀረም። ይበልጥ አሳሳቢ የሆነው ደግሞ የሚስዮናዊነት ቅንዓታቸው ሲሆን ይህም ቁጣንና የሕዝብ ዓመጽን ከማስነሳቱም በላይ ባለ ሥልጣኖች ጣልቃ እንዲገቡ አድርጓል።
በእንግሊዝ፣ ኩዌከሮች ለስደትና ለእስር የተዳረጉ ሲሆን በኒው ኢንግላንድ ደግሞ ከአካባቢው እንዲባረሩ እንዲያውም እንዲገደሉ ጭምር ተደርጓል። ለምሳሌ ያህል፣ ከ1659 እስከ 1661 ባለው ጊዜ ውስጥ ሚስዮናውያን የሆኑት ሜሪ ዳየር፣ ዊልያም ሌድራ፣ ዊልያም ሮቢንሰንና ማርማዱክ ስቲፈንሰን በቦስተን ተሰቅለዋል። ሌሎች ደግሞ በካቴና ታስረዋል፣ በጋለ ብረት ተተኩሰዋል፣ አሊያም ተገርፈዋል፤ እንዲያውም አንዳንዶች ጆሯቸው ተቆርጧል። ዊልያም ብሪንድ የተባለውን ሰው ልብሱን አስወልቀው ሬንጅ በተነከረ ጅራፍ 117 ጊዜ ጀርባውን ገርፈውታል። እንዲህ ዓይነቱ የጭካኔ ድርጊት ቢፈጸምባቸውም እንኳ ኩዌከሮች በቁጥር ይጨምሩ ነበር።
ዊልያም ፔንና ያደረገው “ቅዱስ ሙከራ”
ከ1681 ጀምሮ በሰሜን አሜሪካ የኩዌከሮች ሕይወት በአስገራሚ ሁኔታ መለወጥ ጀመረ። የሶሳይቲ ኦቭ ፍሬንድስ አዲስ ተከታይ የሆነ ዊልያም ፔን (1644-1718) የተባለ አንድ እንግሊዛዊ ወጣት አገርን በማስተዳደር ረገድ “ቅዱስ ሙከራ” የተባለለትን፣ በኩዌከሮች ጽንሰ ሐሳብ ላይ የተመሠረተና በእነርሱ የሚመራ ቅኝ ግዛት አቋቋመ። ፀረ ጦርነት አቋም የነበራቸው የእንግሊዝ የባሕር ኃይል ዋና አዛዥ ልጅ የሆነው ይህ ወጣት አመለካከቱን ለመስበክና በጽሑፍ ለመግለጽ በመሞከሩ ታስሮ ነበር።
የእንግሊዙ ንጉሥ ከፔን አባት የተበደሩትን ለመክፈል ሲሉ በሰሜን አሜሪካ ለፔን ሰፊ መሬት ሰጡት። ንጉሡ፣ ወጣቱ ፔን አዲስ ባቋቋመውና ለአባቱ ለአድሚረል ፔን መታሰቢያነት ፔንስልቬንያ ማለትም “የፔን ደን” ብሎ በሰየመው ግዛቱ ውስጥ ገደብ የለሽ መብት እንዲኖረው ፈቃድ ሰጥተውት ነበር። ይህ ስፍራ ሁሉም ዓይነት ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች ሃይማኖታዊ ነጻነት የሚያገኙበት ቦታ እንዲሆን ታስቦ ነበር።
ፔን በመጀመሪያ የአክስቱ ልጅ የሆነው ዊልያም ማርክሃም እርሱን በመወከል ወደ አሜሪካ እንዲሄድና በአዲሱ ግዛቱ ውስጥ የሚኖሩት ጥቂት አውሮፓውያን ለእርሱ በታማኝነት እንዲገዙ እንዲያደርግ እንዲሁም የአገሩ ተወላጆች ከሆኑት አሜሪካውያን መሬት እንዲገዛ ላከው። በ1682፣ ፔን የዴላዌርን ወንዝ በማቋረጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አዲሱን ግዛቱን ለማየት በቃ። ቀጥሎም በሻክአማክሶን (የፊላደልፊያ ክፍል በሆነችው በአሁኗ ኬንዚንግተን) ከአገሬው ተወላጆች ጋር ፍትሕ የተሞላበት ድርድር አደረገ። ከዚህ በኋላ፣ ከሻክአማክሶን ብዙም ሳይርቅ አዲስ ሰፈራ ለማቋቋም አቀደ፤ ይህንንም ስፍራ ፊላደልፊያ ማለትም “የወንድማማች ፍቅር” ብሎ የሰየመው ሲሆን አካባቢው ፈጣን እድገት ይታይበት ጀመር።
ፔን ወደ እንግሊዝ ተመልሶ ሰዎች አዲስ ወዳቋቋመው ግዛት እንዲሄዱ በማበረታታት አካባቢውን ያስተዋውቅ ነበር። አዲሱ ቅኝ ግዛቱ ለም መሬትና ድንቅ ወንዝ ያለው እንዲሁም በደን የተሸፈነ፣ የዱር አራዊትና የእንስሳት ቆዳ እንደልብ የሚገኝበት እንደሆነ ገልጿል። ለማቋቋም ያሰበው አዲስ መንግሥትም ሃይማኖታዊ መቻቻል ያለበትና ሰላም የሰፈነበት እንደሚሆን ቃል ገብቶ ነበር። ነጋዴዎችን፣ ድሆችን፣ ለመልካም አገዛዝ ይረዳሉ የሚባሉ ሐሳቦችን የሚያመነጩ ግለሰቦችን ጨምሮ ማንኛውም ሰው ወደ ግዛቲቱ መምጣት ይችል ነበር።
ይህ ግብዣ፣ በአውሮፓ ውስጥ ካለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እፎይታ እናገኛለን ብለው ተስፋ ያደረጉ በእንግሊዝና በሰሜናዊ አየርላንድ የሚኖሩ ኩዌከሮችን ትኩረት መሳቡ አልቀረም። በራየን ወንዝ አካባቢ ካሉ የአውሮፓ አገሮችም ሜኖናይቶችና ከእነርሱ ጋር የሚመሳሰሉ ሌሎች ቡድኖች ወደ ግዛቲቱ መምጣት ጀመሩ። ከመጀመሪያዎቹ ሰፋሪዎች መካከል አብዛኞቹ ኩዌከሮች የነበሩ ሲሆን ፔንም የወደፊቱ ጊዜ ብሩህ እንደሚሆን ተናግሮ ነበር። ፔን በ1683 እንዲህ በማለት ጽፏል:- “የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ሁለት ጊዜ ተሰብስቦ . . . ከሰባ ያላነሱ ሕጎችን ያጸደቀ ሲሆን ይህ ነው የሚባል ልዩነት አልተፈጠረም።” ይህን የመሰለው ብሩህ ተስፋ ግን ብዙም አልዘለቀም።
ሙከራው ከሸፈ
የፔን ግዛት ሕገ መንግሥት ሁሉም ሰው ኅሊናው የፈቀደውን እንዲያደርግ ነጻነት ይሰጥ ነበር። በመሆኑም ሕጉን በማስከበር የኅብረተሰቡን ደኅንነት ለማስጠበቅ ሲባል ኃይል መጠቀም አስገዳጅ በሚሆንበት ጊዜ የኩዌከሮች ፀረ ጦርነት አቋም ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ የሚሄድ ችግር አስከተለ። መጀመሪያ ላይ፣ ፔን ራሱ እንዳለው ‘አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በጎረቤቶቻቸው ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ የሚወስዱ’ ኩዌከር ያልሆኑ ሰዎችን ምትክ አድርጎ በመሾም ችግሩን ለጊዜው መፍታት ችሎ ነበር። በ1689 ከፈረንሳይ ጋር መዋጋታቸው የማይቀር መስሎ በታየ ጊዜ ግን የኩዌከሮች የሥነ ምግባር አቋም ይበልጥ ተፈታታኝ ሁኔታ ውስጥ ወደቀ።
ከዚህም በተጨማሪ፣ ኩዌከር ያልሆኑ በርካታ አዲስ ሰፋሪዎች ወደ ግዛቲቱ መምጣታቸውና የአገሩ ተወላጅ ከሆኑት አሜሪካውያን መሬት መቀማታቸው ችግሩን አባባሰው። በመሆኑም ኩዌከሮች በቁጥር እያነሱ በሄዱ መጠን ከአገሩ ተወላጆች ጋር የተፈጠረው አለመግባባትም ይበልጥ እየከረረ ሄደ።
በ1756 አገረ ገዥውና ምክር ቤቱ በዴላዌርና በሾኒ ጎሳዎች ላይ ጦርነት ሲያውጁ የኩዌከሮች ፖለቲካዊ ሥልጣን ፍጻሜ ሆነ። ከዚህ ጋር ተያይዞ ኩዌከሮች ሥልጣናቸውን የለቀቁ ሲሆን የአገዛዝ ሥርዓታቸውም አከተመ። በዚህ ሁኔታ ፔን ግዛቱን ለማስተዳደር ያደረገው “ቅዱስ ሙከራ” ከ75 ዓመታት በኋላ አበቃለት።
ጊዜ እያለፈ ሲሄድ፣ ኩዌከሮች በቁሳዊ ነገሮች በመበልጸጋቸው ሃይማኖታዊ ቅንዓታቸው መቀዝቀዝ ጀመረ። ሳሙኤል ፋዘርጊል የተባሉ ኩዌከር እንዲህ ብለዋል:- “[ኩዌከሮች] መንፈሳቸውና ፍላጎታቸው ወደዚህ ዓለም በማዘንበሉ እነርሱ ራሳቸው የዘነጓቸውን የሥነ ምግባር ደንቦች እንዲጠብቁ ልጆቻቸውን ማስተማር አልቻሉም።” ከጊዜ በኋላ በኩዌከሮች መካከል ሌሎች ኑፋቄዎች ተነሱ።
ፔንና ደጋፊዎቹ በጎ ዓላማ ይዘው የተነሱና ለጊዜው የተሳካላቸው ቢሆንም ኢየሱስ፣ እርሱም ሆነ ደቀ መዛሙርቱ ‘ከዓለም እንዳልሆኑ’ የሰጠውን ትምህርት በትክክል አልተረዱትም አሊያም በቁም ነገር አልተመለከቱትም። (ዮሐንስ 17:16) በመሆኑም በመሠረታዊ ሥርዓት ደረጃ፣ ማንኛውም ሰው የተነሳበት ዓላማ የቱንም ያህል ቀና ቢሆን ሃይማኖትን ከዚህ ዓለም የፖለቲካ ሥርዓት ጋር ለመቀላቀል ከሞከረ የአምላክንም ሆነ የልጁን በረከት አያገኝም። (ያዕቆብ 4:4፤ 1 ዮሐንስ 5:19) ይህም በመሆኑ ስኬታማ ሊሆን አይችልም።—መዝሙር 127:1
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.8 በዛሬው ጊዜ፣ አብዛኞቹ የኩዌከር ቤተ ክርስቲያኖች ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቱን ይበልጥ በተደራጀ መልኩ የሚያካሂድ ደሞዝ የሚከፈለው አገልጋይ አላቸው።
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“የእኔ መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለም”
ኢየሱስ በዮሐንስ 18:36 ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን እነዚህን ቃላት የተናገረው ለምን ነበር? የአምላክን መንግሥት ምንነት ስንረዳ የዚህ ጥያቄ መልስ ግልጽ ይሆንልናል። የኢየሱስ ትምህርት ዋና ርዕሰ ጉዳይ የሆነው የአምላክ መንግሥት፣ ክርስቶስ ገዥ የሚሆንበት ዓለም አቀፋዊ መንግሥት ነው። (ኢሳይያስ 9:6, 7፤ ሉቃስ 4:43) ይህ መንግሥት ዓለምን የሚያስተዳድረው በሰብዓዊ ገዢዎች አማካኝነት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ አሁን ያሉትን መንግሥታት በማጥፋት በምድር ላይ ብቸኛው መስተዳድር ይሆናል። (ዳንኤል 2:44፤ 7:13, 14) ኢየሱስ ባስተማረው የናሙና ጸሎት ላይ “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን” ሲል ይህን ማለቱ ነበር። (ማቴዎስ 6:9, 10) ታዛዥ የሆኑ የአምላክ መንግሥት ተገዥዎች፣ ዊልያም ፔንን የመሰሉ ቅን ሰዎች ማምጣት ያልቻሉትን እጅግ ግሩም ሕይወት የማግኘት ተስፋ አላቸው። እነዚህ ሰዎች ሰላም በሰፈነበት ገነት ውስጥ የተሟላ ጤንነት አግኝተው ለዘላለም ይኖራሉ።—ሉቃስ 23:43፤ ራእይ 21:3, 4
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1800ዎቹ የኩዌከሮች ስብሰባ በፊላደልፊያ
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሜሪ ዳየር የተባለችው ኩዌከር በማሳቹሴትስ ቤይ ግዛት የሞት ቅጣት ወደሚፈጸምባት ስፍራ ስትወሰድ
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1600ዎቹ ኩዌከሮች እንግሊዝን ለቀው ሲሄዱ
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1682 ዊልያም ፔን የአገሩ ተወላጅ ከሆኑ አሜሪካውያን ጋር ሲደራደር
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ፎቶዎቹ:- © North Wind Picture Archives
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ጀልባዎች:- © North Wind Picture Archives; ድርድር:- Brown Brothers