በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ ከመከራዬ ሁሉ አዳነኝ

ይሖዋ ከመከራዬ ሁሉ አዳነኝ

ይሖዋ ከመከራዬ ሁሉ አዳነኝ

ዣንክሎድ ፍራንስዋ እንደተናገረው

በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናዬን ላለመጣስ ስል ለሰባት ዓመታት ከአሥራ ሁለት በሚበልጡ እስር ቤቶች ውስጥ ማቅቄያለሁ። ይህ ሁሉ መከራ ቢደርስብኝም አምላክ እንደባረከኝ ይሰማኛል። እንዲህ የምልበትን ምክንያት እስቲ ላውጋችሁ።

ጥር 9, 1937 አልጀርስ በተባለችው የአልጄሪያ ከተማ ተወለድኩ። በወቅቱ ፈረንሳይ አልጄሪያን ትገዛ የነበረ ሲሆን አባቴ ደግሞ የፈረንሳይ የጦር መኮንን ነበር። አባቴ በሥራ ምክንያት ወደ ግብጽ፣ ኢራቅ፣ ሊባኖስና ሶርያ ሄዶ ለበርካታ ወራት ይቆይ ስለነበር ለአምስት ልጆቹ እምብዛም ጊዜ አልነበረውም።

ትምህርት እወድ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ጥሩ ውጤት አመጣ ነበር። ያም ሆኖ፣ የምንሞተው ለምንድን ነው? አምላክ እጅግ ታላቅ ኃይል ካለውና አፍቃሪ ከሆነ እንዴት ክፋት ሊኖር ቻለ? እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎች ያስጨንቁኝ ነበር። ነገር ግን ምንም ዓይነት አጥጋቢ መልስ አላገኘሁም። ከዚህም በላይ ሕይወት የተገኘው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ በጣም እጓጓ ነበር። ስለ ዝግመተ ለውጥ ከሚናገረው የዳርዊን ጽንሰ ሐሳብ ውጪ ሌላ አሳማኝ ማብራሪያ እንደሌለ ስለተሰማኝ ከጊዜ በኋላ አምላክ የለሽ ሆንኩ።

በመጨረሻ መልስ አገኘሁ!

በ1954 ዦርዥ የሚባል አንድ የይሖዋ ምሥክር ጓደኛዬ ኢቮሉሽን ቨርስስ ዘ ኒው ወርልድ (እንግሊዝኛ) የተባለ ቡክሌት ሰጠኝ። * ቡክሌቱን በከፍተኛ ጉጉት አነበብኩት። ይህ ቡክሌት የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ስሕተት መሆኑን የሚያጋልጥ ከመሆኑም በላይ የቅሪተ አካል መረጃ፣ አምላክ ሕይወት ያላቸውን ነገሮች በሙሉ “እንደየወገናቸው” እንደፈጠረ የሚናገረውን የዘፍጥረት መጽሐፍ ዘገባ እውነተኝነት እንደሚያረጋግጥ ያሳያል። (ዘፍጥረት 1:12, 25) ክፋትን በተመለከተ ያነሳሁት ጥያቄ ግን በአእምሮዬ ውስጥ ይመላለስ ነበር።

ዦርዥ አቅኚ ወይም የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ስለነበር ብዙ ጊዜውን የሚያሳልፈው ፈጽሞ አንብቤው የማላውቀውን መጽሐፍ ቅዱስን ለሰዎች በማስተማር ነበር። ታዲያ ዦርዥ ጥያቄዎቼን መመለስ ይችል ይሆን? ከሌሎች አቅኚዎች ጋር አብሮ ወደሚኖርበት አነስተኛ አፓርታማ ሄጄ ለአብዛኞቹ ጥያቄዎቼ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መልስ አገኘሁ። ከዚያ በኋላ ሥርዓት ባለው መንገድ አስደሳች የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመርኩ። ከዚያን ጊዜ ወዲህ እምነት የሚያጠነክር መንፈሳዊ ሀብት ለማግኘት ስል የአምላክን ቃል ከመቆፈር ወደኋላ ብዬ አላውቅም።—ምሳሌ 2:1-5

በተጨማሪም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርኩ። ስብሰባዎቹ የሚካሄዱት አልጀርስ ውስጥ መሃል ከተማ በሚገኝ አንድ ምግብ ቤት የምድር ቤት ውስጥ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮቹ ሞቅ ያለ አቀባበል ያደረጉልኝ ሲሆን ቀስ በቀስ አዘውትሬ መሰብሰብ ጀመርኩ። አንድ ቀን፣ በአንድ ጎዳና ላይ ስብሰባ እንደሚደረግ ማስታወቂያ ሲነገር እኔም ወደዚያ ለመሄድ ወሰንኩ። ቦታው ስደርስ የይሖዋ ምሥክሮቹ የተገናኙት ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው የስብከት ሥራ ላይ ለመካፈል እንደሆነ ተረዳሁ። (የሐዋርያት ሥራ 20:20) የሆነ ሆኖ እኔም አብሬያቸው የሄድኩ ሲሆን የመስክ አገልግሎት የጀመርኩትም በዚህ መንገድ ነው።

ለሦስተኛ ጊዜ የመስክ አገልግሎት በወጣሁበት ዕለት ብቻዬን ሰዎችን ማነጋገር ጀመርኩ። አንድ ቤት ሄጄ ሳነጋግር የጠቀስኩትን ጥቅስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ማግኘት አቃተኝ። የቤቱ ባለቤት “የኔ ወንድም፣ ለማስተማር ብቃት ሲኖርህ ማስተማር ብትጀምር ይሻላል” አለና በሩን ዘጋብኝ። በጣም ስለተበሳጨሁ አንድ አግዳሚ ወንበር ላይ ተቀመጥኩና የጠፋብኝን ጥቅስ መፈላለግ ጀመርኩ። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ሳገኘው ወደ ሰውየው ተመልሼ ሄድኩና ጥቅሱን አሳየሁት።

መጋቢት 4, 1956 ራሴን ለአምላክ መወሰኔን በጥምቀት አሳየሁ። ከስድስት ወራት በኋላ ትልቅ ውሳኔ የሚጠይቅ አንድ ጉዳይ አጋጠመኝ። የዘወትር አቅኚ ሆኜ ማገልገል ልጀምር ወይስ በአገልግሎት ላይ ጥቂት ሰዓት እያሳለፍኩ በመምህርነት ተቀጥሬ ወደ ገጠሪቱ አልጄሪያ ልሂድ? ሁለቱን አመዛዝኜ አቅኚ ለመሆን ወሰንኩ።

አባቴ በውሳኔዬ በጣም ከመናደዱ የተነሳ ጩቤውን ጉሮሮዬ ላይ አድርጎ ሁልጊዜ ማታ ማታ ወደ ቤት መምጣት እንዳለብኝ አስጠነቀቀኝ። እንዲሁም ወጪዎቼን በሙሉ ራሴ የመሸፈን ሐሳብ የነበረኝ ቢሆንም እንኳ ከዚያ በኋላ ከቤት ምግብ አገኛለሁ ብዬ እንዳልጠብቅ ነገረኝ። በዚህም ምክንያት ጠዋት ቁርሴን ሳልበላ ከቤት እወጣለሁ። ምሳዬን ከሌሎች አቅኚዎች ጋር እበላና እራቴን ደግሞ ማታ ወደ ቤት ከመመለሴ በፊት ሳንዱች እበላለሁ።

ከቦምብ ፍንዳታና ከጥይት እሩምታ ማምለጥ

በወቅቱ አልጄሪያ ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ነፃ ለመውጣት እየታገለች ስለነበር አልጀርስ በቦምብ ድብደባና አስፈሪ በሆነ የአጸፋ እርምጃ ትናወጥ ነበር። በአንድ ወር ውስጥ ከ100 የሚበልጡ ፍንዳታዎች የተከሰቱበት ጊዜ ነበር። በአውቶቡሶች፣ በቡና ቤቶችና በስታዲየሞች ውስጥ ቦምብ ይጠመድ ነበር። በወቅቱ አገልግሎት መውጣት አስቸጋሪ ነበር። ሰዎች በራቸውን ለመክፈት የሚፈሩ ከመሆኑም በላይ በተደጋጋሚ ጊዜ ሰዓት እላፊ ይጣል፣ መታወቂያ ይታይ እንዲሁም ፍተሻ ይደረግ ነበር።

እሁድ መስከረም 30, 1956 ከሌሎች አቅኚዎች ጋር የመሰብሰቢያ ቦታችንን እያዘገጃጀን እያለ ከላይ ባለው ምግብ ቤት ውስጥ ቦምብ ፈንድቶ ብዙዎችን ለሞትና ለአካል ጉዳት ዳረጋቸው። የሚያስደስተው ነገር ምድር ቤት ከነበርነው ውስጥ አንዳችንም አልተጎዳንም። በታኅሣሥ ወር ደግሞ እኔና አንዲት እህት በተጨናነቀ መንገድ ላይ እያገለገልን ሳለ አንዲት መኪና እየበረረች መጥታ በመስኮት በኩል በሕዝቡ ላይ ጥይት ማርከፍከፍ ጀመረች። በዚህ ጊዜ ተሯሩጠን ወደ አንድ በረንዳ በመሄድ እህትን መሬት ላይ እንድትተኛ ከገፋኋት በኋላ እኔም በደረቴ ተኛሁ። ተኝተን ሳለ የጥይት እሩምታ ሲወርድ ይሰማን ነበር። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ሁላችንም በምንመሠክርበት ጊዜ ይበልጥ መጠንቀቅ ጀመርን።

መሣሪያ ለመታጠቅ ፈቃደኛ አልሆንኩም

መጋቢት 1, 1957 የውትድርና አገልግሎት እንድሰጥ ተጠራሁ። ክርስቲያናዊ ሕሊናዬ በጦርነት እንድካፈል ስለማይፈቅድልኝ ይሖዋ ባለሥልጣኖቹ የሚያደርሱብኝን ተጽዕኖ እንድቋቋም የሚያስችለኝን ጥንካሬ እንዲሰጠኝና ከአባቴም ጋር ፊት ለፊት እንዳልገናኝ እንዲረዳኝ ጸለይኩ። ከምኖርበት አገር ርቃ ወደምትገኘው ሊል ወደተባለችው የፈረንሳይ ከተማ ሄጄ ሪፖርት እንዳደርግ ሲነገረኝ ትልቅ እፎይታ ተሰማኝ።

ከስድስት ቀናት በኋላ በ17ኛው መቶ ዘመን በኖረው በንጉሥ ሉዊ አሥራ አራተኛ ዘመን ሊል ከተማ ውስጥ ወደተገነባው ለምሽግነት ወደሚያገለግል ትልቅ ሕንጻ ደረስኩ። እዚያ ለሚገኙት የጦር መኮንኖች ስላለኝ የገለልተኝነት አቋም ከመጽሐፍ ቅዱስ ባብራራላቸውም ወኅኒ ቤት አወረዱኝ። አንድ ቀን ጠዋት ጠባቂዎቹ ከታሰርኩበት ክፍል እየጎተቱ ካወጡኝ በኋላ ሲፈትሹኝ አንድ ትንሽ መጽሐፍ ቅዱስ አገኙ። ከዚያ በኋላ በረዶ ላይ በደረቴ እንድተኛ አድርገው መጽሐፍ ቅዱሴን አጠገቤ ወረወሩት። ጭንቅላቴን በጠመንጃ ሰደፍ ተጭነውኝ ለ30 ደቂቃ ያህል አቆዩኝ። የሚያስደስተው ግን መጽሐፍ ቅዱሴን እንድወስድ የፈቀዱልኝ ሲሆን እስከዛሬ ድረስ መጽሐፉ መደርደሪያዬ ላይ ይገኛል። ነገር ግን በዚያን ቀን ያደረሱብኝ እንግልት ለዓመታት በሆድ ቁርጠት በሽታ እንድሠቃይ አድርጎኛል።

ከጥቂት ቀናት በኋላ የእስር ቤቱ አዛዥ አባቴ ከላከው ደብዳቤ ላይ የተወሰነውን ክፍል አነበበልኝ። ደብዳቤው፣ “ሐሳቡን እንዲቀይር መደረግ አለበት። አስፈላጊ ሆኖ ካገኛችሁት ቅስሙን ስበሩት” ይል ነበር። አቋሜን ለማላላት ፈቃደኛ ባለመሆኔ በአንዲት ጨለማ ክፍል ውስጥ አሰረኝ። እዚያም ትንሽ ብርድ ልብስ ለብሼ አንድ ጣውላ ላይ እተኛ ነበር። መጸዳጃ ቤት ባለመኖሩ አንደኛውን ጥግ ለዚህ ዓላማ መጠቀሙ ግድ ሆኖብኝ ነበር። ሰውነቴን መታጠብም ይሁን ጥርሴን መቦረሽ ወይም የበላሁበትን ሰሃን ማጠብ አልችልም ነበር። ከሁለት ሳምንት በኋላ ፓሪስ ወደሚገኘው ፍሬን የሚባል ወኅኒ ቤት ተላክሁ።

በቀጣዮቹ ስድስት ዓመታት ውስጥ አራት ጊዜ የተፈረደብኝ ሲሆን በ14 እስር ቤቶች ውስጥ ታስሬያለሁ። በአንድ ብርዳማ ወቅት፣ እስር ቤት ሆኖ ያገለግል በነበረውና በልዋር ሸለቆ ውስጥ በሚገኘው ፎንቴቭሮ የሚባል የ12ኛው መቶ ዘመን ገዳም ውስጥ ታስሬ ነበር። እዚያ እንደደረስኩ ንብረቶቼ ሁሉ ተወረሱ። መጽሐፍ ቅዱሴን እንዲሰጡኝ ደጋግሜ ከመጠየቄ የተነሳ ጠባቂዎቹ ለወር ያህል ብቻዬን እንድታሰር አደረጉኝ። እዚያም ሌላው ጠላቴ ብርድ በሽታዬን ስለቀሰቀሰብኝ ደም እስክተፋ ድረስ ያስለኝ ጀመር።

ከዚያ በኋላ ሶሚዩር ከተማ አቅራቢያ ወደሚገኝ ሻቶ ደ ቱርካን ወደተባለ የተሻለ እስር ቤት ተወሰድኩ። እዚህ የታሰሩ ሰዎች ጡረታ ለወጡ የጦር መኮንኖች አንዳንድ የቤት ውስጥ ሥራ ያከናውኑ ነበር። አብረውኝ ከታሠሩት መካከል ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የአልጄሪያ ሪፑብሊክ ፕሬዚዳንት የሆኑት አሕመድ ቤን ቤለ ይገኙበታል። ለበርካታ ወራት የመሠከርኩላቸው ሲሆን በአንድ ወቅት እንዲህ ብለውኝ ነበር:- “የአልጀርስ ተወላጅ ነህ። እዚህ የታሰርከውም በአልጄሪያውያን ላይ መሣሪያ አላነሳም በማለትህ ነው።” እንዲህ ዓይነት አቋም በመያዜ ያከብሩኝ ነበር።

ሌሎች ችግሮችን ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት አገኘሁ

ከጊዜ ወደ ጊዜ የጤንነቴ ሁኔታ እያሽቆለቆለ ሄደ፤ በኋላም የሳንባ ነቀርሳ ስለያዘኝ ደቡብ ፈረንሳይ ወደሚገኘው የሕሙማን ማረፊያ ቤት ተወሰድኩ። እዚያም ለወራት ያህል የአልጋ ቁራኛ ሆንኩ። ዶክተሩ፣ የተጎዳው የሳንባዬ ክፍል በቀዶ ሕክምና እንዲወጣ ሐሳብ አቀረበ። እኔም ደም እንድወስድ እስካልተጠየቅሁ ድረስ ቀዶ ሕክምናው እንዲደረግልኝ የምስማማ መሆኑን ገለጽኩለት። (የሐዋርያት ሥራ 15:29) ዶክተሩ በዚህ ስለተበሳጨ ቀዶ ሕክምና እንደማያደርግልኝ ተናገረ። ስድስተኛውን ዓመት የእስር ጊዜዬን የማጠናቅቀው በዚህ ወቅት ነበር።

በቅዝቃዜው ወራት አጋማሽ ላይ የሕሙማኑን ማረፊያ ቤት ለቅቄ መውጣት ነበረብኝ። በወቅቱ ከለበስኩት ልብስ ሌላ አንዳች ልብስ አልነበረኝም። ሆኖም ይሖዋ ለጳውሎስ ሔኔሲፎሩን እንደላከለት ሁሉ ለእኔ ደግሞ አንድ ረዳት ላከልኝ። አዶልፍ ጋራቶኒ የተባለ አንድ ወንድም ወደ ቤቱ ወስዶ ያስጠለለኝ ሲሆን ‘የብርታት ምንጭ’ ሆኖልኛል። (ቈላስይስ 4:11 NW፤ 2 ጢሞቴዎስ 1:16-18) ይህ ወንድምና ያክመኝ የነበረው ዶክተር ባደረጉልኝ እርዳታ ቀስ በቀስ ማገገም ቻልኩ።

በወቅቱ ብዙ ወጪዎች ስለነበሩብኝ እነዚህን ለመሸፈን ገንዘብ ያስፈልገኝ ነበር። ይህን ችግር እንዴት እንደምወጣው አላውቅም ነበር። አንድ ቀን አንዲት የማላውቃት ሴት ወዳረፍኩበት ቤት መጣችና ጠበቃ እንደሆነች ነገረችኝ። ከዚያም “የአልጄሪያ ፕሬዚዳንት ሚስተር ቤን ቤለ ይህን እንድሰጥዎት ልከውኛል” ብላ አንድ ፖስታ ሰጠችኝ። ፖስታው ውስጥ ያለው ገንዘብ ወጪዬን ለመሸፈን ከሚያስፈልገኝ በላይ ነበር። ‘ጸሎት ሰሚ’ የሆነውን ይሖዋን ከልቤ አመሰገንኩት።—መዝሙር 65:2

ግሩም መብቶችና ጥሩ የትዳር ጓደኛ

አሁን ከእስር ቤት ስለወጣሁ እንደገና የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመርኩ። ፓሪስ አቅራቢያ ባለው ሜሎን ጉባኤ ውስጥ አንድሬ ሞሬል ከምትባል ባሏ የሞተባት የ35 ዓመት እህት ጋር ተዋወቅሁ። የይሖዋ ምሥክር የነበረው የመጀመሪያ ባሏ ሕይወቱ ያለፈው በመኪና አደጋ ነው። መስከረም 26, 1964 ተጋባንና ነሐሴ 1, 1965 ልዩ አቅኚዎች ሆነን ማገልገል ጀመርን። አንድሬ ጥሩ ጤንነት የነበራት ባይሆንም ለ28 ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ተካፍላለች!

በ1967 የወረዳ የበላይ ተመልካች ማለትም የይሖዋ ምሥክሮችን ጉባኤዎች የሚጎበኝና ማበረታቻ የሚሰጥ አገልጋይ ሆኜ ተሾምሁ። ከቦርዶ እስከ ሞናኮ ድረስ ባሉት የደቡብ ፈረንሳይ ጉባኤዎች ውስጥ ያገለገልን ሲሆን ለአንድ ዓመት ደግሞ በፓሪስ አገልግለናል። የጤና እክል ስለነበረብን የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ ማገልገሉ ቀላል አልነበረም። ሆኖም እንደገና ልዩ አቅኚ እስከሆንበት እስከ 1986 ድረስ በይሖዋ እርዳታ ለ20 ዓመታት ወንድሞቻችንን አገልግለናል።

አሁን ያለሁበት ሁኔታ

አሁን 70 ዓመት ሊሞላኝ ነው። ይሖዋ ምንጊዜም ለአገልጋዮቹ መከራን እንዲቋቋሙ የሚያስችላቸውን ጥንካሬ እንደሚሰጣቸው በተደጋጋሚ ጊዜያት ተመልክቻለሁ። እርግጥ አንዳንድ ጊዜ ጥንካሬ የምናገኘው በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን ቃሉን በማንበብ ነው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን በየዓመቱ ከዳር እስከ ዳር ለማንበብ እጥራለሁ።—ኢሳይያስ 40:28-31፤ ሮሜ 15:4፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16

እኔና አንድሬ ሰዎች ለመንግሥቱ ምሥራች በጎ ምላሽ ሰጥተው ራሳቸውን ለይሖዋ ሲወስኑ መመልከት ያበረታታናል። ባለፉት ዓመታት 70 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን ራሳቸውን ለይሖዋ ሲወስኑ ለማየት ችለናል። ይህ ደግሞ በቃላት ሊገለጽ የማይችል ዘላቂ ደስታ አስገኝቶልናል። ሕይወታችንን መለስ ብዬ ስመለከት መዝሙራዊው “ይህ ችግረኛ ጮኸ፤ እግዚአብሔርም ሰማው፤ ከመከራውም ሁሉ አዳነው” ሲል የጻፈው የእኛን ስሜት እንደሚያንጸባርቅ ይሰማኛል።—መዝሙር 34:6

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ። አሁን ግን መታተም አቁሟል።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሶሚዩር አቅራቢያ ባለው ሻቶ ደ ቱርካን እስር ቤት በነበርኩበት ወቅት

[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ከባለቤቴ ጋር በ1967 እና አሁን