‘በጣም ንጹሕ ከሆኑ ወላጆች የተወለደ’
‘በጣም ንጹሕ ከሆኑ ወላጆች የተወለደ’
ብራዚል የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
ጨው “በጣም ንጹሕ ከሆኑ ወላጆች ይኸውም ከፀሐይና ከባሕር የተወለደ” እንደሆነ ተደርጎ ተገልጿል። በእርግጥም ጨው በአብዛኛው የሚመረተው የባሕርን ውኃ በፀሐይ ሙቀት እንዲተን በማድረግ ስለሆነ እንዲህ መባሉ የተገባ ነው።
በሰሜናዊው ምሥራቅ ብራዚል የባሕር ዳርቻ ላይ የምትገኘው ሪዮ ግራንደ ዶ ኖርቴ የተባለችው ክፍለ ሃገር በጨው ማምረቻ ተቋሞቿ በሰፊው ትታወቃለች። ሞቃታማው የአየር ንብረት፣ ዝቅተኛው የዝናብ መጠንና ያለማቋረጥ የሚነፍሰው ደረቅ ነፋስ አካባቢውን በፀሐይ ሙቀት ጨው ለማምረት ምቹ እንዲሆን አድርጎታል። ብራዚል ከምታመርተው የተጣራም ሆነ ያልተጣራ ጨው ውስጥ 95 በመቶ ያህሉ የሚገኘው ከዚህ ቦታ ነው። በብራዚል ካሉት የጨው ማምረቻ ተቋማት መካከል አንደኛው የሚገኘው ኤሪያ ብራንካ በምትባለው አነስተኛ የወደብ ከተማ ውስጥ ነው።
የጨው ማምረቻ ተቋምን መጎብኘት
በፀሐይ ኃይል ጨው እንደሚያመርቱት እንደ አብዛኞቹ ተቋማት ሁሉ የኤሪያ ብራንካ ጨው ማምረቻ ተቋምም እጅግ በጣም ሰፊ ነው። ጎብኚዎች አውራ ጎዳናውን ይዘው ወደ ኤሪያ ብራንካ ሲቃረቡ ብዙውን ጊዜ በጨው ማምረቻው ተቋም ስፋት ይደነቃሉ። ማለዳ ላይ የፀሐይዋ ብርሃን ለዓይን የሚያታክት ስፋት ባላቸው ኩሬዎች ላይ ሲያርፍ ውኃው በጣም ያንጸባርቃል። ተቋሙ ከያዘው ቦታ ውስጥ 90 በመቶ ያህሉ የሚያገለግለው የባሕሩን ውኃ ለማትነን ሲሆን የተቀረው ደግሞ ክሪስታላይዜሽን የሚባለው
ጨዉ ወደ ጠጣርነት የሚለወጥበት ሂደት ይከናወንበታል።ሁሉም ነገር የፀሐይዋን ጨረር በሚያንጸባርቀው ነጭ የጨው ምንጣፍ ተሸፍኗል። ጎብኚዎች የፀሐይ መነጽር ማድረጋቸው የግድ አስፈላጊ ነው። ጨው የማምረቱ ሂደት የሚጀምረው የባሕሩን ውኃ በተለያዩ ግድቦች በተከፋፈሉና የእንጨት በሮች ባሏቸው በርካታ ኩሬዎች ውስጥ እንዲያልፍ በማድረግ ነው። በዚህ ተቋም ውስጥ በጠቅላላው 67 የሚያህሉ ኩሬዎች ይገኛሉ። የፀሐይዋ ሙቀትና ነፋሱ 650 ሊትር የሚያህል ውኃ በየሴኮንዱ እንዲተን ያደርጋሉ! ሆኖም ውኃው ሙሉ በሙሉ ተንኖ እስኪያልቅ ከ90 እስከ 100 ቀናት ያህል ይወስዳል።
የባሕሩ ውኃ ሲተን በአብዛኛው የሚቀረው ሶዲየም ክሎራይድ ቢሆንም በውኃው ውስጥ አነስተኛ መጠን ያለው ካልሲየም ካርቦኔት፣ ካልሲየም ሰልፌት፣ ማግኒዝየም ሰልፌትና ሌሎች የጨው ዓይነቶችም ይገኛሉ። እነዚህ የጨው ዓይነቶች ትነቱ በሚካሄድበት ሂደት ውስጥ ተራ በተራ ከውኃው እየተለዩ በኩሬዎቹ ወለል ላይ ይዘቅጣሉ።
በእነዚህ ኩሬዎች ውስጥ የቀረው ከፍተኛ የጨው መጠን ያለው ውኃ ጨዉ ወደ ጠጣርነት ወደሚለወጥባቸው 20 የሚያህሉ ሌሎች ኩሬዎች ውስጥ እንዲገባ ይደረጋል። በአንዳንዶቹ ኩሬዎች ውስጥ የባሕሩ ውኃ ሙሉ በሙሉ ተንኖ ስለሚያልቅ ከፍተኛ መጠን ያለው ጨው ብቻ ይቀራል። በዚህ ጊዜ አንድ ግዙፍ ማሽን ጨዉን እየፈረካከሰ በትላልቅ መኪናዎች ላይ ይጭናል። የጭነት መኪናዎቹ ደግሞ ጨዉን አጥቦ ቆሻሻውን ውኃ ካስወገደ በኋላ በንፁሕ ውኃ አለቅልቆ አንድ ቦታ ላይ ወደሚያከማቸው ሌላ በጣም ግዙፍ ማሽን ይወስዱታል።
በመጨረሻም ጨዉ በመርከብ ተጭኖ ከባሕሩ ዳርቻ 12 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ ወደሚገኘው የኤርያ ብራንካ ሰው ሰራሽ የወደብ ደሴት ይወሰዳል። ይህ 92 በ166 ሜትር ስፋት ያለው ባለ አራት ማዕዘን ቅርጽ ደሴት 100,000 ቶን የሚያህል መጠን ያለው ጨው ማከማቸት ይችላል። ጨዉ ተሽከርካሪ ቺንጊያ ባለው ረጅም ማሽን (conveyor belt) አማካኝነት ትላልቅ መርከቦች ወደቆሙበት መጫኛ ጣቢያ ተጓጉዞ ወደተለያዩ የብራዚል ከተሞች ይወሰዳል።
ሁለገብ የሆነ ጠቃሚ ንጥረ ነገር
ሰውነታችን የሚያስፈልገው የጨው መጠን በጣም አነስተኛ ቢሆንም ይህ ንጥረ ነገር ለሰው ልጆችም ሆነ ለሌሎች እንስሳት ሕይወትና ጤንነት በጣም አስፈላጊ ነው። ምናልባት ጨውን ምግብን ለማጣፈጥ እንደሚገባ አንድ ነጭ ቅመም ብቻ አድርገን እንመለከተው ይሆናል። ሆኖም በኬሚካል፣ በጨርቃ ጨርቅ፣ በብረታ ብረትና እንደነዚህ በመሳሰሉ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የሚያበረክታቸው ሌሎች በርካታ ጥቅሞችም አሉት። ከዚህም በላይ ሳሙናንና እንደ ዝገት መከላከያ ያሉ በርካታ ኬሚካሎችን ለማምረት ያገለግላል። በዛሬው ጊዜ ጨው ከ14,000 የሚበልጡ ጥቅሞች እንዳሉት ይነገርለታል!
በምድር ላይ ያለው የጨው መጠን ማለቂያ የለውም ማለት ይቻላል። በአንድ ኪሎ ሜትር ኩብ የባሕር ውኃ ውስጥ 25 ሚሊዮን ቶን የሚያህል ሶዲየም ክሎራይድ ማለትም የምግብ ጨው ይገኛል! ባለፉት ዘመናት ግን ጨው እንዲህ በቀላሉ የሚገኝ ነገር አልነበረም። ለምሳሌ በጥንቷ ቻይና ጨውን በዋጋ የሚበልጠው ወርቅ ብቻ ነበር። ጨው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ጊዜ የተጠቀሰ ከመሆኑም በላይ ለተለያየ አገልግሎት እንደሚውልም ተገልጿል።
አንዳንድ ጊዜ ሕፃናት ገና እንደተወለዱ በጨው ይታሻሉ፤ ምናልባትም ሰዎች ይህን የሚያደርጉት ጨው የመድኃኒትነት አሊያም ጀርም የመግደል ጠባይ ስላለው ሊሆን ይችላል። (ሕዝቅኤል 16:4) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ጨውን በምሳሌያዊ ሁኔታ ይጠቀምበታል። ለአብነት ያህል፣ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “የምድር ጨው” እንደሆኑ ነግሯቸዋል። ምክንያቱም በሚናገሩት ሕይወት ሰጪ መልእክት አማካኝነት በሰዎች ላይ ዘላቂ የሆነ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። (ማቴዎስ 5:13) ከዚህም በላይ ጨው አስተማማኝና የማይለወጥ ነገርን ለማመልከት አገልግሏል። ለምሳሌ ያህል “የጨው ኪዳን” የሚለው አነጋገር ጽኑ የሆነ ስምምነትን ያመለክታል።—ዘኍልቍ 18:19
በኤርያ ብራንካ የሚገኘውን የጨው ማምረቻ ተቋም መጎብኘታችን ጨው ምን ያህል ተፈላጊና ጠቃሚ እንደሆነ እንዲሁም በታሪክ ዘመናት ከፍተኛ ግምት የተሰጠው ለምን እንደሆነ የበለጠ ግንዛቤ እንድናገኝ ረድቶናል። ‘በጣም ንጹሕ ከሆኑ ወላጆች ይኸውም ከፀሐይና ከባሕር የተወለደውን’ ይህን ንጥረ ነገር በገፍ ስለምናገኘው አመስጋኝ ልንሆን ይገባል።
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጨዉን የሚፈነካክተው ማሽን
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ያልታጠበ ጨው
[በገጽ 16 እና 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጨዉ የሚታጠብበት፣ የሚለቀለቅበትና የሚከማችበት ሥፍራ