በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አህዮች ባይኖሩ ኖሮ ምን እንሆን ነበር?

አህዮች ባይኖሩ ኖሮ ምን እንሆን ነበር?

አህዮች ባይኖሩ ኖሮ ምን እንሆን ነበር?

ኢትዮጵያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ኢትዮጵያ በሕዝብ ብዛት በዓለም ካሉ አገሮች በ16ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። የአገሪቱ ዋና ከተማ በሆነችው በአዲስ አበባ መንገዶች ላይ አህዮች ዕቃ ሲያጓጉዙ መመልከት በጣም የተለመደ ነው። አህዮች ወዴት እንደሚሄዱ ጠንቅቀው ስለሚያውቁና አንዴ መንገድ ከጀመሩ ስለማይመለሱ አብዛኞቹ የመኪና አሽከርካሪዎች ብዙ ጊዜ አህያ ሲያጋጥማቸው ግራ አይጋቡም። አህዮች የመኪና ብዛት አያስፈራቸውም፤ የተጫኑት ትልቅ ዕቃም ቢሆን ለመኪና አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ ወደኋላ ዞር ብለው አይመለከቱም። ስለዚህ የጫኑት ከሰል፣ ኩበት፣ ወይም ሌላ ማንኛውም ነገር እንዳይነካህ ከፈለግህ ከፊታቸው ዞር ብትል ይሻላል!

በኢትዮጵያ ወደ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ አህዮች እንዳሉ የሚገመት ሲሆን ይህም አንድ አህያ ለ12 ሰው ይደርሳል ማለት ነው። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የሚኖሩት ገደላ ገደል በሚበዛባቸው ከከተማ ራቅ ብለው በሚገኙ ኮረብታማ አካባቢዎች ነው። በመካከለኛው የአገሪቱ ሜዳማ ቦታዎች ደግሞ ለቁጥር የሚታክቱ ትናንሽ ጅረቶች ይገኛሉ። በየትኛውም አገር ቢሆን እንዲህ ያለ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ ባላቸው ቦታዎች ላይ ድልድዮችን መሥራት ወይም አንዱን መንደር ከሌላው የሚያገናኙ ጥርጊያ መንገዶችን መዘርጋት ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ግልጽ ነው። ስለዚህም እንዲህ ያሉት ችግሮች የማይበግሯቸውና መሬቱን ቆንጥጠው የመያዝ ችሎታ ያላቸው እነዚህ እንስሳት በዚህ ዓይነቱ ቦታ የመጓጓዣ አገልግሎት ለመስጠት ተስማሚ ናቸው።

አህዮች በደጋም ሆነ በወይናደጋ እንዲሁም ቆላማ በሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች መኖር ይችላሉ። ከዚህም ሌላ ኃይለኛ ቁልቁለቶችን የመውረድ፣ በጠባብ የእግር መንገድ ላይ የመሄድ፣ ድንጋያማ ወንዞችን የማቋረጥ፣ በጭቃ የቦኩ መተላለፊያዎችን የማለፍ እንዲሁም በሌሎች ወጣገባ መንገዶች ላይ የመሄድ አስደናቂ ችሎታ አላቸው። ለፈረሶች ወይም ለግመሎች እንኳ አስቸጋሪ በሆኑ ቦታዎች መሄድ ይችላሉ። አህዮች በተለይ መኪና በማይገባባቸው ቦታዎች በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ዋነኛ የዕቃ ማጓጓዣ ሆነው ያገለግላሉ።

አህዮች ጠባብ በሆኑ መታጠፊያዎችና በአጥሮች መካከል ባሉ ቀጭን ጠመዝማዛ መንገዶች ላይ መጓዝ ፈጽሞ አይቸግራቸውም። ውድ የሆነ ጎማ አያስፈልጋቸውም፤ በሚያዳልጡ መንገዶች ላይ እንኳ እምብዛም ችግር አይገጥማቸውም። የትኛውም ዓይነት ቅርጽና መጠን ያለውን ዕቃ ተሸክመው በየትኛውም ቦታ ወደሚገኝ ቤት በማድረስ ተገቢውን አገልግሎት ይሰጣሉ። ከተማ ውስጥ የመኪና መጨናነቅ ተፈጥሮ መንገድ ሲዘጋ አሽከርካሪዎች ከመናደዳቸው የተነሳ ቁጭ ብለው ጥሩንባቸውን ሲያንባርቁ አህዮች ግን በመኪናዎቹ መካከል ተሽሎክልከው መንገዳቸውን ይቀጥላሉ። ከዚህም ሌላ አንዲት አህያ በአንድ አቅጣጫ ብቻ በሚያስኬድ መንገድ ላይ በተቃራኒ አቅጣጫ ስትሄድ የትራፊክ ፖሊስ ቢያገኛት ለመቅጣት አያስብም። የማቆሚያ ሥፍራን በተመለከተም ምንም ችግር የለም። አንድ አህያ እስከ 500 ብር ድረስ ያወጣል፤ ይህ ገንዘብ በመኪና ዕቃ ለማጓጓዝ ከሚወጣ ወጪ ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም!

አህዮች በዋና ከተማ ውስጥ

ጠዋት ጠዋት በሺህ የሚቆጠሩ አህዮች ከ3,000,000 የሚበልጡ ሰዎች ወደሚኖሩባት ወደ አዲስ አበባ ይጎርፋሉ፤ ብዙውን ጊዜ የሚመጡት ከ25 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀው ከሚገኙ አካባቢዎች ተነስተው ነው። ረቡዕና ቅዳሜ ሳምንታዊ የገበያ ቀናት እንደመሆናቸው መጠን አብዛኛውን ጊዜ በእነዚህ ቀናት ሥራ ይበዛባቸዋል። ጉዞው ሦስት ሰዓታት ያህል ስለሚወስድባቸው ጎህ ከመቅደዱ በፊት መነሳት ይኖርባቸዋል። አንዳንድ ጊዜ የአህዮቹ ባለቤቶች ቀስ ብለው እየነዷቸው አብረው የሚጓዙ ሲሆን ብዙ ጊዜ ግን አህዮቹ ላይ ለመድረስ ከኋላቸው ይሮጣሉ።

አብዛኛውን ጊዜ አህዮች እህል፣ አትክልት፣ የማገዶ እንጨት፣ ሲሚንቶ፣ ከሰል፣ ጄሪካን እንዲሁም የለስላሳና የቢራ ጠርሙሶች ይጫንባቸዋል። አንዳንድ አህዮች 90 ኪሎ ግራም ወይም ከዚያ የበለጠ ክብደት ያለው ነገር መሸከም ይችላሉ። እንደ ቀርከሃ ወይም የባሕር ዛፍ ግንድ የመሳሰሉ ረጃጅም ጭነቶች በጀርባቸው ላይ ከታሠረ በኋላ መሬት ለመሬት እየጎተቱ እንዲሄዱም ይደረጋሉ። ይበልጥ ትኩረት የሚስበው ጭነት ግን አህዮቹን ሙሉ ለሙሉ የሚሸፍነው የሳር ወይም የጭድ እስር ነው።

አህዮች ጠዋት ከባድ ጭነት ተሸክመው ወደ ገበያ ሲሄዱ ፈጠን ፈጠን በማለት ይራመዳሉ። የጫኑት ዕቃ ተሸጦ ባዷቸውን ወደ ቤት ሲመለሱ ግን ረጋ ብለው እንዲያውም አንዳንዴም በመንገድ ዳር የሚያገኙትን ሣር እየጋጡ ይጓዛሉ። አህዮች ዕቃ ተጭነው ወደ ገበያ በማይሄዱባቸው ቀናት እዚያው አካባቢያቸው ውኃና የማገዶ እንጨት በማመላለስ ሥራ ተጠምደው ይውላሉ። አሊያም ሌላ ሰው ተውሶ ወይም ተከራይቶ ይወስዳቸው ይሆናል። እንዲያውም አንዳንድ ሰዎች የጭነት አገልግሎት የሚሰጡ በርካታ አህዮች አሏቸው! በአንዳንድ ቦታዎች አንድ ወይም ሁለት አህዮች የዕቃ መጫኛ ጋሪ ሲጎትቱ ማየት የተለመደ ነው።

በተገቢው መንገድ ሊያዙ ይገባል

ከሌሎች እንስሳት አንጻር ሲታይ አህዮች ያን ያህል እንክብካቤ የሚሹ አይደሉም። የራሳቸውን ምግብ ፈልገው የሚመገቡ ከመሆናቸውም ሌላ ያገኙትን ይበላሉ። አህዮች በደንብ ከተያዙ ለባለቤቶቻቸው ታማኝ ናቸው። ከፈረስ በተሻለ ብልህ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ከመሆኑም ሌላ አቅጣጫን በመለየት ረገድ ጥሩ የማስታወስ ችሎታ አላቸው። የሚጭንላቸውና የሚያወርድላቸው ሰው ካገኙ ማንም ሰው ሳይመራቸው ከስምንት ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዘው ውኃ ማመላለስ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች አህዮቹ አንገት ላይ ቃጭል ያደርጉላቸዋል፤ ይህም አህዮቹ የተጫኑትን ዕቃ ይዘው ሲመጡ ድምፁን ሰምተው ለማውረድ ይረዳቸዋል።

ምንም እንኳ አህዮች ጠንካራ ሠራተኞች ቢሆኑም ጭነት ከበዛባቸው ወይም በጣም ከደከማቸው ባለቤታቸው ሁኔታውን እንዲረዳላቸው ከማድረግ ወደኋላ አይሉም። እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ካጋጠሟቸው ወይም ጭነታቸው ወደ አንድ ጎን አጋድሎ ካሳመማቸው ሊተኙ ይችላሉ። ይህንን በሚያደርጉበት ወቅት አብዛኛውን ጊዜ ባለቤቶቻቸው ችግራቸውን ስለማይረዱላቸው የስድብ ወይም የዱላ ናዳ ያወርዱባቸዋል። ምናልባት እንዲህ ያለ ሁኔታ እንደተፈጸመ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ታስታውስ ይሆናል።—ዘኍልቍ 22:20-31

ለአህዮች አሳቢነት ልናሳያቸው እንዲሁም እንክብካቤ ልናደርግላቸው ይገባል። ጭነቱ በደንብ ሳይጫን ቀርቶ ወደ አንድ ወገን በማጋደሉ ምክንያት አህያው ቦይ ውስጥ ወድቆ እግሩ ሲሰበር ማየት የሚያሳዝን ነው። ቁስል፣ የተለያዩ ጥገኛ ነፍሳት፣ የእግር በሽታ፣ የሳምባ ምችና ሌሎች ችግሮች እነዚህን ብርቱ የሸክም እንስሳት ደካማ ሊያደርጓቸው ይችላሉ። ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት ከአዲስ አበባ ብዙም በማትርቀው በደብረ ዘይት ከተማ ዘመናዊ የአህዮች ክሊኒክ ተቋቁሟል። ክሊኒኩ በኮምፒውተር የሚታገዝ ከመሆኑም በላይ የሕክምና ክፍሎች፣ በየቦታው እየተዘዋወሩ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ተሽከርካሪዎች አልፎ ተርፎም ቀዶ ሕክምና ለማድረግ የሚያገለግል የተሟላ ክፍል አለው። በ2002፣ 40,000 የሚያክሉ አህዮች የተለያየ ሕክምና ተደርጎላቸዋል።

የእምነት አባት የሆነው አብርሃም ወደ ሞሪያ ተራራ በሄደበት ወቅት ተራራማውን አካባቢ ለማቋረጥ የተጠቀመው በአህያ ነበር። (ዘፍጥረት 22:3) ረጅሙ የእስራኤላውያን ታሪክ እንደሚጠቁመው አህያ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ውስጥ ትልቅ ቦታ ነበረው። ሌላው ቀርቶ ኢየሱስ ክርስቶስ በከፍተኛ ክብር ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ የገባው በአህያ ላይ ተቀምጦ ነበር።—ማቴዎስ 21:1-9

በኢትዮጵያም አህዮች የረጅም ጊዜ ታሪክ አላቸው። አሁንም ቢሆን ለሰዎች በሚያበረክቱት አገልግሎት ረገድ ጠቀሜታቸው አልቀነሰም። መኪኖች በየጊዜው ሞዴላቸው የሚቀያየር ቢሆንም አህዮች ግን ዛሬም ያው ናቸው። በእርግጥም አህዮች በተገቢው መንገድ ሊያዙ የሚገባቸው እንስሳት ናቸው!

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል ምንጭ]

‘The Donkey Sanctuary’, Sidmouth, Devon, UK