በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ በጣም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ለምንድን ነው?

ኢየሱስ በጣም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ለምንድን ነው?

ኢየሱስ በጣም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ለምንድን ነው?

ለፉት 2,000 ዓመታት ለኢየሱስ ልደት ትልቅ ቦታ ሲሰጥ ቆይቷል። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ሐኪም የነበረው ሉቃስ እንደገለጸው አንድ መልአክ ማርያም ለምትባል ወጣት ድንግል “እነሆ፤ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ” ብሎ ነገራት። መልአኩ ስለ ኢየሱስ ከዚህ ሌላስ ምን ተናገረ? “እርሱም ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል ልጅም ይባላል፤ . . . ለዘላለም ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም” አላት።—ሉቃስ 1:31-33

በእርግጥም የሰው ዘር የሚያስፈልገው ምድርን ፍቅራዊ በሆነ መንገድ የሚያስተዳድር እንዲህ ያለ ጻድቅ መሪ ነው! ኢየሱስ ከመወለዱ ከብዙ ጊዜ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው በማለት ትንቢት ተናግሮ ነበር:- “ሕፃን ተወልዶልናልና፤ ወንድ ልጅ ተሰጥቶናል፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል። ስሙም፣ . . . የዘላለም አባት፣ የሰላም ልዑል ይባላል። ለመንግሥቱ ስፋት፣ ለሰላሙም ብዛት ፍጻሜ የለውም።”—ኢሳይያስ 9:6, 7

ጻድቅ መንግሥትና ሰላም—እንዴት ያለ ታላቅ ተስፋ ነው! ይህ መንግሥት በአንድ ልዑል፣ ማለትም ‘በሰላም ልዑል’ ጫንቃ ላይ እንደሚሆን መገለጹን ልብ በል፤ ይህም የፍጥረታት ሁሉ ንጉሥ የሆነው ሁሉን ቻይ አምላክ ይህን አገዛዝ ለልጁ እንደሚሰጥ ያሳያል። በመሆኑም ኢየሱስ እሱ ገዢ የሚሆንበትን ይህን መንግሥት ‘የእግዚአብሔር መንግሥት’ እያለ በተደጋጋሚ ጠርቶታል።—ሉቃስ 9:27, 60, 62

ኢየሱስ ገና አገልግሎቱን እንደጀመረ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል መስበክ ይገባኛል፤ የተላክሁት ለዚሁ ዐላማ ነውና” ብሎ ተናግሯል። (ሉቃስ 4:43) አልፎ ተርፎም ኢየሱስ ተከታዮቹ ይህ መንግሥት እንዲመጣ እንዲጸልዩ አስተምሯል። (ማቴዎስ 6:9, 10) ክርስቲያኒቲ ኤንድ ክራይስስ የተሰኘ አንድ መጽሔት “[የአምላክ] መንግሥት [የኢየሱስ] ትምህርት ዋና ጭብጥ ነበር” በማለት ገልጿል፤ አክሎም “ኢየሱስ የዚህን ያህል ትኩረት የሰጠው ወይም የመልእክቱ ፍሬ ነገር የሆነ ሌላ ርዕስ አልነበረም። ይህ መንግሥት በወንጌል ዘገባዎች ውስጥ ከመቶ ጊዜ በላይ ተጠቅሷል” ብሏል።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ጥያቄዎች

ታዲያ ዛሬ ስለ ኢየሱስ ስታስብ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? ብዙውን ጊዜ በታኅሣሥ ወር ኢየሱስ በግርግም ውስጥ እንደተኛ ሕፃን ተደርጎ በሥዕል ይቀርባል። ኢየሱስ በሕይወቱ ውስጥ ለአጭር ጊዜ ራሱን መርዳት የማይችል ሕፃን እንደነበር አይካድም። (ሉቃስ 2:15-20) ይሁን እንጂ በዋነኝነት ሊታወስ የሚገባው በዚህ መንገድ ነው? እስቲ አስበው፤ ኢየሱስ ሰው ሆኖ የተወለደው ለምን ነበር? ኢየሱስ በእርግጥ ማን ነበር?

የ1996 ኢንካርታ ይርቡክ “ኢየሱስ የአምላክ ልጅና በዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ ነበር?” የሚል ጥያቄ አቅርቦ ነበር። አክሎም “ወይስ ከተራው ሰው የተለየ ቢሆንም ያው ሰው ነበር?” በማለት ጠይቋል። እንዲህ ያሉት ጥያቄዎች በጥሞና ሊታሰብባቸው ይገባል። ለምን? ምክንያቱም ሕይወታችንና ደስታችን የተመካው ለኢየሱስ ባለን አመለካከትና ከእርሱ ጋር በተያያዘ በምናደርገው ነገር ላይ ስለሆነ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “በወልድ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው፤ በወልድ የማያምን ግን . . . ሕይወትን አያይም” ይላል።—ዮሐንስ 3:36

ተራ ሰው አልነበረም

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ የ12 ዓመት ልጅ ሳለ በኢየሩሳሌም በነበረው ቤተ መቅደስ ያደረጋቸውን ነገሮች ከገለጸ በኋላ ከማርያምና ከባሏ ከዮሴፍ ጋር ወደ ቤት እንደተመለሰ፣ “ይታዘዝላቸውም” እንደነበር ይናገራል። (ሉቃስ 2:51, 52) ኢየሱስ ካደገ በኋላ ግን ተራ ሰው አለመሆኑ ግልጽ ሆነ።

ኢየሱስ ማዕበል ያናወጠውን ባሕር ጸጥ ካሰኘ በኋላ ፍርሃት ያደረባቸው ጓደኞቹ “ይህ ማን ነው?” ሲሉ በመደነቅ ጠይቀዋል። (ማርቆስ 4:41) ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ በሐሰት ተከሶ ለገዢው ለጴንጤናዊው ጲላጦስ አልፎ ተሰጠ። ጲላጦስ፣ ኢየሱስ ምንም ጥፋት እንደሌለበት በማረጋገጡና በጭካኔና ፍትሕ በጎደለው ሁኔታ እየተሠቃየም እንኳን ባሳየው የሚያስደንቅ እርጋታ ልቡ በመነካቱ ወደ ሕዝቡ ፊት አወጣውና “እነሆ፤ ሰውየው!” በማለት በአድናቆት ተናገረ። አይሁድ ግን “እኛ ሕግ አለን፤ ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ ስላደረገ በሕጋችን መሠረት መሞት አለበት” አሉ።—ዮሐንስ 19:4-7

ጲላጦስ፣ ኢየሱስ “የእግዚአብሔር ልጅ” መባሉን ሲሰማ ፍርሃት አደረበት። ትንሽ ቀደም ብሎ ሚስቱ ስለ ኢየሱስ በሕልሟ ያየችውን ስትገልጽ “ጻድቅ ሰው” በማለት ጠርታው ነበር። (ማቴዎስ 27:19 የ1954 ትርጉም) ስለዚህ ጲላጦስ ‘ኢየሱስ በእርግጥ ማን ይሆን?’ የሚለው ነገር አሳስቦታል! ጲላጦስ፣ ኢየሱስ የገሊላ ሰው መሆኑን ቢያውቅም “ከየት ነው የመጣኸው?” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን ሲቀር ውይይታቸው ተደመደመ።—ዮሐንስ 19:9, 10

በግልጽ ማየት እንደምንችለው ኢየሱስ ሰው ነበር፤ ይሁን እንጂ ከሌሎች ሰዎች በተለየ መልኩ እርሱ፣ ቀደም ሲል መንፈሳዊ አካል ለብሶ ይኖር የነበረ ከመሆኑም ሌላ በሰማይ ሳለ ቃል በመባል ይጠራም ነበር። ከዚያም አምላክ በተአምራዊ መንገድ ሕይወቱን ወደ ማርያም ማሕፀን አዛወረው። “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ በመካከላችንም አደረ” በማለት ሐዋርያው ዮሐንስ መስክሯል።—ዮሐንስ 1:1, 2, 14, 18፤ ራእይ 3:14 የ1954 ትርጉም

አምላክ በሰማይ የነበረውን ልጁን ወደ ምድር መላክ ያስፈለገው ለምንድን ነው?

የመጀመሪያው ሰው አዳም ልጆች ከመውለዱ በፊት በኃጢአት ወደቀ። ዲያብሎስና ሰይጣን ተብሎ የተጠራ አንድ ዓመጸኛ መልአክ አዳም የአምላክን ትእዛዝ እንዲጥስ አደረገው። በዚህም የተነሳ አምላክ ቀደም ብሎ እንዳስጠነቀቀው አዳም የአምላክ ልጅ የመሆን መብቱን አጣ። በዚህ መንገድ አለመታዘዙ ያስከተለበትን መዘዝ ተቀበለ። ፍጽምናውን አጣ፣ እያረጀ ሄደ፣ በመጨረሻም ሞተ።—ዘፍጥረት 2:15-17፤ 3:17-19፤ ራእይ 12:9

መጽሐፍ ቅዱስ የአዳም አለመታዘዝ ዝርያዎቹ በሆንነው በሁላችንም ላይ ያስከተለውን መዘዝ ሲገልጽ “ኀጢአት በአንድ ሰው በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ ሁሉ፣ ሞትም በኀጢአት በኩል ገብቶአል፤ በዚሁ መንገድ ሞት ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ፤ ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል” ይላል። (ሮሜ 5:12) የሚያሳዝነው ነገር፣ ሁላችንም ከቅድመ አያታችን ከአዳም ኃጢአትን አስከፊ ከሆኑት ውጤቶቹ ማለትም ከእርጅናና ከሞት ጋር ወረስን።—ኢዮብ 14:4፤ ሮሜ 3:23

እንደዚህ ካሉት አስከፊ መዘዞች መላቀቅ የሚቻለው ኃጢአትንና አሰቃቂ ውጤቶቹን ያልወረሰ ፍጹም አባት በማግኘት ብቻ ነው። አዳም ኃጢአት ከመሥራቱ በፊት ከነበረው ፍጽምና ጋር ተመጣጣኝ ፍጽምና ያለው አዲስ አባት ሊገኝ የቻለው እንዴት እንደሆነ ተመልከት።

የሚፈለገው ሰው ተገኘ

“የሰላም ልዑል” እንደሚሆን ተስፋ የተሰጠበት አካል “የዘላለም አባት” ተብሎም እንደተጠራ ታስታውሳለህ። ይህ ልዑል ሰው ሆኖ እንደሚወለድ የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት “እነሆ፤ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች” ይላል። (ኢሳይያስ 7:14፤ ማቴዎስ 1:20-23) ኢየሱስ ሰብዓዊ አባት አልነበረውም፤ የመጀመሪያው ሰው አዳምም ቢሆን እንዲሁ ሰብዓዊ አባት አልነበረውም። የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ጸሐፊ የሆነው ሉቃስ፣ የኢየሱስን የትውልድ ሐረግ የሰው ታሪክ እስከጀመረበት ጊዜ ድረስ ወደኋላ ሲዘረዝር አዳም “የእግዚአብሔር ልጅ” በመሆን ወደ ሕልውና መምጣቱን ገልጾአል። (ሉቃስ 3:38) ይሁን እንጂ ቀደም ሲል እንደተማርነው አዳምም ሆነ ዘሮቹ የአምላክ ልጅ የመሆን መብታቸውን አጥተዋል። ስለዚህ ሁላችንም አዳም ሲፈጠር ከነበረው ፍጽምና ጋር የሚመጣጠን ሕይወት ባለቤት የሆነ አዲስ አባት ያስፈልገናል።

አምላክ፣ የመጀመሪያውን አዳም የሚተካ አዲስ አባት እንዲሆን ልጁን ከሰማይ ላከው። መጽሐፍ ቅዱስ “‘የመጀመሪያው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ’ ተብሎ ተጽፎአል፤ የኋለኛው አዳም ግን ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። የመጀመሪያው ሰው ከምድር የተገኘ ምድራዊ ነው፤ የኋለኛው ግን ከሰማይ ነው” በማለት ይገልጻል። (1 ቆሮንቶስ 15:45, 47) “ኋለኛው አዳም” የሆነው ኢየሱስ በምድር ላይ በፍጽምና ለዘላለም መኖር የሚችሉ ፍጹም ልጆች መውለድ የሚችል ፍጹም ሰው ስለነበረ በዚህ መልኩ ‘ከመጀመሪያው አዳም’ ጋር ይመሳሰላል።—መዝሙር 37:29፤ ራእይ 21:3, 4

ምንም ልጅ ያልወለደው ኢየሱስ ከሰይጣን ብዙ ጥቃት ቢሰነዘርበትም እስከ ሞት ድረስ ለአምላክ ታማኝነቱን ጠብቋል። ኢየሱስ መሥዋዕት ያደረገው ነቀፋ የሌለበት ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ቤዛ ተብሎ ተገልጿል። መጽሐፍ ቅዱስ “[በኢየሱስ ደም] በተደረገ ቤዛነት” ከአዳም ከወረስነው ኀጢአትና ሞት “ይቅርታ አገኘን” ይላል። በተጨማሪም “በአንዱ ሰው [በአዳም] አለመታዘዝ ብዙዎች ኀጢአተኞች እንደ ሆኑ፣ በአንዱ ሰው [በኢየሱስ] መታዘዝ ደግሞ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ” ይላል።—ኤፌሶን 1:7፤ ሮሜ 5:18, 19፤ ማቴዎስ 20:28

በኢየሱስ ካመንን “የዘላለም አባት” እና “መድኅን” ይሆንልናል። ኢየሱስ በአባቱ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ ሲያገለግል መስፍናዊ አገዛዙን ግሩም በሆነ መንገድ ይጠቀምበታል። ከዚህ ቀጥለን በእርሱ አገዛዝ ሥር መኖር ምን እንደሚመስልና አገዛዙ የሚያመጣቸውን ታላላቅ በረከቶች የምናገኘው መቼ እንደሆነ እንመርምር።—ሉቃስ 2:8-11

[በገጽ 5 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ዛሬ ስለ ኢየሱስ ስታስብ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው?

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ “ኋለኛው አዳም” ተብሎ የተጠራው ለምንድን ነው?