በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ ያስገኘው ሕይወት

ኢየሱስ ያስገኘው ሕይወት

ኢየሱስ ያስገኘው ሕይወት

“እነሆ፤ ንጉሥ በጽድቅ ይነግሣል።” የኢየሱስን ንጉሣዊ አገዛዝ የሚገልጹ እንዲህ ያሉ አስደሳች ተስፋዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጉልህ ገጽታዎች ናቸው። ሌላው ተስፋ ደግሞ “ችግረኛው በጮኸ ጊዜ፣ ምስኪኑንና ረዳት የሌለውን ይታደገዋል። ለድኾችና ለችግረኞች ይራራል፤ ምስኪኖችንም ከሞት ያድናል። . . . ደማቸውም በእርሱ ፊት ክቡር ነው” ይላል።—ኢሳይያስ 32:1፤ መዝሙር 72:12-14

በመላው ዓለም ያሉ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ጻድቅ አገዛዝ እንደሚያስፈልጋቸው የሚክድ ሰው ይኖራል? ኢየሱስ ተከታዮቹን የአምላክን መንግሥት እውን መስተዳድር እንደሆነ አድርገው እንዲመለከቱት አሳስቦአቸዋል። “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን” እያሉ እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል።—ማቴዎስ 6:9, 10

የአምላክ መንግሥት መቅረቡን የሚያሳይ ማስረጃ

ይህ ጸሎት መልስ አግኝቶ መንግሥቱ የሚመጣው መቼ እንደሆነ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ተከታዮች የዚህን ጥያቄ መልስ ለማወቅ ጓጉተው ስለነበር “[ንጉሥ ሆነህ] የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክትስ ምንድን ነው?” ብለው ጠይቀውት ነበር። ኢየሱስ መልስ ሲሰጥ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ . . . ይነሣል፤ በተለያየ ስፍራም ራብና የመሬት መንቀጥቀጥ ይሆናል፤ ይህ ሁሉ ግን የምጡ መጀመሪያ ነው” አለ። በተጨማሪም “ክፋት ስለሚገን የብዙ ሰዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል” በማለት አስጠንቅቋል።—ማቴዎስ 24:3-12

ሌላው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ደግሞ እንዲህ ይላል:- “በመጨረሻው ዘመን የሚያስጨንቅ ጊዜ እንደሚመጣ ይህን ዕወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉ፤ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክሕተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ለዕርቅ የማይሸነፉ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በከንቱ በትዕቢት የተወጠሩ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉና። ሃይማኖታዊ መልክ አላቸው፤ ኀይሉን ግን ክደዋል።”—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5

‘ስለ መጨረሻው ዘመን’ የተሰጠው ይህ መግለጫ የምንኖርበትን ዘመን በትክክል እንደሚገልጸው ሳትስማማ አትቀርም። የሚከተለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት የሚፈጸምበት ጊዜ አሁን መሆኑን የሚያረጋግጡ ብዙ ማስረጃዎች አሉ:- “የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”—ዳንኤል 2:44

‘በሰላሙ ልዑል’ የሚመራው መንግሥታዊ አገዛዝ፣ ከዚህ ዓለም ፍጻሜ በሕይወት የሚተርፉትን ሰዎች ሰላም ሊያደፈርስ የሚችለውን ማንኛውንም ነገር ያስወግዳል። (ኢሳይያስ 9:6) የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት “ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል” በማለት ተስፋ ይሰጣል። (1 ዮሐንስ 2:17) የዚህ ዓለም መጥፋት፣ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርጉ ሰዎች የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ ካመጹበት ጊዜ ጀምሮ ሰብዓዊው ቤተሰብ ያጣውን ነገር መልሰው እንዲያገኙ መንገድ ይከፍታል።

በቅርቡ የሚመጣው ሕይወት

ኢየሱስ “በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን [ይቀመጣል]” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 19:28 የ1954 ትርጉም) ይህ “ዳግመኛ ልደት” ምንድን ነው? አዲሱ መደበኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም “በሚመጣው አዲስ ዓለም” የሚል አገላለጽ ይጠቀማል። ይህንኑ ሁኔታ የመዘገበው ሌላው የወንጌል ጸሐፊ “በሚመጣውም ዘመን [“ሥርዓት፣” NW]” ይላል። (ሉቃስ 18:30) በዚያን ጊዜ ኢየሱስ፣ የሰላም ልዑል እንዲሆን አምላክ የሰጠውን ሥልጣን በመጠቀም እሱ ባቀረበው ቤዛዊ መሥዋዕት ላመኑት ሰዎች ሁሉ የዘላለም ሕይወት ይሰጣቸዋል።—ዮሐንስ 5:21

በመጪው የአምላክ አዲስ ሥርዓት ውስጥ ሰዎች፣ አምላክ አዳምንና ሔዋንን በምድራዊ ገነት ባስቀመጣቸው ጊዜ የሰጣቸው ዓይነት ሕይወት ያገኛሉ። አዳምና ሔዋን ልጆች ወልደው ‘ምድርን እንዲሞሏትና እንዲገዟት’ አምላክ አዟቸው እንደነበር አስታውስ። የተሰጣቸው ሥራ መላዋን ምድር ኤደን ገነት ማድረግ ነበር! (ዘፍጥረት 1:28) በተመሳሳይም በሚመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ምድር፣ ከዚህ ዓለም ጥፋት በሕይወት በሚተርፉ ሰዎችና በልጆቻቸው እንዲሁም በትንሣኤ አማካኝነት እንደገና ሕይወት በሚያገኙ ሰዎች ትሞላለች። እነዚህ ሰዎች በአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ መሠረት ምድርን ወደ ገነትነት በመለወጡ ሥራ ይካፈላሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ በዚያ ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ ሰዎች እንደሚያገኟቸው ከሚናገራቸው በረከቶች አንዳንዶቹን ተመልከት።—2 ጴጥሮስ 3:13

በእነዚህ ገጾች ላይ በሥዕል የተገለጹት ተስፋዎች ይፈጸማሉ ብሎ ማመን አዳጋች ቢመስልም “በሚመጣው አዲስ ዓለም” እንደሚፈጸሙ የተረጋገጠ ነው። ኢየሱስ ለአምላክ ባቀረበው ጸሎት ላይ ሰዎች እነዚህን በረከቶች ለማግኘት ምን እንደሚፈለግባቸው ሲገልጽ “እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ብሏል። (ዮሐንስ 17:3) ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ይህን ሕይወት ሰጪ እውቀት ከሚፈልጉ ሰዎች መካከል እንድትሆን እንመኛለን።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ስሙም . . . የሰላም ልዑል ይባላል። ለመንግሥቱ ስፋት፣ ለሰላሙም ብዛት ፍጻሜ የለውም።”—ኢሳይያስ 9:6, 7

[በገጽ 8 እና 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ሁሉም ሰው ቤትና ሥራ ይኖረዋል

“ሰዎች ቤት ይሠራሉ፤ በውስጡም ይኖራሉ፤ . . . ሌላው እንዲበላው አይተክሉም።”—ኢሳይያስ 65:21, 22

ሁሉም ሰው የተትረፈረፈ ምግብ ያገኛል

“ምድር ፍሬዋን ሰጠች።” “በምድሪቱ ላይ እህል ይትረፍረፍ።”—መዝሙር 67:6፤ 72:16

ዓለም አቀፋዊ ሰላም ስለሚኖር እንስሳትም ጭምር ሰላማዊ ይሆናሉ

“ተኵላ ከበግ ጠቦት ጋር ይኖራል፤ ነብርም ከፍየል ግልገል ጋር ይተኛል፤ . . . ትንሽ ልጅም ይመራቸዋል።”—ኢሳይያስ 11:6

ጦርነት ይወገዳል፤ ለዘላለም ሰላም ይሰፍናል

“ሕዝብ በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፤ ጦርነትንም ከእንግዲህ አይማሩም።” “ለመንግሥቱ ስፋት፣ ለሰላሙም ብዛት ፍጻሜ የለውም።”—ኢሳይያስ 2:4፤ 9:7

በሞት የተለዩን የምንወዳቸው ሰዎች ይነሳሉ

‘በመቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ የኢየሱስን ድምፅ ሰምተው የሚወጡበት ጊዜ ይመጣል።’—ዮሐንስ 5:28, 29

በሽታና ሞት አይኖሩም

“በጽዮን ተቀምጦ፣ ‘ታምሜአለሁ’ የሚል አይኖርም።” “ከእንግዲህ ወዲህ ሞት . . . አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና።”—ኢሳይያስ 33:24፤ ራእይ 21:3, 4