በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው

እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው

እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው

እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው ማን እንደሆነ ብትጠየቅ ማንን ትመርጣለህ? ከጥፋት ውኃ ተርፎ ዛሬ በምድር ላይ ላሉት ሰዎች ሁሉ ቅድመ አያት ለመሆን የበቃውን ኖኅን ትጠቅሳለህ? (ዘፍጥረት 7:1, 21, 22፤ 9:18, 19) ወይስ ታላቂቷ ባቢሎን ብሎ የሰየማትን ውብ ከተማ የገነባውንና ጥንት የዓለም ገዢ የነበረውን ናቡከደነፆርን? (ዳንኤል 4:28-30) ምናልባትም ባከናወናቸው ነገሮች የተነሳ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችም ጭምር የተጠቀሰውን ታላቁ እስክንድርን ታስታውስ ይሆን? (ዳንኤል 8:5-8, 21-22) ወይስ ዝነኛ የሮማ ገዢ የነበረውን ጁሊየስ ቄሣርን?

ጁሊየስ ቄሣር ከሞተ ከ45 ዓመታት በኋላ በቤተልሔም ኢየሱስ የሚባል ልጅ ተወለደ። ይህ ልጅ በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ ሰው ለመሆን በቅቶ ይሆን? ከመቶ ዓመት ገደማ በፊት ዘ ሂስቶሪያንስ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ወርልድ የተሰኘ መጽሐፍ የሚከተለውን ብሎ ነበር:- “[ኢየሱስ] ያደረጋቸው ነገሮች በታሪክ ላይ ያስከተሉት ውጤት ከሃይማኖታዊ አመለካከት ውጪ እንኳን ሲታይ ማንኛውም ሌላ የታሪክ ሰው ካደረገው እጅግ የሚልቅ ነው። በዓለም ከፍተኛ የሥልጣኔ ደረጃ ላይ በደረሱ አገሮች ዘንድ እውቅና ያገኘ አዲስ ዘመን የጀመረው ከኢየሱስ ልደት ወዲህ ነው።”

እስከ ዛሬም ድረስ ለኢየሱስ ክርስቶስ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጠዋል። ከጥቂት ዓመታት በፊት የዩናይትድ ስቴትስ ታዋቂ የዜና መጽሔቶች የሆኑት ታይም፣ ኒውስዊክ እና ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ዎርልድ ሪፖርት በተመሳሳይ ጊዜ በመጀመሪያ ገጻቸው ላይ ስለ ኢየሱስ አትተው ነበር። ለኢየሱስ የሚሰጠው ትኩረት ከዚህ በኋላም እየጨመረ የሚሄድ ይመስላል። በ2004 ቶሮንቶ ስታር የተባለው ጋዜጣ “[የኢየሱስ] መንፈስ በፊልሙ፣ በሙዚቃውና በፋሽኑ ዓለም አሁንም ሕያው ነው” ብሎ ነበር። “ኢየሱስ ታዋቂ ከሆኑት ሰዎች አንዱ ሆኗል።”

የሚገርመው ነገር፣ ከቅርብ ጊዜ በፊት አንዳንዶች ኢየሱስ በሕይወት የነበረ ሰው አይደለም እያሉ ሲከራከሩ ነበር። ከ1809-1882 የኖረው ብሩኖ ባወር የተባለ እውቅ አስተማሪ እንዲህ በማለት ያስተምር ነበር። ከተማሪዎቹ መካከል አንዱ ደግሞ ካርል ማርክስ ነበር። በቅርቡ ሮበርት ቫን ቮርስት ጂሰስ አውትሳይድ ዘ ኒው ቴስታመንት (ኢየሱስ ከአዲስ ኪዳን ውጪ) በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ እንደሚከተለው በማለት ጽፈዋል:- “ማርክስ፣ ኢየሱስ በአፈ ታሪክ የተፈጠረ ሰው ነው የሚለውን የባወርን አስተሳሰብ ውሎ አድሮ በራሱ ፍልስፍና ውስጥ ያካተተ ሲሆን ከዚያ በኋላም የሶቪየት ሥነ ጽሑፎችና ሌሎችም የኮሚኒስት ፕሮፓጋንዳዎች ይህንኑ ትምህርት አሰራጭተዋል።”

በአሁኑ ጊዜ ግን ብዙዎች ኢየሱስ በእርግጥ በሕይወት የኖረ ሰው መሆኑን አይክዱም። እንዲያውም አብዛኞቹ ሰዎች ኢየሱስ በእርግጥ በሕይወት ኖሮ የሚያውቅ ሰው ብቻ ሳይሆን በጣም ታላቅ ሰውም እንደነበረ ያላንዳች ማንገራገር ይቀበላሉ። በታኅሣሥ 2002 አንድ የዎል ስትሪት ጆርናል አዘጋጅ “ሳይንስ ኢየሱስን ገሸሽ ሊያደርገው አይችልም” የሚል ርዕስ አውጥቶ ነበር። ጸሐፊው ሲያጠቃልል “አልፎ አልፎ ከሚያጋጥሙን አምላክ የለሾች በቀር አብዛኞቹ ምሁራን የናዝሬቱን ኢየሱስን በታሪክ እንደነበረ ሰው አድርገው ተቀብለውታል” ብሏል።

ይሁን እንጂ ኢየሱስ እንዲሁ በታሪክ የታወቀ ሰው ብቻ አልነበረም። ታይም መጽሔት “በእነዚህ ሁለት ሺህ ዓመታት ብቻ ሳይሆን በሰው ዘር ታሪክ በሙሉ በጣም ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረው ሰው የናዝሬቱ ኢየሱስ መሆኑን መካድ ምክንያታዊነት የጎደለው አስተሳሰብ ይሆናል” ብሏል። አክሎም “የኢየሱስን ያህል በጣም ከፍተኛና ዘላቂ ተጽዕኖ ያሳደረ መሆኑ የተረጋገጠለት ሌላ ማንም ሰው እንደሌለ ጠንካራ ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል” ብሏል።

የሆነ ሆኖ ኢየሱስ በእርግጥ ማን ነበር? ከየትስ መጣ? በምድር ላይ የኖረበት ዓላማ ምን ነበር? ደግሞስ ስለ እርሱ የቻልነውን ሁሉ ማወቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? የሚሉት ጥያቄዎች መልስ ይሻሉ።