በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአንባቢዎቻችን

ከአንባቢዎቻችን

ከአንባቢዎቻችን

ፍቅር የጠፋው ለምንድን ነው? (መጋቢት 2006) ዓለም የፍቅርን ትርጉም ያዛባው ሲሆን ሰይጣን ደግሞ ፍቅር ከነጭራሹ እንዲጠፋ ይፈልጋል። እንዲህ የመሰለው ጽሑፍ ከራስ ወዳድነት በራቀ መንገድ ፍቅራችንን እንድንገልጽ ይረዳናል። ይሖዋ ይህን ከፍተኛ ኃይል ያለው ባሕርይ እንዴት እንድንጠቀምበት እንደሚፈልግ ያለኝን ግንዛቤ ስላሳደጋችሁልኝ አመሰግናችኋለሁ።

ዪ. ቢ.፣ ዩናይትድ ስቴትስ

በጣም የምቀርባቸው ሁለት ጓደኞቼ በውጭ አገር ቋንቋ በሚካሄዱ ጉባኤዎች ውስጥ ለማገልገል ሲሄዱ ብቸኝነት ተሰምቶኝ ነበር። ሆኖም ከፍተኛ የብቸኝነት ስሜት ተሰምቶኝ በነበረበት ወቅት ይህ መጽሔት ደረሰኝ። “በሌሎች ዘንድ ለመወደድ ከፈለጋችሁ አፍቃሪዎች ሁኑ” ለሚለው ማሳሰቢያ አመስጋኝ ነኝ። ከአሁን በኋላ አዲስ ጓደኝነት ለመመሥረት እንድችል ‘ልቤን ለመክፈት’ እንዲሁም ለሌሎች ከልብ የመነጨ ፍቅር ለማሳየት ወስኜያለሁ።—2 ቆሮንቶስ 6:12, 13

ኤም. ቲ.፣ ጃፓን

የዕድሜ መግፋት የሚያስከትለውን ችግር ተቋቁሞ መኖር (የካቲት 2006) አንዳንድ ጊዜ አረጋውያን ችላ እንደተባሉ ይሰማኛል። ሕመምተኛ የሆነውን ባለቤቴን ለ11 ዓመታት ስንከባከብ ቆይቻለሁ። አሁንም ቢሆን አንዳንድ ጊዜ ብቸኝነት ይሰማኛል። ይህንን ንቁ! መጽሔት ደጋግሜ ከማንበቤም በላይ ካሴቱን ብዙ ጊዜ አዳምጬዋለሁ። የሚያስፈልገኝ በዚህ መጽሔት ላይ የሰፈረው ዓይነት ማበረታቻ ነበር። በጣም አመሰግናችኋለሁ።

ኤስ. ቲ.፣ ጃፓን

ሰው ሠራሽ እጅና እግር (የካቲት 2006) ስለ ሰው ሠራሽ እጅና እግር ለሚናገረው ርዕስ እጅግ አመስጋኝ ነን። የአራት ወር ነፍሰ ጡር እያለሁ፣ ልጃችን ሲወለድ እጅና እግር እንደማይኖረውና አንድ ዓመት ሲሞላው ሰው ሠራሽ እግር ሊተከልለት እንደሚችል ተነገረን። ይህ መጽሔት የደረሰን ልጃችን ዳሪል ልክ አንድ ዓመት ሲሆነው ነበር። አሁን መቆምና መራመድ እየተለማመደ ነው። እኔና ባለቤቴ፣ ዳሪል ‘እንደ ሚዳቋ ሲዘል’ በማየት የምንደሰትበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን።—ኢሳይያስ 35:6

ዋይ. ኤ.፣ ፈረንሳይ

በሕይወት መኖርን የመሰለ ነገር የለም (ኅዳር 2001) የኅዳር 2001 ንቁ! መጽሔትን ደጋግሜ ያነበብኩት ሲሆን በተለይ የተስፋ መቁረጥ ስሜት በሚሰማኝ ጊዜ መጽሔቱን አውጥቼ አነበዋለሁ። በመጽሔቱ ላይ የሰፈረው ሐሳብ ለእኔ ጊዜ እንደማያልፍበት መድኃኒት ነው። የያዘው ምክርም ሆነ ለችግሮቻችን የሚሰጠው መፍትሔ እጅግ ጠቃሚ ነው። ንቁ! መጽሔት፣ እንደ እኔ ላሉ ግለሰቦች እንደምታስቡ እንዲሰማኝ ስለሚያደርግ መንፈሴን ያድስልኛል። ‘በሕይወት መኖርን የመሰለ ነገር እንደሌለ’ የሚያስታውሰኝ እንዲህ ዓይነት ጽሑፍ ስለምታዘጋጁ እጅግ ደስተኛና አመስጋኝ ነኝ።

ፒ. ቲ.፣ ማዳጋስካር

ፒልግሪሞች እና ፒዩሪታኖች እነማን ነበሩ? (የካቲት 2006) በዚህ ርዕስ ሥር ሐቁን የሚያዛባ መረጃ ማንበቤ በጣም አስደንግጦኛል። የሰሜን አሜሪካ ሕንዶች ታንክስጊቪንግ የተባለውን በዓል የማያከብሩበት መሠረታዊ ምክንያት አላቸው፤ እናንተ ግን እውነታውን ሸፋፍናችሁታል።

ስም አልተጠቀሰም፣ ዩናይትድ ስቴትስ

የንቁ! መጽሔት አዘጋጆች መልስ:- የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ስለ ታንክስጊቪንግ ቀን በዝርዝር ለመግለጽ እንዳልሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል። “ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካን” ጨምሮ በርካታ የማመሣከሪያ ጽሑፎች በ1621 የመከር ወቅት፣ ፒልግሪሞች ከአሜሪካ ሕንዶች ጓደኞቻቸው ጋር ሆነው ለሦስት ቀናት ግብዣ ማድረጋቸውን ሪፖርት አድርገዋል። ይህም ኤድዋርድ ዊንስሎው ታኅሣሥ 11, 1621 በጻፈው ደብዳቤ ላይ ተገልጿል። ሆኖም በተከታዮቹ ዓመታት የመከር ወቅትን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ክንውኖችንም ለማክበር የታንክስጊቪንግ በዓል ይደረግ ጀመር። በ1637፣ የማሳቹሴትስ ቤይ ግዛት አገረ ገዢ የሆነው ጆን ዊንትሮፕ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፔክዎት ሕንዶች ከተጨፈጨፉ በኋላ እንዲከበር ያደረገው “የታንክስጊቪንግ” በዓል በመጥፎ የሚታወስ ነው። በመሆኑም የታንክስጊቪንግ ቀን መከበር አንዳንድ አንባቢዎቻችንን ለምን ቅር እንደሚያሰኛቸው መረዳት እንችላለን።