በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ካሊፕሶ—የትሪኒዳድ መለያ የሆነ ባሕላዊ ሙዚቃ

ካሊፕሶ—የትሪኒዳድ መለያ የሆነ ባሕላዊ ሙዚቃ

ካሊፕሶ—የትሪኒዳድ መለያ የሆነ ባሕላዊ ሙዚቃ

ትሪኒዳድ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ትሪኒዳድና ቶቤጎ ሪፑብሊክ ስለተባሉት ሁለት ደሴቶች ስትሰማ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? ብዙ ሰዎች በብረት በተሠሩ የሙዚቃ መሣሪያዎች የሚጫወቱ ኦርኬስትራዎችና ሞቅ ያለው የካሊፕሶ ሙዚቃ ትዝ ይሏቸዋል። እንዲያውም ከአእምሮ የማይጠፋው የካሊፕሶ ዜማና ለየት ያለው የሙዚቃ ስልት፣ ሙዚቃው በተገኘበት በደቡብ ካሪቢያን ባሕር አካባቢ ብቻ ሳይሆን በበርካታ አገሮች ታዋቂ ሆኗል። *

ካሊፕሶ ካላሉ የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው ካሊፕሶ የሚለው ስም “ከ1898 ገደማ በኋላ በነበሩት ዓመታት በትሪኒዳድ በሚከበሩ ሕዝባዊ በዓላት ወቅት ሰዎች በጎዳናዎች ላይ የሚዘፍኑትንም ሆነ ልምድ ያላቸውና በትርፍ ሰዓታቸው የሚያቀነቅኑ ሙዚቀኞች በመድረክ ላይ የሚጫወቱትን ሙዚቃ የሚያመለክት ነው።” ካሊፕሶ፣ ታሪክ የማውራት ልማድ ከነበራቸውና በባርነት ወደ ትሪኒዳድ ከመጡ የጥንት አፍሪካውያን የተወረሰ ሊሆን ይችላል። ከጊዜ በኋላም ተወዳጅ የሆነው የአፍሪካ ዘፈን፣ ጭፈራና የከበሮ ምት ከፈረንሳይ፣ ከስፔን፣ ከእንግሊዝና ከሌሎች አገሮች ሙዚቃ ጋር የፈጠረው ጥምረት ለካሊፕሶ መገኘት ምክንያት ሆኗል።

ካሊፕሶ የሚለውን ስም አመጣጥ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። አንዳንዶች ጥሩ ሥራ ያከናወነን ሰው ለማወደስ ይጠቀሙበት ከነበረው ካይሶ ከሚለው የምዕራብ አፍሪካውያን ቃል እንደመጣ ያምናሉ። በ1830ዎቹ በትሪኒዳድና ቶቤጎ የባርነት ሥርዓት ከማብቃቱ በፊት እንኳ በዓመታዊ የሕዝብ በዓላት ወቅት፣ ቻንትዌሎች (ዘፋኞች) ራሳቸውን እያሞገሱና በሌሎች ላይ እያፌዙ ሲያዜሙ ለማዳመጥ ሰዎች ይሰበሰቡ ነበር። እያንዳንዳቸው የካሊፕሶ ዘፋኞች፣ ራሳቸውን ከሌሎች ለመለየት በቅጽል ስም ይጠራሩ እንዲሁም የራሳቸውን ለየት ያለ ስልት ይፈጥሩ ነበር።

የካሊፕሶ ስልትና ያሳደረው ተጽዕኖ

የካሊፕሶ ዘፋኞች ቁም ነገር አዘል በሆነው ጨዋታቸው ሕዝቡን ያስደስቱ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ በርካታ የካሊፕሶ ዘፋኞች ብዙውን ጊዜ ገላጭ በሆኑ ቃላት የተቀመሙና ከዘፈኑ መልእክት ጋር የሚስማሙ በርካታ ስንኞችን ሳይዘጋጁበት ወዲያውኑ በመግጠም የመዝፈን አስደናቂ ችሎታ ነበራቸው። ቀደም ባሉት ጊዜያት አብዛኞቹ የካሊፕሶ ዘፋኞች የአፍሪካውያን ዝርያ ያላቸው የትሪኒዳድ ዜጎች ሲሆኑ በኢኮኖሚም ረገድ ዝቅተኛ ነበሩ፤ ሆኖም በዛሬው ጊዜ የተለያየ ዘር፣ ቀለምና የኑሮ መደብ ያላቸው የካሊፕሶ ዘፋኞች አሉ።

የትሪኒዳድና ቶቤጎ የባሕል ዲሬክተር የነበሩት ዶክተር ሃለስ ሊቨርፑል ታሪክ ጸሐፊና የካሊፕሶ ሙዚቃ ባለሙያ ናቸው። እኚህ ሰው፣ የቀድሞዎቹን የካሊፕሶ ዘፋኞች አስመልክተው ለንቁ! ዘጋቢ እንዲህ በማለት ተናግረዋል:- “ለመዝናናት፣ ወሬ ለማዳመጥና ከዚህ በፊት የሰሙትን ነገር ለማረጋገጥ [የካሊፕሶ ዘፋኞች ወደሚገኙበት] ድንኳን የሚመጡ ሰዎችን የማዝናናት ልዩ ተሰጥኦ ነበራቸው። ከፍተኛ ቦታ ያላቸው ግለሰቦች ዝቅተኛው የኅብረተሰቡ ክፍል ምን እያደረገ እንዳለ የሚወራውን ለመስማት የሚመጡ ሲሆን የአገሩ ገዢ ከረዳቶቻቸው ጋር በመሆን በቦታው የሚገኙት ደግሞ በፖለቲካው ዓለም ሕዝቡ ስለ እነርሱ ምን እንደሚሰማው ለማወቅ ነው።”

ብዙውን ጊዜ የካሊፕሶ ዘፋኞች በባለ ሥልጣናቱና በማኅበረሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ባላቸው ሰዎች ላይ ያሾፋሉ። በዚህም ምክንያት የካሊፕሶ ዘፋኞችን ተራው ሕዝብ እንደ ጀግና ሲመለከታቸው ባለ ሥልጣናቱ ግን ችግር ፈጣሪ እንደሆኑ አድርገው ያዩዋቸው ነበር። የካሊፕሶ ዘፋኞች አንዳንድ ጊዜ የሚያቀናብሯቸው ዘፈኖች ኃይለኛ ትችት ያዘሉ በመሆናቸው በቅኝ ግዛት የያዛቸው መንግሥት እነርሱን ለመቆጣጠር የሚያስችል ሕግ ማውጣት እንደሚያስፈልግ ተሰማው። በምላሹም ዘፋኞቹ በግጥሞቻቸው ውስጥ ቅኔ አዘል ሐሳቦችን ማካተት የጀመሩ ሲሆን በዚህም የተካኑ ሆኑ። እስከ ዛሬም ድረስ በካሊፕሶ ዘፈኖች ግጥም ውስጥ ቅኔ ዋነኛውን ቦታ ይዟል።

የካሊፕሶ ዘፋኞች በቋንቋቸው ጥሩ አድርገው ከመጠቀም አልፈው ቋንቋ ይፈጥሩ ነበር። እንዲያውም በዌስት ኢንዲስ ለሚሠራበት የንግግር ቋንቋ ጉልህ አስተዋጽኦ አድርገዋል። በመሆኑም የፖለቲካ ሰዎችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች አንድን ነጥብ ለማጉላት ሲፈልጉ ብዙ ጊዜ የካሊፕሶ ዘፋኞችን አባባል መጥቀሳቸው አያስደንቅም።

ዘመናዊ የካሊፕሶ ሙዚቃ

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ ልዩ ልዩ የሙዚቃ ምርጫ ያላቸውን ሰዎች የሚያስደስቱና ከሌሎች የሙዚቃ ስልቶች ጋር የተቀላቀሉ የተለያዩ የካሊፕሶ ዜማዎች ይዘጋጃሉ። እንደ አብዛኞቹ ዘፈኖች ሁሉ አንዳንድ የካሊፕሶ ዘፈኖች ግጥምም ከፍተኛ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች የሚንጸባረቁበት አይደለም። በመሆኑም የምናዳምጠውን በመምረጥ ረገድ ጥበበኞች መሆን አለብን። (ኤፌሶን 5:3, 4) ‘ቅኔያዊ በሆነ መንገድ የተገለጹትን ግጥሞች ለልጆቼ ወይም የካሊፕሶን ዘፈን ብዙም ለማያውቅ ሰው ማብራራት ያሳፍረኛል?’ እያልን ራሳችንን ልንጠይቅ እንችላለን።

ወደ ትሪኒዳድና ቶቤጎ ከመጣችሁ፣ ውብ በሆኑት የባሕር ዳርቻዎችም ሆነ በባሕር ውስጥ በሚገኙት ዐለቶች እንደምትደሰቱ እንዲሁም የተለያየ ዘርና ባሕል ያላቸው ሰዎች ተቀላቅለው በሚኖሩባት ደሴት እንደምትደነቁ ጥርጥር የለውም። ከዚህም በተጨማሪ በዓለም ዙሪያ የወጣቶችንም ሆነ የአዋቂዎችን ስሜት በማረከውና ከአእምሮ በማይጠፋው ሞቅ ያለ የካሊፕሶ ዘፈን እንዲሁም በብረት በተሠሩ የሙዚቃ መሣሪያዎች በሚጫወቱት ኦርኬስትራዎች ልትዝናኑ ትችላላችሁ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 ብዙውን ጊዜ ከብረት በተሠሩ የሙዚቃ መሣሪያዎች የሚጠቀሙ ኦርኬስትራዎች የካሊፕሶን ጣዕመ ዜማ የሚጫወቱ ሲሆን የካሊፕሶ ዘፋኞች ግን አብዛኛውን ጊዜ በጊታር፣ በጥሩንባ፣ በሳክስፎንና በታምቡሮች ታጅበው ይዘፍናሉ።

[በገጽ 24 እና 25 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ከብረት የተሠሩ ታምቡሮች