በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያህል መመሪያ የሚበዛብኝ ለምንድን ነው?

ይህን ያህል መመሪያ የሚበዛብኝ ለምንድን ነው?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

ይህን ያህል መመሪያ የሚበዛብኝ ለምንድን ነው?

“በተወሰነ ሰዓት ቤት እንድገባ የሚጠበቅብኝ መሆኑ በጣም ያበሳጨኝ ነበር! ሌሎች ልጆች አምሽተው እንዲገቡ የሚፈቀድላቸው መሆኑ በጣም ያናድደኝ ነበር።”—አለን

“በሞባይል ስልክህ ለማን እንደምትደውል ወይም እነማን እንደሚደውሉልህ ለማወቅ ቁጥጥር ሲደረግብህ በጣም ያናድዳል። እንደ ትንሽ ልጅ የምታይ ይመስለኛል!” —ኤሊዛቤት

ቤት ውስጥ ከልክ በላይ መመሪያዎች እንደበዙብህ ይሰማሃል? ከቤት ሳታስፈቅድ ተደብቀህ ለመውጣት ወይም ያደረግከውን ነገር በተመለከተ ለወላጆችህ ለመዋሸት ተፈትነህ ታውቃለህ? እንዲህ ከሆነ፣ በአሥራዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ የምትገኝ አንዲት ወጣት ስሜቷን በገለጸችበት መንገድ ትስማማ ይሆናል፤ ወላጆቿ ከሚገባው በላይ እንደሚቆጣጠሯት ስለተሰማት ‘መተንፈሻ አሳጡኝ!’ በማለት ተናግራለች።

ወላጆችህ ወይም አሳዳጊዎችህ መመሪያዎችን ያወጡልህ አሊያም ደግሞ ማድረግ ያለብህንና የሌለብህን ነገሮች ይነግሩህ ይሆናል። ይህም ሲባል የትምህርት ቤት ሥራህን፣ የቤት ውስጥ ሥራዎችን እንዲሁም ቤት የምትገባበትን ሰዓትና የስልክ፣ የቴሌቪዥን ወይም የኮምፒውተር አጠቃቀምህን በተመለከተ ምን እንደሚጠበቅብህ የሚገልጹ መመሪያዎችን ሊጨምር ይችላል። እነዚህ መመሪያዎች ከቤት ውጭ በምትሆንበት ጊዜ ማለትም በትምህርት ቤት የምታሳየውን ባሕርይና የጓደኞች ምርጫህንም የሚመለከቱ ሊሆኑ ይችላሉ።

በርካታ ወጣቶች፣ ብዙውን ጊዜ ወላጆቻቸው ያወጡላቸውን መመሪያዎች ይጥሳሉ። በአንድ ጥናት ላይ ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው በጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል ሁለት ሦስተኛ ገደማ የሚሆኑት፣ ወላጆቻቸው የሚያወጡላቸውን መመሪያዎች በመጣሳቸው ምክንያት ተግሣጽ ተሰጥቷቸው እንደሚያውቅና ብዙ ጊዜ ለቅጣት የሚዳርጋቸውም ይህ መሆኑን ተናግረዋል።

አብዛኞቹ ወጣቶች በቤት ውስጥ ሥርዓት እንዲኖር አንዳንድ መመሪያዎች አስፈላጊ መሆናቸውን ያምናሉ። ሆኖም ወላጆች የሚያወጧቸው መመሪያዎች ይህን ያህል አስፈላጊ ከሆኑ አንዳንዶቹ መመሪያዎች ልጆችን የሚያበሳጯቸው ለምንድን ነው? እነዚህ መመሪያዎች የማያፈናፍኑ እንደሆኑ ከተሰማህ፣ በተወሰነ መጠን ነፃነት እንድታገኝ ምን ልታደርግ ትችላለህ?

‘ሕፃን ልጅ አይደለሁም’!

በአሥራዎቹ ዕድሜ የምትገኘው ኤመሊ “ወላጆቼ፣ ሕፃን ልጅ እንዳልሆንኩ እንዲገነዘቡና የተወሰነ ነፃነት ሰጥተውኝ በራሴ አንዳንድ ነገሮችን እንዳከናውን እንዲፈቅዱልኝ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?” በማለት ጠይቃለች። አንተስ እንዲህ ተሰምቶህ ያውቃል? ልክ እንደ ኤመሊ አንተም፣ ወላጆችህ ምንም ማድረግ እንደማይችል ሕፃን አድርገው እንደሚመለከቱህ ስለሚሰማህ የሚያወጧቸው መመሪያዎች ያበሳጩህ ይሆናል። የወላጆችህ አመለካከት ከዚህ የተለየ እንደሚሆን ግልጽ ነው። እንዲያውም የሚያወጡልህ መመሪያዎች፣ አንተን ከጉዳት በመጠበቅም ሆነ አዋቂ ስትሆን የምትሸከማቸውን ኃላፊነቶች በሚገባ መወጣት እንድትችል ከወዲሁ በማዘጋጀት ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱ ይሰማቸዋል።

ምናልባት በተወሰነ መጠን ነፃነት ይኖርህ ይሆናል፤ ሆኖም እያደግክ ስትሄድ ወላጆችህ ልጅ ሳለህ ያወጡልህ መመሪያዎች ምንም እንዳልተለወጡ ይሰማህ ይሆናል። በተለይ ደግሞ ወላጆችህ በወንድሞችህና በእህቶችህ ላይ ያን ያህል ጥብቅ ካልሆኑ ሁኔታው ይበልጥ ሊያበሳጭህ ይችላል። ማርሲ የተባለች ወጣት እንዲህ ትላለች:- “17 ዓመቴ ቢሆንም ከቤት ውጭ እንዳመሽ አይፈቀድልኝም። አንድ ነገር ሳጠፋ ከቤት እንዳልወጣ እደረጋለሁ። ሆኖም ወንድሜ በእኔ ዕድሜ ላይ በነበረበት ጊዜ በተወሰነ ሰዓት እንዲገባ አይጠበቅበትም ነበር፤ እንዲሁም ሲያጠፋ ከቤት እንዳይወጣ ተከልክሎ አያውቅም።” ማቲው ወጣት የነበረበትን ጊዜ በማስታወስ ስለ ታናሽ እህቱና ስለ አክስቱ ልጆች ሲናገር “ምንም ዓይነት ከባድ ጥፋት ቢያጠፉም እንኳ አይቀጡም!” ብሏል።

ጨርሶ መመሪያ ባይኖርስ?

ከወላጆችህ ቁጥጥር ነፃ የምትወጣበትን ጊዜ ትናፍቅ ይሆናል። ሆኖም ከእነርሱ ቁጥጥር ነፃ መውጣትህ የሚጠቅምህ ይመስልሃል? ምናልባት እስከፈለጉበት ሰዓት አምሽተው ቤታቸው የሚገቡ፣ ያሻቸውን የሚለብሱ ብሎም ከጓደኞቻቸው ጋር ወደፈለጉበት ቦታ ባሰኛቸው ሰዓት የሚሄዱ በአንተ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶችን ታውቅ ይሆናል። የእነዚህ ልጆች ወላጆች በሥራ ከመጠመዳቸው የተነሳ ልጆቻቸው ምን እንደሚያደርጉ ሳያስተውሉ ቀርተው ይሆናል። ያም ሆነ ይህ፣ እንዲህ ዓይነቱ የልጅ አስተዳደግ የተሳካ ውጤት እንደማያስገኝ ተረጋግጧል። (ምሳሌ 29:15) ዛሬ በዓለም ላይ ለሚታየው የፍቅር መጥፋት ዋነኛው መንስኤ ቁጥጥር በማይደረግበት ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ ራስ ወዳድ ሰዎች መብዛታቸው ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5

የወላጅ ቁጥጥር ስለማይደረግበት ቤት ያለህ አመለካከት አንድ ቀን ይለወጥ ይሆናል። ብዙም መመሪያ በማይሰጥበትና ወላጆች ምንም ቁጥጥር በማያደርጉበት ቤት ውስጥ ባደጉ ወጣት ሴቶች ላይ በተደረገው ጥናት የተገኘውን ውጤት ተመልከት። ያሳለፉትን ጊዜ መለስ ብለው ሲያስቡት ያለ ቁጥጥር በማደጋቸው ማናቸውም አይደሰቱም። እንዲያውም ወላጆቻቸው ለእነርሱ ደኅንነት ግዴለሾች እንደነበሩ ወይም ልጅ የማሳደግ ችሎታ እንዳልነበራቸው ይሰማቸዋል።

ደስ ያላቸውን ነገር ሁሉ እንዲያደርጉ የሚፈቀድላቸውን ወጣቶች በማየት ከመቅናት ይልቅ ወላጆችህ የሚያወጡልህን መመሪያዎች ለአንተ ያላቸውን ፍቅርና አሳቢነት የሚያሳዩ እንደሆኑ አድርገህ ለመመልከት ጥረት አድርግ። እንዲያውም ምክንያታዊ የሆኑ ገደቦችን የሚያወጡ ወላጆች “አስተምርሃለሁ፤ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ እመክርሃለሁ፤ በዐይኔም እከታተልሃለሁ” በማለት ለሕዝቦቹ የተናገረውን ይሖዋ አምላክን ይመስላሉ።—መዝሙር 32:8

ሆኖም አሁን ስታስበው መመሪያዎቹ ከመጠን በላይ እንደበዙና በጣም ጥብቅ እንደሆኑ ይሰማህ ይሆናል። እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ከቤተሰብህ ጋር ያለህን ግንኙነት ይበልጥ አስደሳች ለማድረግ ልትወስዳቸው የምትችላቸውን አንዳንድ ተግባራዊ እርምጃዎች እንመልከት።

ውጤታማ የሆነ ውይይት ማድረግ

የበለጠ ነፃነት ለማግኘትም ይሁን አሁን በሚሰጥህ ነፃነት ረክተህ ለመኖር፣ ቁልፉ ውጤታማ የሆነ ውይይት ማድረግ ነው። አንዳንዶች ‘ወላጆቼን ለማነጋገር ሞክሬያለሁ፤ ግን ምንም የፈየድኩት ነገር የለም!’ ይሉ ይሆናል። እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ‘አነጋገሬን ማሻሻል ያስፈልገኝ ይሆን?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። መነጋገር በጣም አስፈላጊ ሲሆን የፈለግከውን ለማግኘት ወይም የፈለግከውን ነገር ለምን እንደተከለከልክ ለማወቅ ያስችልሃል። በእርግጥም፣ እንደ አዋቂ መታየት ከፈለግክ የንግግር ችሎታህን ማዳበርህ ምክንያታዊ ነው።

ስሜትህን መቆጣጠር ተማር። መጽሐፍ ቅዱስ “ተላላ ሰው ቍጣውን ያለ ገደብ ይለቀዋል፤ ጠቢብ ሰው ግን ራሱን ይቈጣጠራል” ይላል። (ምሳሌ 29:11) ጥሩ ውይይት ማድረግ ማጉረምረምን አይጨምርም። የምታጉረመርም ከሆነ ወላጆችህ ተጨማሪ ተግሣጽ እንዲሰጡህ ሊያደርጋቸው ይችላል። ስለዚህ አትነጫነጭ፣ አታኩርፍ እንዲሁም እንደ ልጅ እልኸኛ አትሁን። ወላጆችህ አንድ ነገር ሲከለክሉህ በር የምታላትም ወይም እየተመናጨቅክ የምትሄድ ከሆነ ይህ ዓይነቱ ባሕርይ ይበልጥ ነፃነት እንድታገኝ ከማድረግ ይልቅ ተጨማሪ ገደቦች እንዲጣሉብህ ያደርጋል።

የወላጆችህን አመለካከት ለመረዳት ሞክር። በነጠላ ወላጅ ያደገች ትሬሲ የተባለች ወጣት ይህን ምክር ጠቃሚ ሆኖ አግኝታዋለች። እንዲህ ትላለች:- “‘እናቴ መመሪያውን ያወጣችበት ምክንያት ምንድን ነው?’ በማለት ራሴን እጠይቃለሁ። የተሻልኩ ሰው መሆን እንድችል ለመርዳት እየጣረች ነው።” (ምሳሌ 3:1, 2) የወላጆችህን ስሜት ለመረዳት መሞከርህ አንተም የሚሰማህን ነገር ለወላጆችህ እንድትናገር ሊገፋፋህ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ወደ አንድ ግብዣ እንድትሄድ አልፈቀዱልህም እንበል። ከመከራከር ይልቅ ‘አንድ የጎለመሰና እምነት የሚጣልበት ጓደኛዬ ከእኔ ጋር ቢሄድስ?’ ብለህ መጠየቅ ትችላለህ። እርግጥ ወላጆችህ የጠየቅከውን ነገር ሁልጊዜ አይፈቅዱልህ ይሆናል፤ ሆኖም ያሳሰባቸውን ነገር ከተረዳህላቸው ተቀባይነት ሊያገኝ የሚችል ሐሳብ ማቅረብ ትችላለህ።

ወላጆችህ የሚተማመኑብህ ልጅ ለመሆን ጥረት አድርግ። የወላጆችህን አመኔታ ማትረፍ በባንክ ውስጥ ገንዘብ እንደ ማስቀመጥ ነው። ከባንክ ገንዘብ ልታወጣ የምትችለው ቀደም ብለህ ካጠራቀምክ ብቻ ነው። በባንክ ሒሳብህ ውስጥ ካለህ ገንዘብ በላይ ለማውጣት መሞከር ወደ ቅጣት የሚያመራህ ሲሆን በተደጋጋሚ ጊዜ እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ደግሞ የባንክ ሒሳብህ ሙሉ በሙሉ ሊዘጋ ይችላል። ተጨማሪ ነፃነት ማግኘት ገንዘብህን ከባንክ እንደማውጣት ሲሆን፣ ይህን ማድረግ የምትችለው ግን ከዚህ ቀደም እምነት የሚጣልብህ ዓይነት ልጅ መሆንህን ካስመሰከርክ ብቻ ነው።

በምትጠብቅባቸው ነገሮች ረገድ ምክንያታዊ ሁን። ወላጆችህ አንተን ሚዛናዊ በሆነ መልኩ የመቆጣጠር ኃላፊነት አለባቸው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ “የአባትህን ትእዛዝ” እና ‘የእናትህን ትምህርት’ በተመለከተ ይናገራል። (ምሳሌ 6:20) ሆኖም ወላጆችህ የሚያወጡልህ መመሪያ ሕይወትህን አሰልቺ እንደሚያደርገው አድርገህ አታስብ። ከዚህ በተቃራኒ ግን ለወላጆችህ ሥልጣን የምትገዛ ከሆነ የወደፊት ሕይወትህ ‘መልካም እንደሚሆንልህ’ ይሖዋ ቃል ገብቷል!—ኤፌሶን 6:1-3

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “የወጣቶች ጥያቄ . . .” የሚሉትን ተከታታይ ርዕሶች ማግኘት ይቻላል።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

▪ ለመታዘዝ አስቸጋሪ የሚሆኑብህ መመሪያዎች የትኞቹ ናቸው?

▪ በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ወላጆችህ ያወጡልህን መመሪያ ለመቀበል የሚረዱህ ምን ነጥቦች አሉ?

▪ ወላጆችህ በአንተ ላይ ይበልጥ እምነት እንዲጥሉ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የወላጆችህን መመሪያ ስትጥስ

ብዙውን ጊዜ እንደሚከተለው ያለ ሁኔታ ሊከሰት ይችላል:- በተወሰነልህ ሰዓት ቤት ሳትገባ ቀርተሃል እንበል፤ ወይም የታዘዝከውን ሥራ አልሠራህም አሊያም ደግሞ ከተፈቀደልህ ሰዓት በላይ ስልክ አውርተሃል። በዚህ ጊዜ ለወላጆችህ ማብራሪያ መስጠት ይኖርብሃል! ታዲያ የተፈጠረው ችግር ይበልጥ እንዳይካረር ምን ልታደርግ ትችላለህ?

እውነቱን ተናገር። ወላጆችህን ለማታለል መሞከር ምንም አይጠቅምህም። ስለዚህ ሐቀኛ ሁን፤ እንዲሁም ጉዳዩን አድበስብሰህ ለማለፍ አትሞክር። (ምሳሌ 28:13) የማይመስል ታሪክ የምታወራ ከሆነ ወላጆችህ በአንተ ላይ ያላቸው እምነት ጨርሶ ሊጠፋ ይችላል። ድርጊቱ ትክክል እንደሆነ አድርገህ ወይም ያደረግኸውን ነገር አቃልለህ ከመናገር ተቆጠብ። “የለዘበ መልስ ቍጣን ያበርዳል” የሚለውን ምክር ሁልጊዜ አስታውስ።—ምሳሌ 15:1

ይቅርታ ጠይቅ። ወላጆችህን በማስጨነቅህ፣ በማበሳጨትህ ወይም በእነርሱ ላይ ጫና በመፍጠርህ በጣም እንዳዘንክ መግለጽህ ተገቢ ከመሆኑም በላይ የሚደርስብህን ቅጣት ሊያቀልልህ ይችላል። (1 ሳሙኤል 25:24) ሆኖም የተጸጸትከው ከልብ መሆን አለበት።

ጥፋትህ የሚያስከትለውን ቅጣት ለመቀበል ፈቃደኛ ሁን። መቀጣትህ ተገቢ አይደለም ብለህ ካሰብክ መጀመሪያ ላይ ቅጣቱን ለመቀበል ትቸገር ይሆናል። (ምሳሌ 20:3) ሆኖም ድርጊትህ ያስከተለውን ውጤት መቀበል የጉልምስና ምልክት ነው። (ገላትያ 6:7) ከሁሉ የተሻለው አማራጭ የወላጆችህን አመኔታ መልሰህ ለማግኘት መጣር ሊሆን ይችላል።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የወላጆችህን ስሜት ለመረዳት ሞክር