በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሳይንስ በሽታን ሊያስቀር ይችላል?

ሳይንስ በሽታን ሊያስቀር ይችላል?

ሳይንስ በሽታን ሊያስቀር ይችላል?

ዘመናዊው ሳይንስ በሽታን ፈጽሞ ሊያስወግድ ይችላል? በኢሳይያስና በራእይ መጻሕፍት ላይ የሚገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የሚጠቁሙት የሰው ልጅ በገዛ ራሱ ጥረት በሽታን ስለሚያስወግድበት ዘመን ነው? አንዳንዶች በጤና አጠባበቅ ረገድ የተደረገውን መሻሻል በመመልከት ይህ ሊሆን የማይችልበት ምክንያት እንደሌለ ይሰማቸዋል።

በአሁኑ ጊዜ መንግሥታት ብሎም በጎ አድራጊ ግለሰቦችና ድርጅቶች ጥረታቸውን ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በማስተባበር በበሽታ ላይ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ ዘመቻ በማካሄድ ላይ ናቸው። በዚህ ዘርፍ ከሚደረጉት ጥረቶች አንዱ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ለሚኖሩ ሕፃናት ክትባት በመስጠት ላይ ያተኩራል። የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) እንደሚለው ከሆነ አገራት በዚህ ረገድ ያወጡትን ግብ ማሳካት ከቻሉ “እስከ 2015 ድረስ በዓለማችን ላይ በጣም ድሃ በሚባሉት አገሮች ውስጥ የሚኖሩ 70 ሚሊዮን የሚያክሉ ሕፃናት በየዓመቱ የሚከተሉትን በሽታዎች ለመከላከል የሚያስችል ክትባት ያገኛሉ:- ሳንባ ነቀርሳ፣ ዲፕቴሪያ (ዘጊ አናዳ)፣ መንጋጋ ቆልፍ፣ ትክትክ፣ ኩፍኝ፣ ሩቤላ፣ ቢጫ ወባ፣ ሂሞፊለስ ኢንፍሉዌንዛ ታይፕ ቢ፣ ሄፐታይተስ ቢ፣ የልጅነት ልምሻ፣ ሮታቫይረስ፣ ኒሞኮከስ፣ መኒንጎኮከስ እና የጃፓን ኤንስፋላይትስ።” ከዚህም በተጨማሪ ንጹሕ ውኃን፣ የተመጣጠነ ምግብንና የንጽሕና አጠባበቅ ትምህርትን የመሳሰሉ ለጥሩ ጤንነት መሠረታዊ የሆኑ ነገሮችን ለማቅረብ አንዳንድ እርምጃዎች በመወሰድ ላይ ናቸው።

ይሁን እንጂ የሳይንቲስቶች ጥረት መሠረታዊ የሆኑትን የጤና እንክብካቤ አገልግሎቶች በመስጠት ብቻ የተወሰነ አይደለም። እጅግ የተራቀቁ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችም በሕክምናው ዘርፍ ከፍተኛ ለውጥ በማስገኘት ላይ ናቸው። ሳይንቲስቶች በየስምንት ዓመቱ የሕክምና እውቀታቸውን በእጥፍ እንደሚያሳድጉ ይነገራል። ለናሙና ያህል የቀረቡት የሚከተሉት ነገሮች ከበሽታ ጋር በሚደረገው ትግል የተገኙ ድሎችና ሊደረስባቸው የታቀዱ ግቦች ናቸው።

የኤክስሬይ ወይም የራጅ ምስል ዶክተሮችና ሆስፒታሎች ሲቲ ስካን በሚባለው መሣሪያ መጠቀም ከጀመሩ ከ30 ዓመት በላይ ሆኗቸዋል። ሲቲ የሚለው ምሕጻረ ቃል ኮምፒውትድ ቶሞግራፊ የሚሉትን ቃላት የሚወክል ነው። የሲቲ ስካን መሣሪያዎች የውስጥ አካላችንን ክፍሎች ከተለያዩ አቅጣጫዎች ራጅ ማንሳት ይችላሉ። እነዚህ የራጅ ምስሎች የውስጥ አካል በሽታዎችንና እክሎችን ለመመርመር እንዲሁም ለመለየት ይጠቅማሉ።

በእነዚህ መሣሪያዎች መጠቀም ለጨረር አደጋ ያጋልጣል ብለው የሚከራከሩ ባይጠፉም የሕክምና ሊቃውንት ይህ እየተራቀቀ የመጣ ቴክኖሎጂ ወደፊት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያበረክታል የሚል እምነት አላቸው። በቺካጎ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የራዲዮሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ማይክል ቫኒር “ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ እንኳ ከፍተኛ እድገት ታይቷል” ብለዋል።

በአሁኑ ጊዜ የሲቲ ስካን መሣሪያዎች ይበልጥ ፈጣኖች፣ ትክክለኛና ወጪ ቆጣቢ ሆነዋል። አዲሶቹ መሣሪያዎች ካስገኙት ጥቅም አንዱ ፍጥነት ነው። በተለይ ይህ በጣም ጠቃሚ ሆኖ የተገኘው ልብን ራጅ በማንሳት ረገድ ነው። ልብ ያለማቋረጥ የሚመታና የሚንቀሳቀስ በመሆኑ ቀደም ባሉት ጊዜያት የልብ የራጅ ምስሎች ደብዛዛና አጥርቶ ለማየት የሚያስቸግሩ ነበሩ። ኒው ሳይንቲስት መጽሔት አዲሶቹ የሲቲ ስካን መሣሪያዎች “መላውን ሰውነት ለመዞር የአንድ ሴኮንድ አንድ ሦስተኛ ጊዜ ብቻ” እንደሚወስድባቸው ይናገራል፤ “ይህም አንድ የልብ ምት ከሚወስደው ጊዜ በጣም ያነሰ ነው።” ይህ ደግሞ የበለጠ ጥራት ያለው ምስል ለማንሳት ያስችላል።

ዶክተሮች በተራቀቁት የሲቲ ስካን መሣሪያዎች አማካኝነት የውስጥ ሰውነት ክፍሎችን ሁኔታ በዝርዝር ከማየት አልፈው የአንድን የሰውነት ክፍል ባዮኬሚካላዊ እንቅስቃሴ መመርመር ይችላሉ። ይህም የካንሰርን ሕመም ገና ሥር ከመስደዱ በፊት ለይቶ ለማወቅ ያስችላል።

የሮቦት ቀዶ ሕክምና በተራቀቁ ሮቦቶች መጠቀም በፊልም ዓለም ብቻ የሚታይ ነገር መሆኑ ቀርቷል። እነዚህ ሮቦቶች ቢያንስ በሕክምናው መስክ ጥቅም ላይ መዋል ጀምረዋል። በአሁኑ ጊዜ በሮቦቶች እርዳታ በሺዎች የሚቆጠሩ ቀዶ ሕክምናዎች ይከናወናሉ። በአንዳንድ ሁኔታዎች ሥር የቀዶ ሕክምና ዶክተሮች በርካታ እጆች ያሉትን ሮቦት በርቀት መቆጣጠሪያ መሣሪያ አማካኝነት በመቆጣጠር ቀዶ ሕክምና ማድረግ ችለዋል። እነዚህ እጆች ለቀዶ ሕክምና የሚያገለግሉ ቢላዎች፣ መቀሶች፣ ካሜራዎችና ሌሎች መሣሪያዎች የተገጠሙላቸው ናቸው። ይህ ዓይነቱ ቴክኖሎጂ የቀዶ ሕክምና ዶክተሮች በጣም የተወሳሰቡ ሕክምናዎችን ፍጹም ትክክል በሆነ ሁኔታ እንዲያከናውኑ አስችሏል። “በዚህ ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙ የቀዶ ሕክምና ዶክተሮች በሽተኞቻቸው ብዙ ደም እንደማይፈሳቸው፣ በጣም እንደማያማቸው፣ በቀዶ ሕክምናው ምክንያት የሚመጣ በሽታ እምብዛም እንደማያስቸግራቸው፣ ሆስፒታል የሚቆዩበት ጊዜ በጣም አጭር እንደሆነና በተለመደው የቀዶ ሕክምና ዘዴ ከታከሙ ሕመምተኞች ፈጥነው እንደሚያገግሙ” ማረጋገጣቸውን ኒውስዊክ መጽሔት ዘግቧል።

ናኖሜዲስን ናኖሜዲስን ሲባል ናኖቴክኖሎጂን ለሕክምና አገልግሎት መጠቀም ማለት ነው። ናኖቴክኖሎጂ ደግሞ በአጉሊ መነጽር ብቻ ሊታዩ የሚችሉ በጣም ረቂቅ የሆኑ መሣሪያዎችን የመፈልሰፍና በእነዚህ መሣሪያዎች የመገልገል ጥበብ ነው። በዚህ ቴክኖሎጂ የሚሠራበት መለኪያ ናኖሜትር የሚባል ሲሆን መጠኑም የአንድ ሜትር አንድ ቢሊዮንኛ ነው። *

ይህ መለኪያ ምን ያህል መጠን እንዳለው ለመገመት እንዲቻል ሁኔታውን በምሳሌ ለማየት እንሞክር። ይህ የምታነበው ገጽ 100,000 ናኖሜትር የሚያክል ውፍረት ያለው ሲሆን የአንድ ሰው ፀጉር ደግሞ 80,000 ናኖሜትር ይሆናል። አንድ ቀይ የደም ሴል 2,500 ናኖሜትር የሚያክል ውፍረት አለው። አንድ ባክቴሪያ 1,000 ናኖሜትር የሚያክል ቁመት ሲኖረው አንድ ቫይረስ ደግሞ ቁመቱ 100 ናኖሜትር ይሆናል። በሴሎቻችን ውስጥ የሚገኘው ዲ ኤን ኤ 2.5 ናኖሜትር የሚያክል ውፍረት አለው።

የዚህ ቴክኖሎጂ ደጋፊዎች፣ የሳይንስ ሊቃውንት በጥቂት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ወደ ሰውነት ውስጥ ገብተው የሕክምና ተግባር የሚያከናውኑ ጥቃቅን መሣሪያዎች ሊሠሩ እንደሚችሉ ይናገራሉ። ናኖማሽን ተብለው የሚጠሩት እነዚህ ጥቃቅን ሮቦቶች የተለየ ተግባር የማከናወን ችሎታ ያላቸው በጣም አነስተኛ ኮምፒውተሮች ይኖሯቸዋል። በጣም የሚያስደንቀው የእነዚህ ውስብስብ መሣሪያዎች የአካል ክፍሎች ከ100 ናኖሜትር አይበልጡም። ይህም ሲባል መጠናቸው ከአንድ ቀይ የደም ሴል ውፍረት ከ25 ጊዜ በላይ ያንሳል ማለት ነው!

እነዚህ መሣሪያዎች በጣም ጥቃቅን ከመሆናቸው የተነሳ ካፒላሪስ በሚባሉ ጥቃቅን የደም ቧንቧዎች ውስጥ እየተዘዋወሩ ደም ለማይደርስባቸው የሰውነት ክፍሎች ኦክሲጅን ያደርሳሉ፣ የተዘጉ የደም ቧንቧዎችን ይከፍታሉ፣ በአንጎል ሴል ውስጥ የረጉ ቆሻሻዎችን ያስወግዳሉ አልፎ ተርፎም እንደ ቫይረስና ባክቴሪያ ያሉትን ተውሳኮች አድነው ይገድላሉ የሚል ተስፋ ተጥሎባቸዋል። በተጨማሪም ችግር ላለባቸው ሴሎች መድኃኒት ለማድረስ ሊያገለግሉ ይችላሉ ተብሎ ይታሰባል።

ሳይንቲስቶች በናኖሜዲስን የሕክምና ጥበብ አማካኝነት የካንሰርን ሕመም ገና ሥር ከመስደዱ በፊት ለይቶ ማወቅ እንደሚቻል ይተነብያሉ። የሕክምና፣ የፊዚክስና የባዮሜዲካል ምህንድስና ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ሳሙኤል ዊክላይን እንዲህ ብለዋል:- “በጣም ትናንሽ ካንሰሮችን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ቀደም ብሎ ማወቅና እጢው ያለበትን ቦታ ለይቶ በጣም ኃይለኛ በሆኑ መድኃኒቶች ማከም የሚቻልበት አጋጣሚ በጣም ሰፊ ነው፤ በሕክምና ምክንያት የሚመጡ ተጓዳኝ ጉዳቶችንም መቀነስ ይቻላል።”

ይህ ሁኔታ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የታየ ሕልም እንደሆነ የሚሰማቸው ባይጠፉም አንዳንድ ሳይንቲስቶች ናኖሜዲስን ሥራ ላይ መዋሉ የማይቀር ለመሆኑ ከፍተኛ እምነት አላቸው። በዚህ መስክ በመሰማራት ረገድ ግንባር ቀደም የሆኑ ተመራማሪዎች ከአሥር ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በናኖቴክኖሎጂ አማካኝነት ሕያው የሆኑ ሴሎችን መጠገንና ማስተካከል የሚቻልበት ደረጃ ላይ እንደሚደረስ ያምናሉ። አንድ የዚህ ቴክኖሎጂ ደጋፊ “ናኖሜዲስን የ20ኛውን መቶ ዘመን የተለመዱ በሽታዎች በሙሉ፣ እንዲሁም በበሽታ ምክንያት የሚመጣውን ሥቃይና መከራ ሁሉ ለማስወገድ ብሎም የሰውን ልጅ አቅም ለማራዘም ያስችላል” ብለዋል። አሁንም እንኳ አንዳንድ ሳይንቲስቶች ናኖሜዲስንን በእንስሳት ላይ ተጠቅመው ጥሩ ውጤት እንዳገኙ በመናገር ላይ ናቸው።

ጂኖሚክስ በጂኖች አፈጣጠርና አሠራር ላይ የሚደረግ ጥናት ጂኖሚክስ ይባላል። በሰው አካል ውስጥ የሚገኝ እያንዳንዱ ሴል በሕይወት ለመኖር የግድ አስፈላጊ በሆኑ በርካታ ነገሮች የተሞላ ነው። ከእነዚህ ነገሮች አንዱ ጂን ነው። እያንዳንዳችን የፀጉራችንን ቀለምና ዓይነት፣ የቆዳችንንና የዓይናችንን ቀለም፣ ቁመታችንንና እኛነታችንን ለይተው የሚያሳውቁ ሌሎች ነገሮችን የሚወስኑ 35,000 የሚያክሉ ጂኖች አሉን። ጂኖች መልክና ቁመናችንን ከመወሰን በተጨማሪ የውስጣዊ ብልቶቻችንን ጥራትና ጥንካሬ በመወሰን ረገድ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው።

በጂኖች ላይ ጉዳት መድረሱ በጤንነታችን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። እንዲያውም አንዳንድ ተመራማሪዎች የማንኛውም በሽታ መንስኤ ጄኔቲካዊ ቀውስ እንደሆነ ያምናሉ። ጉዳት ያለባቸውን አንዳንድ ጂኖች የምንወርሰው ከወላጆቻችን ሲሆን በአካባቢያችን ለሚገኙ ጎጂ ክስተቶች በመጋለጣችን ምክንያት በጂኖቻችን ላይ ጉዳት የሚደርስበት ጊዜም አለ።

የሳይንስ ሊቃውንት ለበሽታዎች የሚያጋልጡንን ጂኖች በቅርብ ዓመታት ውስጥ ለይተው ለማወቅ እንደሚችሉ ይሰማቸዋል። ይህም ዶክተሮች፣ አንዳንድ ሰዎች ከሌሎች የበለጠ ለአንዳንድ የካንሰር ዓይነቶች የሚጋለጡበትን ምክንያት ወይም አንዳንድ የካንሰር ዓይነቶች በተወሰኑ ሰዎች ላይ ይበልጥ የሚበረቱበትን ምክንያት እንዲያውቁ ያስችላቸዋል። በተጨማሪም በጂኖሚክስ አማካኝነት አንዳንድ መድኃኒቶች ለአንዱ ሕመምተኛ ሲሠሩ ለሌሎች የማይሠሩበትን ምክንያት ለማወቅ ይቻላል።

እንዲህ ያለው ጄኔቲካዊ መረጃ ለእያንዳንዱ ሕመምተኛ ከሁኔታውና ከባሕርይው ጋር የሚጣጣም የተለየ ሕክምና ለመስጠት ያስችላል። ከዚህ ዓይነቱ የቴክኖሎጂ ውጤት ጥቅም ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው? ከማንም ሌላ ሰው ጋር ለማይመሳሰለው ለጂንህ የሚስማማና ለአንተ ብቻ የሚያገለግል ሕክምና ሊሰጥህ ይችላል ማለት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በጂኖችህ ላይ በተደረገ ምርመራ በአንድ በሽታ የመጠቃት አዝማሚያ እንዳለህ ቢታወቅ ዶክተሮች ምንም ዓይነት የሕመም ምልክት ከመታየቱ በፊት በሽታውን ለይተው ለማወቅ ይችላሉ። ሕመሙ ገና ባይጀምርህም እንኳ ትክክለኛውን ሕክምናና አመጋገብ ብትከተል እንዲሁም አስፈላጊውን የባሕርይ ለውጥ ብታደርግ በሽታው እንዳይዝህ መከላከል እንደምትችል የዚህ ቴክኖሎጂ ደጋፊዎች ይናገራሉ።

በተጨማሪም ዶክተሮች በጂን ምርመራ አማካኝነት አንዳንድ መድኃኒቶች ጉዳት ያስከትሉብህ እንደሆነና እንዳልሆነ ማወቅ ይችላሉ። እንዲህ ያለው መረጃ ለአንተ በግል የሚጠቅምህ መድኃኒት የቱ እንደሆነና ምን ያህል መጠን መውሰድ እንደሚገባህ ለመወሰን ያስችላቸዋል። ዘ ቦስተን ግሎብ የተባለው ጋዜጣ እንዲህ በማለት ዘግቧል:- “በ2020 [የግለሰቦችን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት] የሚሰጠው ሕክምና የሚያስገኘው ውጤት ዛሬ ማናችንም ብንሆን ልንገምተው ከምንችለው በላይ ይሆናል። ስኳር በሽታን፣ የልብ ሕመምን፣ አልዛይመርን፣ ስኬዞፍሪኒያ የተባለውን የአእምሮ በሽታና በማኅበረሰባችን ውስጥ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ላይ የሚገኙ ሌሎች በርካታ በሽታዎችን ለማከም የሚረዱ የጂን ባሕርይን መሠረት በማድረግ የተዘጋጁ መድኃኒቶች ይመረታሉ።”

ከላይ የተጠቀሱት የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሳይንስ ወደፊት እንደሚደርስበት ተስፋ ከሰጠው ውስጥ ለናሙና ያህል ብቻ የተጠቀሱ ናቸው። የሕክምና እውቀት ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት በማደግ ላይ ነው። ይሁን እንጂ ሳይንቲስቶች መቼም ቢሆን በሽታዎችን ሙሉ በሙሉ እናስወግዳለን ብለው ተስፋ አያደርጉም። አሁንም እንኳ ፈጽሞ መፍትሔ የሚገኝላቸው የማይመስሉ በርካታ መሰናክሎች ከፊት ለፊታቸው ተደቅነውባቸዋል።

ፈጽሞ መፍትሔ የሚገኝላቸው የማይመስሉ ችግሮች

የሰዎች ባሕርይ በሽታን ለማጥፋት የሚደረገውን ግስጋሴ ሊገታ ይችላል። ለምሳሌ ሳይንቲስቶች የሰው ልጅ በአንዳንድ ሥነ ምሕዳሮች ወይም የተፈጥሮ ገጽታዎች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት አዳዲስና አደገኛ የሆኑ በሽታዎችን እንዳመጣ ያምናሉ። የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለ አደራ ማኅበር ፕሬዚዳንት የሆኑት ሜሪ ፐርል የኒውስዊክ መጽሔት አዘጋጅ ላደረገላቸው ቃለ መጠይቅ መልስ ሲሰጡ “ከ1970ዎቹ ዓመታት አጋማሽ አንስቶ ኤድስን፣ ኢቦላን፣ ላይም በሽታንና ሳርስን ጨምሮ ከ30 የሚበልጡ አዳዲስ በሽታዎች ብቅ ብለዋል። ከእነዚህ በሽታዎች መካከል ብዙዎቹ ከዱር አራዊት ወደ ሰዎች የተላለፉ እንደሆኑ ይታመናል” ብለዋል።

በተጨማሪም ሰዎች አትክልትና ፍራፍሬ መመገባቸውን እየተዉና በይበልጥ ስኳር፣ ጨውና ቅባት የበዛባቸውን ምግቦች በማዘውተር ላይ ናቸው። ይህ ዓይነቱ የአመጋገብ ለውጥ በቂ አካላዊ እንቅስቃሴ አለማድረግና ሌሎች ጤናማ ያልሆኑ ልማዶች ታክለውበት የልብ በሽታና የደም ዝውውር ችግር እንዲበራከት ምክንያት ሆኗል። ትንባሆ ማጨስ በጣም እየጨመረ በመምጣቱ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች በበሽታ መማቀቅና በሞት መቀጠፍ ምክንያት ሆኗል። በየዓመቱ 20 ሚሊዮን የሚያክሉ ሰዎች በከባድ የመኪና አደጋ ይሞታሉ ወይም ከፍተኛ ጉዳት ይደርስባቸዋል። በጦርነትና በሌሎች የዓመጽ ድርጊቶች ሳቢያ የሚገደሉ እንዲሁም የአካል ጉዳተኛ የሚሆኑ ሰዎችም ቁጥር እንዲህ ቀላል አይደለም። ሌሎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ አልኮልና አደገኛ ዕፅ አላግባብ በመውሰዳቸው ምክንያት ሕመምተኞች ይሆናሉ።

ምክንያቶቹ ምንም ይሁኑ ምን፣ የሕክምና ቴክኖሎጂ ይህን ያህል እድገት እያሳየም እንኳ አንዳንድ በሽታዎች አሁንም ሰዎችን ለከፍተኛ ሥቃይ መዳረጋቸውን ቀጥለዋል። የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እንደሚለው ከሆነ ‘ከ150 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች በአንድ ወቅት በከፍተኛ የመንፈስ ጭንቀት፣ 25 ሚሊዮን የሚያክሉ ሰዎች ስኬዞፍሪኒያ በሚባለው የአእምሮ ሕመም፣ 38 ሚሊዮን የሚያክሉት ደግሞ በሚጥል በሽታ ይሰቃያሉ።’ ኤች አይ ቪ/ኤድስ፣ የተቅማጥ በሽታዎች፣ ወባ፣ ኩፍኝ፣ የሳንባ ምች ወይም ኒሞንያ እንዲሁም ሳንባ ነቀርሳ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከማጥቃታቸውም በላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሕፃናትና ትላልቅ ሰዎችን ይገድላሉ።

በሽታን ለማጥፋት ለሚደረገው ጥረት ጋሬጣ የሆኑና መፍትሔ የሚገኝላቸው የማይመስሉ ሌሎች ከባድ ችግሮችም አሉ። ከእነዚህ መካከል ዋና ዋናዎቹ ድህነትና የመልካም አስተዳደር እጦት ናቸው። የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት ላይ የገንዘብ እጥረት ባያጋጥምና የአስተዳደር ብልሹነት ባይኖር ኖሮ በተላላፊ በሽታዎች የሚሞቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት መታደግ ይቻል እንደነበረ ገልጿል።

ታዲያ የሳይንሳዊ እውቀት መስፋፋትና በሕክምና ቴክኖሎጂ ላይ የሚታየው ከፍተኛ ለውጥ እነዚህን እንቅፋቶች ሊያስወግድ ይችላል? በቅርቡ በሽታ የሌለበትን ዓለም ለማየት እንታደል ይሆን? ከላይ የቀረቡት መረጃዎች ለእነዚህ ጥያቄዎች ቁርጥ ያለ መልስ እንዳልሰጡ የሚካድ አይደለም። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠው መልስ አለ። የሚቀጥለው ርዕስ መጽሐፍ ቅዱስ በሽታ ስለማይኖርበት ዘመን የሚሰጠውን ተስፋ ያብራራል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.10 “ናኖ” ድንክ የሚል ትርጉም ያለው የግሪክኛ ቃል ሲሆን “አንድ ቢሊዮንኛ” ማለት ነው።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

የራጅ ምስል

የሰውን የውስጥ አካላት በግልጽ የሚያሳዩ ምስሎች በሽታዎችን ሥር ከመስደዳቸው በፊት ለይቶ ለማወቅ ያስችላሉ

[ምንጮች]

© Philips

Siemens AG

የሮቦት ቀዶ ሕክምና

የቀዶ ሕክምና መሣሪያዎች የተገጠሙላቸው ሮቦቶች፣ ዶክተሮች በጣም የተራቀቁና የተወሳሰቡ ቀዶ ሕክምናዎችን እንዲያከናውኑ በመርዳት ላይ ናቸው

[ምንጭ]

© 2006 Intuitive Surgical, Inc.

ናኖሜዲስን

ዶክተሮች በአጉሊ መነጽር ብቻ ሊታዩ የሚችሉ ሰው ሠራሽ መሣሪያዎችን በመጠቀም ሴሎችን ነጥለው ማከም ይችሉ ይሆናል። ይህ ፎቶግራፍ የአንድን ቀይ የደም ሴል ሥራ ተክቶ የሚሠራ ናኖማሽን ምን እንደሚመስል የሚያሳይ ነው

[ምንጭ]

አርቲስት:- Vik Olliver (vik@diamondage.co.nz)/ ንድፍ አውጪ:- Robert Freitas

ጂኖሚክስ

ሳይንቲስቶች የአንድን ግለሰብ ጄኔቲካዊ አወቃቀር በማጥናት ግለሰቡ ምንም ዓይነት የሕመም ምልክት ከማየቱ በፊት በሽታውን ለማወቅና ለማከም የሚቻልበት ጊዜ እንደሚመጣ ያምናሉ

[ምንጭ]

ክሮሞዞሞች:- © Phanie/ Photo Researchers, Inc.

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ስድስት የማይበገሩ ጠላቶች

የሕክምና እውቀትም ሆነ ከዚህ ጋር ተዛማጅነት ያለው ቴክኖሎጂ ከዚህ በፊት ታይቶ በማያውቅ መጠን ማደጋቸውን ቀጥለዋል። ያም ሆኖ ግን ተላላፊ በሽታዎች አሁንም በዓለም ላይ ጥፋት በማድረስ ላይ ይገኛሉ። ቀጥሎ የተጠቀሱት ገዳይ በሽታዎች ፈጽሞ ሊበገሩ አልቻሉም።

ኤች አይ ቪ/ኤድስ

እስካሁን 60 ሚሊዮን የሚያህሉ ሰዎች በኤች አይ ቪ ሲያዙ 20 ሚሊዮን የሚሆኑት በኤድስ ሳቢያ ለሕልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል። በ2005፣ አምስት ሚሊዮን የሚያህሉ አዳዲስ ሰዎች ኤች አይ ቪ የተገኘባቸው ሲሆን ከኤድስ ጋር በተያያዘ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሞተዋል። ከእነዚህ መካከል ከ500,000 የሚበልጡት ልጆች ናቸው። ብዙዎቹ የኤች አይ ቪ ሰለባዎች በቂ ሕክምና አያገኙም።

ተቅማጥ

በየዓመቱ አራት ቢሊዮን የሚያህሉ ሰዎችን የሚይዘው የተቅማጥ በሽታ በድሃ አገሮች ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለው ገዳይ በሽታ እንደሆነ ተደርጎ ተገልጿል። ይህ በሽታ የሚከሰተው በተበከለ ውኃ ወይም ምግብ አለዚያም የግል ንጽሕናን ባለመጠበቅ ምክንያት ሊዛመቱ በሚችሉ ተላላፊ በሽታዎች ሳቢያ ነው። እነዚህ ተላላፊ በሽታዎች በየዓመቱ ከሁለት ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎችን ለሕልፈተ ሕይወት ይዳርጋሉ።

ወባ

በየዓመቱ 300 ሚሊዮን የሚያህሉ ሰዎች በወባ በሽታ ይያዛሉ። ከሚታመሙት ሰዎች ውስጥ በየዓመቱ አንድ ሚሊዮን የሚያህሉት የሚሞቱ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ብዙዎቹ ልጆች ናቸው። በአፍሪካ በየ30 ሴኮንዱ አንድ ሕፃን ይሞታል። በዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ዘገባ መሠረት “ሳይንስ እስካሁንም ድረስ ለወባ ፈጣንና የማያዳግም ፈዋሽ መድኃኒት ማግኘት ያልቻለ ሲሆን ብዙዎች ለወደፊቱም ቢሆን እንዲህ ያለ መፍትሔ መገኘቱን ይጠራጠራሉ።”

ኩፍኝ

በ2003 ብቻ ኩፍኝ ከ500,000 በላይ ሰዎችን ገድሏል። ለልጆች መሞት ምክንያት ከሚሆኑት በሽታዎች መካከል ቀዳሚውን ሥፍራ የሚይዘው ኩፍኝ በከፍተኛ ፍጥነት የሚተላለፍ በሽታ ነው። በየዓመቱ 30 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በኩፍኝ ይያዛሉ። የሚገርመው ነገር ይህ ሁሉ ሰው የሚታመመው ላለፉት 40 ዓመታት ኩፍኝን ለመከላከል የሚያስችል ርካሽና ፍቱን የሆነ ክትባት እያለ መሆኑ ነው።

የሳንባ ምች

የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚናገረው ከሆነ ከማናቸውም ተላላፊ በሽታዎች የበለጠ ልጆች የሚሞቱት በሳንባ ምች ነው። በየዓመቱ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሁለት ሚሊዮን የሚያህሉ ልጆች በሳንባ ምች ይሞታሉ። በዚህ በሽታ ሳቢያ ከሚሞቱት ውስጥ አብዛኞቹ የሚኖሩት በአፍሪካና በደቡብ ምሥራቅ እስያ ነው። በብዙዎቹ የዓለም ክፍሎች የበሽታው ሰለባዎች ወደ ጤና ተቋማት የመድረስ አጋጣሚያቸው ውስን መሆኑ ሕይወት አድን ሕክምና እንዳያገኙ እንቅፋት ይሆንባቸዋል።

ሳንባ ነቀርሳ

በ2003 በሳንባ ነቀርሳ (ቲቢ) ሳቢያ ከ1,700,000 የሚበልጡ ሰዎች ለሕልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል። ለጤና ጥበቃ ባለ ሥልጣናት ራስ ምታት የሆነባቸው ነገር መድኃኒት የመቋቋም ኃይል ያላቸው የቲቢ ጀርሞች መከሰታቸው ነው። አንዳንዶቹ ጀርሞች ዋና ዋናዎቹን የሳንባ ነቀርሳ መድኃኒቶች መቋቋም ጀምረዋል። የሳንባ ነቀርሳ በሽታ መድኃኒት የመቋቋም ኃይል የሚያዳብረው ታማሚዎች ተገቢውን የሕክምና ክትትል ሳያደርጉ ሲቀሩ ወይም መድኃኒት ሲያቋርጡ ነው።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አማራጭ የሕክምና ዓይነቶች እየተበራከቱ ነው

በዘመናዊ ሕክምና ባለሞያዎች ዘንድ እምብዛም ተቀባይነት የሌላቸው በርካታ የፈውስ ማግኛ ዘዴዎች አሉ። እነዚህ ዘዴዎች በጥቅሉ ባሕላዊ ሕክምና እና አማራጭ ሕክምና በመባል ይታወቃሉ። በታዳጊ አገሮች ውስጥ አብዛኛው ሕዝብ የጤና ችግር ሲያጋጥመው የሚሄደው ወደ ባሕላዊ ሕክምና ነው። ድህነት በተስፋፋባቸው አካባቢዎች ብዙዎች ዘመናዊ ሕክምና ለማግኘት የገንዘብ አቅማቸው የማይፈቅድላቸው ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ከዘመናዊ ሕክምና ይልቅ ባሕላዊውን ዘዴ ይመርጣሉ።

አማራጭ የሕክምና ዘዴዎች በሀብታም አገሮችም ጭምር በመስፋፋት ላይ ናቸው። ሰፊ ተቀባይነት ካገኙት አማራጭ የሕክምና ዘዴዎች መካከል አኩፓንክቸር፣ ቺሮፕራክቲክ፣ ሆሚዮፓቲ፣ ናቹሮፓቲ እና ከዕፅዋት የሚዘጋጁ የባሕል መድኃኒቶች ይገኙበታል። ከእነዚህ አማራጭ ሕክምናዎች መካከል አንዳንዶቹ ሳይንሳዊ ጥናት ተካሂዶባቸው ለአንዳንድ የጤና ችግሮች ጠቃሚ መሆናቸው ተረጋግጧል። ይሁን እንጂ የአንዳንዶቹ ውጤታማነት በበቂ ሁኔታ አልተረጋገጠም። የአማራጭ የሕክምና ዘዴዎች ተፈላጊነት እየጨመረ መምጣቱ ከጥንቃቄ አኳያ አንዳንድ ጥያቄዎችን አስነስቷል። በብዙ አገሮች እንዲህ ዓይነቶቹ ሕክምናዎች ሕግ ወጥቶላቸው ቁጥጥር አይደረግባቸውም። ይህም ሰዎች ጎጂ በሆነ ሁኔታ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያክሙ፣ ተመሳስለው የሚሠሩ የሐሰት መድኃኒቶች እንዲመረቱና የተለያዩ የማጭበርበር ድርጊቶች እንዲስፋፉ በር ከፍቷል። ብዙውን ጊዜ ጓደኞችና ዘመዶችም በቂ እውቀት ሳይኖራቸው እንዲያው በበጎ ዓላማ በመነሳሳት ብቻ የሕክምና ምክር ሲሰጡ ይታያል። ይህ ሁሉ የከፋ ውጤትና ከባድ የጤና ችግር አስከትሏል።

ይህን የተመለከተ ሕግ በወጣባቸው አንዳንድ አገሮች ውስጥ አማራጭ የሕክምና ዓይነቶች በዘመናዊ የሕክምና ባለሙያዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኙ ሲሆን ሐኪሞችም ለሕመምተኞቻቸው እንዲህ ያለውን ሕክምና ያዝዛሉ። ያም ሆኖ ግን እነዚህ አማራጭ የሕክምና ዘዴዎች በሽታ የሌለበት ዓለም ያመጣሉ ብሎ በእርግጠኝነት ለመናገር የሚያበቃ ምክንያት የለም።