በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንድ ንጉሥ ጥበብን ለማግኘት ያደረገው ጥረት

አንድ ንጉሥ ጥበብን ለማግኘት ያደረገው ጥረት

አንድ ንጉሥ ጥበብን ለማግኘት ያደረገው ጥረት

ስፔን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

አሥራ ሦስተኛው መቶ ዘመን የከረረ አለመቻቻልና ከፍተኛ ዓመጽ የሰፈነበት ወቅት ነበር። በዚያ ወቅት አውሮፓ በአሰቃቂው ኢንኩዊዝሽንና በአስከፊው የመስቀል ጦርነት ትታመስ ነበር። ሆኖም በዚህ በደም የተበከለ ዘመን ውስጥ አንድ የስፔን ንጉሥ በዘመኑ በነበረው ዓለም የሰከነ አስተሳሰብ እንዲሰፍን ለማድረግ ሞክሯል። የዚህ ንጉሥ ስም አልፎንሶ 10ኛ ሲሆን ጠቢቡ አልፎንሶ በመባልም ይታወቃል።

ይህ ንጉሥ በሥነ ጥበብ መስክ እድገት እንዲኖር በማድረጉ የሚታወቅ ሲሆን እርሱ ያከናወነው ሥራ አንዳንድ ጊዜ የ13ኛው መቶ ዘመን የሥነ ጥበብ ማንሰራራት ተብሎ ይታወቃል። ራቅ ካሉ አካባቢዎች ያገኘው አዲስ እውቀት በስፔን እንዲስፋፋ አድርጓል። በተለይም ደግሞ ለሥነ ጥበብ፣ ለታሪክ፣ ለሕግና ለሳይንስ መስኮች ልዩ ትኩረት ይሰጥ ነበር። ይህም በስፔንና በተቀሩት የአውሮፓ አገሮች ለተካሄደው የሥነ ጥበብ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበረው። ንጉሡ ጥበብን ለማግኘት ካደረገው ጥረት ሁሉ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲስፋፋ መርዳቱ ጉልህ ሥፍራ የሚሰጠው ነው።

አልፎንሶ የተማሩ አይሁዶች፣ ሙስሊሞችና ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች አብረው የሚሠሩበት የትምህርት ማዕከል በማቋቋም ረገድ ከፍተኛ ድርሻ ነበረው። ንጉሡ፣ ለምሑራኑ ሥራ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ሲል ወጪውን ራሱ በመሸፈን በዓለም ቀደምት ከሆኑት የመንግሥት ቤተ መጻሕፍት አንዱ የሆነውን በመክፈቱ ይታወቃል።

አልፎንሶ ራሱም በሕግ፣ በሳይንስና በታሪክ መስኮች ልዩ ልዩ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን በመጻፍና በማሰባሰብ ረገድ ትልቅ ተሳትፎ አድርጓል። ንጉሡ በሥነ ጽሑፍና በሥነ ግጥም መስኮች እድገት እንዲኖር አበረታቷል፤ ካንቲጋስ የተባለው የታወቀ ጽሑፉ እንደሚያሳየው እርሱ ራሱ በእነዚህ መስኮች የላቀ ችሎታ ነበረው። * እነዚህ ግጥሞች የተጻፉት በወቅቱ ስሜት የሚነኩ የግጥም ጽሑፎች ይዘጋጁበት በነበረው ጋሌጎ (ጋሊሸን) በሚባል ቋንቋ ነበር።

የተርጓሚዎች ስብስብ

በቶሌዶ የነበረውን የተርጓሚዎች ቡድን ያደራጀውና ወጪውን የሚሸፍነው አልፎንሶ ነበር። ላ ኤስክዌላ ዴ ትራዱክቶሬስ ዴ ቶሌቶ (በቶሌዶ የነበረው የተርጓሚዎች ቡድን) የተሰኘው መጽሐፍ እንደሚገልጸው “ንጉሡ ተርጓሚዎችንም ሆነ የሚተረጉሟቸውን ጽሑፎች ይመርጥ ነበር። . . . የትርጉም ሥራዎቻቸውን ያርም፣ ምሑራዊ ውይይቶች እንዲደረጉ ያበረታታ እንዲሁም ለአዳዲስ የጽሑፍ ሥራዎች የገንዘብ ድጋፍ ያደርግ ነበር።”

የቶሌዶ ምሑራን ሥራቸውን የጀመሩት ብዛት ያላቸውን የአረብኛ ጽሑፎች በመተርጎም ነበር። ሙስሊም ምሑራን ከዚያ ቀደም የሕንድን፣ የሶርያን፣ የግሪክንና የፋርስን ሥልጣኔዎች የሚገልጹ በጣም ጠቃሚ የሆኑ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን ወደ አረብኛ ተርጉመው ነበር። እነዚህ ምሑራን በዚህ የእውቀት ክምችት በመጠቀም በሒሳብ፣ በሥነ ፈለክ፣ በታሪክና በጂኦግራፊ መስኮች ቀጣይ እድገት ማድረግ ችለዋል። በቶሌዶ የሚገኘው የምሑራን ቡድንም በበኩሉ በጣም ጠቃሚ የሆኑ የአረብኛ መጻሕፍትን ወደ ላቲንና ወደ ስፓንኛ ቋንቋ በመተርጎም ይህን የእውቀት ክምችት ጥቅም ላይ አውሎታል።

የቶሌዶ ምሑራን ስላከናወኑት ሥራ በሌሎች አገሮችም ተሰማ። ብዙም ሳይቆይ በሰሜን አውሮፓ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ምሑራን ወደ ቶሌዶ መጉረፍ ጀመሩ። ይህም አውሮፓ በሳይንስና በሥነ ጽሑፍ መስክ ላደረገችው መሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። እንዲያውም ይህ ሰፊ የትርጉም ሥራ ያሳደረው ተጽዕኖ የሥነ ጥበብና የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች እንዲያንሰራሩ መንገድ ጠርጓል።

በቶሌዶ የነበሩት ተርጓሚዎች ያደረጉት ጥረት በጋሌን፣ በሂፖክራተስና በአቪሴና የተዘጋጁ የሕክምና ጽሑፎችን የዘመኑ ሐኪሞች በቋንቋቸው ማንበብ እንዲችሉ ረድቷቸዋል። እነዚህ ሰዎች ያዘጋጁት ካነን (የሕክምና መመሪያ) እስከ 17ኛው መቶ ዘመን ድረስ በምዕራብ አውሮፓ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ዋነኛ የመማሪያ መጽሐፍ ሆኖ አገልግሏል። የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎችም የቶሌሚን ጽሑፎች እንዲያነቡ እንዲሁም በአረብኛው ትሪጎኖሜትሪና አል ክዋሪዝሚ ባዘጋጃቸው የፕላኔቶችን እንቅስቃሴ የሚያሳዩ ሠሌዳዎች እንዲጠቀሙ አስችሏቸዋል። *

አልፎንሶ እነዚህ የትርጉም ሥራዎች ለጥቂት ምሑራን ብቻ ሳይሆን ለጠቅላላው ሕዝብ በሚገባ ቋንቋ እንዲዘጋጁ ፈለገ። ይህም የስፓንኛ ቋንቋ ሳይንሳዊና ሥነ ጽሑፋዊ ሐሳቦች ለሕዝብ የሚተላለፉበት ቋንቋ እንዲሆን አድርጓል። አልፎንሶ የጀመረው ሥራ፣ ለሥነ ጥበብ የሚያገለግለው ቋንቋ ላቲን ብቻ ነው የሚለውን አመለካከት ለመለወጥ ረድቷል።

የአልፎንሶ መጽሐፍ ቅዱስ

በቶሌዶ የነበሩት ምሑራን እነዚህን ብዛት ያላቸው ጽሑፎች ሲተረጉሙ ያካበቱት ተሞክሮ፣ አልፎንሶ የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ወደ ስፓንኛ እንዲተረጎሙ ባዘዘ ጊዜ በጣም እንደጠቀማቸው አያጠራጥርም። ሁዋን ዴ ማርያና የተባሉ ስፔናዊ ታሪክ ጸሐፊ እንደተናገሩት፣ ንጉሡ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራ በራሱ ወጪ እንዲካሄድ ያደረገው የመጽሐፍ ቅዱሱ መተርጎም የስፓንኛን ቋንቋ ጥራት ለመጨመርና ለማዳበር እንደሚረዳ ተስፋ በማድረግ ነው። እንደዚህ ያለው ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ለስፓንኛ ቋንቋ እድገት አስተዋጽኦ እንዳደረገ ጥርጥር የለውም።

ንጉሡ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ለሰው ልጅ ጠቃሚ መመሪያ እንደያዘ አድርጎ ይመለከተው ነበር። ክሮኒካ ዴ ኤስፓኒያ በተሰኘው መጽሐፉ መግቢያ ላይ “ከቅዱሳን ጽሑፎች የምናገኘውን ጥቅም ካሰብን ስለ ዓለም ፍጥረት፣ ስለ ዕብራውያን አባቶች . . . ተስፋ ስለተሰጠበት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና ስለ መከራው፣ ስለ ትንሣኤው እንዲሁም ስለ ዕርገቱ የሚገልጹት ዘገባዎች ትምህርት ይገኝባቸዋል” በማለት ጽፏል።

በተጨማሪም ንጉሡ ኸነራል ኢስቶርያ በማለት የጠራውን አስቸጋሪ ሆኖም ታላቅ የሥነ ጽሑፍ ሥራ ዝግጅት በበላይነት ተቆጣጥሯል። ኸነራል ኢስቶርያ በስፓንኛ የተተረጎሙ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ክፍሎችንም ይጨምር ነበር። (ቆይቶም የግሪክኛው ቅዱሳን መጻሕፍት ክፍሎች ተተርጉመው ተጨምረዋል።) የአልፎንሶ መጽሐፍ ቅዱስ (ቢብሊያ አልፎንሲና) በመባል የሚታወቀው ይህ አስደናቂ ሥራ በመካከለኛው ዘመን ከተዘጋጁት የዚህ ዓይነት መጻሕፍት ሁሉ ትልቁ ነበር። መጽሐፉ ብዙ ጊዜ የተገለበጠ ሲሆን በከፊልም ወደ ፖርቹጋልና ካታላን ቋንቋዎች ተተርጉሟል።

አልፎንሶ ያቆየልን ቅርስ

በአልፎንሶ ዘመን የተዘጋጁት የመካከለኛው ዘመን የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍሎች፣ መንፈሳዊ ጨለማ በሰፈነበት በዚያ ዘመን ቅዱስ ጽሑፋዊ እውቀት እንዳይጠፋ አድርገዋል። የእነዚያ ትርጉሞች መኖር ሕዝቡ መጽሐፍ ቅዱስን በቋንቋው የማግኘት ፍላጎት እንዲያድርበት አድርጓል። በቀጣዮቹ ሁለት መቶ ዓመታት በስፓንኛ ቋንቋ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ተዘጋጅተዋል።

የማተሚያ መሣሪያ መፈልሰፉ እንዲሁም በ16ኛው መቶ ዘመን በስፔንና በሌሎችም የአውሮፓ አገሮች የነበሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ያደረጉት ያላሰለሰ ጥረት አልፎንሶና የዘመኑ ሰዎች የጀመሩት ሥራ እንዲቀጥል አድርጓል። ከዚህ ሁሉ በኋላ በመላው አውሮፓ የነበሩ ሰዎች በራሳቸው ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት ቻሉ። በአልፎንሶ 10ኛ የግዛት ዘመን ጦርነትና ዓመጽ የነበረ ቢሆንም ንጉሡ ለእውቀት የነበረው ጥማት መለኮታዊው ጥበብ በስፋት እንዲሰራጭ አድርጓል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.6 ካንቲጋስ የሚባሉት በአዝማሪዎች የሚዘፈኑ የመካከለኛው ዘመን ግጥሞች ናቸው።

^ አን.11 አል ክዋሪዝሚ በዘጠነኛው መቶ ዘመን ይኖር የነበረ ታዋቂ ፋርሳዊ የሒሳብ ሊቅ ነው። ይህ ሰው አልጀብራ እንዲዳብር ያደረገ ከመሆኑም በላይ ዜሮንና የአሪትሜቲክ መሠረታዊ ሐሳቦችን ጨምሮ የአረብ ቁጥሮችን እንደመጠቀም የመሳሰሉትን የሕንዶች የሒሳብ አሠራር ዘዴዎች አስተዋውቋል። “አልጎሪዝም” የሚለው ቃል አል ክዋሪዝሚ ከሚለው ስም የተወሰደ ነው።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ጥንታዊ የስፓንኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች

ወደ ስፓንኛ ቋንቋ የተተረጎሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን በማካተት ረገድ የአልፎንሶ 10ኛ የትርጉም ሥራዎች የመጀመሪያዎቹ አይደሉም። ከዚያ ጥቂት ዓመታት ቀደም ብሎ በቶሌዶ ከነበሩት ተርጓሚዎች አንዱ የሆነው ኸርማነስ አሌማነስ፣ መጽሐፈ መዝሙርን ከዕብራይስጥ በቀጥታ ወደ ስፓንኛ ቋንቋ ተርጉሞት ነበር። በተጨማሪም በ13ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ቢብሊያ ሜዲየቫል ሮማንሴአዳ ፕሪአልፎንሲና (በመካከለኛው መቶ ዘመን በስፓንኛ ቋንቋ የተዘጋጀ ቅድመ አልፎንሶ መጽሐፍ ቅዱስ) የተባለ ትርጉም ተዘጋጅቶ ነበር። (በስተ ግራ ያለውን ፎቶ ተመልከት።) ይህ የትርጉም ሥራ በስፓንኛ ቋንቋ የተዘጋጀ ጥንታዊ የተሟላ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሆነ ይታሰባል። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ከጥቂት ዓመታት በኋላ በአልፎንሶ 10ኛ ትእዛዝ ለተተረጎመው መጽሐፍ ቅዱስ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ጥርጥር የለውም።

ይህን ቅድመ አልፎንሶ መጽሐፍ ቅዱስ በሚመለከት ቶማስ ሞንትጎሜሪ የተባሉ ምሑር እንደሚከተለው ብለዋል:- “ከትክክለኝነቱና ያማረ ቋንቋ ከመጠቀሙ አንጻር ስናየው የዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ የሚደነቅ ሥራ አከናውኗል። ይህ ትርጉም የላቲን ቋንቋን አገላለጾች ወይም አባባሎች በብዛት ሳይጠቀም የላቲኑን ቩልጌት መልእክት በትክክል አስተላልፏል። በቂ የላቲን ቋንቋ ችሎታ ለሌላቸው ሰዎች ከተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚፈለገው ሁሉ ይህም ትርጉም ቀላልና ግልጽ በሆነ ቋንቋ የተተረጎመ ነው።”

[ምንጭ]

መጽሐፍ ቅዱስ:- Patrimonio Nacional. Real Biblioteca de El Escorial

[በገጽ 12 እና 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማድሪድ በሚገኘው በስፔን ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት መግቢያ ላይ ያለው የአልፎንሶ 10ኛ ሐውልት

[በገጽ 13 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ንጉሡ ከቶሌዶ ከመጡ ተርጓሚዎች ጋር (ከላይ)፣ የአልፎንሶ ጸሐፊዎች (ከታች)፣ “ቢብሊያ አልፎንሲና” ውስጥ የሚገኘው የሉቃስ ወንጌል (ከግርጌ)

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከአልፎንሶ 10ኛ ሐውልት በስተቀር ሁሉም ፎቶዎች የተወሰዱት:- Oronoz