በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የበሊዝ ባሪየር ሪፍ የዓለም ቅርስ

የበሊዝ ባሪየር ሪፍ የዓለም ቅርስ

የበሊዝ ባሪየር ሪፍ የዓለም ቅርስ

ሜክሲኮ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

“ማንኛውም ባሕላዊ ወይም ተፈጥሯዊ ቅርስ መበላሸቱ ወይም መጥፋቱ ሁሉንም የዓለም ሕዝቦች ለቅርስ ድህነት የሚዳርግ ጎጂ ሁኔታ ያስከትላል። . . . ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአጠቃላይ የላቀ ዓለም አቀፋዊ ጠቀሜታ ላላቸው ባሕላዊም ሆኑ ተፈጥሯዊ ቅርሶች ጥበቃ የማድረግ ግዴታ አለበት።”—ከዩኔስኮ የዓለም ቅርሶች ስምምነት ላይ የተወሰደ

ከላይ ከተገለጹት ቃላት ጋር በሚስማማ መልኩ፣ የበሊዝ ባሪየር ሪፍ የተባለው ጥበቃ የሚደረግለት ክልል በ1996 የዓለም ቅርስ በመባል ተመዝግቧል። ይህም ክልሉን በፔሩ ከሚገኘው ማቹ ፒቹ የተባለ የኢንካዎች ምሽግ፣ በዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኘው ግራንድ ካኒየን የሚባል ገደላማ ሸለቆ እንዲሁም በዓለም ዙሪያ ከሚገኙት ሌሎች አስደናቂ ቅርሶች ጋር እንዲመደብ አድርጎታል። ሆኖም ይህ ሥፍራ “የላቀ ዓለም አቀፋዊ ጠቀሜታ” እንዳለው የተገለጸው ለምንድን ነው?

ጥበቃ ሊደረግለት የሚገባ ቅርስ

የበሊዝ ባሪየር ሪፍ፣ ከታላቁ የአውስትራሊያ ባሪየር ሪፍ ቀጥሎ ሕይወት ያላቸው ኮራሎች (ዛጎላማ እንስሳት) በብዛት የሚገኙበት የዓለማችን ክፍል ሲሆን በምዕራቡ ክፍለ ዓለምም በርዝመቱ ተወዳዳሪ የለውም። ይህ ክልል በዩካታን ባሕረ ገብ መሬት በኩል 300 ኪሎ ሜትር ያህል ርዝመት ያለው ሲሆን የበሊዝን የባሕር ዳርቻ አብዛኛውን ክፍል ይሸፍናል። ክልሉ፣ እንደ ሰንሰለት ከተያያዘው ሪፍ በተጨማሪ 450 ትንንሽ ደሴቶችን እንዲሁም ውብ በሆኑ ኩሬዎች ዙሪያ የሚገኙ ሦስት የኮራል ክምችቶችን ይዟል። በዚህ ክልል ውስጥ የሚገኙት 960 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ ሰባት የውኃ አካላት በዓለም የቅርሶች ስምምነት መሠረት ልዩ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ተወስኗል።

ኮራል ሪፍ ወይም ዛጎል ተሬ (ኮራል ፖሊፕ በሚባሉ ከካልሲየም ካርቦኔት ወይም ከበሃ ድንጋይ የተሠራ ጠንካራ ሽፋን ባላቸውና እጅብ ብለው በሚኖሩ ሥጋ በል እንስሳት የተገነባ አለት መሰል ነገር ነው) 25 በመቶ ለሚሆኑት የባሕር እፅዋትና እንስሳት መኖሪያ በመሆኑ ጥበቃ ሊደረግለት እንደሚገባ ግልጽ ነው። በእርግጥም የተለያዩ ሕያዋን ፍጥረታት መኖሪያ ከመሆን አንጻር ጥቅጥቅ ባሉ ደኖች ከተሸፈኑ አካባቢዎች ቀጥሎ ሁለተኛውን ደረጃ የሚይዘው ዛጎል ተሬ ነው። ሆኖም የሰው ልጆች ለባሕር መበከል ምክንያት የሚሆኑትን የተለያዩ ነገሮች፣ ቁጥጥር የማይደረግበትን ቱሪዝም እንዲሁም ሳይናይድ በተባለው ኬሚካል አማካኝነት ዓሣ እንደማጥመድ ያሉትን ጎጂ ድርጊቶች ማስቆም ካልቻሉ በፕላኔታችን ላይ ካሉት ኮራሎች ውስጥ 70 በመቶ የሚሆኑት በሚቀጥሉት ከ20 እስከ 40 በሚደርሱ ዓመታት ውስጥ እንደሚጠፉ የሳይንስ ሊቃውንት ያስጠነቅቃሉ።

በበሊዝ ባሪየር ሪፍ ጥበቃ የሚደረግለት ክልል ውስጥ፣ 70 ዓይነት ጠንካራ ኮራሎችና 36 ዓይነት ለስላሳ ኮራሎች እንዲሁም 500 ዓይነት የዓሣ ዝርያዎች እንዳሉ ታውቋል። ክልሉ፣ ለመጥፋት ለተቃረቡ የባሕር እንስሳት መኖሪያ ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን ከእነዚህም መካከል እንደ ሎገርሄድ፣ ግሪን እና ሆክስቢል ያሉት የባሕር ኤሊዎች እንዲሁም ማነቴ እና የአሜሪካ አዞ ይገኙበታል። ጁሊያን ሮቢንሰን የተባሉ እንዲህ ዓይነቱን አካባቢ የሚያጠኑ ተመራማሪ፣ በዚህ ክልል ውስጥ ስለሚኖሩት ልዩ ልዩ የባሕር ፍጥረታት ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል:- “የበሊዝ ባሪየር ሪፍ ለተመራማሪዎችም ሆነ ለጎብኚዎች በርካታ ለየት ያሉ አጋጣሚዎች ይሰጣቸዋል። . . . ክልሉ ድንግል ተፈጥሮን ልትመለከቱ ከምትችሉባቸው ጥቂት ቦታዎች አንዱ ነው፤ ሆኖም አካባቢው አደጋ ተጋርጦበታል።”

የበሊዝ ሪፍ እንዲበላሽ ከሚያደርጉት ነገሮች ዋነኛው በቀለማት ያሸበረቁት ኮራሎች እየገረጡ መምጣታቸው ነው። (በገጽ 26 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።) ናሽናል ጂኦግራፊክ ኒውስ እንደዘገበው በ1997 እና በ1998 ሃሪኬን ሚች የተባለውን አውሎ ነፋስ ተከትሎ የደረሰው ከፍተኛ የኮራል መገርጣት ሕይወት ያለውን ኮራል በ48 በመቶ ቀንሶታል። ይህን ጥፋት ያስከተለው ምንድን ነው? ጥናቱ ገና ያልተጠናቀቀ ቢሆንም ይህን ሁኔታ የሚያጠኑ ሜላኒ መክፊልድ የተባሉ ሳይንቲስት እንዲህ ብለዋል:- “ይህ የኮራል መገርጣት ከውቅያኖስ ሙቀት መጨመር ጋር በጣም የተያያዘ ነው። . . . አልትራቫዮሌት ጨረርም የኮራል መገርጣትን የሚያስከትል ሲሆን ይህ ዓይነቱ ጨረር ከውቅያኖስ ሙቀት መጨመር ጋር በሚጣመርበት ጊዜ ደግሞ ችግሩን ያባብሰዋል” ብለዋል። ደስ የሚለው ግን የበሊዝ ሪፍ ቀስ በቀስ ወደ ቀድሞ ሁኔታው እየተመለሰ መሆኑ ነው። *

በውኃ ውስጥ ያለ ገነት

አማካይ ሙቀቱ 26 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የሆነው በበሊዝ ሪፍ የሚገኘው ጥርት ያለ ውኃ ለዋናተኞች አስደሳች ነው። ከበሊዝ ሪፍ ውስጥ 90 በመቶ የሚሆነው ክፍል ገና ጥናት አልተካሄደበትም። የበሊዝ ሪፍ፣ አምበርግሪስ በምትባለው ደሴት ላይ ካለችው ከሳን ፔድሮ ከተማ ጥቂት መቶ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን ሰዎች በቀላሉ ሊደርሱበት የሚችሉት ከዚሁ አካባቢ የሆነውም ለዚሁ ነው። ከሳን ፔድሮ በስተ ደቡብ ምሥራቅ 6 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ደግሞ ሆል ቻን የተባለው ጥበቃ የሚደረግለት ክልል ይገኛል። በዚህ ክልል ውስጥ ሪፉን ሰንጥቆ የሚያልፍ ዋሻ የሚታይበት 8 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ጥልቀት የሌለው የውኃ ውስጥ ፓርክ ይገኛል።

በምድር ላይ ለዋና አመቺ ከሆኑት አስደናቂ ቦታዎች አንዱ ብሉ ሆል የተሰኘው ጥበቃ የሚደረግለት የዓለም ቅርስ ክልል ሲሆን ሥፍራው ከበሊዝ ግዛት 100 ኪሎ ሜትር ርቆ ላይትሃውስ በተባለው ሪፍ ላይ ይገኛል። ይህ ቦታ ሊታወቅ የቻለው ስመ ጥር የሆነው ፈረንሳዊ የውቅያኖስ ተመራማሪ ዣክ-ኢቭ ኮስቴኡ በ1970 ካሊፕሶ በተባለችው የምርምር መርከብ ባደረገው ጉዞ ነው። ወደ አረንጓዴ የሚወስደው ሰማያዊ መልክ ባለው ባሕር ላይ የሚገኘው ብሉ ሆል የተባለው ጉድጓድ መሃሉ የተቦረቦረ በሃ ድንጋይ ሲሆን ውኃው ደማቅ ሰማያዊ ቀለም አለው። ዙሪያውን ደግሞ ሕይወት ባላቸው ኮራሎች ተከቧል። ብሉ ሆል መሃል ለመሃል ሲለካ ርዝመቱ 300 ሜትር ያህል ሲሆን ወደ ታች ጥልቀቱ ደግሞ ከ120 ሜትር በላይ ይሆናል። የባሕሩ ወለል ከፍ ከማለቱ በፊት ይህ ቦታ በመሬት ውስጥ የሚገኝ ደረቅ ዋሻ የነበረ ሲሆን ከጊዜ በኋላም አናቱ ተደረመሰ። ጉድጓዱ እስከ 35 ሜትር ጥልቀት ድረስ ቀጥ ብሎ የሚወርድ ሲሆን ከዚያ በታች ባለው ክፍል ግን ከግድግዳው ላይ የበቀሉ የሚመስሉ ሹል አለቶች ተንጠልጥለው ይታያሉ። ውኃው ውስጥ 60 ሜትር ያህል ርቀት ድረስ በሁሉም አቅጣጫ የሚታየው ነገር የሚያስደምም ነው። በዚህ ጉድጓድ ውስጥ ሻርክ ከሚባለው የዓሣ ዝርያ በቀር ሌሎች ፍጥረታት እምብዛም አይገኙም። ኦክሲጅን ይዘው ውኃ ውስጥ ጠልቀው የሚገቡ ዋናተኞች፣ ብሉ ሆል ልምድ በሌላቸው ሰዎች የማይሞከር ቦታ እንደሆነ መገንዘብ አለባቸው። ምክንያቱም አየሩ ከባድ በሆነበት ጥልቀት ባለው የባሕሩ ክፍል ሲዋኙ ከቆዩ በኋላ ወደ ላይ ሲወጡ ጥንቃቄ ማድረግ ያሻቸዋል ይሁን እንጂ ኮራሎቹ ባሉበት ክልል ውስጥ ለመተንፈስ የሚረዳ ቱቦ በመጠቀም ውኃው ውስጥ ጠልቀው ሳይገቡ ለመዋኘት የሚያመች ኩልል ያለ ውኃ አለ።

በአቅራቢያው ደግሞ በሊዝ ውስጥ ካሉ ጥበቃ የሚደረግላቸው ሰባት የዓለም ቅርሶች መካከል አንዱ የሆነው ሃፍ ሙን ኬ ተብሎ የሚጠራ እጅግ ማራኪ ደሴት አለ። በዚህ ደሴት ላይ ቀላ ያለ እግር ያላቸው ቡቢ የሚባሉ ብርቅዬ የባሕር ወፎች ይገኛሉ። እዚህ ቦታ ላይ ሌሎች 98 ዓይነት የወፍ ዝርያዎችም እንደሚገኙ ተመዝግቧል። ውብ በሆኑ ለስላሳ ኮራሎች በተሸፈነውና 1,000 ሜትር ጥልቀት ባለው በሃፍ ሙን ኬ ደሴት ዙሪያ በሚገኘው ባሕር ውስጥ መዋኘት በጣም ያስደስታል።

የበሊዝን ባሪየር ሪፍ ከቃኘንበት ከዚህ አጭር ጉብኝት መመልከት እንደሚቻለው ይህንን ውድ ሀብት ለመጪዎቹ ትውልዶች ጠብቆ ለማቆየት የሚያነሳሳ ጥሩ ምክንያት አለ። በእርግጥም በዚህ ውድ ሀብት ላይ የሚደርስ ጥፋት “ሁሉንም የዓለም ሕዝቦች ለቅርስ ድህነት የሚዳርግ ጎጂ ሁኔታ” ያስከትላል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.9 የባሕር ሙቀት እንዲጨምር የሚያደርገውን ዓለም አቀፍ የሙቀት መጨመር በተመለከተ በአንድ አካባቢ ብቻ ብዙም ሊደረግ የሚችል ነገር አይኖር ይሆናል፤ ሆኖም የበሊዝ ሪፍ የዓለም ቅርስ ሆኖ መመዝገቡ የአገሪቱ ነዋሪዎች ሥፍራውን ለመጠበቅ የበለጠ ጥረት እንዲያደርጉ አበረታቷቸዋል።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

የኮራል መገርጣት

ሪፍ የሚባለው ኮራል ፖሊፕ በሚባሉ ከካልሲየም ካርቦኔት ወይም ከበሃ ድንጋይ የተሠራ ጠንካራ ሽፋን ያላቸውና እጅብ ብለው በሚኖሩ ሥጋ በል እንስሳት የተገነባ ወጣ ገባ የሆነ አለት መሰል ነገር ነው። ሕይወት ያላቸው ኮራሎች ቀደም ሲል በሞቱ ኮራሎች አጽም ላይ ተለጥፈው ያድጋሉ። በአጉሊ መነጽር ብቻ የሚታዩ አልጌዎች በኮራል ሪፍ (ዛጎል ተሬ) ላይ ተለጥፈው ይኖራሉ፤ እነዚህ አልጌዎች ወደ ውጭ የሚያስወጡትን ኦክሲጅንና አልሚ ምግብ ኮራል ፖሊፖች የሚጠቀሙበት ሲሆን በምላሹ ደግሞ ኮራል ፖሊፖች የሚያስወጡትን ካርቦን ዳይኦክሳይድ አልጌዎቹ ይወስዳሉ። ኮራል ፖሊፖች የውኃው የሙቀት መጠን መለዋወጥ በቀላሉ ስለሚሰማቸው ሙቀቱ ሲጨምር አልጌዎቹን ከላያቸው ላይ ማራገፍ ይጀምራሉ፤ ይህም አረንጓዴ ቀለማቸው ተገፎ የገረጣ መልክ እንዲይዙ ያደርጋቸዋል። ኮራሎቹ እንዲህ በተዳከሙበት ወቅት ለበሽታና ለሞት በቀላሉ ይጋለጣሉ። ይሁን እንጂ ኮራል ሪፍ ጥበቃ ከተደረገለት ወደ ቀድሞ ሁኔታው መመለስና ማገገም ይችላል።

[ምንጭ]

ከጀርባ ያለው ፎቶ:- Copyright © 2006 Tony Rath Photography - www.trphoto.com

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ሜክሲኮ

በሊዝ

ካሪቢያን ባሕር

ሰላማዊ ውቅያኖስ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

300 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የበሊዝ ሪፍ በሳተላይት ሲታይ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ራንዴቩ ኬ

[ምንጭ]

kevinschafer.com

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሆክስቢል የተባለው የባሕር ኤሊ

[በገጽ 24, 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ላይትሃውስ በሚባለው ሪፍ ላይ የሚገኘውና አናቱ በተደረመሰ የበሃ ድንጋይ ዋሻ ምክንያት የተፈጠረው ብሉ ሆል

[ምንጭ]

kevinschafer.com

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የበሊዝ ባሪየር ሪፍ 500 ለሚሆኑ የዓሣ ዝርያዎች መኖሪያ ነው

[ምንጭ]

ውስጠኛው ፎቶ:- © Paul Gallaher/Index Stock Imagery

[ገጽ 23 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]

የሳተላይት ምስል:- NASA/The Visible Earth (http://visibleearth.nasa.gov/); ዋናተኞቹ:- © Paul Duda/Photo Researchers, Inc.

[ገጽ 24 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Copyright © Brandon Cole