በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የኖኅ መርከብ እና የመርከብ ምህንድስና

የኖኅ መርከብ እና የመርከብ ምህንድስና

የኖኅ መርከብ እና የመርከብ ምህንድስና

ከ40 ለሚበልጡ ዓመታት የመርከብ ንድፍ አውጪና መሃንዲስ ሆኜ ሠርቻለሁ። ሥራዬ የተለያየ ቅርጽና መጠን ላላቸው መርከቦች ዲዛይን ከማውጣት ጀምሮ የሚያንቀሳቅሳቸውን ሞተርና የሌሎች ክፍሎቻቸውን ዲዛይን መሥራትን ያጠቃልላል። በ1963 ካናዳ በምትገኘው ብሪትሽ ኮሎምቢያ እያለሁ አንዲት የይሖዋ ምሥክር ከዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ የኖኅ መርከብ ረጅም ሣጥን ትመስል እንደነበር አስነበበችኝ። ይህ አገላለጽ ትኩረቴን ስለሳበው ስለ ሁኔታው ይበልጥ ለማጥናት ወሰንኩ።

የዘፍጥረት ዘገባ አምላክ ምድርን ከክፋት ለማጽዳት በውኃ እንዳጥለቀለቃት ይናገራል። አምላክ ኖኅ ራሱን፣ ቤተሰቡንና የተለያዩ የእንስሳት ዝርያዎችን ከዚህ የጥፋት ውኃ ለማዳን መርከብ እንዲሠራ ትእዛዝ ሰጠው። ኖኅ የሚሠራት መርከብ ርዝመቷ 140 ሜትር፣ ወርዷ 23 ሜትር፣ ከፍታዋ 13.5 ሜትር መሆን እንዳለበት ነገረው። (ዘፍጥረት 6:15) የዚህች ግዙፍ መርከብ መጠን በግምት 40,000 ሜትር ኩብ የሚያክል ሲሆን የቅንጦት መርከብ ከነበረችው ከታይታኒክ ጋር ተመጣጣኝ ነው።

የመርከቧ ንድፍ

መርከቧ ባለ ሦስት ፎቅ ተደርጋ የተሠራች መሆኗ ጥንካሬ እንዲኖራት የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ በጠቅላላ 8,900 ስኩዌር ሜትር የወለል ስፋት እንዲኖራት ያደርጋል። መርከቧ የተገነባችው በውኃ የመራስ ባሕርይ በሌለው በጎፈር እንጨት ነው። ምናልባት ይህ ዛፍ የጥድ ዝርያ ሊሆን ይችላል። ከዚያም ውጪዋም ሆነ ውስጧ በቅጥራን ተለቅልቋል። (ዘፍጥረት 6:14-16) ኖኅ ጣውላዎቹን በምን እንዳያያዛቸው የምናውቀው ነገር የለም። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የጥፋት ውኃው ከመምጣቱ በፊት ከብረትና ከናስ ልዩ ልዩ መሣሪያዎችን የሚሠሩ ሰዎች እንደነበሩ ይናገራል። (ዘፍጥረት 4:22) ያም ሆነ ይህ በዘመናችንም ቢሆን እንጨቶችን ያለምንም ማያያዣ እርስ በርስ በመሰካካት መርከቦችን መሥራት የተለመደ ነው።

መርከቧ የተለያዩ ክፍሎች የነበሯት ሲሆን ከጎን በኩል በር እንዲሁም ጣራውና ግድግዳው በሚገናኙበት ቦታ ላይ ግማሽ ሜትር የሚያህል ክፍተት አላት። ይህ ክፍተት ወደ መርከቧ አየርና ብርሃን እንዲገባ የሚያገለግል ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ የዘፍጥረት ዘገባ መርከቧ ከሥሯ የደጋን ቅርጽ ያለው ረጅም እንጨት እንዲሁም ሸራና መቅዘፊያ ያላት ስለመሆኑ ምንም የሚናገረው ነገር የለም። እንዲያውም ይህን መርከብ ለማመልከት የገባው የዕብራይስጥ ቃል ሙሴ ሕፃን ሳለ እናቱ በዓባይ ወንዝ ላይ እንዲንሳፈፍ ለማድረግ የተጠቀመችበትን ከደንገል የተሠራ ቅርጫት ለማመልከት ከገባው ቃል ጋር ተመሳሳይ ነው።—ዘፀአት 2:3, 10

መርከቧ የነበራት ነፋስና ሞገድን የመቋቋም ችሎታ

የመርከቧ ርዝመት ወርዷን ስድስት እጥፍ እንዲሁም ቁመቷን አሥር እጥፍ ይበልጣል። በዘመናችን የሚሠሩ ብዙ መርከቦች ርዝመት፣ ወርድና ቁመት ከዚህ ጋር ተመጣጣኝ ነው። እርግጥ እነዚህ መርከቦች ርዝመታቸው ከወርዳቸው ጋር ተመጣጣኝ እንዲሆን የሚደረገው ውኃውን ሰንጥቀው እንዲሄዱ ከሚያስችላቸው ኃይል ጋር በተያያዘ ነው። የኖኅ መርከብ ግን የተሠራችው በውኃ ላይ እንድትንሳፈፍ ብቻ ነው። ሆኖም ይህን ዓላማዋን ምን ያህል በብቃት ተወጥታለች?

መርከቦች በባሕር ላይ ሲጓዙ የሚያጋጥማቸው ነፋስና ሞገድ የማይበግራቸው ከሆኑ ጥሩ የመቋቋም ችሎታ (seakeeping behavior) እንዳላቸው ተደርጎ ይታሰባል። ይህም ቢሆን የመርከቦቹ ርዝመት፣ ወርድና ቁመት ተመጣጣኝ በመሆኑ ላይ በእጅጉ የተመካ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እጅግ ታላቅ ዝናብ በመዝነቡ ምክንያት የውኃ መጥለቅለቅ እንደተከሰተ እንዲሁም አምላክ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ነፋስ እንዲነፍስ እንዳደረገ ይናገራል። (ዘፍጥረት 7:11, 12, 17-20፤ 8:1) ምንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ ነፋሱ ወይም ሞገዱ ምን ያህል ከባድ እንደነበረ ባይናገርም በዛሬውም ጊዜ እንደሚታየው ሁሉ ነፋሱም ሆነ ሞገዱ ኃይለኛና ተለዋዋጭ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ነፋሱ ረዘም ላለ ጊዜ በኃይል በነፈሰ መጠን ሞገዱም የዚያኑ ያህል በጣም ወደ ላይ እንዲነሳ ያደርገዋል። በተጨማሪም ማንኛውም ዓይነት የመሬት ነውጥ ከባድ ሞገድ እንዲነሳ ምክንያት ይሆናል።

መርከቧ ተመጣጣኝ ተደርጋ መሠራቷ ከመጠን በላይ እንዳትዋልል ከመርዳቱም ሌላ ከመገልበጥ አድኗታል። እንዲሁም መርከቧ የተሠራችው እንድትዋልል የሚያደርጋትን ግፊት መቋቋም እንድትችል ተደርጋ ነው። ሞገዱ መርከቧን በአንደኛው ጫፍ በተደጋጋሚ ጊዜያት ወደ ላይ ወደ ታች የሚያደርጋት በመሆኑ ምክንያት ከመጠን በላይ መዋለሏ በውስጧ የተሳፈሩትን ሰዎችም ሆነ እንስሳት እንዲንገላቱ ያደርጋቸዋል። ከዚህም በላይ ይህ ግፊት በመርከቧ ላይ ከባድ ጫና ይፈጥራል። የተዋቀረችበት መንገድ ኃይለኛ ሞገድ መርከቧን በአንድ ጊዜ ከፊትና ከኋላ ወደ ላይ ቢያነሳት መሃል ለመሃል ልምጥ እንድትል የሚያደርጋትን ኃይል መቋቋም የሚያስችል መሆን አለበት። ያም ሆኖ ግን ከባድ ሞገድ መርከቧን መሃል ለመሃል ወደ ላይ ካነሳት ከፊትና ከኋላ ምንም የሚደግፋት ነገር ስለማይኖር ወደ ላይ ልምጥ ልትል ትችላለች። ስለዚህ አምላክ ለኖኅ የመርከቧን ርዝመት ከቁመቷ በአሥር እጅ አስበልጦ እንዲሠራት አዘዘው። አሁን ያሉት የመርከብ ሠራተኞች በመርከብ ላይ የሚደርሰውን እንዲህ ያለውን ጫና ለመቋቋም በዚህ ሬሾ መርከብ መገንባት ጠቃሚ መሆኑን የተረዱት ብዙ ችግር ካሳለፉ በኋላ ነው።

አስተማማኝ እንዲሁም ምቹ

የመርከቧ ቅርጽ ሣጥን መሰል መሆኑ እንድትንሳፈፍ የሚያደርጋት ኃይል ከጫፍ እስከ ጫፍ ተመሳሳይ እንዲሆን ይረዳል። ክብደቷም ቢሆን በሁሉም ቦታ ላይ ተመጣጣኝ መሆን ነበረበት። ኖኅ ጭነቱን ማለትም እንስሳቱን ብሎም ከአንድ ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ የሚያገለግላቸውን ምግብ በየትኛውም ቦታ ላይ እንዳይበዛ አድርጎ እንደጫነ እርግጠኛ መሆን ይቻላል። ጭነቱ በሁሉም ቦታ ላይ ተመጣጣኝ መሆኑ መርከቧ ላይ የሚደርሰውን ተጨማሪ ጫና ለመቀነስ ይረዳል። መርከቧም ሆነች ተሳፋሪዎቹ ከባድ ችግር ሳይገጥማቸው የጥፋቱን ውኃ ማሳለፍ የቻሉት በሁለት ምክንያቶች የተነሳ ነው፤ አንደኛው ይሖዋ ያወጣው ንድፍ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ እርሱ ጥበቃ ማድረጉ ነው። አምላክ መርከቧ አስተማማኝና ምቹ በሆነ ቦታ ላይ እንድታርፍ እንዳደረገ ምንም ጥርጥር የለውም።

በዚህ ጉዳይ ላይ ያደረግሁት ጥልቅ ምርምር መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኖኅ መርከብ የሚናገረው ነገር ሁሉ እውነት መሆኑንና አሠራሯም ቢሆን ከዘመናዊ የመርከብ ግንባታ ጋር እንደሚመሳሰል እንዳምን አድርጎኛል። እርግጥ ነው በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ስለ መርከቧም ሆነ ስለ ጥፋት ውኃው ያልተጠቀሱ ብዙ ዝርዝር ነገሮች አሉ። ከትንሣኤ በኋላ ኖኅን ረጅም ጊዜ ወስዶ በብዙ ጥረት በሠራው መርከብ አማካኝነት በተረፉት ሰብዓዊ ቤተሰብና እንስሳት መካከል እዚሁ ምድር ላይ አገኘዋለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። (የሐዋርያት ሥራ 24:15፤ ዕብራውያን 11:7) ያኔ እርሱንና ቤተሰቡን ላደረጉት ነገር ካመሰገንኳቸው በኋላ ኖኅን ብዙ ጥያቄዎች እጠይቀዋለሁ።—ተጽፎ የተላከልን

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የመርከቧን ሞዴል መሥራት

ከዚህ በታች ያለውን ንድፍ ተከትለህ የመርከቧን ሞዴል መሥራትና ሙከራ ማድረግ ትችላለህ። (ንድፉን በማሳደግ ተለቅ ያለ የመርከብ ሞዴል መሥራት ትችላለህ።) ማንኛውንም ዓይነት ወረቀት ሙሉ በሙሉ ሰም በመቀባት ውኃ እንዳያስገባ ማድረግ ይቻላል። ከዚያም ወረቀቱን መስመሩን ተከትለህ ካጠፍከው በኋላ በፕላስተር ወይም በሙጫ አጣብቀው። የሠራኸው መርከብ ከአንድ ሦስተኛው በላይ ውኃ ውስጥ እስኪሰምጥ ድረስ በወለሉ ላይ ሣንቲሞችን የመሳሰሉ ከበድ ያሉ ነገሮች አመጣጥነህ አስቀምጥበት።

የኖኅ መርከብ በውኃ ላይ በነበረችበት ወቅት ሁኔታው ምን ይመስል እንደነበር ለማየት በገላ መታጠቢያ ገንዳ ወይም ሳፋ ውስጥ ውኃ ሞልተህ ሞዴሉን መሃል ላይ አስቀምጠው፤ ከዚያም ከመርከቧ በስተኋላ አራት ማዕዘን ቅርፅ ያለው አነስተኛ ካርቶን (የብስኩት ካርቶን ሊሆን ይችላል) ቀስ ብለህ ብቅ ጥልቅ በማድረግ ሞገድ ለመፍጠር ጥረት አድርግ።

[ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ወደ ውስጥ እጠፍ ወደ ውስጥ እጠፍ

 

ወደ ውስጥ እጠፍ ወደ ውስጥ እጠፍ

[ሥዕል]

የኖኅ መርከብ ርዝመት፣ ወርድና ቁመት ተመጣጣኝነት የውቅያኖስ ላይ መርከቦች ከሚሠሩበት መጠን ጋር ተመሳሳይ ነው

[በገጽ 20, 21 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ/ሥዕሎች]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ከፊት

ከጎን

ከላይ

ከፊት

ከጎን

ከላይ

[ሥዕሎች]

የመርከቧ መጠን “ከታይታኒክ” ጋር ተመጣጣኝ ነው

[ምንጮች]

የታይታኒክ ንድፍ:- Courtesy Dr. Robert Hahn/​www.titanic-plan.com; ፎቶ:- Courtesy of The Mariners’ Museum, Newport News, VA