በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የክርስትና እምነት ችግር አለው?

የክርስትና እምነት ችግር አለው?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

የክርስትና እምነት ችግር አለው?

አንድ ሦስተኛ የሚሆነው የምድር ሕዝብ ክርስቲያን እንደሆነ ይናገራል። ሆኖም ዓለም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በፖለቲካ የተከፋፈለችና የዓመጽ ድርጊቶች የተስፋፉባት ሆናለች። ይህ መሆኑ ኢየሱስ ያቋቋመው የክርስትና እምነት ችግር እንዳለው ያመለክታል? ወይስ ችግር የፈጠረው ብዙዎች የክርስቶስን ትምህርቶች በተግባር የሚያውሉበት መንገድ ነው?

በዚህ ርዕስ ውስጥ ክርስቶስ ያስተማረውን ትምህርትና ለተከታዮቹ የተወውን ምሳሌ እንመረምራለን። እንዲሁም ከክርስትና እምነት እውነተኛ ትርጉም ጋር ስለሚጋጨውና ክርስቲያን ነን በሚሉ ብዙ ሰዎች ዘንድ ተስፋፍቶ ስለሚገኘው አመለካከት ይብራራል።

ፈሩን የሳተ የክርስትና እምነት

ክርስቶስ ከሞተ ከአራት መቶ ዓመታት ገደማ በኋላ፣ ፈሩን የሳተ የክርስትና እምነት በሮማ ግዛት ተቀባይነት ማግኘት ጀመረ። ክርስቲያን ነን የሚሉት የዚህ ቡድን አባላት መገለላቸው ቀርቶ በሮም ኅብረተሰብ ውስጥ በፖለቲካው መስክና በማኅበራዊው ሕይወት ትልቅ ቦታ ተሰጣቸው። እንደ አውጉስቲን ያሉ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ይህንን ለውጥ ሲመለከቱ ሲጠበቅ የነበረው የአምላክ መንግሥት እንደመጣ ማስተማር ጀመሩ። እነዚህ መሪዎች በፖለቲካውም ሆነ በሃይማኖቱ መስክ ያገኙት ቦታ የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲሆን ለማድረግ እንደሚያስችላቸው ያስተምሩ ነበር። በዚህ መንገድ፣ የሰው ልጅ ምድርን ለመምራት ለሚያደርገው ጥረት ከፍተኛ ቦታ ሰጥተውታል።

ይህም ብዙዎች፣ አንድ ክርስቲያን በፖለቲካው መስክ ተሳትፎ ሊኖረው ይገባል ብለው እንዲያምኑ አድርጓቸዋል። ስለዚህ አንድ ክርስቲያን የሚኖርበትን ኅብረተሰብ ፍላጎት ለማሟላት ሲል አንዳንድ ጊዜ የሚያምንባቸውን ነገሮች መተው እንዳለበት አብዛኞቹ ሰዎች ያምናሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ብዙ ሰዎች ክርስቶስ ስለ ፍቅርና ስለ ሰላም ያስተማራቸውን ትምህርቶች እንደሚቀበሉ ቢናገሩም አረመኔያዊ ጦርነቶችን ይደግፋሉ። በተመሳሳይም ቤተ ክርስቲያናት ምዕመኖቻቸውን ስለ አምላክ መንግሥት እንዲጸልዩ ያበረታቷቸው ይሆናል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ጨቋኝ ለሆኑ ገዢዎች ድጋፍ ያደርጋሉ።

ይህ ዓይነቱ የይምሰል ክርስትና ኢየሱስ ካቋቋመው ክርስትና ፈጽሞ የተለየ ነው። ክርስቲያን ነን የሚሉ ብዙዎች የሚከተሉት ይህ ክርስትና ሰዎች ያመነጩት ነው። በዛሬው ጊዜ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ግዴለሽ መሆናቸው፣ ይህ ዓይነቱ የክርስትና እምነት ችግር እንዳለበት የሚያሳይ ማስረጃ ነው።

ኢየሱስ ያስተማረው ምን ነበር?

አንዳንድ ሰዎች፣ ኢየሱስ ተከታዮቹን በተመለከተ “እኔ ከዓለም እንዳልሆንሁ ሁሉ፣ እነርሱም ከዓለም አይደሉም” ብሎ እንደተናገረ ሲያውቁ ይገረሙ ይሆናል። (ዮሐንስ 17:15, 16) ክርስቶስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ይህን የመሰለ አቋም እንዲወስዱ ያሳሰባቸው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙር ማለትም ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጠናል:- “መላው ዓለምም በክፉው ሥር [ነው]።”—1 ዮሐንስ 5:19

በመሆኑም የክርስቶስ ትምህርቶች፣ በምድር ላይ ፍትሕና ጽድቅ የሰፈነበት ዓለም የሚያመጡት ሰብዓዊ ድርጅቶች ሳይሆኑ በሰማይ የሚገኘው የአምላክ መንግሥት እንደሆነ ያሳያሉ። (ማቴዎስ 6:10) ኢየሱስ ራሱ በጊዜው በነበረው ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ፈጽሞ ጣልቃ አልገባም። የፖለቲካ ሥልጣን ለመቀበልም ጨርሶ ፈቃደኛ አልነበረም። (ዮሐንስ 6:15) ከዚህም በላይ አለመግባባቶችን ለመፍታት የኃይል እርምጃ መውሰድን አውግዞ ነበር። (ማቴዎስ 26:50-53፤ ዮሐንስ 18:36) ኢየሱስ ሕገ መንግሥትም ሆነ የግለሰቦችን መብት ለማስከበር የሚረዳ ደንብ አላረቀቀም። በጊዜው በነበረው የፖለቲካ ጉዳይ ውስጥ እጁን አላስገባም። ለምሳሌ ያህል፣ የባሮች መብት ተሟጋች አልነበረም ወይም ደግሞ አይሁዳውያን በሮማውያን ላይ ባስነሱት ዓመጽ አልተካፈለም።

እንዲህ ሲባል ግን ኢየሱስ ስለ ሰዎችም ሆነ ስለሚደርስባቸው ችግር አያስብም ነበር ማለት አይደለም። ኢየሱስ፣ አንድ ሰው ለሌሎች ማድረግ ስለሚኖርበት ነገር በርካታ ትምህርቶችን አስተምሯል። ግብር በመክፈል ረገድ ታማኝ መሆንን ያበረታታ ከመሆኑም ሌላ ሕጋዊ ሥልጣን ላላቸው አካላት የመገዛትን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። (ማቴዎስ 22:17-21) ለተቸገሩ ሰዎች ልባዊ አሳቢነት እንዳለን በተግባር ማሳየት የሚቻልበትን መንገድ አስተምሯል። ከዚህም በተጨማሪ ሌሎችን በአክብሮት መያዝና ስሜታቸውን መረዳት እንዲሁም ይቅር ባዮችና ርኅሩኆች መሆን የሚቻልበትን መንገድ አስተምሯል። (ማቴዎስ ምዕራፍ 5 እስከ 7) የክርስቶስ ትምህርቶች ትኩረት ያደረጉት አምላክንና ባልንጀራን በመውደድ ላይ እንደሆነ የታወቀ ነው።—ማርቆስ 12:30, 31

በዛሬው ጊዜ ያለው እውነተኛ ክርስትና

ታዲያ አንድ እውነተኛ የክርስቶስ ተከታይ ሕይወቱን መምራት ያለበት እንዴት ነው? የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ልክ እንደ እርሱ ያደርጋል። የአገሪቱን ሕግ በታማኝነት የሚታዘዝ ቢሆንም በፖለቲካዊ ጉዳዮች ረገድ ገለልተኝነቱን ይጠብቃል። (ዮሐንስ 12:47, 48) በከባድ ፈተናዎች ሥር እያለም ክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን አይጥስም። (1 ጴጥሮስ 2:21-23) በሌላ በኩል ደግሞ በአካባቢው ስለሚከናወነው ነገር ግዴለሽ መሆን የለበትም። አንድ እውነተኛ ክርስቲያን ልክ ኢየሱስ እንዳደረገው ለሌሎች ደኅንነት ከልቡ እንደሚያስብ በተግባር ያሳያል። (ማርቆስ 6:34) ከዚህም በተጨማሪ ሰዎች የክርስቶስን ትምህርቶች ተገንዝበው በሥራ ላይ በማዋል ደስተኛ ሕይወት መምራት እንዲችሉ ለመርዳት ሲል ጊዜውን፣ ጉልበቱንና ሌሎች ነገሮችን ይሠዋል።—ዮሐንስ 13:17

በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ከዓለም ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ ክርስቶስን ለመምሰል ይጥራሉ። ሰላማዊና ሕግ አክባሪ ዜጎች ቢሆኑም የዓለም ክፍል አይደሉም። ልክ እንደ ኢየሱስ በዛሬው ጊዜ የተለመደ እየሆነ በመጣው ዓመጽና ፖለቲካዊ ውዝግብ ውስጥ አይካፈሉም። በዓለም ላይ ላሉት ችግሮች ብቸኛ መፍትሔ እንደሆነ ተስፋ የሚያደርጉት የአምላክን መንግሥት ነው። እውነተኛ ክርስትና በተከታዮቹ መካከል አንድነት እንዲኖርና ሕይወት ይበልጥ አስደሳች እንዲሆን ያደርጋል። (ዮሐንስ 13:34, 35) በመሆኑም እውነተኛው የክርስትና እምነት ችግር የለውም።

ይህን አስተውለኸዋል?

▪ ክርስቲያኖች በፖለቲካዊ ጉዳዮች መካፈል ይኖርባቸዋል?—ዮሐንስ 6:15

▪ ክርስቶስ አለመግባባቶችን ለመፍታት የኃይል እርምጃ መውሰድን ደግፏል?—ማቴዎስ 26:50-53

▪ የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ ምልክት ምንድን ነው?—ዮሐንስ 13:34, 35

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

EL COMERCIO, Quito, Ecuador