በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስቫልባርድ—ቀዝቃዛ የባሕር ዳርቻዎች ያሉባት አገር

ስቫልባርድ—ቀዝቃዛ የባሕር ዳርቻዎች ያሉባት አገር

ስቫልባርድ—ቀዝቃዛ የባሕር ዳርቻዎች ያሉባት አገር

ኖርዌይ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ጥቅጥቅ ባለ ደመና ውስጥ ምንም ነገር ሳይታየን ስንበር ከቆየን በኋላ አውሮፕላናችን ድንገት ከደመናው ውስጥ ብቅ ሲል ከበታቻችን የአርክቲክ ምድር ታየን። የሚታየው ነገር ሁሉ ዕፁብ ድንቅ ነው! የበረዶ ግግሮችን፣ ፈዘዝ ያለ ሰማያዊ ቀለም ያላቸውን ባሕረ ሰላጤዎችና በበረዶ የተሸፈኑ ተራሮችን በግርምት ተመለከትን። ዓይናችን ማየት እስከቻለው ድረስ ከፊታችን በአመዳይና በግግር በረዶ የተሸፈነ ጠፍ መሬት ተንጣሎ ይታያል። በሰሜን ዋልታ አካባቢ በ74ና በ81 ዲግሪ ኬንትሮስ መሥመሮች መካከል የሚገኘው ይህ ቦታ ስቫልባርድ በመባል ይታወቃል፤ እኛም ወደዚህ የመጣነው የተበታተኑ ደሴቶች የሚገኙበትን ይህን አካባቢ ለመጎብኘት ነው!

ስቫልባርድ የሚለው ስም “ቀዝቃዛ የባሕር ዳርቻ” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን በአይስላንድ ቋንቋ በተዘጋጀ ዜና ታሪክ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰፈረው በ1194 ነበር። ይሁን እንጂ ስቫልባርድ በዓለም ካርታ ላይ የወጣችው ከ400 ዓመታት በኋላ ማለትም በ1596 አካባቢው በአሰሳ “በተገኘ” ጊዜ ነበር። በዚያ ዓመት በቪለም ባረንትስ የተመራው የደች አሳሾች ቡድን በመርከብ ወደ ሰሜን አቅጣጫ ተጉዞ ነበር። አንድ ቀን በመርከቧ ማማ ላይ የሚቀመጠው ሰው አሻግሮ ሲመለከት ከአድማስ ባሻገር እንደ ሰንሰለት የተያያዙ ተራሮች ያሉባት ከዚያ በፊት የማትታወቅ አገር አየ። ከዚያም እነዚህ አሳሾች ወደ ሰሜን ምዕራብ ስቫልባርድ የመጡ ሲሆን ባረንትስ አገሪቱን “ስፒትስበርገን” ብሎ ሰየማት፤ ትርጉሙ “የሾሉ ተራሮች” ማለት ነው። በአሁኑ ጊዜ በዚያ አካባቢ ካሉት ደሴቶች መካከል ትልቁ የሚጠራው በዚህ ስም ነው። ይህ የባረንትስ ግኝት በስቫልባርድ አካባቢ ዓሣ ነባሪንና አቆስጣን ማጥመድ፣ እንስሳትን በወጥመድ መያዝ፣ አዳዲስ ቦታዎችን አስሶ ማግኘት፣ ከጊዜ በኋላ ደግሞ የድንጋይ ከሰል ማውጣት፣ ሳይንሳዊ ምርምር ማድረግና ቱሪዝም የመሳሰሉት እንቅስቃሴዎች በሰፊው እንዲጀመሩ በር ከፍቷል። ለብዙ ዓመታት በአካባቢው በሚካሄደው እንቅስቃሴ አያሌ አገሮች ቢካፈሉም ከ1925 ወዲህ ግን ደሴቶቹ የኖርዌይ ግዛት ሆነዋል።

ፐርማፍሮስት መሬትና የሰሜን ውጋጋን

አውሮፕላናችን ወደ በረዷማው ባሕረ ሰላጤ ዝቅ ብላ መብረር ከጀመረች በኋላ በስቫልባርድ አውሮፕላን ማረፊያ አረፈች። በተከራየነው መኪና ተሳፍረን በጆን ሎንግይር ስም ወደተሰየመው ሎንግዪርባየን ወደሚባል ሥፍራ አቀናን። በዚህ አካባቢ የድንጋይ ከሰል ማውጣቱን ሥራ በ1906 ያስጀመረው ይህ አሜሪካዊ ባለ ሀብት ነበር። ሎንግዪርባየን በስቫልባርድ ወደ 2,000 የሚጠጋ የሕዝብ ብዛት ያለው ትልቁ ከተማ ነው። አዎን፣ ተፈጥሯዊ ውበቱን ጠብቆ በሚገኘው በዚህ ሰፊ ክልል ውስጥ ሱፐርማርኬት፣ ፖስታ ቤት፣ ባንክ፣ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት፣ ትምህርት ቤቶች፣ መዋዕለ ሕፃናት፣ ሆቴሎች፣ ቡና ቤቶችና ምግብ ቤቶች፣ ሆስፒታልና ጋዜጣ የመሳሰሉት በጣም የተለመዱ ነገሮች ያሉበት አንድ ዘመናዊ ከተማ አገኘን። በሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ ከ78 ዲግሪ ኬንትሮስ ከፍ ብሎ የሚገኘው ሎንግዪርባየን በዓለም ላይ ወደ ሰሜን ዋልታ በጣም የተጠጋው ትልቁ ከተማ ነው።

እዚያ ከደረስን በኋላ ቀደም ሲል የድንጋይ ከሰል የሚያወጡ ሠራተኞች ይኖሩበት በነበረው ሠፈር ውስጥ ማረፊያ አገኘን። ያረፍንበት ቦታ ሎንግዪርባየንንም ሆነ ዮርትፍጀለ የሚባለውን ግርማ ሞገስ የተላበሰ ተራራ አሻግሮ ለማየት የሚያስችል ነበር። ወሩ ጥቅምት ስለሆነ ተራሮቹ በበረዶ ተሸፍነዋል። የሸለቆው ግርጌ በረዶ ባይኖረውም መሬቱ በጣም ቀዝቃዛ ነው። በዚህ አካባቢ ያለው መሬት ምንጊዜም ከፍተኛ ቅዝቃዜ ያለበት ስለሆነ ፐርማፍሮስት ይባላል። ከላይ ያለው አፈር በበጋ ወራት ለዚያውም ለጥቂት ጊዜ በረዶነቱ ይለቀዋል። የሆነ ሆኖ አካባቢው ከየብስም ሆነ ከውቅያኖስ ተስማሚ ነፋስ ስለሚያገኝ የአየር ንብረቱ በተመሳሳይ የኬንትሮስ መሥመር ላይ ካሉ ሌሎች ቦታዎች ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ነው። እኛ ካረፍንበት ቦታ ሆነን ስናይ በተራሮቹ ላይ የፀሐይ ብርሃን ፈንጥቆባቸዋል፤ ሸለቆው ደግሞ ሰማያዊ ሆኖ ይታያል። በሎንግዪርባየን ዙሪያ ከጥቅምት 26 እስከ የካቲት 16 ድረስ ባሉት ወራት ፀሐይ ከአድማስ ከፍ አትልም። ነገር ግን አውሮራ ቦሪያሊስ በመባል የሚታወቀው የሰሜን ውጋጋን የክረምቱን ጨለማ ገፍፎ አካባቢውን ብርሃን ያለብሰዋል። በሌላ በኩል ደግሞ በስቫልባርድ በፀደይና በበጋ ወራት ፀሐይ እኩለ ሌሊት ላይ ብቅ የምትልበት ክስተት የሚፈጠር ሲሆን በሎንግዪርባየን ይህ ሁኔታ የሚቆየው ከሚያዝያ 20 እስከ ነሐሴ 23 ድረስ ባሉት ወራት ነው።

ዕፅዋትና እንስሳት

አካባቢውን ለመጎብኘት በወጣንበት ዕለት ቅዝቃዜው ከዜሮ በታች 8 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሲሆን ኃይለኛ ነፋስ ይነፍስ ነበር፤ ሰማዩ ግን ጥርት ብሎ ይታያል። አስጎብኚያችን በእግር ወደ ሳርኮፋገን ተራራ ይዞን ከወጣ በኋላ እንደገና ቁልቁል ወደ ሎንግዪርባየን የበረዶ ግግር ወሰደን። እጅግ ቀዝቃዛ የሆነውን ተራራ በመውጣት ላይ እያለን አስጎብኚው በዚያ አካባቢ በጸደይና በበጋ ወራት የሚያማምሩ በርካታ አበቦች እንደሚበቅሉ ነገረን። እንዲያውም በስቫልባርድ በርካታ የዕፅዋት ዓይነቶች ያሉ ሲሆን 170 የሚሆኑ አበባ የሚያወጡ የዕፅዋት ዝርያዎች ይገኛሉ። በክልሉ ስቫልባርድ ፖፒ የሚባሉት ነጭ ወይም ቢጫ ቀለም ያላቸው አበቦችና ሳክሲፍሬጅ የሚባለው ወይን ጠጅ ቀለም ያለው ባለ ጥሩ መዓዛ አበባ በብዛት ይገኛሉ።

በረዷማውን ተራራ ሽቅብ መውጣታችንን ስንቀጥል በመንገዳችን ላይ ታርሚገን የምትባለውን ከዓመት ዓመት ከስቫልባርድ የማትጠፋ ወፍ ዱካ አገኘን። ከዚህች ወፍ በስተቀር ብሩኒችስ ጊለሞት፣ ሊትል ኦክ፣ የተለያዩ ጭላቶች፣ የወይን ጠጅ ቀለም ያለው ሳንድፓይፐር እና የመሳሰሉት ሌሎች የወፍ ዝርያዎች በሙሉ ወቅት ጠብቀው የሚፈልሱ ናቸው። ትኩረታችንን በጣም የሳበችው አርክቲክ ተርን የምትባለው ወፍ ናት። አብዛኞቹ የዚህች ወፍ ዝርያዎች ከዚያ ተነስተው በተቃራኒው አቅጣጫ እስከሚገኘው አንታርክቲካ እስከሚባለው የምድር ጫፍ ድረስ ይሄዳሉ።

በተጨማሪም በመንገዳችን ላይ የአርክቲክ ቀበሮን ዱካ አገኘን። ይህ መሰሪ እንስሳ በድንና ከዋልታ ድብ የተራረፈውን እየለቃቀመ የሚበላ ሲሆን ካልጠገበ የወፍ ጫጩቶችንና እንቁላሎችን ፈልጎ በመብላት ሆዱን ይሞላል። ይህ ቀበሮ በስቫልባርድ ካሉት ሁለት የየብስ አጥቢ እንስሳት መካከል አንዱ ነው። ሌላው የየብስ አጥቢ እንስሳ ገራገር የሆነው የደጋ አጋዘን ነው። ይህን አጋዘን በስቫልባርድ ቆይታችን ወቅት በቅርብ ርቀት ብዙ ጊዜ አይተነዋል። እርሱም በእርጋታ ይመለከተንና ቀረብ ብለን ፎቶግራፍ እስክናነሳው ድረስ ሳይሸሽ ቆሞ ይጠብቀናል። ይህ አጋዘን አጫጭር እግሮችና ጥቅጥቅ ያለ የሚሞቅ ፀጉር አለው። በተለይ በበረዶ ወራት ወፍሮ ይታያል። ያከማቸውን ስብ መጠባበቂያ ምግብ አድርጎ የሚጠቀምበት ሲሆን ይህ ስብ በጣም ቀዝቃዛ ለሆነው የክረምቱ ወራት በእጅጉ ያስፈልገዋል።

የአርክቲክ ንጉሥ የሆነው የዋልታ ድብ አቆስጣን ለማደን ሲል አብዛኛውን ጊዜውን በባሕር በረዶ ላይ ስለሚያሳልፍ ብዙዎች በውኃ ውስጥ ከሚገኙ አጥቢ እንስሳት መካከል ይፈርጁታል። ይሁን እንጂ በስቫልባርድ እነዚህን ድቦች በማንኛውም ቦታ ብቻቸውን ወዲያ ወዲህ ሲሉ ልታገኟቸው ትችላላችሁ። አስጎብኚያችን ድብ እንደማያጋጥመን ተስፋ አድርጓል። የዋልታ ድብ ሰው ሊተናኮል ስለሚችል አስጎብኚው ለደኅንነታችን ብሎ ጠመንጃ ይዟል። ሆኖም ከ1973 ጀምሮ የዋልታ ድብን ማደን ፈጽሞ ስለተከለከለ በምንም ዓይነት ምክንያት ቢሆን ይህን እንስሳ መግደል በወንጀል ሊያስጠይቅ ይችላል። በአሁኑ ጊዜ በስቫልባርድ የዋልታ ድብ ቁጥር ከበፊቱ ቢጨምርም ግርማ ሞገስ ያለው የዚህ እንስሳ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በጣም አሳሳቢ ሆኗል። የአርክቲክ አካባቢ ነጭ፣ ንጹሕና ያልተበከለ መስሎ ቢታይም እንደ ፖሊክሎሪኔትድ ባይፌነል (polychlorinated biphenyl) ያሉ መርዛማ ኬሚካሎች ጉዳት እያደረሱበት ነው። የዋልታ ድቦች በክልሉ የምግብ ሰንሰለት ውስጥ በመጨረሻው ደረጃ ላይ ስለሚገኙ በሌላ አነጋገር እነርሱን አድኖ የሚመገብ ሌላ እንስሳ ስለሌለ እነዚህ በካይ ኬሚካሎች በሰውነታቸው ውስጥ ይከማቻሉ። ይህ ደግሞ በመራባት ችሎታቸው ላይ ችግር ያስከተለ ይመስላል።

ሳርኮፋገን ተራራ ጫፍ ላይ ደርሰን አናታቸው በበረዶ የተሸፈነና ለዓይን ማራኪ የሆኑ በርካታ ተራሮችን በርቀት ለማየት ቻልን። በደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ የፀሐይ ብርሃን የፈነጠቀበትን ኖርደንሾልድፍዬለት ተብሎ የሚጠራ ክብ ቅርጽ ያለው በጣም አስደናቂ ተራራ አየን። ከበታቻችን ራቅ ብሎ ሎንግዪርባየን ይታያል፤ ከበላያችን ደግሞ ፈዘዝ ያለ ሰማያዊ መልክ ያለው የአርክቲክ ሰማይ ተንጣሏል። በዚህ ጊዜ ነበር በምድር አናት ላይ እንደቆምን የተሰማን። በአንድ ኩባያ የጥቁር ዘቢብ “ቶዲ” እያወራረድን ጥቂት ዳቦ ተመግበን ኃይላችንን ካደስን በኋላ ቁልቁል ወደ ሎንግዪርባየን ግግር በረዶዎች ጉዞ ለመጀመር ተነሳን። በጥቁር ዘቢብ ጭማቂ፣ በስኳርና በፈላ ውኃ የሚዘጋጀው ይህ አልኮልነት የሌለው መጠጥ ብዙውን ጊዜ በእግር በሚጓዙ ጎብኚዎች ይዘወተራል።

የድንጋይ ከሰል የማውጣት ሥራና ለመጥፋት የተቃረቡ እንስሳት

ቀደም ሲል የድንጋይ ከሰል ይወጣበት በነበረው ቦታ ያደረግነው ጉብኝት ሌላው አስደሳች ተሞክሮ ነበር። የድንጋይ ከሰል በማውጣት ሥራ ተሞክሮ ያለውና ጠብደሉ አስጎብኚያችን ከሎንግዪርባየን ትንሽ ወጣ ብሎ የሚገኘውን ቁጥር 3 የሚባለውን ጉድጓድ አሳየን። ቱታ ለብሰንና መብራት የተገጠመለት የራስ ቁር አድርገን ወደ ዋሻው ውስጥ አብረነው ገባን። በስቫልባርድ ገና ከ1900ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ አንስቶ የድንጋይ ከሰል የማውጣቱ ሥራ ዋነኛው መተዳደሪያ እንደነበረ ነገረን። በዚህ ሥራ ላይ የተሰማሩት ሰዎች ለብዙ ዓመታት በጣም አስቸጋሪ ሕይወት ይመሩ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ሠራተኞቹ ሥራቸውን የሚያከናውኑት ከ70 ሴንቲ ሜትር ብዙም የማይበልጥ ስፋት ባላቸው ረዥም መተላለፊያዎች ውስጥ በእጅና በእግራቸው እየዳኹ በመሄድ ነበር። እኛም በመተላለፊያዎቹ ውስጥ ለማለፍ ሞክረን ነበር፤ በእርግጥ ሥራው የሚመኙት ዓይነት አይደለም። ሥራው ከባድ የነበረ ከመሆኑም በላይ አየሩ በከሰሉ ጠረንና በአቧራ የታፈነ ነበር፤ ጩኸቱም ይህ ነው የሚባል አይደለም። በሌላ በኩል ደግሞ በድንገት የፍንዳታና የመደርመስ አደጋ ሊያጋጥም ይችላል። በአሁኑ ጊዜ ሥራው የሚካሄደው ይበልጥ ዘመናዊ በሆኑ ዘዴዎች በመታገዝ ነው። የድንጋይ ከሰል ቁፋሮ አሁንም የስቫልባርድ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ቢሆንም ከጥቂት አሥርተ ዓመታት ወዲህ ግን ቱሪዝም የበለጠ ትኩረት እያገኘ ነው።

ሰዎች ብዙውን ጊዜ በአርክቲክ አካባቢ ያሉት ዕፅዋትና እንስሳት በቀላሉ ለአደጋ ሊጋለጡ እንደሚችሉ ያን ያህል አይታያቸውም። በስቫልባርድ ዓሣ ነባሪዎች፣ ዎልረስ የተባለው የባሕር እንስሳ፣ የደጋ አጋዘን፣ የዋልታ ድብና ሌሎችም እንስሳት ከመታደናቸው የተነሳ አንዳንድ ዝርያዎቻቸው ለመጥፋት የተቃረቡበት ጊዜ ነበር። ይሁን እንጂ እነዚህን እንስሳት ለመጠበቅ ሲባል ሕግና ደንብ መውጣቱ የመጥፋት አደጋ ከተጋረጠባቸው ዝርያዎች መካከል ብዙዎቹ ቁጥራቸው እንዲጨምር አስተዋጽኦ አበርክቷል።

የጂኦሎጂስቱ ገነት

ስቫልባርድ “የጂኦሎጂስቶች ገነት” የሚል ስያሜ ተሰጥቷታል። የዕፅዋቱ መጠን በጣም ዘርዛራ በመሆኑ መልክዓ ምድሩን ላየው የጂኦሎጂ የሥዕል መጽሐፍ ይመስላል። አካባቢውን ከሌሎች ቦታዎች ልዩ የሚያደርጉትንና የተነባበረ ኬክ የሚመስሉትን የተራሮች ጂኦሎጂያዊ ገጽታዎችም አየን። በአካባቢው በታሪክ ዘመናት ሁሉ የነበሩት ጥንታዊ ዓለቶች አሁንም ይገኛሉ። አንዳንዶቹ ከአሸዋና ከሸክላ አፈር የተሠሩ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ሕይወት ባላቸው ነገሮች ቅሪተ አካሎች የተገነቡ ናቸው። በዘመናት ሁሉ የሞቱ ዕፅዋትና እንስሳት በሸክላ አፈር ተሸፍነው ቅሪተ አካላቸው በዚያ ይገኛል። እንዲያውም በዓለቶቹ ውስጥ በሁሉም ዘመናት የነበሩ ቅሪተ አካሎች ይገኛሉ።

በስቫልባርድ ሙዚየም ውስጥ በአንድ ወቅት በአካባቢው ደሴቶች ላይ የነበረው የአየር ጠባይ ከአሁኑ ይልቅ ሞቃት እንደነበረ የሚጠቁም በሞቃት የአየር ጠባይ ክልል የሚኖሩ የበርካታ ዕፅዋትንና እንስሳትን ቅሪተ አካላት ተመለከትን። በስቫልባርድ እስከ 5 ሜትር የሚደርስ ውፍረት ያላቸው የድንጋይ ከሰል ንብርብሮች ያሉባቸው ቦታዎች አሉ! በድንጋይ ከሰሉ ንብርብር ውስጥ ወቅት ጠብቀው ቅጠላቸው የሚረግፉም ሆነ የማይረግፉ ዛፎች ቅሪተ አካላት ተገኝተዋል። በዚያ አካባቢ ዕፅዋትን የሚበላው የዳይኖሶር ዱካ ቅሪተ አካል መገኘቱ በአንድ ወቅት አካባቢው ትንሽ ሞቅ የሚል የአየር ጠባይ እንደነበረው ብሎም ብዙ ዓይነት ዕፅዋት ይበቅሉበት እንደነበረ የሚጠቁም ሌላ ማስረጃ ነው።

ታዲያ ይህን ያህል ትልቅ የአየር ንብረት ለውጥ ሊከሰት የቻለው እንዴት ነው? ይህን ጥያቄ የሎንግዪርባየን ማዕድን ማውጫ ዳይሬክተሮች ቦርድ ተወካይ ለሆኑት ለጂኦሎጂስቱ ቱርፊን ካርነት አቅርበንላቸው ነበር። እርሳቸውም ብዙ ጂኦሎጂስቶች ለዚህ ዋነኛው ምክንያት የአህጉራት መንሸራተት ነው ብለው እንደሚያስቡ ነገሩን። ጂኦሎጂስቶች ስቫልባርድ ምናልባትም ከምድር ወገብ አካባቢ አንስቶ ለረጅም ጊዜ ቀስ በቀስ ወደ ሰሜን ሲንሸራተት በቆየ መሬት (tectonic plate) ላይ እንደምትገኝ ይናገራሉ። በዘመናዊ ሳተላይት የሚደረገው ክትትል እንደሚያሳየው ከሆነ ስቫልባርድ አሁንም ቢሆን በየዓመቱ የተወሰኑ ሴንቲ ሜትሮች ወደ ሰሜን ምሥራቅ እየተንሸራተተች ነው።

አውሮፕላናችን ከስቫልባርድ ሲነሳ ጉብኝታችን ብዙ የምናሰላስልባቸውን ነገሮች እንዳስገኘልን ተሰማን። ሰፊውን የአርክቲክ ምድር፣ ከአየሩ ጠባይ ጋር በሚገባ የተላመዱትን እንስሳት እንዲሁም የተለያዩ የዕፅዋት ዓይነቶችን መመልከታችን ስለ ፍጥረታት ብዛትና ዓይነት፣ ስለ ሰው ኢምንትነት ብሎም ሰዎች በተፈጥሮ ላይ ያላቸውን የበላይነት ስለሚጠቀሙበት መንገድ ቆም ብለን እንድናስብ አድርጎናል። ወደ ደቡብ አቅጣጫ መብረር ከጀመርን በኋላ ቀዝቃዛ የባሕር ዳርቻዎች ያሉባትን ምድር ለመጨረሻ ጊዜ በዓይናችን ቃኘናት፤ አናታቸው በበረዶ የተሸፈኑት አንዳንድ ተራራዎች በደመናው ውስጥ ብቅ ብቅ ብለው የሚታዩ ሲሆን የከሰዓት በኋላው የፀሐይ ብርሃን ሲያርፍባቸው ፈዘዝ ያለ ሮዝ ቀለም ያላቸው ይመስላሉ።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ሰሜን ዋልታ

ግሪንላንድ

ስቫልባርድ

ሎንግዪርባየን

75° ሰሜን

አይስላንድ

ኖርዌይ

60° ሰሜን

ሩሲያ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሎንግዪርባየን ከተማ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወይን ጠጅ ቀለም እንዳለው ሳክሲፍሬጅ ያሉ በርካታ የአበባ ተክሎች የአርክቲክን መጥፎ የአየር ጠባይ ተቋቁመው መኖር ይችላሉ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የስቫልባርድ ታርሚገንና የስቫልባርድ የደጋ አጋዘን

[ምንጭ]

Knut Erik Weman