በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አብያተ ክርስቲያናት በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?

አብያተ ክርስቲያናት በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?

አብያተ ክርስቲያናት በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?

ላቲን አሜሪካውያን በሰሜን ካለችው ሜክሲኮ ጀምሮ በደቡብ እስካለችው እስከ ቺሊ ድረስ በብዙ ነገሮች የሚመሳሰል ባሕል አላቸው። በዕድሜ የገፉ ላቲን አሜሪካውያን ከሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በስተቀር ሌላ ሃይማኖት ያልነበረበትን ጊዜ ያስታውሳሉ። በ16ኛው መቶ ዘመን የሮማ ካቶሊክ ሃይማኖትን እንዲቀበሉ ያስገደዷቸው የስፓኝ ቅኝ ገዢዎች ነበሩ። ብራዚልን አሸንፋ ቅኝ ግዛቷ ያደረገቻት የሮማ ካቶሊክ ሃይማኖት ተከታይ የነበረችው ፖርቱጋል ነበረች። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ ብሎም የመንግሥት ሃይማኖት በመሆን እውቅና ለማግኘት ስትል ለ400 ዓመታት ያህል በሥልጣን ላይ የነበሩ መንግሥታትን ስትደግፍ ቆይታለች።

በ1960ዎቹ ዓመታት ግን አንዳንድ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቀሳውስት ከገዢው መደብ ጋር መተባበራቸው የሕዝብን ድጋፍ እያሳጣቸው መሆኑን ተገነዘቡ። በመሆኑም የድሆችን ድጋፍ ለማግኘት በተለይ የነፃነት ንቅናቄ ተብሎ የሚጠራውን እንቅስቃሴ በማራመድ ዘመቻ ማካሄድ ጀመሩ። በላቲን አሜሪካ ንቅናቄው የተጀመረው አያሌ ካቶሊኮች የነበሩበትን የጉስቁልና ኑሮ በመቃወም ነበር።

ቀሳውስት በፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በመሳተፍ ሁኔታዎችን ለማስተካከል ጥረት ቢያደርጉም እንኳ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የካቶሊክ ሃይማኖትን ትተው ሌሎች አብያተ ክርስቲያናትን መሞከር ጀመሩ። ማጨብጨብ፣ መዝሙሮችን በጋለ ስሜት መዘመር ወይም የሮክ የሙዚቃ ትርኢት የሚመስል አቀራረብ የሚታይባቸው ሃይማኖቶች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ መጣ። ደንከን ግሪን የተባሉ ሰው ፌስስ ኦቭ ላቲን አሜሪካ በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ “በላቲን አሜሪካ የነበረው የወንጌላዊነት ንቅናቄ ተከፋፍሎ ቁጥር ስፍር የሌላቸውን አብያተ ክርስቲያናት ወለደ” በማለት ተናግረዋል። “ብዙውን ጊዜ እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት አንድ ቄስ እንደፈለገው የሚያሽከረክራቸው ቡድኖች ናቸው። በአብዛኛው አንድ ሃይማኖታዊ ቡድን ሲያድግ እርስ በርሱ ተከፋፍሎ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ይፈጠራሉ።”

አውሮፓ ለአብያተ ክርስቲያናት ጀርባዋን ሰጠች

ከ1,600 ለሚበልጡ ዓመታት አብዛኞቹ የአውሮፓ አገሮች ክርስቲያን ነን በሚሉ መንግሥታት ይተዳደሩ ነበር። ወደ 21ኛው መቶ ዘመን ዘልቀን በገባን መጠን ሃይማኖትን በተመለከተ አውሮፓ ውስጥ የሚታየው ሁኔታ እየተሻሻለ ይሆን? ስቴቭ ብሩስ የተባሉ ሶሺዮሎጂስት በ2002፣ ጎድ ኢዝ ዴድ—ሴኩላራይዜሽን ኢን ዘ ዌስት በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ ብሪታንያን በሚመለከት ሲናገሩ “በ19ኛው መቶ ዘመን ሁሉም ሰዎች ጋብቻቸውን የሚፈጽሙት በሃይማኖታዊ ሥርዓት ነበር ለማለት ይቻላል” ብለዋል። ይሁን እንጂ በ1971 እንግሊዝ ውስጥ በሃይማኖታዊ ሥርዓት ጋብቻቸውን የፈጸሙት 60 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ነበሩ። በ2000 ደግሞ በሃይማኖታዊ ሥርዓት የተከናወኑት ጋብቻዎች 31 በመቶ ብቻ ነበሩ።

በለንደን ለሚታተመው ዴይሊ ቴሌግራፍ ጋዜጣ ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን የሚዘግብ አንድ ጋዜጠኛ ይህን ጉዳይ በሚመለከት “የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያንን፣ የሮማ ካቶሊክንና የሜቶዲስት ቤተ ክርስቲያንን እንዲሁም ዩናይትድ ሪፎርምድ ቸርችስ የተባለውን ቤተ ክርስቲያን ጨምሮ በእንግሊዝ ውስጥ ያሉት ዋና ዋና ሃይማኖቶች ከረጅም ጊዜ በፊት አንስቶ ውድቀት እያጋጠማቸው ነው” የሚል አስተያየት ሰጥቷል። አክሎም አንድን ዘገባ አስመልክቶ ሲናገር “በ2040፣ እሁድ ዕለት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚካሄደው ሥነ ሥርዓት ላይ የሚገኙት ምእመናን ቁጥር ሁለት በመቶ ብቻ ስለሚሆን በብሪታንያ የሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት የመጥፋት አደጋ ተደቅኖባቸዋል” ብሏል። በኔዘርላንድ ስለሚገኙ ሃይማኖቶችም ተመሳሳይ አስተያየት ተሰንዝሯል።

ደች ሶሻል ኤንድ ካልቸራል ፕላኒንግ ኦፊስ የተባለ አንድ ቢሮ ባዘጋጀው ሪፖርት ላይ “ከጥቂት አሥርተ ዓመታት ወዲህ በአገራችን ሃይማኖታዊ ዝንባሌ በከፍተኛ ሁኔታ እየጠፋ የመጣ ይመስላል” በማለት ገልጿል። አክሎም “በ2020 ከአጠቃላዩ ሕዝብ መካከል 72 በመቶ የሚሆነው ምንም ዓይነት ሃይማኖት እንደማይኖረው ይገመታል” ብሏል። አንድ የጀርመን የዜና ምንጭ ደግሞ እንደሚከተለው ብሏል:- “ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ጀርመናውያን በአንድ ወቅት ከአብያተ ክርስቲያናት፣ ከሥራቸውና ከቤተሰባቸው ያገኙት የነበረውን መጽናኛ ለማግኘት ፊታቸውን ወደ ጥንቆላና ወደ ምትሀት እያዞሩ ነው። . . . በመላ አገሪቱ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት በተሰብሳቢ እጦት ምክንያት ለመዘጋት ተዳርገዋል።”

በአውሮፓ አሁንም ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱት ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ እንደዚያ የሚያደርጉት አምላክ የሚፈልግባቸውን ነገር ለማወቅ አይደለም። ከጣሊያን የተገኘ አንድ ዘገባ እንደሚናገረው “ጣሊያናውያን ሃይማኖታቸው ከአኗኗራቸው ጋር እንዲስማማላቸው ለማድረግ ይሞክራሉ።” በዚያ የሚኖሩ አንድ ሶሺዮሎጂስት “ጳጳሱ ከሚናገሩት መካከል የምንቀበለው እኛን የሚስማማንን ብቻ ነው” ብለዋል። በስፔን ያሉት ካቶሊኮች ሁኔታም ተመሳሳይ ነው፤ በዚህ አገር ካቶሊኮች ሃይማኖታዊ ቅንዓታቸውን ቁሳዊ ነገሮችን ጨምሮ የፈለጉትን ሁሉ አሁኑኑ ማግኘት በሚል አመለካከት ተክተውታል።

ይህ ዓይነቱ ዝንባሌ ክርስቶስና ተከታዮቹ ካስተማሩትና ተግባራዊ ካደረጉት ክርስትና ጋር ፈጽሞ የሚቃረን ነው። ኢየሱስ የፈለግነውን መርጠን ያልፈለግነውን የምንተውበትን የሃይማኖት “ቢፌ” አላቀረበልንም። ከዚህ ይልቅ “በኋላዬ ሊመጣ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም [“የመከራውንም እንጨት፣” NW] በየዕለቱ ተሸክሞ ይከተለኝ” በማለት ተናግሯል። ኢየሱስ ሰዎችን ያስተማረው ክርስቲያናዊው አኗኗር የግል ጥቅምን መሥዋዕት ማድረግንና መጣጣርን የሚጠይቅ መሆኑን ነው።—ሉቃስ 9:23

በሰሜን አሜሪካ የሚታየው የሃይማኖት ገበያ

ሕዝቦቿ ለሃይማኖት ጥሩ አመለካከት እንደሌላቸው ከሚነገርላት ከካናዳ በተቃራኒ በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ ሰዎች ከሃይማኖት ጋር የተያያዙ ነገሮችን በቁም ነገር ይመለከታሉ። የሕዝብ አስተያየት የሚሰበስቡ አንዳንድ ተቋማት ባወጡት መረጃ መሠረት ጥናት ከተደረገባቸው ሰዎች መካከል 40 ከመቶ የሚሆኑት በየሳምንቱ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንደሚሄዱ ቢናገሩም የተደረገው ቆጠራ እንደሚያሳየው ግን እንደዚያ የሚያደርጉት 20 በመቶ ገደማ የሚሆኑት ናቸው። ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን እንደሚያምኑ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ የአንድ ቤተ ክርስቲያን አባል ሆነው የሚቆዩት ለአጭር ጊዜ ብቻ ሊሆን ይችላል። በዩናይትድ ስቴትስ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱ ብዙ ሰዎች ሃይማኖታቸውን በቀላሉ ይቀያይራሉ። አንድ ሰባኪ ከተሰለቸ ወይም የሚስብ ካልሆነ ብዙም ሳይቆይ ተከታዮቹን ብሎም ያገኝ የነበረውን ከፍተኛ ገቢ ሊያጣ ይችላል!

አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶቻቸውን “ለገበያ ማቅረብ” የሚችሉባቸውን መንገዶች ለማሻሻል የንግድ ሙያ ዘዴዎችን እያጠኑ ነው። አብያተ ክርስቲያናት በዚህ ረገድ የሚያማክሯቸውን ድርጅቶች ለመቅጠር በብዙ ሺህ የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላር ያወጣሉ። እንዲህ ያሉ ድርጅቶችን አስመልክቶ የወጣ አንድ ዘገባ እንደገለጸው በሁኔታው የተደሰቱ አንድ ቄስ “ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የፈሰሰበት ነው” ብለዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ተሰብሳቢዎች ያሏቸው ትላልቅ አብያተ ክርስቲያናት በንግዱ ዘርፍ ስኬታማ ከመሆናቸው የተነሳ ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል እና ዚ ኢኮኖሚስት የመሳሰሉትን የንግድ ጽሑፎች ትኩረት ስበዋል። እነዚህ መጽሔቶች ብዙ ተሰብሳቢዎች ያሏቸው አብያተ ክርስቲያናት “አንድ ሰው ሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ነገሮችን ‘በአንድ ቦታ መገብየት’” የሚችልበትን አጋጣሚ እንዳመቻቹ ዘግበዋል። የቤተ ክርስቲያኖቹ ሕንጻዎች ምግብ ቤቶችን፣ ካፌዎችን፣ የውበት ሳሎኖችን፣ ሳውናዎችን እና የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን አጣምረው የያዙ ሊሆኑ ይችላሉ። ለመስህብነት ከሚያገለግሉት ነገሮች መካከል ቲያትሮች፣ ታዋቂ ሰዎች የሚጋበዙባቸው ዝግጅቶችና ዘመናዊ ሙዚቃዎች ይገኙባቸዋል። ይሁንና ሰባኪዎቹስ የሚያስተምሩት ምንድን ነው?

በዋነኝነት የሚያስተምሩት ‘የብልጽግናን ወንጌል’ መሆኑ ምንም አያስገርምም። አማኞች ምንም ሳይሰስቱ ለቤተ ክርስቲያናቸው መዋጮ ካደረጉ ብልጽግናና ጤንነት እንደሚያገኙ ይነገራቸዋል። ሥነ ምግባርን በሚመለከት ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ አምላክ ታጋሽና አይቶ እንዳላየ የሚያልፍ እንደሆነ ተደርጎ ይነገራቸዋል። አንድ ሶሺዮሎጂስት “የአሜሪካ አብያተ ክርስቲያናት አንድ ሰው በመጥፎ ሥራው ምክንያት አእምሮው እንዳይረበሽ ለማረጋጋት የሚጥሩ እንጂ ትክክልና ስህተት ስለሆነው ነገር ብይን የሚሰጡ አይደሉም” በማለት ተናግረዋል። በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ሃይማኖቶች አብዛኛውን ጊዜ የሚያተኩሩት አንድ ሰው በኑሮው ስኬት ለማግኘት ራሱን እንዴት መርዳት እንደሚችል ምክር በመስጠት ላይ ነው። ሰዎች በአብዛኛው መሄድ የሚያስደስታቸው መከፋፈልን ያመጣሉ ተብለው የሚታሰቡት መሠረተ ትምህርቶች እምብዛም ወደማይነሱባቸው ሃይማኖታዊ ቡድኖች ነው። ይሁን እንጂ በእነዚህ ቡድኖች ውስጥ ፖለቲካዊ ጉዳዮች በግልጽ መነሳታቸው የተለመደ ነው። አብያተ ክርስቲያናት ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ በቅርብ የፈጸሙት ሁኔታ አንዳንድ ቀሳውስትን ለእፍረት ዳርጓቸዋል።

ታዲያ በሰሜን አሜሪካ ሃይማኖት እያንሰራራ ነው? በ2005፣ ኒውስዊክ መጽሔት “መጮህ፣ ራስን ስቶ መውደቅ፣ ወለሉን በኃይል እየረገጡ መራመድ” እና እነዚህን የመሳሰሉ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ተወዳጅነት እያገኙ መሆናቸውን ከዘገበ በኋላ “እዚያ የሚደረገው ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱት ሰዎች ቁጥር በጣም ጨምሯል ማለት አይደለም” ሲል ገልጿል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ይህ ነው የሚባል ሃይማኖት እንደሌላቸው የሚናገሩ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ እያሻቀበ ነው። አንዳንድ ሃይማኖቶች የተሰብሳቢዎቻቸው ቁጥር እየጨመረ የሚሄደው የሌሎቹ እየቀነሰ ስለሆነ ነው። ሕዝቡ የጥንት ሃይማኖቶችን ከነሥነ ሥርዓቶቻቸው፣ ከነሙዚቃቸውና ልብሰ ተክህኗቸውን ከለበሱ ቀሳውስቶቻቸው ጋር ትቶ “ግልብጥ” ብሎ እየወጣ መሆኑ እየተነገረ ነው።

በዚህ ርዕስ ውስጥ አብያተ ክርስቲያናት በላቲን አሜሪካ እየተከፋፈሉ መሆናቸውን፣ በአውሮፓ የተሰብሳቢዎቻቸው ቁጥር በእጅጉ መቀነሱን፣ በዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ የተሰብሳቢዎቻቸውን ድጋፍ ላለማጣት ወደ መዝናኛው ማዘንበላቸውን በአጭሩ ተመልክተናል። እርግጥ በሁሉም ቦታ ሁኔታው ተመሳሳይ ነው ማለት አይደለም፤ ሆኖም አጠቃላዩን ሁኔታ ስንመለከተው አብያተ ክርስቲያናት የነበራቸውን ተቀባይነት ላለማጣት እየታገሉ ነው። ታዲያ ይህ ሲባል ክርስትና ውድቀት እያጋጠመው ነው ማለት ነው?

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

“የሃይማኖት ሱፐርማርኬት”

የፈረንሳይ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ብሔራዊ የሙያ አገልግሎት ዳይሬክተር የሚከተለውን እንዳሉ ይነገራል:- “የሃይማኖት ሱፐርማርኬት እያየን ነው። ሰዎች የአንድ ቤተ ክርስቲያን ደንበኛ ይሆኑና ሳይስማማቸው ሲቀር ወደ ሌላው ይሄዳሉ።” ስለ አውሮፓ ሃይማኖቶች በተደረገ ጥናት ላይ የብሪታንያ ኤክሰተር ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑ ግሬስ ዳቬ የተባሉ ሴት ሲናገሩ “ግለሰቦች ከቀረቡላቸው የተለያዩ ሃይማኖቶች ውስጥ ደስ ያላቸውን መርጠው በመውሰድ ይቀላቅሉታል። ሃይማኖት እንደ ሌሎች ነገሮች ሁሉ ሰዎች ለአኗኗራቸውና ለስሜታቸው የሚስማማቸውን መምረጥ የሚችሉበት ጉዳይ ሆኗል” ብለዋል።

[በገጽ 4,5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኔፕልስ፣ ጣሊያን በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን መግቢያ ላይ የተጻፈ ጽሑፍ

[ምንጭ]

©Doug Scott/age fotostock

[በገጽ 4, 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሜክሲኮ ውስጥ ብዙ ሰዎች የካቶሊክ እምነታቸውን ትተዋል