በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው የአኻያ ዛፍ

ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው የአኻያ ዛፍ

ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው የአኻያ ዛፍ

በቼክ ሪፑብሊክ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

አንደኛው ዝርያ ረጅምና ቀጥ ብሎ የሚያድግ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ወደ ታች የተንዠረገጉ ቅርንጫፎች ያሉት ነው። ከላይ ሲታዩ የሚለያዩ ቢመስሉም በጣም ተመሳሳይ ናቸው። ለመሆኑ እነዚህ ነገሮች ምንድን ናቸው? ፖፕላርና ዊፒንግ የተባሉ የአኻያ ዛፍ ዝርያዎች ናቸው።

የአኻያ ዛፎች አብዛኛውን ጊዜ የሚበቅሉት በወንዞችና በጅረቶች ዳርቻ ላይ ነው። ይህ ዛፍ በቼክ ሪፑብሊክ ረግረጋማ ቦታዎች ላይ የሚበቅል ሲሆን ከትንሽ ችግኝ ተነስቶ በፍጥነት በማደግ ቅጠልና ቅርንጫፍ ያወጣል። የአኻያ ዛፎች አንዳንድ ጊዜ ርዝመታቸው ከ30 ሜትር በላይ ሊደርስ ይችላል። አንዳንዶቹ ቅጠላቸው ረጅምና ቀጭን ሲሆን ቅርንጫፎቻቸውም ወደታች የተንዠረገጉ ናቸው። እንደ ሻይኒንግ ዊሎው እና ፐሲ ዊሎው ያሉት የአኻያ ዝርያዎች ደግሞ ቅጠላቸው ሰፋፊ ነው።

ምንም እንኳ ከ350 የሚበልጡ የአኻያና የፖፕላር ዛፍ ዝርያዎች ቢኖሩም ይበልጥ ትኩረት የሚስበው ዊፒንግ ዊሎው የሚባለው ነው። ጎት ዊሎው የሚባለው ሌላው ዝርያ ደግሞ እጅብ ብለው በሚወጡ ጸጉራማ አበባዎቹ ተለይቶ ይታወቃል። እነዚህ አበባዎች የሚያብቡት ዛፉ ቅጠል ከማውጣቱ በፊት ሲሆን የአበባዎቹ ማበብ ጸደይ ሊገባ መቃረቡን እንደሚጠቁም ይነገራል።

በርካታ ዝርያዎች ያሉት ዛፍ

የቼክ ዋና ከተማ የሆነችው ፕራግ በምትገኝበት በቦሂሚያ የፖፕላር ዛፍ ዝርያዎችን በብዛት ማየት የተለመደ ነው። በዚያ አካባቢ ቢያንስ 35 የፖፕላር ዛፍ ዝርያዎች ሲኖሩ ሁሉም በአኻያ ዛፍ ሥር የሚጠቃለሉ ናቸው። ከእነዚህ ዝርያዎች መካከል በብዛት የሚገኘው አብዛኛውን ጊዜ በጅረቶች ዳርና ረግረግነት ባላቸው የቦሂሚያ ጫካዎች ውስጥ የሚበቅለው ብላክ ፖፕላር ሳይሆን አይቀርም። ኢታሊያን ወይም ሎምባርዲ የሚባለው አንደኛው የብላክ ፖፕላር ዝርያ ቀጭን ግንድና በግንዱ ትይዩ ወደ ላይ ቀጥ ብለው የሚያድጉ ቅርንጫፎች አሉት። ማራኪ የሆነው ይህ ዛፍ ቁመቱ እስከ 35 ሜትር ሊደርስ ይችላል። ይህም ሲባል 11 ፎቅ ያለው ሕንጻ ሊያክል ይችላል ማለት ነው! ኢታሊያን ፖፕላር የተባለው የአኻያ ዛፍ ዝርያም በየመንገዱ ዳር ስለሚገኝ በተለይ ቅጠሎቹ ወደ ደማቅ ቢጫነት በሚለወጡበት የመከር ወራት ለገጠራማው ክልል የተለየ ድምቀት ይጨምርለታል።

ሌላው የፖፕላር ዛፍ ዝርያ ደግሞ አስፐን ይባላል። ይህ ዝርያ እንደ ሌሎቹ ዛፎች ረጅም አይደለም እንዲሁም ከላይ አካባቢ ቀጠን ያለ ነው። የአስፐን ዛፎችን ከሌሎች የፖፕላር ዛፍ ዝርያዎች ልዩ የሚያደርጋቸው ሌላ ነገር አላቸው። ይኸውም ቅጠሎቻቸው በትንሽ የነፋስ ሽውታ እንኳ የሚንቀጠቀጡ መሆናቸው ነው።

የአኻያ ዛፍ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሷል?

የአኻያ ዛፍ ከቼክ በስተ ደቡብ እስከ መካከለኛው ምሥራቅ ድረስ ይበቅላል ብለህ አታስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እስራኤላውያን በባቢሎን ምርኮ በነበሩበት ጊዜ በገናዎቻቸውን በአኻያ ዛፎች ላይ እንደሰቀሉ ይገልጻል። (መዝሙር 137:2) እንዲህ ያደረጉት ለምንድን ነው? በገና አምላክን ለማወደስ የሚያገለግል መሣሪያ ቢሆንም እንኳ ያዘኑት እስራኤላውያን በዚያ የመከራ ወቅት በገናቸውን ለመጫወት ስላልተገፋፉ ነው። (ኢሳይያስ 24:8, 9) በተጨማሪም የአምላክ ቃል የመከር በዓል በሚከበርበት ጊዜ ዳስ ለመሥራት ከሚያገለግሉ ዛፎች መካከል አንዱ አኻያ እንደሆነ ይናገራል። (ዘሌዋውያን 23:40) የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የኢዮብ መጽሐፍ ደፋር የሆነው ጉማሬ በውኃ ውስጥ እንደሚኖርና ‘የወንዝ አኻያ ዛፎች እንደሚሸፍኑት’ ይናገራል።—ኢዮብ 40:22

በዛሬው ጊዜ የፖፕላርም ሆነ የአኻያ ዛፍ ዝርያዎች የተለያዩ የእንጨት ሥራ ውጤቶችን ለመሥራት ያገለግላሉ። ለምሳሌ ያህል የፖፕላር ዛፍ አብዛኛውን ጊዜ ኮምፖንሳቶ፣ ችፑድ፣ ሣጥን፣ ካርቶንና የተለያዩ የወረቀት ምርቶችን ለመሥራት ያገለግላል። የአኻያ ዛፍም እንዲሁ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። የእጅ ባለሙያዎች በቀላሉ በሚተጣጠፉት ቅርንጫፎቹ ቅርጫቶችንና አንዳንድ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶችን ይሠራሉ። በእርግጥም አኻያ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው የዛፍ ዝርያ ነው!

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዊፒንግ ዊሎው

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአስፐን ዛፍ ቅጠሎች

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሎምባርዲ ፖፕላር

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጎት ዊሎው

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብላክ ፖፕላር