በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የትራፊክ መጨናነቅ የሚፈጥረውን ችግር መቋቋም

የትራፊክ መጨናነቅ የሚፈጥረውን ችግር መቋቋም

የትራፊክ መጨናነቅ የሚፈጥረውን ችግር መቋቋም

ስፔን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ሐኪምህ ዘንድ ቀጠሮ ስላለህ ቀደም ብለህ ከቤት ወጥተሃል። ይሁን እንጂ ሊገጥምህ የሚችለውን የትራፊክ መጨናነቅ ከግምት አላስገባኸውም ነበር። ደቂቃዎች እያለፉ ሲሄዱ ካለህበት ብዙም ፈቅ እንዳላልክ ሲሰማህ ጭንቀትህ እየጨመረ ይመጣል። በመጨረሻም ግማሽ ሰዓት ዘግይተህ ሐኪምህ ዘንድ ትደርሳለህ።

የከተማ ኑሮ ከሚያስከትላቸው አስቸጋሪ ሁኔታዎች አንዱ የትራፊክ መጨናነቅ ነው። ሁኔታውን ይበልጥ አስቸጋሪ የሚያደርገው ደግሞ መንገዱ ላይ የሚታየው ረጅም የመኪና ሰልፍና እነርሱ የሚፈጥሩት የአየር ብክለት ነው። የሚያሳዝነው ነገር በሚሊዮን የሚቆጠሩ የከተማ ነዋሪዎችን በየዕለቱ የሚያጋጥማቸው ይህ ችግር ምንም ዓይነት የመሻሻል ምልክት አይታይበትም።

የቴክሳስ የትራንስፖርት ተቋም ዩናይትድ ስቴትስን በተመለከተ “በትልልቆቹም ሆነ በትንንሾቹ ከተሞች፣ የመንገድ መጨናነቅ በሁሉም ቦታ እየጨመረ መጥቷል” ሲል ዘግቧል። ዘገባው በማከል ባለ ሥልጣናት እየጨመረ የሚሄደውን የከተማ ውስጥ ተጓጓዦች ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችል መፍትሔ መዘየድ እንዳልቻሉ ገልጿል። ሁኔታው በመላው ዓለም ተመሳሳይ ነው። በቅርቡ በቻይና በሺዎች የሚቆጠሩ ባለ መኪናዎች 100 ኪሎ ሜትር የሚደርስ የትራፊክ መጨናነቅ አጋጥሟቸው የነበረ ሲሆን ፖሊሶች ችግሩን ለመፍታት የተወሰኑ ቀናት ፈጅቶባቸዋል። በሜክሲኮ ሲቲ በከተማው መሃል አቋርጦ በሚያልፍ 20 ኪሎ ሜትር ርዝመት ባለው መንገድ ላይ በመኪና ለመጓዝ ከአራት ሰዓት በላይ ይፈጃል፤ የሚገርመው አንድ እግረኛ በመካከለኛ ፍጥነት ቢጓዝ እንኳ ይህን ያህል ሰዓት አይፈጅበትም።

የከተማ መንገዶች ይህን ያህል የተጨናነቁት ለምን እንደሆነ መረዳት ያን ያህል አስቸጋሪ አይደለም። ከተሞች ያለማቋረጥ እያደጉ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ከዓለም ሕዝብ ውስጥ ግማሽ ያህሉ የሚኖረው በከተማ ክልል ውስጥ ነው። ከተሞች እየሰፉ ሲሄዱ ደግሞ የተሽከርካሪዎች ቁጥርም የዚያኑ ያህል እየጨመረ ይሄዳል። አንድ ጸሐፊ ሁኔታውን እንደሚከተለው በማለት ገልጸውታል:- “አብዛኞቹ ሰዎች ብዙ መኪኖች አሏቸው፤ እነዚህ ሰዎች ደግሞ ባለችው ጠባብ መንገድ ላይ በአንድ ጊዜ መንዳት ይፈልጋሉ።”

ችግሮቹን መፍታት ከባድ የሆነበት ምክንያት

የሰው ልጅ እንቅስቃሴ በመኪናዎች ላይ የተመካ ከሆነ ከተሞች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄደውን የተሽከርካሪዎች ቁጥር ማስተናገድ ግድ ይሆንባቸዋል። አራት ሚሊዮን የሚያህል የሕዝብ ብዛት ያላት ሎስ አንጀለስ የምትባለው የዩናይትድ ስቴትስ ከተማ በአሁኑ ጊዜ ከሕዝቧ ቁጥር በላይ የሚሆኑ መኪናዎች ይንቀሳቀሱባታል! በሌሎች ከተሞች ውስጥ ያለው የመኪና ብዛት ይህን ያህል ባይሆንም ብዙዎቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄደውን የተሽከርካሪ ብዛት ማስተናገድ አይችሉም። የማድሪድ የከተማ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት የሆኑት ካርሎስ ጉዝማን “ከተሞች የተቆረቆሩት አውቶሞቢሎችን ግምት ውስጥ በማስገባት አልነበረም” በማለት ተናግረዋል። በትራፊክ እንቅስቃሴ በይበልጥ የሚጨናነቁት ጠባብ መንገዶች ያሏቸው ጥንታዊ ከተሞች ቢሆኑም ሰፋፊ መንገዶች ያሏቸው ትላልቅ ዘመናዊ ከተሞችም በተለይም በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት ላይ ሲጨናነቁ ይታያል። ዶክተር ዣን ፖል ሮድሪግ “የከተማ የትራንስፖርት ችግሮች” በተሰኘው ሪፖርታቸው ላይ “በአሁኑ ጊዜ ትልልቅ ከተሞች በአብዛኛው የቀኑ ክፍል በትራፊክ እየተጨናነቁ ሲሆን ይህ ችግር ይበልጥ እየባሰበት ነው” ብለዋል።

መኪናዎች የሚሸጡበት ፍጥነት መንግሥታት መንገድ ከሚሠሩበት ፍጥነት በጣም ስለሚበልጥ የመኪናዎች ቁጥር በእጅጉ መጨመሩ ወትሮ ደህና የነበረውን መንገድ እንኳ መተንፈሻ ሊያሳጣው ይችላል። ስታክ ኢን ትራፊክ—ኮፒንግ ዊዝ ፒክ አወር ትራፊክ ኮንጄስሽን የተሰኘው መጽሐፍ “አዳዲስ መንገዶችን መሥራትም ሆነ የነበሩትን መንገዶች ማስፋት በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት ላይ የሚፈጠረውን መጨናነቅ ምንም ያህል አይቀንሰውም” ብሏል።

በቂ የሆነ የመኪና ማቆሚያ አገልግሎት አለመኖሩም የትራፊክ መጨናነቅን ያስከትላል። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መኪናዎች ከተማ ውስጥ ወዲያ ወዲህ የሚዘዋወሩት የሚቆሙበት ሥፍራ ፍለጋ ሊሆን ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ በከተሞች ውስጥ የመኪና ጭስ በሚፈጥረው ብክለት ሳቢያ በየዓመቱ 400,000 የሚያህሉ ሰዎች ለሕልፈተ ሕይወት እንደሚዳረጉ ይገመታል። በአንድ ዘገባ መሠረት በሚላን፣ ጣሊያን ውስጥ ያለው የአየር ብክለት አስከፊ ከመሆኑ የተነሳ በከተማው ውስጥ አንድ ቀን መዋል 15 ሲጋራ ከማጨስ ጋር እኩል ነው።

የትራፊክ መጨናነቅ የሚያስከትለው ኪሣራ ከሚባክነው ሰዓትና በአሽከርካሪዎቹ ላይ ከሚፈጥረው ውጥረት አንፃርም መታየት አለበት። ሁኔታው በስሜት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ማስላት አስቸጋሪ ቢሆንም በዩናይትድ ስቴትስ በተደረገ አንድ ጥናት መሠረት በ75 የአገሪቱ ትልልቅ ከተሞች ውስጥ በሚፈጠረው የትራፊክ መጨናነቅ ሳቢያ በዓመት 70 ቢሊዮን ዶላር ኢኮኖሚያዊ ኪሣራ እንደሚያጋጥም ተደርሶበታል። ታዲያ ይህን ችግር ለማቃለል ሊደረግ የሚችል ነገር ይኖር ይሆን?

ችግሩን ለማቃለል የሚረዱ አንዳንድ የመፍትሔ ሐሳቦች

አንዳንድ ከተሞች ጥብቅ እርምጃዎችን ወስደዋል። በዓለም ላይ ከፍተኛ የመኪና ብዛት ከሚታይባቸው ከተሞች አንዷ የሆነችው ሲንጋፖር ግለሰቦች በሚገዙት የመኪና ቁጥር ላይ ቁጥጥር ታደርጋለች። እንደ ሚላንና ቦሎኛ ያሉት ታሪካዊ የጣሊያን ከተሞች በአብዛኛው የቀኑ ክፍል መኪናዎች መሃል ከተማ ጨርሶ ዝር እንዳይሉ አግደዋል።

ሌሎች ከተሞች ያቀረቡት የመፍትሔ ሐሳብ ደግሞ አሽከርካሪዎች ወደ መሃል ከተማ ሲገቡ ገንዘብ እንዲከፍሉ የሚደረግበት ሁኔታ ነው። ይህ የመፍትሔ ሐሳብ በለንደን ከተማ በትራፊክ መጨናነቅ ሳቢያ የሚፈጠረውን መዘግየት 30 በመቶ ለመቀነስ ያስቻለ ሲሆን ሌሎች ከተሞችም ይህን ዘዴ ተግባራዊ የሚያደርጉበትን ጊዜ በጉጉት የሚጠባበቁ ይመስላል። የሜክሲኮ ዋና ከተማ እንደሆነችው እንደ ሜክሲኮ ሲቲና የኮሪያ ሪፑብሊክ ዋና ከተማ እንደሆነችው እንደ ሴኡል ባሉት ቦታዎች መኪናዎች ወደ መሃል ከተማ እንዲገቡ የሚፈቀድላቸው በሳምንቱ ውስጥ በተወሰኑ ቀናት ነው፤ የሚገቡበት ቀን የሚወሰነው በሠሌዳ ቁጥራቸው ቅደም ተከተል በወጣላቸው ተራ መሠረት ነው።

የከተማ ባለ ሥልጣናት የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ ሥርዓቱን ዘመናዊ ለማድረግ፣ መንገዶችን ለማሻሻልና ቀለበት መንገዶችን ለመሥራት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ አውጥተዋል። በተጨማሪም የትራፊክ መብራቶችን ለመቆጣጠርና የመኪና ግጭት ሲያጋጥም ፖሊሶች ቶሎ በቦታው ደርሰው የተፈጠረውን ጭንቅንቅ በፍጥነት እንዲያስወግዱ ትእዛዝ ለማስተላለፍ በኮምፒውተር የሚታገዝ አሠራር ይጠቀማሉ። በአንድ መንገድ ላይ አውቶቡስ ብቻ የሚሄድባቸው ልዩ መስመሮች እንዲኖሩ ማድረግ እንዲሁም እንደሁኔታው በሁለቱም አቅጣጫዎች የሚያስኬዱ መስመሮችን መጠቀምም የሚፈጠረውን መጨናነቅ ለማቃለል ሊረዳ ይችላል። ይሁንና የዚህ ሁሉ ጥረት ስኬታማነት በአብዛኛው የተመካው በዜጎች ተባባሪነት ላይ ነው።

አንተ በግልህ ምን ማድረግ ትችላለህ?

ኢየሱስ ክርስቶስ “ሌሎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር እናንተም አድርጉላቸው” ብሏል። (ማቴዎስ 7:12) ይህ ጥበብ ያዘለ ምክር እጅግ የተወሳሰቡ የትራፊክ ችግሮችንም ለማቃለል ሊረዳ ይችላል። በሌላ በኩል ግን ሁሉም ሰው የራሱን ምቾት ብቻ የሚፈልግ ከሆነ በጣም ግሩም የተባለው ዘዴ እንኳ ፋይዳ ቢስ ይሆናል። ባለህበት ከተማ ውስጥ የሚያጋጥምህን የትራፊክ መጨናነቅ መቋቋም እንድትችል የሚረዱ አንዳንድ ሐሳቦች ከዚህ ቀጥሎ ቀርበውልሃል።

የምትሄድበት ቦታ ቅርብ ከሆነ በእግርህ አለዚያም በብስክሌት ብትሄድ የተሻለ ሊሆን ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ከእነዚህ ሁለት አማራጮች ውስጥ በአንዱ መጠቀም በቀላሉ ፈጥኖ ለመድረስ የሚረዳ ሲሆን ለጤንነትም ጥሩ ነው። ራቅ ያለ ቦታ የምትሄድ ከሆነ ደግሞ የሕዝብ ማመላለሻዎችን መጠቀሙ የተሻለ አማራጭ ሊሆን ይችላል። ብዙ ከተሞች ሰዎች ከመኪኖቻቸው ይልቅ በሕዝብ ትራንስፖርት ዘዴዎች እንዲጠቀሙ ለማበረታታት የአውቶቡስና የባቡር አገልግሎቶችን ለማሻሻል ጥረት እያደረጉ ነው። በእነዚህ የመጓጓዣ አገልግሎቶች መጠቀም ገንዘብንም ይቆጥባል። ምንም እንኳ እስከ አውቶቡስ ፌርማታ ወይም ባቡር ጣቢያ ድረስ በመኪናህ መሄድ ቢኖርብህም ወደ መሃል ከተማ ለመሄድ በሕዝብ መጓጓዣ መጠቀም ትችል ይሆናል።

የግድ በመኪና መሄድ ካለብህ በአንድ መኪና በርከት ብሎ መሄዱ የተሻለ ሊሆን ይችላል። በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት የሚፈጠረውን የትራፊክ ጭንቅንቅ ለመቀነስ ከሚረዱት ውጤታማ ዘዴዎች አንዱ ይህ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ ራቅ ካለ ቦታ ተመላልሰው ከሚሠሩ ሰዎች መካከል 88 በመቶ የሚሆኑት የራሳቸውን መኪና የሚጠቀሙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት የሚጓዙት ብቻቸውን ነው። ስታክ ኢን ትራፊክ የተባለው መጽሐፍ ብዙ ሰዎች ወደ ሥራ ሲሄዱ በአንድ መኪና እንዲጓዙ ማሳመን ቢቻል “በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት የሚፈጠረውን መዘግየትና የትራፊክ መጨናነቅ በእጅጉ ለመቀነስ ይቻል ነበር” በማለት ይናገራል። ከዚህም በላይ በብዙ ቦታዎች ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ሰዎችን የጫኑ መኪናዎች ብቻ የሚሄዱባቸው ልዩ መንገዶች እንዲኖሩ ተደርጓል። አንድ ሰው ብቻ ያለባቸው መኪኖች በእነዚህ መንገዶች እንዲጠቀሙ አይፈቀድላቸውም።

የምትቸኩልበት ጉዳይ ከሌለህ የሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት ካለፈ በኋላ ለመሄድ ጥረት አድርግ። ይህም ለአንተም ሆነ ለሌሎች ባለ መኪናዎች ነገሮችን ያቀልላችኋል። መንገድ ዳር መኪናህን በተገቢው መንገድ ካቆምክ ሌሎች እንደልብ እንዳይተላለፉ እንቅፋት አትሆንም። እርግጥ ነው፣ ከሁሉ የተሻሉ ናቸው የተባሉት የመፍትሔ ሐሳቦችም እንኳ የትራፊክ መጨናነቅ እንደማያጋጥምህ ዋስትና ሊሆኑህ አይችሉም። የትራፊክ መጨናነቅ ሲያጋጥምህ ትክክለኛ አመለካከት መያዝህ የሚሰማህን ብስጭት ለመቀነስ በእጅጉ ይረዳሃል።—ሣጥኑን ተመልከት።

በግልጽ ለማየት እንደምንችለው በትልቅ ከተማ ውስጥ የምትኖር ከሆነ የሚያጋጥምህን የትራፊክ መጨናነቅ ችለህ መኖር ይኖርብሃል። የሆነ ሆኖ ግን በግልህ ኃላፊነት እንደሚሰማህ የሚያሳዩ እርምጃዎችን በመውሰድና ለሌሎች አሽከርካሪዎች አክብሮትና ትዕግሥት በማሳየት የትራፊክ መጨናነቅ የሚያስከትለውን ችግር መቋቋም የምትችልበትን መንገድ መማር ትችላለህ።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የትራፊክ መጨናነቅ በሚያጋጥምበት ጊዜ መረጋጋት

በማድሪድ፣ ስፔን ታክሲ በመንዳት የሚተዳደረው ሃይማ ከ30 ለሚበልጡ ዓመታት የትራፊክ መጨናነቅ የሚፈጥረውን ችግር ችሎ ኖሯል። ይህ ሰው በጣም የሚያበሳጭ ሁኔታ በሚያጋጥመው ጊዜ ራሱን የሚያረጋጋበትን መንገድ እንደሚከተለው በማለት ገልጿል:-

▪ ምንጊዜም የማነበውን ጽሑፍ እይዛለሁ። ስለሆነም ከቆምኩበት ቦታ ፈጽሞ ፈቅ ባልል እንኳ እምብዛም አልበሳጭም።

▪ ከባድ የትራፊክ መጨናነቅ ከመፈጠሩ የተነሳ እየተንፏቀቅን የምንሄድ ከሆነ የመኪናዬን ሬዲዮ ከፍቼ ዜና እሰማለሁ፤ አለዚያም በቴፕ የተቀዳ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ አዳምጣለሁ። ይህ ዘዴ በተፈጠረው መጨናነቅ ላይ ሳይሆን በሌላ ነገር ላይ እንዳተኩር ያስችለኛል።

▪ ሌሎችን ከመረበሽ በቀር የሚፈይደው ነገር ስለሌለ ፈጽሞ ጥሩንባ አልጠቀምም። ለሌሎች አሽከርካሪዎች አክብሮት በማሳየት ውጥረትን ለማስወገድና ሌሎችም እንዲሁ እንዲያደርጉ ለመርዳት እጥራለሁ።

▪ መጥፎ ባሕርይ ያላቸው አሽከርካሪዎች ሲያጋጥሙኝ ለመረጋጋት እጥራለሁ፤ እንዲሁም እንደዚህ ካሉት ሰዎች እርቃለሁ። እንዲህ ባለው ጊዜ መታገሥን የመሰለ ነገር የለም።

▪ ቶሎ ለመድረስ የሚያስችሉ አማራጭ መንገዶችን ለመጠቀም የምጥር ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ የትራፊክ መጨናነቅ ወደሚፈልጉበት ቦታ በሰዓቱ እንዳይደርሱ ሊያዘገያቸው እንደሚችል ለተሳፋሪዎቼ እነግራቸዋለሁ። ብዙውን ጊዜ ከተማ ውስጥ እየነዱ በቀጠሮ ሰዓት ይደረሳል ማለት ዘበት ነው።